በፎሊክ አሲድ እጥረት የሚከሰት “ የነርቭ ዘንግ ክፍተት” ን ለመከላከል

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በተሠራው ጥናት ከአንድ ሺህ ህፃናት ውስጥ 131 ሕፃናት የነርቭ ዘንግ ክፍተት አጋጥሟቸዋል፡፡ በአዲአስ አበባ ከተማም በተወሰኑ ተቋማት ከተወለዱ አስር ሺህ ህፃናት መካከል 126ቱ ክፍተቱ እንዳለባቸው ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ በዚሁ መረጃ መሠረት፣ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ደግሞ ከተወለዱ አስር ሺ ሕፃናት፤ 108 ሕፃናት ተገኝተዋል፡፡

እንደ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ከተወለዱ አስር ሺህ ህፃናት ከአምስት በመቶ የበለጡት የነርቭ ዘንግ ከተገኘባቸው ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መደረሱን፤ ወይም ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ያመላክታል፡፡ ከዚህ ቁጥር በመነሳት ኢትዮጵያም የችግሩ ተጋላጭ ከሆኑት ሀገራት መካከል ተጠቃሽ መሆኗን ለመረዳት ቀላል ነው፡፡

ዶክተር ታደሰ ጉሬ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የማህጸን እና የጽንስ ስፔሻሊስት ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው ገለፃ የነርቭ ዘንግ ክፍተት (Neural Tube Defect) (NTD) አንድ ሕፃን ገና በእናቱ ማሕጸን እንደተፀነሰ በሦስተኛው ሳምንት፣ ወይም ከ21ኛ እስከ 26ተኛ ባሉት ቀናት ውስጥ የነርቭ ዘንግ መዘጋት ይኖርበታል። ይህ ሳይሆን ሲቀር ‹‹የነርቭ ዘንግ ክፍተት ተፈጥሯል።›› በዚህም ሳቢያ ከላይኛው የአእምሮ ክፍል እስከ ታችኛው ሕብለ ሰረሰር ድረስ የነርቭ ዘንግና መሸፈኛው ላይ የአፈጣጠር ችግር በታየባቸው ጨቅላ ሕፃናት ላይ የጭንቅላት መጠን ገዝፎ መታየት እና ከጀርባቸው ያበጠ ነገር ይስተዋልባቸዋል፡፡

የነርቭ ዘንግ ክፍተት በተለያዩ ምክንያቶች ይከሰታል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ግን የሚከሰተው የፎሊክ አሲድ እጥረት እንደሆነ ዶክተር ታደሰ ያብራራሉ። ፎሊክ አሲድ በምንመገባቸው ምግቦች አማካኝነት ይገኛል፡፡ ለአብነትም ካሮት፣ ማንጎ ፓፓያ፣ ጎመን እና ሌሎች ቅጣቅጠሎች ውስጥ ይገኛል፡፡ የአንዲት ሴት ፎሊክ አሲድ በሰውነቷ ውስጥ በቂ ሳይሆን ሲገኝ የሕፃኑ የሰውነት ግንባታ ሂደትን በማስተጓጎል የነርቩ ዘንግ ሳይዘጋ ይቀራል፡፡

ሌላኛው ምክንያት ደግሞ አንዲት እናት የሚጥል በሽታ ካለባት እና ለዛ ህመም መድሃኒት የምትወስድ ከሆነ ፎሊክ አሲዱ እንዳይሠራ በማስተጓጎል ክፍተቱ እንዳይዘጋ ያደርጋል፡፡ በተመሳሳይ የስኳር ህመምተኛ የሆኑ እናቶች እርግዝና ሲከሰት የነርቨ ዘንግ እንዳይዘጋ የሚያደርግበት ሁኔታ መኖሩን ዶክተር ታደሰ ይናገራሉ፡፡

አልፎ አልፎ ከአፈጣጠር ጋር በተያያዘ በሰውነታችን ውስጥ ያለው ኢንዛይም ፎሊክ አሲድን የመቀየር ኃይል አለው፡፡ ፎሊክ አሲድ ቢወሰድም እጥረቱን መቀነስ አይቻላቸውም፡፡ ይህም ለክፍተቱ አጋልጦ የሚሠጥ ይሆናል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ችግሩ በፎሊክ አሲድ እጥረት ምክንያት የሚከሰት እንደሆነ አጽንኦት በመስጠት ያስረዳሉ፡፡

ዶክተር ታደሰ እንደሚያብራሩት አንዲት እናት ከማርገዟ በፊት የቅድመ እርግዝና ክትትል (እርግዝና ሳይከሰት በፊት) በማድረግ ከማርገዟ አንድ ወር ቀደም ብላ ፎሊክ አሲድ ብትወስድ ይመረጣል፡፡ እርግዝና ከተከሰተ በኋላ ደግሞ እስከ ሦስተኛ ወር ፎሊክ አሲድ በመውሰድ የነርቭ ዘንግ ክፍተትን መቀነስ ይቻላል። እንዲሁም የተለያዩ በሽታዎች ያሉባቸው እናቶች እርግዝና ከመፈጠሩ በፊት ክትትል እና ህክምናቸውን በማድረግ መከላከል ያስችላቸዋል፡፡ በተለይም የስኳር በሽታ ያለባቸው እናቶች የስኳር መጠናቸውን በመቆጣጠር ከነርቭ ዘንግ ክፍተት ባሻገር ሌሎች በሽታዎችንም ለመከላከል እንደሚረዳቸው ይናገራሉ።

በእኛ ሀገር ያሉ አብዛኛዎቹ እናቶች የእርግዝና ክትትል ማድረግ የሚጀምሩት ነፍሰጡር መሆናቸውን ካረጋገጡ ከሁለት እና ከዛ በላይ ባሉት ወራት እንደሆነ የታዘቡት የማህጸን እና የጽንስ ስፔሻሊስት ዶክተር ታደሰ፣ ክፍተቱ ከተፈጠረ በኋላ ፎሊክ አሲዱን መውሰድ ክፍተቱን የሚዘጋ ባለመሆኑ ጠቀሜታ የለውም ይላሉ፡፡ ስለዚህም አንድ ባል እና ሚስት ልጅ መውለድ ሲፈልጉ ሴቲቱ ከማርገዟ በፊት ‹‹ምን ማድረግ አለብኝ?›› በማለት ከህክምና ባለሙያ ጋር መወያየት እና መነጋገር ይኖርባታል፡፡ በተጨማሪም አስፈላጊ ምርመራዎችን በማድረግ መቆጣጠር እና ሊታከም የሚገባው ችግር ካለ እነርሱን በመታከም፤ ብሎም ፎሊክ አሲድ በውሰድ ክፍተቱን መከላከል እንደሚቻል ይገልፃሉ፡፡

የህክምና አሰጣጡን በተመለከተ ዶክተር ታደሰ እንደሚመክሩት ከሆነ፣ ምንም እንኳን የነርቭ ዘንግ ክፍተቱ ከተከሰተ በኋላ የሚሰጥ ህክምና ይኑር እንጂ ከሁሉም በላይ የሚመከረው ግን ክፍተቱ ሳይከሰት በፊት አስቀድሞ መከላከል ነው፡፡ ለዚህም ፎሊክ አሲድ በምንመገባቸው ምግቦች ውስጥ ከመገኘቱ ባሻገር የሁሉንም አቅም በሚፈቅድ በርካሽ ዋጋ የቀረበ ሲሆን፤ አስቀድሞ በመውሰድ መከላከል እንደሚቻል ዶክተር ታደሰ ይናገራሉ፡፡

ክፍተቱ ከተከሰተ በኋላም ልዩነታቸውን እና ዓይነታቸውን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ህክምናውን እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ በተለይም ወደ ታችኛው የሰውነት ክፍል ነርቩን የከበበው ወደ ውጭ ካልወጣ ከተወለደ በኋላ በቀላሉ መዘጋት እንደሚቻል የሚናገሩት ዶክተር ታደሰ፣ በእኛ ሀገር ደረጃ ብዙ ኒሮሰርጅኖች ያሉ ሲሆን እነርሱም ይህንን መዝጋት ይቻላቸዋል ይላሉ፡፡ ባደጉት ሀገራት ደግሞ ጨቅላ ሕፃናቱ በእናታቸው ሆድ ውስጥ እያሉ በአምስት እና ስድስተኛ ወራቸው ላይ የጀርባ ዘንግ ክፍተት መኖሩ ከተረጋገጠ ሆድ ውስጥ እያለ የመዘጋት ዕድል አለው። በእኛ ሀገር ግን ሆድ ውስጥ እያለ የሚሰጠው ህክምና እንዳልተጀመረ ያስረዳሉ፡፡

ዶክተር ታደሰ እንደሚሰጡት ማብራሪያ፤ ከነክፍተቱ ለሚወለዱ ልጆች ሕክምናው ሀገር ውስጥም፣ ከሀገር ውጭም ያለ ቢሆንም ከህክምናው በኋላ ኢንፌክሽን ሊከሰት ይችላል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ከተዘጋ በኋላ ነርቭ የከበበው ወደ ውጭ ከወጣ እና ተመልሶ እንዲዘጋ ከተደረገ ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ እንደሆነ የሚገልጹት ዶክተር ታደሰ፤ በዚህም ምክንያት በጭንቅላት ውስጥ ውሃ መጠራቀም፣ እግራቸውን አለመቆጣጠር (አለመታዘዝ)፣ ሽንት እና ሰገራ ለመቆጣጠር መቸገርና የመሳሰሉት ያጋጥሟቸዋል። ለአእምሮ ዕድገት ውስንነት የመጋለጥ ዕድላቸውም ሰፊ ነው፡፡

ከኬንያ፣ ማሊ፣ ሞዛምቢክ እና ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ክፍተቱ ያለባቸው ጨቅላ ሕፃናት ቁጥር በእኛ ሀገር ከፍ ብሎ ይታያል ያሉት ዶክተር ታደሰ፣ ባደጉት ሀገራት ጨው፣ ዱቄት እና የመሳሰሉት ምርቶች ላይ ፎሊክ አሲድ እንዲጨመሩ አስገዳጅ ሕግ በመውጣቱ ቁጥሩ እንዲቀንስ አግዟቸዋል። በእኛ ሀገር ደረጃ ፎሊክ አሲድ ለመጠቀም (Folic Acid Fortification) አስገዳጅ መመሪያ ወጥቶ ተግባራዊ እንዲሆን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ እንዲሁም ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሚሠራበት ቻምፐስ ድርጅት እና ሌሎች ድርጅቶች ፎሊክ አሲድን በጨው፣ ዱቄት እና የመሳሰሉት ላይ እንዲጨመር ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። መመሪያው በሀገራችን ተግባራዊ ሲሆን፣ የታማሚው ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ እንደሚችል ተስፋ ማድረጋቸውንም ያስረዳሉ።

“አንዳንድ ሰዎች ስለነርቭ ዘንግ ክፍተት በፊት እንዳልነበር ወይም አዲስ ነገር እንደሆነ ሲያወሩ ይደመጣል፡፡ የእውነት አልነበረም ወይ?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶክተር ታደሰ “የነርቭ ዘንግ ክፍተት አሁን የተከሰተ ነገር አይደለም” የሚል ምላሽን ይሰጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ የደረሰበትን ደረጃ የሚያመላክቱ ጥናቶች ግን አልነበሩም፡፡ ሌላው ከዚህ በፊት አብዛኞቹ እናቶች የነርቭ ዘንግ ክፍተት ያለባቸው ልጆች ሲወልዱ እንደ ፈጣሪ ቁጣ ስለሚያዩት ልጆቻቸውን ይደብቋቸው እንደነበር በማውሳት፤ የፈጣሪ ቁጣ እና እርግማን ሳይሆን ከፎሊክ አሲድ እጥረት የሚመጣ እንደሆነ ሕብረተሰቡን ማስገንዘብ እንደሚገባም ይገልፃሉ፡፡

ዶክተር ታደሰ ጨምረው እንዳስረዱት፤ ጤነኛ ልጅ ማግኘት እናትም ልጅም ጤናማ እንዲሆኑ ያግዛል። ስለዚህም ጤነኛ እናት እና ልጅ እንዲኖሩ ከተፈለገ ባደጉት ሀገራት የተለመደውን የቅድመ እርግዝና ምርመራ በእኛም ሀገር ማስፋፋት ይጠበቃል። እርግዝና ከተከሰተ በኋላም ቢሆንም የእርግዝና ክትትል በማድረግ እናት እና ልጅ ያሉበትን ደረጃ መከታተል ይገባል፡፡ ቀጥሎም ህክምና ተቋማት ሄዶ በመውለድ የእናቶችን ሞት ከመቀነስ ባሻገር የልጆችን ጤንነት ለመጠበቅ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡

ቅድስት ወልደሰንበት በጤና ሚኒስቴር የሥርዓተ ምግብ ማስተባበሪያ ሥራ አስፈጻሚ ክፍል ውስጥ የመከላከል ተኮር ዴስክ ኃላፊ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በግልጽ የሚታወቅ መንስኤ ባይኖረውም ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ግን 75 በመቶ የሚከሰተው የነርቭ ዘንግ ክፍተት በፎሊክ አሲድ እጥረት እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡ ለተጓዳኝ በሽታዎች የሚወሰዱ መድሃኒቶችም ድርሻቸው ከፍተኛ ሲሆን፣ ለሚጥል ሕመም የሚወሰድ መድሃኒትን ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡

እንደ ጤና ሚኒስቴር፣ ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት መከላከል ላይ መሠራት እንዳለበት የሚታመን ሲሆን፤ እንደ ሥርዓተ ምግብ ማስተባበሪያ ክፍልም መከላከል ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን እየተሠሩ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ የነርቭ ዘንግ ክፍተትን ለመቀነስ አስቀድሞ መከላከል ላይ ቢሠራ ችግሩን በሚገባ መቀነስ እንደሚቻልም ጨምረው ያስረዳሉ፡፡

አንዲት እናት ከመጸነሷ በፊት አንድ ወር ቀደም ብላ እንዲሁም እስከ ሦስት ወር ድረስ የፎሊክ አሲድ እንክብል በመውሰድ የሰውነት ክብደትን (መጨመርም ሆነ መቀነስ) ማስተካከል እና የተመጣጠነ ምግብ መውሰድ አለባት ያሉት ኃላፊዋ፣ በተለይም ምግብን ማስተካል፣ ከሁሉም የምግብ አይነቶች አመሳጥሮ እና አመጣጥኖ መመገብ ይገባል፡፡ በፎሊክ አሲድ የበለጸጉ፣ እንደ ጎመን ያሉ ደማቅ አረንጓዴ ምግቦችን፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ፤ ከጥራጥሬ ደግሞ እንደ ምስር፣ ባቄላ እና አተር ያሉትን መመገብ ችግሩን ለመከላከል እንደሚረዳ ይመክራሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር ምግብን የማበልጸግ መመሪያ (Food Fortification) የተዘጋጀ ሲሆን፤ በመመሪያው መሠረት በምንመገበው ዘይት እና ዱቄት ላይ ጥቃቅን ማዕድናትን ጨምሮ ሌሎች ምግቦችን ማበልጸግ እንደሚገባ አስገዳጅ መመሪያ ተዘጋጅቶ መፅደቁን ይጠቁማሉ፡፡ እንዲሁም፣ ከቫይታሚን ኤ እና ቫይታሚን ዲ በሚመረቱ ዘይቶች ላይ፤ ፎሊክ አሲድን ደግሞ በዱቄት ላይ እንዲጨመር የሚያስገድድ ሕግ መውጣቱ ችግሩን ሊቀንስ እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡

በመመሪያ ደረጃ አሁን የተዘጋጀ ሲሆን፣ በቀጣይ ደግሞ በሁሉም የጤና ተቋማት “እንዴት ልንሰጥ እንችላለን” የሚለውን እየሠራንበት ነው ያሉት ቅድስት፤ አሁን ላይ በቤተሰብ ደረጃ ታቅዶ የተገኘ እርግዝና ለእናትም፣ ለልጅም፣ ለሀገርም ውጤታማነት ድርሻው ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የዴስክ ኃላፊዋ ቅድስት እንደሚያብራሩት ከሆነም፤ የነርቭ ዘንግ ክፍተት ላለባቸው ልጆች የሚሰጥ ህክምና አሁን ካለው ፍላጎት አንፃር በቂ ነው ብሎ ደፍሮ ለመናገር ያዳግታል፡፡ በሀገር ኢኮኖሚ፣ በጤና እና በሥነ ልቦና ላይ የሚያደርሰውን ችግር በመገንዘብ መከላከሉ ላይ እና የሰዎችን ግንዛቤ ከፍ የማድረግ ሥራ ከሁሉም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆን ይኖርበታል፡፡

በአጠቃላይ፣ እንደ ጤና ሚኒስቴር ችግሩ አሳሳቢ እየሆነ የመጣ መሆኑን በመረዳት ሕብረተሰቡ ስለነርቭ ዘንግ ክፍተት ምንነት እና እንዴት መከላከል እንደሚቻል የግንዛቤ ሥራ በሰፊው ለመሥራት ታስቧል፡፡ እንዲሁም ከዚህ በፊት ጥናት ተደርጎባቸው ቁጥሩ ከፍ ወዳለባቸው ክልሎች በመዘዋወር የግንዛቤ ማስጨበጥና መሰል ሥራዎች ይሠራሉ፡፡

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You