አዲስ አበባ፡– በአሁኑ ጊዜ ተመሳሳይ የሆኑ የምግብ አይነቶች መዘወተራቸው ለሰዎች ጤና ስጋት እየሆነ መምጣቱን የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈለቀ ወልደየስ ‹‹ብዝሃ ሕይወታችን ምግባችን፣ ጤናችን›› በሚል መሪ ቃል 18ኛው ዓለም አቀፍ የብዝሃ ሕይወት ቀን ትናንት በኢንስቲትዩቱ ሲከበር እንደገለጹት፤ የተለያዩ የምግብ አይነቶች እያሉ በአሁኑ ጊዜ ግን ተመሳሳይ የሆነ የምግብ አይነት ወደመጠቀም የማጋደል ሁኔታ በስፋት እየተስተዋለ ሲሆን፣ችግሩም ዓለም አቀፍ ነው፡፡ ተመሳሳይ ምግብ ማዘውተር በምግብ፣በብዝሃ ሕይወትና በጤና መካከል ያለውን ቁርኝት ያዛንፋል፡፡ የተወሰኑ የምግብ አይነቶች መመገብ ለስኳር በሽታ ከመጠን በላይ ለሆነ ውፍረትና ለሌሎችም ለጤና ችግር ያጋልጣል፡፡
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ትላልቅ ፋብሪካዎች ሳይቀሩ ተመሳሳይ የሆኑ የምግብ ምርቶችን ለዓለም ማቅረባቸው፣ ሰዎች ወደ አንድ አይነት ምግብ ማዘበላቸው እንዲሁም ከአርሶ አደሩ ማሳዎች እስከ 90 በመቶ የሰብል እህል በተሻሻሉ የአዝርዕት ዝርያዎች መተካታቸው እና እስከ 50 በመቶ የሚደርሱ ነባር እንስሳት ዝርያዎች ከምድረ ገጽ መጥፋት በምክንያትነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ዶክተር ፈለቀ ወልደየስ አብራርተዋል፡፡
ተመሳሳይ የሆኑ የምግብ አይነቶችን ማዘውተር በጎ ጅምር አለመሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ፈለቀ፣የምግብ መሰረትን ማስፋት ተገቢ መሆኑ በምግብ ሳይንስ ባለሙያዎች፣ በዘርፉ ተቋማት እና ፖሊሲ አውጭዎችም የሚታመንበት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ በብዝሃ ሕይወት ላይ አትኩሮ በመስራት ከብዝሃ ሕይወት ምግብና ጤንነት መገኘት እንዳለበት፣ በአስፈላጊነቱ ላይ ምክክር ማድረግና ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2011
በሙሐመድ ሁሴን