በፈተና የበረታ ማንነት

የአያት ልጅ…

የተወለደው ደቡብ ክልል ሆሳዕና ከተማ ነው:: ልጅነቱ ምቹ የሚባል አልነበረም:: ወላጆቹ በፍቺ የተለያዩት ገና ልጅ ሳለ ነበር:: ይህ እውነት ደስታ ይሉት ፈገግታን አሳጥቶታል:: የእሱ ልጅነት እንደ እኩዮቹ አይደለም:: እናት አባቱን ከጎኑ አድርጎ ‹‹እማዬ ፣አባዬ›› ሊል አልታደለም:: በየምክንያቱ ያዝን፣ ይከፋ ነበር::

መኮንን ሽፈራው በወቅቱ የአያት ልጅ ከመሆን ሌላ ምርጫ አልነበረውም:: የተሰበረ ቅስሙ ግን በዚህ ብቻ አልዳነም :: ከወላጅ ዕቅፍ አውጥቶ አያት እጅ ያደረሰው ሐቅ ከአንድ አላረጋውም:: ከሴት አያቱ፣ ወንድ አያቱ ቤት ይመላለስ ያዘ::

ወንድ አያቱ በሳልና በሃይማኖት ትምህርት የበቁ ናቸው:: የልጅ ልጃቸው ከፍ ሲል የእሳቸውን መንገድ እንዲከተል ይሻሉ:: ይህን ፍላጎት ለማጋባት የተከተሉት መንገድ ግን ለመኮንን የተመቸ አልሆነም:: እሳቸው ጥንት ያለፉበት መንገድ መከራ የሞላው፣ ስቃይ የዳሰሰው ነው:: ዕውቀት ለመቅሰም አገር ቆርጠው፣ ወንዝ ተሻግረው ሄደዋል:: ‹‹አኩፋዳ›› ይዘው በጫካ፣ በገደል፣ በዱር በበረሀው ተንከራተዋል:: ይህ እውነት የእሳቸው ዕድሜና ያለፉበት ጊዜ ነው ::

አሁን ደግሞ ሕጻኑ መኮንን ከሌላው ዘመን ቆሟል:: ከአያቱ በተሻለ የመኖር ዕድል አለው:: እንደጥንቱ ዕውቀትን ፍለጋ በየሀገሩ አይባዝንም:: ለመማር አገር ቆርጦ፣ ወንዝ አቋርጦ አይሄድም:: እንደአቅሙ የቀለም ትምህርት ከደጁ አለ:: አያቱ ግን ይህ አይገባቸውም:: እሱም በእሳቸው መንገድ ለፍቶ ፣ ጥሮ፣ ከስቶና ጠቁሮ እንዲያገኝ ይሻሉ::

ትንሹ መኮንን ተቸገረ:: ኑሮ በአያቱ ቤት አልደላውም:: ባልተመቸ መንገድ ትምህርት ቤት ገብቶ እንዲማር ተገዷል:: አሁን ባለበት ሕይወት ያሻውን መጠየቅ፣ ያማረውን መምረጥ አይችልም:: የተባለውን ያደርጋል፣ የታዘዘውን ይፈጽማል:: እንዲህ መሆኑ ወላጆቹን ለሚናፍቅ፣ ፍቅርን ለተራበ ታዳጊ እጅግ ከባድ ነበር::

የልጅ ጉልበት…

የትምህርት ሳምንቱ አልፎ ቅዳሜ ሲደርስ ለትንሹ መኮንን ሌላ ስቃይ ይሆናል:: እሱ ይህ ጊዜ ባይመጣ ይወዳል:: ሌቱን ሙሉ ሲያስብ፣ ሲተክዝ ማደር ልማዱ ነው:: ማለዳውን ወፍ ሲንጫጫ የአጎቱ ሚስት ከዕንቅልፉ ቀስቅሰው ገበያ ሲያንከራትቱት ይውላሉ ::

ቤት ሲመለሱ የልጅ አናቱ ከባድ ጭነት ተሸክሞ ሲንገዳገድ ይደርሳል:: ይህ ልማድ ሁሌም የቅዳሜ ገበያ ግዴታው ነው:: ያለእሱ የሳምንቱ ጓዝ አይጫንም:: ያለእሱ የቅዳሜ ገበያ አይታሰብም:: ይህ ይሆን ዘንድ የአያቱ ቤት ኑሮ በደንብና ሕግ ያዘዋል::

መኮንን ልጅነቱን ተሻግሮ ከፍ ማለት እስኪጀምር ሕይወቱ አልተቀየረም:: እንደወጉ እየተማረ ከአቅሙ በላይ ይሠራል:: ቅዳሜ ሲደርስ ገበያ ውሎ በአናቱ ዕቃ ይጫናል:: በየጊዜው የልጅነት ጉልበቱን ይከፍላል:: ትከሻው ጎብጦ አንገቱ እስኪዞር ፣ በድካም ይናውዛል:: ይህኔ ስልችት፣ ምርር ይለዋል::

መኮንን ይህ ሁሉ የሚሆነው ሰው ጠፍቶ እንዳልሆነ ያውቃል:: የአያቱ ቤት ግን ኑሮን በስቃይ እንዲገፋ ግዳጅ ጥሎበታል:: መኮንን ባልተመቸ ሕይወት ትምህርቱን እየተማረ ነው:: አስራ አንደኛ ክፍል ሲደርስ ግን በደሉን መቋቋም ተሳነው:: የእድሜው መብሰል አርቆ እያሳየ ብዙ አሳሳበው::

ሌት ተቀን ለራሱ ሕይወት ራሱ መወሰን እንዳለበት ያስብ ጀመር:: ውሎ አድሮ ተስፋ ሲቆርጥ፣ ሕልሙ ሲጠፋ ‹‹ትምህርቱ ቢቀርብኝስ ›› ሲል ወሰነ :: ውሳኔው አድሮ ውሎ አልተለወጠም ::

ግርግሩ …

ወቅቱ የንጉሡ ሥርዓት ተገርስሶ የደርግ መንግሥት የተተካበት ነበር :: የዘመኑ ንፋስ የነመኮንን ሀገር ሆሳዕናን ማናወጥ ጀምሯል:: አካባቢው በየምክንያቱ እየታመሰ ነው:: ግርግሩ ጠብ አጭሮ ቅንጣት ሰላም ጠፍቷል:: እሱና የአያቱ ቤተሰቦች ከዚህ ማዕበል አልዳኑም:: ችግሩ ሲገፋ፣ ሁኔታው ሲከፋ ስፍራውን ጥለው ሊወጡ ግድ አላቸው ::

የለውጡ ሰበብ መኮንንን ወደ አሰላ አደረሰው:: በዚህ ስፍራ በአንድ እህቱ ቤት በእንግድነት ተቀምጦ ጊዜውን አሳለፈ :: ውሎ ሲያድር ዝም አላለም:: በነበረው የትምህርት ማስረጃ ዘመኑ በሚፈቀደው ሥራ ሊወዳደር የቻለውን ሞከረ:: በየቦታው ማስታወቂያ እያነበበ ማመልከቻውን አስገባ:: ጊዜው በዘመድ አዝማድ የሚሠራበት ነው:: ያሰበው ሳይሳካ፣ ያቀደው ሳይሰምር ቀረ::

ማንነትን ፍለጋ …

አሰላና መኮንን ለወራት ያለሥራ ተፋጠጡ:: በእንግድነት ያለአንዳች ተግባር መቀመጥ የከበደው ወጣት አብዝቶ ተጨነቀ:: የልጅነቱ ስቃይ፣ ያለፈበት አስቸጋሪ የሕይወት መንገድ ውል እያለው ብዙ አሰበ:: መኮንን ቁጭ ሲልና ሲተክዝ ማንጎራጎር ይወዳል:: ግጥምና ዜማ ይጽፋል:: ድምፁን የሚሰሙ ብዙዎች ጆሮ ሰ ጥተው ያደምጡታል::

የዛኔ በትኩረት ከሚሰሙት መካከል የአንድ ሰው እይታ ከሌሎች የተለየ ሆነ:: ሰውዬው በወቅቱ አጠራር የአርሲ ክፍለሀገር ፖሊስ አዛዥ ነበሩ:: ሁሌም የመኮንን ችሎታ ባስገረማቸው ጊዜ ቀረብ ብለው አድናቆት ይቸሩታል:: ድምፃዊነቱን ከሚጽፈው ግጥምና ዜማ አስተያይተውም ለችሎታው የሚመጥነውን ዕቅድ ያስቡለታል::

አዛዡ በአድናቆት ብቻ አልቀሩም:: ሙያና ችሎታውን የሚያሳይበትን መንገድ ሽተው አቅጣጫውን ጠቆሙት:: መኮንን በአዛዡ ምሪት ተመላክቶ አዲስ አበባ ሲደርስ መገኛው ከፖሊስ የሙዚቃ ክፍል ሆነ:: ከመድረኩ ቆሞ መረዋ ድምፁን አሰማ:: በእጁ ያለውን ግጥምና ዜማ አስነብቦም ይዘቱን አስገመገመ ::

ድምፁን ሰምተው ችሎታውን ያስተዋሉ የተለመደውን አድናቆት ቸሩት:: እነ ተስፋዬ አበበ/ፋዘር/፣ የሳክስፎኑ ንጉሥ ጌታቸው መኩሪያ፣ ዕውቁ የትራምፔት ተጫዋች መኮንን መርሻ ስለእሱ እይታቸው መልካም ሆነ:: ከእነሱ በተቃራኒ የቆሙ አንዳንዶች የመኮንንን ችሎታ ላለማድነቅ ፊታቸውን ሊያዞሩ ሞከሩ:: እንጀራ ፈላጊው ወጣት ሁሉንም በበጎ አይቶ ተቀበለ:: ከግራ ቀኝ የሚሰጠውን አስተያየት ሁሉ በይሁንታ አለፈው ::

የስልሳ ብር ደሞዝተኛ…

በብዙ ውጣ ውረድ የልቡን መሻት ያገኘው መኮንን የሙዚቃ ክፍሉን በስልሳ ብር ደሞዝ ተቀላቀለ:: ሙዚቀኛው ወጣት የልቡ መሻት ደረሰ:: ፍላጎቱን ከሞላለት ሙያ መገናኘቱ እፎይታን ሰጠው:: አዲሱ ሙዚቀኛ ከታዋቂዎቹ ድምፃውያን ሒሩት በቀለ፣ ተስፋዬ በላይ፣ ካሳሁን ገርማሞ ታደለ በቀለ፣ ቱቱ ለማ ከመሰሉት ጋር በሙያው ሊሰለፍ ጊዜው ደረሰ:: መኮንን እነዚህን ስመጥሩዎች ባየ ቁጥር ነገውን እያሰበ ብሩህ ተስፋውን አለመ::

መኮንን በፖሊስ ሙዚቃ ክፍል እሱን ከመሰሉ ባለሙያዎች ጋር ሥራውን ቀጠለ:: ጆሮ ገብ ድምጹ በርካቶችን ቢስብ አድማጮቹ በዙ:: ስርቅርቅ ቅላፄው ከሙዚቃ ተዛምዶ ተወዳጅ መሆን ያዘ:: የሀሳቡ ቢሞላ ደስ አለው:: በውስጡ እፎይታ ተመላለሰ:: ደሞዙን እየቆጠረ ጥቂት ጊዜያትን ቆየ ::

ጊዜው የአብዮት ነው:: የዛኔ ስለደርግና ስለሀገር ከማቀንቀን ሌላ እንዳሻ መዝፈን አይቻልም:: ማንም ድምፃዊ ከልቡ ያለውን የፍቅር ዘፈን አውጥቶ ማዜም አይፈቀድለትም:: ‹‹ልዝፈን›› የሚል ካለም በጥንቃቄ ነው:: ብዙ ግዜ ግጥሙ እንደፀጉር ተሰንጥቆ በሌላ ሊተረጎም ይችላል:: ለባለሙያው ወቅቱ የሚያዘውን፣ ዘመኑ የዋጀውን ግጥም ከዜማ አዋዶ ለአድማጮች የማቅረብ ግዴታ ተጥሏል:: መኮንን እንደ ሙያ አጋሮቹ መስሎ ሥራውን ቀጥሏል::

ውሎ አድሮ ግን ፈተና አላጣውም:: ከቅርብ አለቆቹ የሚደርስበት በደል ሰላሙን አሳጣው:: ሕይወቱ ታወከ:: ስለመብቱ ‹‹እምቢ ባይ›› መሆኑ በበላዮቹ ዘንድ ጥርሰ አስነከሰበት:: አለቆቹ እንደዋዛ ዝም አላሉም:: ስለእሱ ሌት ተቀን መምከር ያዙ:: ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› ያሉ ኃላፊዎች ያሰቡትን ከማድረግ አልተዉም:: ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ርምጃ ወሰዱበት ::

የሚከፈለው ደሞዝ በግማሽ እንዲቀነስና ከሲቪል ወደ ውትድር መደብ እንዲዘወር ሆነ:: ይህን ተከትሎም በአስቸኳይ ወደ ኤርትራ ክፍለ ሀገር የናቅፋ ዘመቻ እንዲሄድ ትዕዛዝ ተሰጠው:: ባልተመቸ መንገድ ሥራውን የቀጠለው ወጣት በፈተናዎች መሐል ሊመላለስ ግድ አለው:: ሠርቶ እንዳይበላ፣ ለሚወደው ሙያ እንዳያድር ጋሬጣው በዛበት:: የሆነበትን ባወቀ ጊዜ ከልብ አዘነ:: ዕቅድ ውጥኑ ባሰበው መንገድ እንደማይሰምር ገባው::

በናቅፋ ተራሮች ስር …

መኮንን በተሰጠውን ውሳኔ ቢያዝንም ለትዕዛዙ ተገዛ:: በተመደበበት ስፍራ አቅንቶ ሦስት ዓመታትን በጽናት ቆየ:: አራተኛውን ዓመት ከመጀመሩ በፊት ግን ወደሚመለከተው ቀርቦ ጥያቄዎችን አነሳ:: እስካሁን የሠራው እንዳለ ሆኖ ወደ ሲቪል መደብ መቀየር እንደሚሻ አስታወቀ::

የመኮንን አቤቱታ በበጎ አልተወሰደም:: ከውትድርና ወደ ሲቪል ‹‹ካልቀየርኩ›› ማለቱ እንደወንጀል ታየበት:: በየደረሰበት ስሙ እየተነሳ ተወቀሰ፣ በበላይ ኃላፊዎቹ ዘንድ ሀሳቡ ተወገዘ:: ተስፋ አልቆረጠም:: ቀናት ቆጥሮ የጥያቄውን ምላሽ ጠበቀ:: የተሰጠው ውሳኔ ቁርጥ ያለ ነበር:: ለእሱ ከሚሊቴሪ ሌላ ቦታ እንደሌለና በተመደበበት ቦታ ሥራውን እንዲቀጥል ተነገረው::

በተሰጠው መልስ ንዴትና እልህ ውስጥ ገባ:: ጉዳዩን ይዞ እስከበላይ አመራሮች አደረሰው:: ሁኔታውን የሰሙና ወሬው ተጨማምሮ የተነገራቸው አዛዦች በግንባር ሲያገኙት ፊት ነሱት:: ጥያቄውን የሚቀበለው አካል አላገኘም:: ከቀናት በኋላ የደረሰው ምላሽ ደግሞ ሥራውን ጥሎ እንዲሰናበት የሚያረዳ ነበር::

ስለ መኖር …

መኮንን አሁን አንዳች ተስፋ የለውም:: አራት ዓመታትን ከቆየበት ሥራው ሲለቅ በእጁ በቂ ጥሪት አልያዘም:: ‹‹ለእኔ›› የሚለው ዘመድና ጎኑን የሚያሳርፍበት የአንገት ማስገቢያ የለውም:: ኑሮውን ለመምራት የመጀመሪያ ምርጫው በጥቂት ክፍያ ተማሪዎችን ማስጠናት ነበር::

ሥራውን ለቆ የጀማመራቸው ውሎዎች ለመተዳደሪያው አልበቁትም:: አንዱ ሲሞላ ሌላው እየጎደለ በኑሮው ተፈተነ :: እንዲህ በሆነ ጊዜ ግራ ገባው:: ጉልበቱ በሚፈቅደው ሊያድር ትከሻውን አስፍቶ የሸክም ሥራ ጀመረ:: መኮንን ሲጠሩት ‹‹አቤት ፣ሲልኩት ወዴት›› ማለትን ለመደው:: የትናንቱ ወጣት ድምፃዊ ወታደርነትን ርቆ ከወዛደርነት ተዋወቀ:: በላቡ ወዝ ሊኖር ዝቅ፣ ጎንበስ ይል ጀመረ::

መኮንን ለሥራ ካሉት ጉልበቱን አይሰሰትም:: የተሰጠውን ከአቅሙ በላይ ይሸከማል:: በየጊዜው ያለእረፍት ሲሮጥ፣ ሲባትል ይውላል:: የየእለት ሕይወቱ በመውደቅ መነሳት የተያዘ ነው :: ቢደክመውም፣ ውስጡ ቢዝልም ማረፍን አይሻም:: ያገኘውን ለመሥራት ጉልበቱን ይከፍላል:: ነጭ ላቡን ያፈሳል::

ይህ አይነቱ ልማድ ሮጦ ለሚያድረው መኮንን ፈተና መሆኑ አልቀረም:: ሸክም የበዛበት አካሉ ውሎ አድሮ በሕመም ተያዘ:: መነሳት መቀመጥ ተሳነው:: ወገቡን ጨምሮ እጅ እግሩ ተሳሰረ:: በድካም መላ ሰውነቱ ዛለ:: ቆይቶ የዲስክ መንሸራተት እንዳጋጠመው ቢያውቅም ምንም ማድረግ አልቻለም::ከእጁ ርጋፊ ሳንቲም የሌለው ሰው በስቃይ ተንገላታ::

መኮንን እንደምንም ራሱን አጠንክሮ ለመቆም ሞከረ:: እንዳሰበው አልተሳካለትም:: ሕመም የዞረው አካሉ ከዳው:: እጅ እግሩ ከእሱ አልሆን ቢል ያለ ምርጫ ከመንገድ ወደቀ:: ለነፍስ ያሉ የእጃቸውን ጣሉለት:: እሱን እየቀመሰ ሕይወቱን አሰነበተ::

ጥቂት ቀናት እየቆየ ራሱን ሊፈትሽ ሞከረ:: ለውጥ አላገኘም:: ሥራና ሕመም ያደቀቀው አካሉ መልሶ ከመሬት ዋለ:: ድኖ ተሸሎት አልተነሳም:: ጤናው ተስፋ የሚያጣልበት አልሆነም:: የነበረው እንደነበረ ቀጠለ:: ይህን ያዩ ልበ መልካሞች ከወደቀበት ስፍራ ላስቲክ ወጥረው ካርቶን አንጥፈው መኖሪያውን ሠሩለት::

ሕይወት በጎዳና…

መኮንን በላስቲክ ጎጆው ዓመታትን ዘለቀ:: ብርድና ፀሐይ፣ ክረምትና በጋ ተፈራረቁበት:: የሚሆንበትን በምስጋና ተቀብሎ ኑሮን ቀጠለ:: አብዛኞች በደሳሳዋ ታዛ ስር ስለወደቀው ጎልማሳ ማንነት አያውቁም:: ሁኔታው ባሳዘናቸው ጊዜ የእጃቸውን ይጥሉለታል::

ከቀናት በአንዱ አንዲት ሴት በድንገት ወደ እሱ የላስቲክ ጎጆ ደረሰች :: መቅደስ ማርዬ የምትባል ዘማሪ ናት:: ከጎዳና ወድቆ አካሉ የከሳ የጠቆረውን፣ ልብሱ አብዝቶ የቆሸሸውን፣ ሰው ባየች ጊዜ ውስጧ በኃዘን ተነካ:: ቀረብ ብላ መኮንንን አዋየችው:: አድማጭ ያገኘው ምስኪን አንደበቱ ተፈታ:: ከልጅነት አንስቶ ያሳለፈውን ሕይወት ተረከላት::

ይህች ሴት መኮንን አይታው ብቻ አልቀረችም:: ‹‹የወደቁትን አንሱ›› ወደተባለው የነዳያን መርጃ ማዕከል ደርሳ እውነታውን አስረዳች:: የማዕከሉ ቤተሰቦች ታሪኩን ሰምተው ወደ ስፍራው ባመሩ ግዜ መኮንን ከአንድ አጥር ጥግ ከተሠራች የላስቲክ ጎጆ ወድቆ አገኙት::

መኮንንና በጎ ፈቃደኞቹ ለመግባባት አፍታ አልፈጁም:: ሊወስዱት መምጣታቸውን ባወቀ ጊዜ በታላቅ ምስጋና ሀሳባቸውን ተቀበለ:: በማዕከሉ ገብቶ ጥቂት እንደቆየ ሕክምና ተጀመረለት:: አስቀድሞ ክፉኛ የተጎዳ አከርካሪው፣ በሕመም የተሸማቀቁ እግሮቹ መዳን አልቻሉም:: ክትትሉ ቢቀጥልም ቆሞ የመሄዱ ጉዳይ ተስፋ አስቆራጭ ሆነ::

ዛሬን …

ዛሬ መኮንን ሽፈራው በዚህ የበጎ አድራጎት ማኅበር ከአስራአምስት ዓመታት በላይ ቆይቷል:: ያለፈበትን ሕይወት መለስ ብሎ ባስታወሰ ጊዜ የማንነቱን ገፆች እየገለጠ ለሌሎች ይተርካል:: ሁሌም ማንም ሰው ምንም ቢገጥመው ማዘንና ማማረር እንደሌለበት መምከር ልማዱ ነው::

መኮንን ያለፈባቸው እሾሀማ መንገዶች ዛሬን መልሰው እንዲያደሙት አይሻም:: እሱ ‹‹ሰው ማለት ደስታና ኃዘንን ፣ ችግርና ፍስሐን ሊሸከም ግድ ይለዋል›› የሚል አቋም አለው:: መቼም የማይናወጥ ጽኑ አቋም ::

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You