ኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር በቁርጠኝነት በመሥራት ላይ ትገኛለች። ይህንንም እውን ለማድረግ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ቀርጻ ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች። ስትራቴጂው ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ በርካታ ለውጦች እያስመዘገበ ይገኛል።
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለማሳለጥ የዲጂታል ልማቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው እንደመሆኑ መጠን ተደራሽነቱን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የአጋሮች ድጋፍና እገዛ ያስፈልጋል። በተለይም በዘርፉ ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ ያላቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ በእጂጉ አስፈላጊ እንደሆነ ይገለፃል።
በቅርቡም ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለመደገፍ ማይክሮ ሶፍት ኩባንያ ያለውን ፍላጎት አሳይቷል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የማይክሮ ሶፍት ኩባንያ የዲጂታል ልማትና ተደራሽነት ማስፋት የሚያስችሉ ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት ሰሞኑን ምክክር አድርገዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ዲጂታል ልማትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ፕሮግራም ተቀርፆ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉት፤ በ2025 ዓ.ም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ዕቅድ ተይዞ ትግበራዎች እየተፋጠኑ ነው። የዲጂታል ጉዞ ኢትዮጵያ ያለችበትን አቅምና አቋም አጉልቶ የሚያሳይ ነው። በዚህ ሂደት የአጋሮች ድጋፍና እገዛ የላቀ ትርጉም አለው።
በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን እውን ለማድረግና በተለይም የፋይናንስና የአገልግሎት ዘርፉን ለማሳለጥ የዲጂታል ልማት የማይተካ ሚና እንዳለው የገለጹት ዶክተር በለጠ፤ ለዚህም ከማይክሮ ሶፍት ኩባንያ ጋር በሥልጠና እና ተያያዥ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ዙሪያ በጋራ መሥራት መቻሉ ለስኬቱ ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘመን የመሪነት ሚና እንድትጫወት ለማድረግ ሀገሪቱን ወደ ፈጠራ እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ለመምራት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተጨማሪም ሀገሪቱ አካታች እና የበለጸገ ዲጂታል ጉዞን ለማረጋገጥ ከማይክሮሶፍት ኩባንያ ጋር የዲጂታል ልማት ፕሮግራም ማዕቀፍ ተጠቃሚ እንድትሆን በትብብር እንደሚሰራ አመላክተዋል።
በማይክሮሶፍት ኩባንያ የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ ልማት አስተባባሪ አሌክሳንደር ጆሴ ፒንሆ በበኩላቸው የማይክሮሶፍት ኩባንያ የተለያዩ የልማት ዘርፎችን የሚያዘምኑ ቴክኖሎጂዎችና መተግበሪያዎችን በማምረት ሥራን በማቃለልና በማፋጠን የላቀ አበርክቶ ያለው መሆኑን ይናገራሉ። በመሆኑም በኢትዮጵያ በዲጂታል ልማት እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን በማገዝና ግንዛቤ በመፍጠር የሚያደርገው እገዛ ትርጉም የሚኖረው እንደሆነ ገልጸዋል።
የዲጂታል ልማት ፕሮግራም ቴክኒካል ክህሎት፣ ዲጂታል አገልግሎቶች እና የአቅም ግንባታ ስልጠና መሳሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን በማቅረብ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ሀገራት በመርዳት ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል። በኢትዮጵያም የተጀመረውን የዲጂታል ልማት ዕውን ለማድረግም የአቅም ግንባታና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
አስተባባሪው አሌክሳንደር ‹‹የዲጂታል ልማት ፕሮግራም እንደ ትምህርት፣ ጤና አጠባበቅ እና የሕዝብ አገልግሎቶችን የመሳሰሉ ቁልፍ ዘርፎችን በመለወጥ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። የዲጂታል ክፍተቶችን ለመቅረፍ፣ ማንበብና መጻፍን ለማጎልበት እና ፈጠራን እና ሥራ ፈጠራን ለማጎልበት አስፈላጊውን መሠረተ ልማት ለማቅረብ የሚያግዝ ነው›› ብለዋል።
የኢኖቪሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አማካሪ አብዮት ባዩ (ዶ/ር) በበኩላቸው በተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ላይ ማይክሮ ሶፍት ኩባንያ ሀገራትን በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ረገድ ለመርዳት ቃል ገብቶ እንደነበር አስታውሰው፤ በዚህም ኩባንያው አምስት ሀገራት መምረጡን ጠቅሰው፤ ከእነዚህ ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗንና በጋር ለመሥራት በሚችሉበት ሁኔታዎች ላይ ውይይት እንደተደረገ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት የዲጂታል ስትራቴጂን በመተግበር ላይ የምትገኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ስትራቴጂ እውን ለማድረግ ደግሞ የመንግሥት ጥረት ዋንኛ ቢሆንም የተለያዩ የልማት አጋሮች በዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑ ላይ እንዲሳተፉ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
‹‹የምክክር መድረኩን ማዘጋጀት ያስፈለገበት ዋንኛ ምክንያት ኢትዮጵያ አሁን ላይ ምን ላይ እንደምትገኝና ማይክሮሶፍት ኩባንያ ደግሞ በምን ሊያግዝ እንደሚችል የሚያመላክቱ ሃሳቦችን ለማቀናጀት ታስቦ ነው። ማይክሮሶፍት ኩባንያ ድጋፍ የሚያደርገው የዲጂታል ስትራቴጂውን መሠረት በማድረግና አዳዲስ እድገቶችን ተከትሎ ያሉ ነገሮችን መሠረት በማድረግ ነው›› ብለዋል።
ዶክተር አብዮት እንደሚሉት፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ውስጥ የተሰሩ ሥራዎች በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል ተገምግመዋል። ከማይክሮሶፍት ጋር ወደ ሥራ በሚገባበት ጊዜ አካታች የሆነ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመመስረት፣ ለአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽና የሌሎች የልማት እቅዶችን መደገፍ ላይ በትኩረት የሚሰራ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማምጣት የሚሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ይህን ለማምጣት ደግሞ የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት አካታች እንዲሆን መሥራት ይገባል ነው ዶክተር አብዮት ያሉት። እሳቸው እንዳሉት፤ አካታች ሲባል ሁሉም ሰው እኩል የማደግ መብትና እድል እንዲኖረው ማድረግ ነው። ይህንን ለማስፈጸም በስትራቴጂው የተቀመጡት ነገሮች በርካታ አሉ። እነዚህም መሥሪያ ቤቱ በቀጥታ ፕሮጀክት ቀርጾ የሚያከናወናቸው እና ሌሎች ደግሞ በሌላ ተቋማት የሚከናወኑት ተግባራት ናቸው። በመሆኑም መሥሪያ ቤቱ የዲጂታል ልማቱን የማቀናጀት ሥራን በመሥራት በመሠረታዊነት ትኩረት አድርጎ የዲጂታል መሠረቶቹን ልማት ላይ ይሰራል ብለዋል።
የዲጂታል መሠረተ ልማቶች ስንል ለሌሎች የዲጂታል ልማት ሥራዎች የሚጠቅሙ ሥራዎች መሥራት እንደሆነ የሚገልጹት ዶክተር አብዮት፤ ለምሳሌ የዲጂታል የመታወቂያ፣ የዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማቶችን መገንባት እና እነዚህ የመሳሰሉት ነገሮች አንድ ዘርፍ ብቻ የሚጠቀምባቸው አይደሉም ይላሉ።
ግብርና፣ ንግድ፣ ኢንዱስትሪውና የመሰል በርካታ ተቋማት የሚጠቀሙባቸው ናቸው። እነዚህን ዘርፎች እንዲጠቀሙ የሚያስችሉ መሠረተ ልማቱን ማልማት፣ የሕግና የቁጥጥር ማዕቀፎች እንዲኖሩ ማድረግ ከሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ የሚጠበቁ ሥራዎች ሲሆኑ፤ ከማይክሮሶፍት ኩባንያ ጋር የሚሰራው ሥራ ይህንን የተከተለ እንደሚሆን ይገልጻሉ። በዚህም ከመንግሥት ተቋማት፣ ከግሉ ዘርፍ፣ ከዩኒቨርሲቲዎች እና ከልማት አጋሮች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት የሚካሄድ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከውይይቱም በኋላ የሁሉንም ፍላጎቶች በመውሰድ የሚሰራበት እንደሆነ አመላክተዋል።
በዲጂታል ስትራቴጂ ላይ እንደተግዳሮት የሚነሳው ከመሠረተ ልማት አቅርቦት ጎን ለጎን ዲጂታል ቴክኖሎጂ የመጠቀም አቅም በጣም ዝቅተኛ መሆን እንደሆነ የገለጹት ዶክተር አብዮት፤ ይህንን ለመቀነስ የሚያስችል በቀጣይ የሚሰሩ ሥራዎች መኖራቸው አመላክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስንል የመጨረሻው ነገር ሰው ነው። ሰው አንደኛ ከሂደቱ መጠቀም አለበት። ሁለተኛ ደግሞ አገልግሎትንም ሊሰጥ የሚችለው ነው። ስለዚህ ሰው ከሂደቱም ተጠቃሚ ሆኖ አገልግሎትም ሊሰጥ እንዲችል መጀመሪያ ግንዛቤ እና ክህሎት ሊኖረው ይገባል።
ተፈላጊው ግንዛቤና ክህሎት ከሌለ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አላማዎች አይሳኩም ያሉት ዶክተር አብዮት፤ በሀገራችን በአጠቃላይ የዲጂታል ግንዛቤ እጥረት የሚለው በጣም በብዙ ቦታዎች ላይ ተስፋፍቶ የሚገኝ እንደሆነ አንስተው፤ ዲጂታል ላይ ስናመጣው ደግሞ ክፍተቱ የበለጠ ጎልቶ የሚታይ እንደሆነ አመላክተዋል። ‹‹በተለይ በገጠር የሚኖሩ በልዩ ልዩ ሁኔታዎች ከዋናው ኢኮኖሚ አውታር የተገለሉ ሰዎች የዲጂታል ክህሎት አይኖራቸውም። እነዚህ አካላት የዲጂታል ክህሎቱ ከሌላቸው በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ተጠቃሚ ሊሆኑ አይችሉም። ከእነርሱ የሚጠበቁ ነገር ላይም አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ አይችሉም። ስለዚህ እነዚህ ማብቃትና መደገፍ ቁልፍ ነገር ነው» ብለዋል።
እንደ ዶክተር አብዮት ማብራሪያ፤ መደገፍ ስንል በተለያየ መልኩ የሚታይ ሲሆን የረጂም ጊዜ እይታ ያስፈልጋል። በተለይ በትምህርት ቤቶች አሁን ላይ 26 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች አሉ። ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎች ተገቢውን የዲጂታል እውቀት ካገኙ በኋላ ወደ ኢኮኖሚ ሲቀላቀሉ ያንን እውቀት ይዘው ይመጣሉ ማለት ነው። ሌላ በሥራ ላይ ያሉና በተለያዩ ቢዝነሶች ውስጥ ያሉት እውቀት እንዲያገኙ ማድረግ ከተቻለ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማድረስ ይቻላል። ሌላው አስቸጋሪ የሚሆነው ደግሞ የሥራም ከትምህርት ወጪ የሆኑ በርካታ ወጣቶች ተደራሽ ማድረግ ነው። የሆነው ሆኖ ሁሉንም አማራጮች ተጠቅሞ ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል።
ከትምህርት ጋር የተያያዘውን በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ካሪኩለሞችን በመከለስ፣ የትምህርት ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ(ICT) ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በማውጣት በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ያሉት ዶክተር አብዮት፤ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም በኩል በተለይ ከትምህርት ውጭ ያሉትን ተደራሽ ለማድረግ የዲጂታል ኢንኩሊሽን ስትራቴጂ ተነድፎ ወደሥራ መገባቱ ገልጸዋል። ይህም ሁሉንም መንግሥት ይሰራው ማለት ሳይሆን ተቋሙ የስትራቴጂ ፍሬም ወርክ ያቀርባል በየደረጃ ያሉ ባለድርሻ አካላት ይተገበሩታል ማለት ነው ሲሉ አስረድተዋል።
የዲጂታል ኢኮኖሚው እየተሰፋፋ ሲመጣ ከዚያ ጋር ተያይዘው የሚነሱ በርካታ ችግሮች ይኖራሉ ያሉት ዶክተር አብዮት፤ ችግሮች ተፈርተው ሥራዎች አይሰሩም ማለት አይደለም፡፤ በዚህ ረገድ የሚከሰቱትን የማጨበርበር ሆነ ሌሎች የደህንነት አደጋዎችን ለመቀነስ የህብረተሰቡን የግንዛቤ ደረጃ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የህብረተሰቡ ግንዛቤ ማሳደግ ላይ ካልተሰራ የተመራጭ የሆነ የደህንነት መጠበቂያ ቴክኖሎጂ ቢኖርም እንኳ ከኛ የበለጠ ቴክኖሎጂ ያለው አካል ጥቃት በመፈጸሙ ሊሰርቅ ስለሚችል ዋንኛው መደረግ ያለበት ነገር የህብረተሰቡ ግንዛቤ ማሳደግ እንደሆነ አመላክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ተቋማት ለዳታ ጥበቃ የሚያደርጉትን ተግባራት ማጠናከር ይገባል ያሉት ዶክተር አብዮት፤ በቅርቡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የግል ዳታ ጥበቃ አዋጂ አጽድቆ ወደ ፓርላማ የመራው መሆኑን ጠቅሰው፤ ፓርላማውም በቅርቡም ያጸድቀዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይናገራሉ። እነዚህ መሰል ጠንካራ የሆኑ የሕግ ማዕቀፍ መውጣት እንደሚጠበቅ ጠቁመው፤ በተለይ በርካታ የግል ዳታ የሚይዙ ተቋማት በምን ደረጃ ለዳታ ጥበቃ ማድረግ አለባቸው የሚሉት አስገዳጂ ሥርዓቶች በሕግ ውስጥ ተካተው እንዲተገበሩ ማድረግ የሚጠይቅ እንደሆነ ይገልጻሉ። ምክንያቱም የግል ዳታዎች የማይጠበቁ ከሆነ ዳታ እንዲጠበቅላቸው የሚፈልጉ አካላት በቀጣይ በዲጂታል ኢኮኖሚው የሚያደርጉት ተሳትፎ ሊገታ ይችላል። ይህ እንዳይሆን ደግሞ የግል ዳታ ጥበቃ አዋጁ ትልቅ ጥቅም ይሰጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል ሲሉ ተናግረዋል።
‹‹ማይክሮሶፍት ኩባንያ በዋናነት እንዲረዳና እንዲያግዝ የሚጠበቀው የአቅም ግንባታ ላይ ነው›› ያሉት ዶክተር አብዮት፤ ‹‹የሀገራችን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የሚረጋገጠው በራሳችን ነው። ራሳችንን ማረጋገጥ ካልቻልን ማንም ሊያረጋግጥልን አይችልም፤ ራሳችን መሥራት እና የቴክኖሎጂ ባለቤት መሆን እንድንችል ድጋፍ እንዲያደርግ ያስፈልጋል። ስለዚህ ማይክሮ ሶፍትም ይህንን አቅም እንዲፈጥርልን እንፈልጋለን›› ብለዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 9 ቀን 2016 ዓ.ም