የኢትዮጵያየዲፕሎማሲ ሳምንት የሀገሪቱን ስኬታማ የዲፕሎማሲ ጉዞ አጉልቶ የሚያሳይ ነው

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት የሀገሪቱን ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ጉዞ አጉልቶ የሚያሳይ ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት ኤግዚቢሽን ከጥር ሁለት ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ “ከአፍሪካ መዲናነት እስከ ዓለም መድረክ” በሚል መሪ ቃል በሳይንስ ሙዚየም እንደሚከፈትም ተጠቁሟል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት በኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በኩል ዜጎችን ያማከለ የዲፕሎማሲ አገልግሎት እንዲረጋገጥ እየተሠራ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ሳምንት የሀገሪቱን ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ጉዞ አጎልቶ የሚያሳይ ነው፡፡

ከጥር ሁለት እስከ 24 ቀን 2016 ዓ.ም በሳይንስ ሙዚየም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰናዳው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት ኤግዚቢሽን ብዙ ዓላማዎች እንዳሉት የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ የኢትዮጵያን ያለፉ ዲፕሎማሲያዊ ድሎች እና ተግዳሮቶች ማሳየት፣ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ዲፕሎማሲያዊ መንገድ

 ማንጸባረቅ እና የዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴው የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሳየት የሚሉት ጥቂቶቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን እና የግዛት አንድነትዋን ያስከበረች ጥንታዊት ሀገር እንደመሆኗ ለመላው ጭቁን ሕዝቦች የነፃነት ዓርማ መሆኗን አውስተው፤ “በሊግ ኦፍ ኔሽን” የተወከለች ብቸኛ ነፃ አፍሪካዊት ሀገር ኢትዮጵያ እንደነበረች ተናግረዋል።

እ.ኤ.አ. በ1945 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች አባል እንደነበረች አስታውሰው፤ ኢጋድን በማቋቋም እና በመምራት ላይም ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና እንዳላት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ አፍሪካን በመወከል የአየር ንብረት ድርድርን መምራቷን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በአምስት ዓመታት ውስጥም ከ32 ነጥብ አምስት ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ለዓለም አርዓያ እየሆነች እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያላት የውጭ ግንኙነት በቀጣናው፣ በአህጉሩ እንዲሁም በዓለም ላይ አዎንታዊ ስሜት የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል ።

እንደ አምባሳደር ብርቱካን ገለጻ “ከአፍሪካ መዲናነት እስከ ዓለም መድረክ” በሚል መሪ ቃል የሚደረገው ኤግዚቢሽን ቀደም ሲል እና አሁን ያለውን የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ጎዞ የሚያሳይ ነው።

ኤግዚቢሽኑ አሳታፊ እና መረጃ ሰጭ መሆኑን ተናግረው የውጭ ጉዳይ ከተመሠረተ ጀምሮ ያሉትን የ116 ዓመታት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጉዞ በኤግዚቢሽኑ በብቃት ለማሳየት በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በኤግዚቢሽኑ ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው የዲፕሎማሲ ሥራዎች እና ፈተናዎች በተለያዩ መንገዶች እንደሚቀርቡ ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች እና ምሑራን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉበት የፓናል ውይይትም እንደተሰናዳ አመልክተዋል፡፡

ኤግዚቢሽኑ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ እና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አባላት ልዩ ዕድል ይፈጥራል የሚሉት አምባሳደር ብርቱካን፤ የማኅበረሰቡ አባላት ወደ ኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየም በመምጣት የሀገሪቱን ዲፕሎማሲያዊ ታሪክ እንዲያውቁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኤግዚቢሽኑ ማራኪ አቀራረቦች እና የበለፀጉ ይዘቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ወደ ሀገራቸው የመጡ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያንም ኤግዚቢሽኑን በመጎብኘት ስለ አገራቸው እንዲያውቁ እና በአዕምሮአቸው ውስጥ ዘላቂ ትውስታን እንዲያኖሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You