‹‹ኢትዮጵያ በድርድሩ ላይ የአካሄድ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅባታል›› -አቶ ግርማ ባልቻ- ዲፕሎማትና ደራሲ

አቶ ግርማ ባልቻ በግብ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ ለስድስት ዓመታት በዲፕሎማትነት አገልግለዋል። ከዚያ በፊትም በዜግነትና የኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት ውስጥ በተለያዩ የሥራ መደቦች ለሀገራቸውን ግልጋሎት ሰጥተዋል። እኚህ ዲፕሎማት ከግብጽ ተልዕኳቸው መልስ “ናይልና እና የግብጽ ኢኮኖሚያዊ ይዞታ ከትናንት እስከ ዛሬ” የሚል መጽሐፍ አሳትመው ለንባብ አብቅተዋል። አዲስ ዘመን ጋዜጣ በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ እየተካሄዱ ያሉትን ድርድሮችና በተለይም 4ኛው ዙር ውይይት ያለ ውጤት መጠናቀቅን አስመልክቶ ቃለ ምልልስ አድርጎ እንዲህ አቅርቧል።

አዲስ ዘመን፦ በሕዳሴ ግድብ ድርድር ወቅት በግብጾች በተደጋጋሚ ከሚነሱ የመከራከሪያ ጥያቄዎች ውስጥ ታሪካዊ የውሃ መብት የሚለው ይነሳል፡፡ ለመሆኑ ግብጾች ታሪካዊ መብት የሚሉት ምን ማለት ነው?

አቶ ግርማ ፦ ግብጾች በዓባይ ወይም በናይል ላይ አለን የሚሉት ታሪካዊ መብት እንግዲህ ባለፉት መቶ ዓመታት ውስጥ በተለይም ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ጀምሮ ናይልን አስመልክቶ ያወጧቸው ሕጎች ናቸው። ለምሳሌ 1929ኙ ስምምነት የሚባለ አለ:: ይህ ስምምነት በውሃ አጠቃቀሙ ላይ ሙሉ መብቱን የሚሰጠው ለግብጾች ነው። በመሆኑም እነዚህን ሕገ ወጥ የሆኑ የተፋሰሱን ሀገሮች በሙሉ ያላሳተፈ በተለይም ኢትዮጵያ ደግሞ የሁነቱ አካል ያልሆነችበት ስምምነትን መነሻ በማድረግ ነው እንግዲህ ታሪካዊ ባለመብት ነን የሚሉ ሃሳቦችን እያራመዱ ያሉት።

ከዚህ በመነሳትም ቀደም ካለው ጊዜ ጀምሮ ውሃው ላይ ሙሉ ባለመብት ነን የሚል የኮሎኒያሊስት አስተሳሰብ ሲያራምዱ ቆይተዋል። ለዘመናት ይህንን ሃሳብ ይዘው ወደ ክርክርና ድርድር አውድ ይውጡ እንጂ ዓለም አቀፉ ሕግም ግን የሚቀበለው አይደለም።

አዲስ ዘመን፦ በ1929 እና በ1959 በተፈረሙት ውሎች ላይ ኢትዮጵያ የነበራት ሚና ምንድን ነበር? እንዴትስ ይገለጻል?

አቶ ግርማ ፦ ይህ ስምምነት አንደኛ ደረጃ ሁለት ወገኖች ያደረጉት ነው፡፡ ሁሉም ባለመብቶችም ተካተውበታል ማለት አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያን ያላሳተፈ ውል ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ መብት ሊኖረው አይችልም፡፡ ኢትዮጵያም የምትከተለውን ክርክር አሳማኝ የሚያደርገው አንዱ ቅድመ ሁኔታም ይህ ነው።

በወቅቱ እንግሊዞች በቅኝ ግዛት የያዙት ግብጾችን ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ራሷን በራሷ የምታስተዳድር በማንም ቅኝ ግዛት ውስጥ ያልነበረች ነፃ ሀገር ነበረችና ስምምነቱ እሷን አይመለከትም ነበር። በሌላ በኩልም የ1959ኙ ስምምነት በግብጽና በሱዳን መካከል የተደረገ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ቀደም ብላ ነው የማይመለከታት መሆኑን ያሳወቀችው።

በእነዚህ ምክንያቶች ሁለቱም ስምምነቶች ኢትዮጵያን ሊገዙ የማይችሉ እና ስምምነቱንም ልታከብር የማትገደድ መሆኑም ሊታወቅ ይገባል። በመሆኑም ሕጎቹ ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው እንደውም ሕገ ወጥነታቸው ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የውሃውን ዋነኛ ምንጭ ሀገር አግልሎ መስማማት ዘለቄታዊ ያልሆነ ከመሆኑም በላይ ሕጋዊነትም ስለሌለው ነው።

አዲስ ዘመን፦ ስለዚህ በግብጽ በኩል እነዚህ ወሎችና ስምምነቶች በመከራከርያነት የሚነሱት ድርድሩን ለማደናቀፍ ነው ብሎ ማለት ይቻላል?

አቶ ግርማ ፦ እኔ የሕዳሴውን ግድብ ድርድር የማየው አጀንዳ መቀየሪያ አድርጌ ነው። ይህ ድርድር የመጣው 2010 የተፈረመው ሁሉን አቀፍ ስምምነት (የተፋሰሱ ሀገሮች) የሚተዳደሩበት ነው። ይህ መድረክ ግብጾች የተሸነፉበት ሲሆን በወቅቱም ሱዳንና ግብጽ ከስምምነት ማዕቀፉ ወጡ። ሌሎቹ በግላቸው ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ አሁን ደግሞ በተደጋጋሚ የሚያደርጉት ነገር ይህንን ተሸንፈው የወጡበትን ስምምነት ለማፍረስ እና አጀንዳ ለማስቀየር የሚያደርጉት ጥረት እንጂ የግድቡ ግንባታ ይህንን ያህል ትልቅ አጀንዳቸው ሆኖ አይደለም።

መጀመሪያ ሲጀምሩትም ውሸታቸውን ነበር፤ ነገር ግን በተለይም እኛን በዚህ መልኩ አታካች በሆነ የድርድር ሂደት ውስጥ አስገብተውንና አስረውን ከቻሉም ደግሞ ሃሳባችንን አስቀይረው ወደመስመራቸው በማስገባት ሊያስፈርሙን ነበር ፤ በጠቅላላው ግን ስምምነቱ ዝም ብሎ ጊዜ መግዢያ ነው። በመሆኑም ከተጀመረ ጀምሮ ስኬት የማይታይበት በጣም እያዘገመ ያለው ያን ያህል ውስብስ ነገር ስላለው ሳይሆን አጀንዳው ሌላ ስለሆነ ነው።

በጠቅላላው ግን ድርድር ድርድር እየተባለ የሚደከመው ነገር በግብጾች በኩል ጊዜ መግዢያ እንጂ ሌላ ውጤት የሚያመጣ ካለመሆኑም በላይ በተለይም እኛን ከመሠረታዊ ነገር አውጥቶን ቅርንጫፍ ላይ እንድናተኩር ለማድረግ ነው።

አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተያዘች ብሎም እነሱ የሚያነሷቸው ስምምነቶች ላይ እጇን ያላስገባች ከመሆኑ አንጻር ይህንን ውል የመቀበል ግዴታ አለባት?

አቶ ግርማ ፦ በፍጹም ይህንን ለማስገደድ የሚችሉበት ምንም ዓይነት የሕግ መሠረት የላቸውም። የሕግ መሠረት ስለሌላቸውም እንዲሁ በድርድሮች ወቅት በማንሳት ላለመስማማት ምክንያት ያደርጉታል እንጂ አንድም ቀን ፍርድ ቤት ይዘነው እንሂድ ብለው አያውቁም።

ብዙ ጊዜ ሀገሮች መሰል ችግሮች ሲገጥሟቸው ወደዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ነው የሚሄዱት እነሱ ግን ያንን መንገድ ሲከተሉ አናይም። ይህ የሚያመለክተው ጉዳዩ ምንም ዓይነት የሕግ መሠረት እንደሌለው ነው፤ ልቦናቸውም ጠንቅቆ ያውቀዋል።

አዲስ ዘመን፦ ይህ መሰሉ አካሄድ አሁን ባለው ሁኔታ ለግብጾች ያዋጣል ብለው ይላሉ?

አቶ ግርማ ፦ እውነቱን ለመናገር ምንም የሚያዋጣቸው ነገር የለውም። እንደውም ተጎጂ ነው የሚሆኑት፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ በተሳካ ሁኔታ የግድቡን ግንባታ ወደማጠናቀቁ ደረጃ ተቃርባለች። በተፋሰሱ ውስጥም እንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክት ተሰርቶ አልቆ አያውቅም። በመሆኑም ፕሮጀክቱ ለሌሎች ሀገሮችም ዓይን ገላጭ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ሌሎች ግድቦችንም የመገንባት አቅም እንዳለን ከማሳየታችንም በላይ ሌሎች ሀገሮችም ልክ እንደ ኢትዮጵያ መሥራት ይቻላል ለካ ብለው ሞራል እንዲሰማቸው አድርጓል።

አዲስ ዘመን፦ በፈረንጆቹ 2015 ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የተፈራረሙት የመርህ ስምምነት ምንድን ነው፤ ይህ ስምምነትን ለመተግባር ግብጾች አሻፈረኝ ያሉት ለምንድን ነው?

አቶ ግርማ ፦ የመርህ ስምምነቱ አንዱ ኢትዮጵያን የመጥለፊያ ሴራ ነበር። ሲጀመር የነበረው ዓላማ ኢትዮጵያን ስህተት ውስጥ ከቶ ውል በማስፈረም የራሳቸውን ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ ያሳዩት ፍላጎት ነው። በፊትም እኔ እዛ ሀገር ዲፕሎማት ሆኜ በሰራሁበት ወቅት ሳስተውል ኢትዮጵያ አንድም ፊርማ ፈርማልን አታውቅም ይሉ ነበር። ከዚህ አንጻር እኛን በማናቸውም ነገር ላይ ፊርማችንን እንድናኖር ማድረግ መቻል እንደ ትልቅ ድል ነው የሚያስቡት። በመሆኑም ይህ ስምምነት ሲፈረም የራሱ ድክመት ቢኖርበትም ለኢትዮጵያም መጠነኛ እውቅናን የሰጠ ነው። ነገር ግን መጀመሪያ የነበረበትን ዓላማ ስቶ ከፍላጎታቸው ውጭ ሄዷል:: በዚህም ሲጀምሩት በነበረው ሁኔታ ማጠናቀቅ አልቻሉም።

እውነት ለመናገር የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድኖች ይህንን የመሰለ ሴራ ማክሸፋቸው በጣም ትልቅ ነገር ነው። እዚህ ላይ ባብራራው አንደኛ ሕጋዊ መሠረትን እንዳይዙ አድርገናቸዋል፤ አስገዳጅ ነገሮቹም ያን ያህል ጠንካራ አልሆኑም፡፡ በዚህም እነሱ ሊያደርጓቸው ለሚፈልጓቸው ነገሮች መሳሪያ ሊሆንላቸው አልቻለም።

በጠቅላላው ግብጾች ይህንን ስምምነት ለመፈረም ባይፈልጉም እንኳን ኢትዮጵያ መስማማቷ ለሌላ ሴራቸው የሚመቻቸው መስሏቸው ይህንን ከፈረመች ሌላውንም ትቀበላለች በሚል ነው ፊርማ ውስጥ የገቡት። ነገር ግን ቀጥሎ የመጣው የድርድር ሂደት ግን ኢትዮጵያ ወጥመዱ ውስጥ ስላልገባችላቸው ስምምነቱ ጥቅም አልባ ለመሆን ችሏል።

በዚህ ስምምነት አልሳካ ሲላቸውም የአሜሪካን መንግሥት አስተዳደርን በማግባባት ኢትዮጵያን ማስገደድ ውስጥ ገቡ፡፡ በጸጥታው ምክር ቤት በኩል መግባትና የመሳሰሉትን ተግባራት ቢፈጽሙም እስካሁን ድሉ የኢትዮጵያ ከመሆን አላለፈም፡፡

አዲስ ዘመን፦ የሕዳሴውን ግድብ ጉዳይ በቅርበት እንደሚከታተል ዜጋ እስከ አሁን የመጣንበትን የድርደር ሂደት ጠቅለል አድርገው ሲመለከቱት ምን ዓይነት ሥዕል ይፈጥርቦታል?

አቶ ግርማ ፦ ለእኔ ሀገሬ ብዙ ዓለም አቀፋዊ የድርደር ልምድ የሌላት ከመሆኑ አንጻር ትልቅ ትምህርት እንደ ሀገር ያገኘንበት ሆኖ ይሰማኛል። ሀገራችን በታሪኳ እንደዚህ ዓይነት ድርደር ውስጥ ገብታ የማታውቅ እንደመሆኗ ይህ ሂደት በጣም ትልቅ እንዲሁም ተግባራዊ ልምድ የቀሰምንበት ነው።

 በሌላ በኩል ልምድ መቅሰሙ ትምህርት ማግኘቱ እንዳለ ሆኖ ብዙ ጊዜ የባከነበት ነው። ይህንን ያልኩበት ዋናው ምክንያት ድርድር የሁለት ወገኖችን ፍቃደኝነት የሚፈልግ ነው። እነሱ ግን በውስጣቸው ተንኮል ሴራ ይዘው የሚመጡ ከመሆናቸው አንጻር ስናየው የባከነ ጊዜም ሆኖ ይሰማኛል። ያም ሆነ ይህ ግን ድርድሩ ሂደቱ አሰልቺና ጊዜ ጨራሽ ቢሆንም እኛ ደግሞ የግድብ ግንባታ ሥራችንን ጎን ለጎን የሰራንበት በመሆኑ አትርፈናል ባይ ነኝ።

አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ በድርድሩ ላይ የአካሄድ ለውጥ ማድረግ አለባት የሚሉ ወገኖች አሉ፤ በዚህ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ ?

አቶ ግርማ ፦ ይህ በጣም ጥሩ ነጥብ ነው። ኢትዮጵያ አሁን ላይ በድንበር ተሻጋሪ የውሃ ድርድር ላይ በቂ ትምህርትና ልምድ ወስዳለች፤ ከዚህ ቀጥሎ የስትራቴጂ ለውጥ ማድረግ በጣም ያስፈልጋታል። አሁን ባለው ሁኔታ እነሱ ሲፈልጉ ይቀላቀላሉ ካልፈለጉ ይተውታል፡፡ በዚህ መንገድ መቀጠል አዋጭ አይደለም። በነገራችን ላይ አሁን በሰሞኑ ድርድር ስብሰባ ረግጠው ሲወጡ ምናልባትም ለአራተኛ ጊዜያቸው ይመስለኛል። በመሆኑም በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ አዋጭ ባለመሆኑ አሁን ላይ የድርድር አጀንዳችንን መቀየር ይገባናል።

የድርድሩ አጀንዳ ቢሆን ብዬ የማስበው በሁለት ነገሮች ላይ ነው። አንደኛው በተፋሰሱ ሀገራት ውስጥ በተጨባጭ እየሆነ ያለው ነገር ምንድን ነው፤ ግብጽ ምን እያደረገች ነው? የሚለውን አይቶ አቅጣጫን ማሳመር ያስፈልጋል።

እዚህ ላይ ብነግርሽ ግብጽ እኤአ ከ2021 ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የግብርና ልማት በመላ ሀገሪቷ እየሰራች ነው። በዚህም በረሃውን ከ45 ኪሎ ሜትር በላይ በማቋረጥ በሰው ሠራሽ ውሃ መተላለፊያ በመጠቀምና ሐይቅ በመስራት ከፍ ያለ የልማት ሥራን እያከናወነች ትገኛለች። ይህ እንግዲህ የሚሰራው የሌሎች ሀገሮችን ጠይቃ ይሁንታን ሳታገኝ ፤ ስምምነት በሌለበት የተፋሰሱ ሀገሮች በውሃ አጠቃቀማቸው ላይ ተጨባጭ የሆነ ውሳኔ ላይ ሳይደርሱ የምትሰራው ሥራ ነው።

በአንጻሩ ግን ይህንን ሁሉ ጊዜ የደረሰ ድርድርና ንግግር እየተደረገ ያለው ኢትዮጵያ ሳታማክረንና ሳታስፈቅደው ግድብ ገነባች የሚል ነው። የእኛ ግድብ ግን ኤሌክትሪክ አመንጭቶ መሄድ ነው ሥራው፤ ውሃን አናስቀርም፤ እነሱ ግን ከዚህ አልፈው የውሃ እጥረት እያለ ሌሎች ሀገሮች መጠቀም ሳይጀምሩ እየተሽቀዳደሙ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በመሥራት ነገ ለሚያነሱት ቅድሚያውን የያዝነው እኛ ነን ለሚለው ሃሳባቸው መደላድል እየፈጠሩ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር እየሰሩ ያሉት ሥራ ሕገ ወጥ ነው፤ ምክንያቱም ውሃውን መጠቀም የሚችሉት እዛው ተፋሰሱ ዙሪያ እንጂ አውጥቶ መጠቀም ሕጉ አይፈቅድላቸውም።

ለምሳሌ እኛ እንጦጦ ተራራን ቆፍረን ዓባይን ወደዚህ እንዲፈስ ማድረግ እንችላለን፤ ነገር ግን ይህ አካሄዳችን ከተፋሰሱ ሕግ ውጭ ስለሚያወጣን አልፎም በዓለም አቀፍ ሕጎች ጥያቄ ስለሚያስነሳ ይህንን ማድረግ አንችልም፡፡ ግብጾች ግን በማናለብኝነት እየሰሩ ያሉት እሱ ነው፡፡

ይህ ብቻ አይደለም ግብጽ ውስጥ “ቶሺካ ዲፕረሽን” የሚባል አለ። ሥራው ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከፍተኛ የሆነ የልማት ማስፋፊያ ሥራ እየተከናወነ ነው። ለዚህ ሥራ ውሃ እየተጠለፈ የሚወጣው ደግሞ ከናስር ግድብ ላይ ነው። ይህ አካሄድ ደግሞ ሕገ ወጥ ነው።

የሌሎች ሀገራት እርሻዎችንም በአሁኑ ወቅት ትልቅ በጀት መድበው እየሰሩ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ሲጠቃለል ግብጾች አሁን ላይ እያከናወኗቸው ያሉት ፕሮጀክቶች የሕዳሴውን ግድብ እጥፍ እንደውም ሁለት ሕዳሴ የሚያህል ነው። ውሃው ደግሞ ከግድቡ አውጥቶ ወደሌላ አቅጣጫ አዙሮ የግብርና ሥራን ለማስፋፋት ማለት ነው።

እንደዚህ ዓይነት ሕገወጥነት ከመስፋፋቱ አንጻር እኛ ማድረግ ያለብን በሕዳሴው ግድብ መጨቃጨቅ ሳይሆን እያደረጉ ያሉት ሕገወጥ ተግባር ያቁሙ ማለት መቻል ነው። ይህ ውሃን ከተፈጥሯዊ ጉዞው አውጥቶ የመቀራመት ነገር ተጠያቂነት እንደሚያስከትል ማወቅ አለባቸው።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የውሃው ምንጭ እንደመሆኗ ሕጋዊ ጥያቄን መጠየቅ መቻል አለባት። በተፋሰሱ ውስጥ እየተካሄደ ያለው የውሃ ብክነት ግብጽ እያካሄደችው ያለው ሕገ ወጥ ርምጃዎች በባለሙያ በተጠና ሁኔታ ጥያቄ ሆነው ሊነሱ ይገባል። እንደ ባለመብት እኛ አጀንዳ ተቀባይ ብቻ ሳንሆን አጀንዳንም ፈጣሪ የመሆን አቅማችን ሊጠናከር ይገባዋል። በድርድር መድረኩ ላይም ተጽዕኖ ማሳደር የምንችለው እኛ የራሳችንን አጀንዳ ይዘን መቅረብ አዳዳስ ሃሳቦችን ማመንጨት ስንችል ብቻ ነው። በጠቅላላው ከተከላካይነት ወጥተን ወደአጥቂነት መሸጋገር አለብን።

በመሆኑም ከዚህ በኋላ እኛ እንደ ሀገር ማድረግ ያለብን የአካሄድ ለውጥ ነው። እስከ አሁን ለግብጽ ጥያቄዎች መልስና ማስረጃ እየሰጠን 11 እና 12 ዓመት ከንቱ ጊዜን አባክነናል። ከዚህ በኋላ ግን ግብጽ እኛን በጥያቄ ወጥራ ይዛ ምን እያከናወነች እንዳለች? በውሃ እየተጫወተች መሆኑን መረጃዎችን ማሻተትና መፈለግ አስጠንተንም ለግብጾች እራስ ምታት መሆን መቻል አለብን።

አሁን ላይ ግብጾች የምግብ ምርት ፍላጎታቸውን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በሀገር ውስጥ ለመሸፈን ከፍተኛ ሠራን እየሠሩ ነው፤ በዚህም ከዓሣ ጀምሮ ጥራጥሬዎችን አትክልትና ፍራፍሬን በማምረት አስገራሚ ግስጋሴ ላይ ከመድረሳቸውም በላይ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡትን ፍጆታ ቀንሰው ወደውጭ የሚልኳቸውን ምርቶች በመጨመር ላይ ናቸው። ይህ መልካም የሚሆነው በራሷ ሀገር ላይ በሚፈስ ወንዝ ቢሆን ነበር፤ አሁን ግን ከእኛ በሚመጣ ውሃ የተፋሰሱን ሀገራት ሳያማክሩ መጠቀም ግን ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ በጠቅላላው እኛም እንደ ሀገር በፍጥነት የስትራቴጂ ለውጥ ያስፈልገናል።

ከዚህ ቀደም እኤአ በ2015 የተፈረመውን ስምምነት እስከ አሁን አራት ሀገሮች ፈርመው በሀገራቸውም ሕግ አድርገውታል፤ በመሆኑም አሁን ላይ ያልፈረሙ ሀገራት እንዲፈርሙ በማድረግ እንደ ተቋም ዳግም እንዲደራጅና ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ እንዲወጣ በተለይም እኛ ቀድመን መሥራት አለብን። ምክንያቱም በተፋሰሱ ውስጥ ትልቁን ውሃ አበርካቾች እንደመሆናችን።

ሌላው ውሃ የሚጋሩ ሀገሮች ውሃውን በፍትሃዊነት መከፋፈል መቻል ይኖርባቸዋል። በዚህም ሱዳንና ግብጽ ብቻ ተካፍለውት ያለው የውሃ መጠን በተፋሰሱ ሀገሮች መካከል እንዲሰፋ የሚያደርገውን አጀንዳ ወደ ድርድሩ ማቅረብ ይኖርብናል። ይህ ደግሞ እነሱ በጣም የማይፈልጉትና የሚፈሩት ጥያቄ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ዋና አጀንዳ ሆኖ ወደመድረኩ ሊመጣ ይገባል።

አዲስ ዘመን፦ ጉዳዩን በቅርበት እንደሚከታተል ዜጋ ቢሆን ብለው የሚመኙትስ ነገር ምንድን ነው?

አቶ ግርማ፦ በነገራችን ላይ የዓባይ ውሃ የግጭት የንትርክ የተንኮልና የሴራ ምንጭ ከሚሆን የልማትና የትብብር መንገድ ቢሆን ኖሮ ብዙ የተፋሰሱን ሀገራት በእድገት እንዲመነጠቁ የሚያደርጉ ስኬቶች ይመጡ ነበር። ወደፊትም ውሃውን የልማት፤ የእድገት የሌሎች ትብብሮቻችን ሁሉ መነሻ እርሾ ብናደርገው ምኞቴ ነው።

የተፋሰሱ ሀገራትም ተባብረው የጋራ ፕሮጀክቶችን እየሰሩ ወንዙንም የተፈጥሮ ጉዳት እንዳይደርስበት በመንከባከብ ግንኙነታቸውን ማጠናከርና ሌሎች ግንኙነቶቻቸውን ለማሳደግ ቢጠቀሙበት ጥሩ ነው።

አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።

አቶ ግርማ ፦ እኔም አመሰግናለሁ

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You