አውደ ርዕዩን እንደ ትልቅ እድል የተጠቀመበት ክልል

ባለፈው ጥቅምት ለአንድ ወር በዘለቀው የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ ተሳታፊ ከነበሩት ክልሎች መካከል የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ይገኝበታል። ክልሉ በተፈጥሮ፣ ባሕል፣ ታሪክና መሰል መስህቦች የታጀቡ የቱሪዝም ሀብቶቹን ወሩን ሙሉ በአውደ ርዕዩ ማስተዋወቅ ችሏል።

እንደሚታወቀው፤ የሲዳማ ክልል የውቢቱ ሀዋሳ ከተማና የሀዋሳ ሐይቅ መገኛ ሲሆን፣ በተፈጥሮ ሀብቶች ከታደሉት የኢትዮጵያ ክፍሎች መካከል ይጠቀሳል። በኮንፈረንስ ቱሪዝም፣ በውሀ ቱሪዝምና ታላቁ ሩጫ በየዓመቱ በሚያዘጋጀው የስፖርት ቱሪዝም በስፋት ይታወቃል።

የሲዳማ ክልል የቱሪዝም መስህቦችን በርካታ ጎብኚዎች ሲመለከቱ፣ ሁለት አስጎብኚዎችም ሲያስጎበኙ ተመለከትን። ከሲዳማ ክልል የቱሪስት መስህብ አስጎብኚዎች መካከል ቅድስት አምባቸው አንዷ ናት። ቅድስት በክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ዘርፍ የቱሪዝም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብቃት ማረጋገጫ ኦፊሰር ናት። ስለክልሉ የቱሪስት መስህቦች እንድታብራራልን የጠየቅናት ቅድስት ክልሉ እጅግ በርካታ የባሕል፣ የተፈጥሮ፣ የታሪክና ሌሎች የቱሪዝም መስህቦች ባለቤት መሆኑን ገለጸችልን፤ እንዳንዶቹን መስህቦች በስፍራው ለእይታ የቀረቡ ምስሎች በማሳየት ጭምር አብራራችልን።

እሷ እንዳለችው፤ የክልሉ መቀመጫ የሆነችው ሀዋሳ ከአዲስ አበባ በ275 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፤ ክልሉን ለመጎብኘት ለሚፈልግ በአውሮፕላን 35 ደቂቃ በመኪና ደግሞ ከሶስት እስከ ሶስት ተኩል ሰዓት ብቻ መጓዝ ነው የሚጠበቅበት። የማረፊያ ቦታ በበቂ መልኩ ለማግኘትም አይቸገርም። በከተማዋ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እና ሪዞርቶች በብዛት ይገኛሉና።

“በሀዋሳ ከተማ እና በሀይቅ ዳርቻዎች መቆየት የሚፈልግ በውሀ ቱሪዝም በጀልባ ሽርሽርና ስፖርት መሳተፍ ይችላል” የምትለው ቅድስት፣ ከመኖሪያ ውጪ ራቅ ብለው ለሚዝናኑ የአገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎች ምቹ እድል እንዳለ ትገልፃለች።

ከሀይቁ ዳርቻ ልዩ ልዩ ተግባራትን ማከናወን እንደሚቻል ገልፃ፣ ለአብነትም ጥሬና የተጠበሰ አሳ መመገብ እንደሚቻል፣ በተለይ ጥሬ አሳ መመገብን ብዙዎች እንደሚወዱት ሁሉ ብዙዎች በአግራሞት እንደሚመለከቱትም ትናግራለች። ወደ ከተማዋ የሚመጡ ቱሪስቶች በቀዳሚነት ከሚደሰቱበት ድርጊት መካከልም ከሀይቆቿ የሚገኙ አሳዎችን እየተመገቡ መዝናናት እንደሆነ አመልክታለች።

ከሀዋሳ ከተማ ወጣ ሲባል ደግሞ በወንዶ ገነት እጅግ ማራኪ ስነ ምህዳርና የተፈጥሮ መስህብ ማግኘት እንደሚቻል የምትናገረው ቅድስት፣ የወንዶ ገነት ፍል ውሃ በጎብኚዎች ዘንድ በጣም ተመራጭ መሆኑን ተናግራለች። እነዚህ ፍል ውሀዎች ከመዝናኛነትም ባሻገር ለሕክምና አገልግሎት ተመራጭ እንደሆኑም ይነገርላቸዋል። በርካታ ሰዎችም ይህን ብለው ይሄዱባቸዋል።

ከወንዶ ገነት ሳይወጣ በተፈጥሮ ቱሪዝም መዝናናት የሚሻ ቱሪስት እድሜ ጠገብ ደኖችን፣ ሌሎች እፅዋትን፣ አእዋፍትን ማግኘት እንደሚችልም ጠቁማለች፤ አካባቢው ለእፅዋትና ተፈጥሮ ምርምር ተመራጭ መዳረሻ እንደሆነ ነው ያመለከተችው። በአካባቢው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት ደን ኮሌጅ አንዱ የመገኘቱ ምስጢርም ይሄው ሊሆን ይችላል።

በወንዶ ገነት ሌላም የቱሪስት መስህብ ይገኛል። የቀድሞው ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ቤተመንግስት መገኛ ነች፤ በቤተመንግስቱም ንጉሱ ይገለገሉባቸው የነበሩ ቁሳቁስ ይገኛሉ፤ ከቁሳቁሱ መካከልም የሚመገቡባቸው እና ለመዝናኛነት ይጠቀሙባቸው የነበሩ ቁሳቁስ ይጠቀሳሉ። ከቤተ መንግስቱ በተጨማሪም በወንዶ ገነት ለእንግዳ ማረፊያነት የሚውል በፍራፍሬና በአረንጓዴ እፅዋት የተዋበ ሪዞርት ይገኛል።

በዳሌ ወረዳ ይርጋለም ከተማ አካባቢ ልዩ ልዩ የቱሪስት መስህቦች እንዳሉም ነው ቅድስት የጠቆመችው። እሷ እንዳለችው፤ ከእነዚህ የቱሪስት መስህቦች መካከል አረጋሽ ሎጅ ይጠቀሳል፤ ሎጁ ከከተማዋ ወጣ ባለ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፣ ልዩ ልዩ እጽዋት፣ የዱር እንስሳት፣ ውብ የተፈጥሮ አቀማመጥ ባለው ስፍራ ላይ ይገኛል። ይህ በበርካታ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች የሚጎበኝ የቱሪስት መስህብ ስፍራ መኝታ ቤቶች እና አገልግሎት መስጫዎች/ጎጆዎች/ በሙሉ የተገነቡት በቀርከሃ ነው።

የይርጋ ዓለም አካባቢ በፍል ውሀውም ይታወቃል፤ የጊዳቦ ፍልውሃ ይባላል። አንድ ጎብኚ በዚህ ስፍራ ሲገኝ በፍልውሃው ብቻ አይደለም የሚዝናናው፤ ፍልውሃው ያለበት መልካአምድር፣ እጽዋቱ፣ የዱር እንስሳቱና የጊዳቦ ወንዝ ተረጋግቶ እየወረደ ያለበት ሁኔታም ሌሎች መስህቦቹ ናቸው።

በይርጋለም አቦ ወንሾ በሚባል ወረዳ የሲዳማ “አፊኒ” ባሕላዊ የዳኝነት ስርዓት እንደሚከወን የጠቀሰችው ቅድስት፤ የሲዳማ አባቶች በዚህ ስፍራ “ሶንጎ” ተቀምጠው በአፊኒ ስርዓት እንደሚዳኙ ተናግራለች። ይህ ስርዓት የሲዳማ ብሄረሰብ ቱባ ባሕልና የጥንት አባቶች ከትውልድ ትውልድ ያሻገሩት እሴት ሳይበረዝ ሳይከለስ የሚንጸባረቅበት መሆኑን አብራርታለች።

ቅድስት እንዳለችው፤ በዚያ አካባቢ ሁሌም እሁድ ቀን ችሎት ወይም ዳኝነት የሚሰየም ሲሆን፣ የተበደለ እና ፍትህ ተነፍጌያለሁ ብሎ ያመለከተ ማንኛውም ሰው ወደ አካባቢው በመሄድ ይዳኛል። አባቶች ፍትህ ሲሰጡ ከከሳሽ ወይም ተከሳሽ ምንም አይነት ክፍያ አይደረግላቸውም።

በክልሉ ሎክ አባያ የሚባል ብሄራዊ ፓርክ እንዳለም ጠቁማ፣ በፓርኩም በርካታ ግዙፍ አጥቢ እንስሳት፣ ብርቅዬ አእዋፋት እንደሚኖሩበት ጠቁማለች። የጊዳቦ ግድብም የሚገኘው በዚሁ አካባቢ ነው። ከሎክ አባያ እስከ ነጭ ሳር በውሃ ላይ መጓዝ እንደሚቻልም ቅድስት ትገልፃለች።

ሁለት ፓርኮች የሚጋሩት ይህ ግዙፍ የአባያ ሐይቅ ከሲዳማ እስከ ጌዴኦ፣ ከኦሮሚያ እስከ ወላይታ፣ ከጋሞ እስከ ጋርዱላ የሚዘልቅ መሆኑን ታነሳለች። ከዳር እስከ ዳር 60 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውና አንድ ሺ 162 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የአባያ ሀይቅ የበርካታ ደሴቶች መገኛም መሆኑን ትናገራለች።

በአባያ ሀይቅ ዳርቻ ፍል ውሃዎች እንዳሉም ጠቁማለች። በአካባቢው አባያን እያየ ማደር የሚፈልግ ዳርቻው ላይ ማረፊያ አዘጋጅቶ ጉብኝቱን ማድረግ እንደሚችልም ትናገራለች።

በሲዳማ ክልል ከሚታወቁት የባሕል መስህቦች ውስጥ የደጋ መንደር ጎጆ አሰራር ስርዓትና የቡና ልማት እንደሚጠቀሱ ቅድስት ገልጻ፤ በባሕሉ መሰረት ጎጆ ቤቶቹ የሚሰሩት ከቀርከሀ ዛፍ ብቻ እንደሆነ ትናገራለች። የቡናን ምርት በተመለከተም የሲዳማ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ በካፍ ኦፍ ኤክሰለንስ ተሸላሚ እንደሆነ በመግለፅ ቡናው ተወዳጅ ጣዕም ያለውና የክልሉ ልዩ መገለጫ ተደርጎ እንደሚታይም አስታውቃለች።

በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ፊቼ ጫምባላላ ሌላው የክልሉ የቱሪስት መስህብ መሆኑን ጠቅሳ፣ ፊቼ ጫምባላላ የሲዳማ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ መሆኑንም ነው የገለጸችው። እሷ እንዳለችው፤ የፍቼ ጫምባላላ በዓል የአሮጌው ዓመት መጨረሻ የአዲሱ ዓመት ዋዜማ እንደመሆኑ የብሄሩ ሊቃውንት የጨረቃና ኮከብ አቅጣጫና ቁጥር ተመልክተው የዘመን መለወጫው መቼ እንደሚከበር ትክክለኛውን ወርና ቀን ከወሰኑ በኋላ ለሕዝቡ በፊት ያውጃሉ።

የዘመን መለወጫ ቀኑ ከታወጀ በኋላ የብሔሩ ባሕላዊ መሪዎች (ዎማች) ለፊቼ ሳምንት ሲቀረው ከአንድ ወር በፊት የጀመሩትን ጾምና የሱባኤ (የንስሐ) ጸሎታቸውን ያጠናቅቃሉ። ሴቶች ለበዓሉ ማድመቂያ ቅቤ፣ ቆጮ፣ ወተትና ቅመማቅመም ያዘጋጃሉ። የባሕል መሪዎቹም በእለቱ ቄጣላ የሚባል እየተጫወቱ ያከብሩታል።

የፊቼ ጫምባላላ ዋዜማ ከደረሰ በኋላ የቤተሰቡ አባላትና ከብቶች በእርጥብ ቅጠል በተዘጋጀው መሽሎኪያ (ሁሉቃ/ ውስጥ ጸሐይ ስታዘቀዝቅ ሾልከው እንዲያልፉ ይደረጋል። ክብረ በዓሉም በዚሁ መልኩ ይቀጥላል ስትል ታብራራለች።

“ጫምባላላ” ዞሮ መምጣት ማለት እንደሆነ የምትገልፀው ቅድስት፤ አዲሱ ዓመት የሚጀመርበት፣ ልጆች ምንም ስራ የማይሰሩበትና እየዞሩ የሚመገቡበት፣ ከብቶች ለዚህ ቀን ተከልሎ በቆየ ጥብቅ ስፍራ ውስጥ ተለቀው የሚግጡበት ቀን መሆኑን የብቃት ማረጋገጫ ኦፊሰሯ ትናገራለች።

ልጆቹ ‹‹አይዴ ጫምባላላ›› (ዞረን መጣን) እያሉ ተሰብስበው በየአካባቢው ሲዞሩ፣ እናቶች ‹‹እሌ…እሌ..››፣ ወይም ‹‹ድረሱ….ድረሱ›› በማለት በቅቤ የተዘጋጀውን ቆጮ (ቡሪሳሜ) አቅርበውላቸው ተደስተው የሚውሉበት እንደሆነ ተናግራለች። ይህ ስርዓት ሲዳማ ካሉት ልዩ ባሕላዊ መገለጫዎች አንዱ መሆኑንም ነው የገለጸችው። ጎብኚዎች በዚህ በዓል ወቅት ወደ ሲዳማ ክልል ቢሄዱ በተወዳጁ ፊቼ ጫምባላላ ባሕላዊ ስርዓት ተደስተውና እውቀት ገብይተው እንደሚመለሱ ጠቁማለች።

የሲዳማ ብሄረሰብ ሴቶች የሚዋቡባቸው ባሕላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች እንዳሏቸውም ጠቅሳ፣ እነዚህም የጎብኚዎችን ትኩረት እንደሚስቡ ቅድስት ገልጻለች። ከእነዚህ መካከልም “ጉመይ” በመባል የሚታወቅ የእጅ አምባር፣ አንገት ላይ የሚደረግ “ባእላቶ” አንደሚገኙበት ትናገራለች።

የብቃት ማረጋገጫ ኦፊሰሯ ቅድስት እንዳብራራችው፤ የሲዳማ አባቶችም ከነሀስ የተሰሩ የጀግንነታቸው መገለጫ የሆኑ የአንገትና የእጅ አምባሮችን ያደርጋሉ። አባቶች ይህንን ጌጥ ሲያደርጉ ጦርነት መርተው ጀግንነት ሰርተው እንደነበር ያስታውሳሉ፤ በዚህም ክብርን ያገኙበታል። ሌላው አባቶች በፊቼ ጫምባላላ ክብረ በዓል ቀን ከጉማሬ ቆዳ የተሰራ ጋሻ እንዲሁም በተመረጠ እንጨትና ብረት የተሰራ ጦር ይዘው በበዓሉ በሚከበርበት አደባባይ ጉዱማሌ እንደሚወጡም ታስረዳለች።

“በክልሉ በቱሪስት ማረፊያነት የሚገኙ ሆቴሎች፣ ሎጆችና ሪዞርቶች ባሕላዊ ምግቦችን በራሳቸው ተነሳሽነት ያቀርባሉ” የምትለው ቅድስት፣ አንድ ጎብኚ በሲዳማ ክልል ሲገኝ የክልሉን ማሕበረሰብ ባሕላዊ ጣፋጭ ምግብ አንደ “ቦርሳሜና ጩካሜ” ያሉትን መመገብ እንደሚችልም ትናገራለች። ይህም ሲዳማንና ማሕበረሰቡን ይበልጥ ለማወቅ የባሕል ትስስር ለመፍጠር እንደሚረዳው ታስረዳለች።

ቅድስት በአውደ ርዕዩ በርካታ ሺህ ጎብኚዎች የሲዳማ ክልል የቱሪስት መስህቦችን ማስጎብኘት መቻሉን ጠቅሳለች። ለአንድ ወር የክልሉን መስህብ በሚፈለገው ልክ ማስተዋወቅ መቻሉን ነው የተናገረችው።

ሲዳማ በቅርብ ጊዜ የተመሰረተ ክልል እንደመሆኑ መሰል አውደ ርዕዮች የቱሪዝም ሀብቶችን ለማስተዋወቅ እንደሚረዱ ጠቅሳ፣ ክልሉ ይህን መድረክ ማግኘቱ ትልቅ እድል መሆኑን የብቃት ማረጋገጫ ኦፊሰሯ ቅድስት አስታውቃለች። የሲዳማን ባሕል፣ ታሪክ፣ ተፈጥሮና ልዩ ልዩ ሀብቶች በሚፈለገው ልክ የማያውቁ እንደሚኖሩ ገልፃ፣ በመድረኩ ሲገኙ እነዚህ ሰዎች እድሉን እንዲያገኙና ክልሉ ያለውን ሀብት ተረድተው ለመጎብኘት እንዲነሳሱ ለማስተዋወቅ እድል ማግኘቱን ገልጻለች።

ቅድስት እንዳለችው፤ መድረኩ የሲዳማ ክልል የቱሪዝም ሀብቶችን ለማያውቁት ከማስተዋወቅ ባሻገር፣ ክልሉ ከአቻ ክልሎችና ከልዩ ልዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከመጡ የዘርፉ ተቋማት ጋር ትውውቅ ለማድረግና ልምድ ለመለዋወጥም ረድቶታል። መሰል መድረኮች አንደ ሀገርም እንደ ክልልም በቀጣይም ቢዘጋጁ የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶችን የበለጠ እንዲያውቁ ለማድረግ ይረዳል። ይህ ሲሆን በቱሪዝም ዘርፉ የሚፈለገው ለውጥ እንደሚመጣ ተናግራለች።

ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 28-2016 ዓ.ም በቆየው የሳይንስ ሙዚየም የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ ላይ በርካታ የቱሪዝሙ ዘርፉ ተዋንያን ተሳትፈዋል። አውደ ርዕዩን በአካል 170 ሺህ የሚጠጉ በዲጂታል አማራጭ ደግሞ 9 ሚሊዮን አካባቢ የሚደርሱ ጎብኚዎች እንደተመለከቱት መረጃዎች ጠቁመዋል። በአውደ ርዕዩ ተሳታፊ ከሆኑ ተጋባዦች መካክል የሁሉም ክልሎች ባሕልና ቱሪዝም ቢሮዎች ይገኙበታል።

 ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ኅዳር 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You