‹‹በአብሮነት ለሀገር ሰላም እና እድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን መቅረፍ ይገባል›› – ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

አዲስ አበባ፡- ኅብረተሰቡ እርስ በእርስ በመተሳሰብና በአብሮነት ለሀገር ሰላም ብሎም እድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አሳሰቡ፡፡ የጥምቀት በዓል በትናንትናው እለት በጃንሜዳ በድምቀት ተከብሯል፡፡

በበዓሉ ላይ ለምዕመኑ ቡራኬ የሰጡትና መልዕክት ያስተላለፉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት እንዳሉት፤ ሁሉም ኅብረተሰብ ፈጣሪ የሰጠውን ጸጋ ተጠቅሞ ሊተባበር፣ በፍቅርም ሊቆም ይገባል። ለሀገር ሰላም እና እድገትም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት ይኖርበታል። ለሀገር ሰላምና እድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችንም በመተባበር መቅረፍ ይጠበቅበታል።

የሰው ልጅ ዘላቂ ሕይወትን መቀዳጀት የሚችለው ፈሪሃ እግዚአብሔር ሲኖረው ነው ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ በአሁኑ ጊዜ ፈጣሪ ከሰዎች የሚጠብቀውን መልካም ስብዕና ከመላበስ አኳያ የሚታዩ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከእውነት ይልቅ ተንኮል የእለት ተግባር እየሆነ መምጣቱ ከእግዚአብሔር መንገድ የመራቂያ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

ዓለም ለጦርነትና ለግጭት የምታውለውን አጥፊ ድርጊት ማቆም እንዳለባትና ዜጎች ለሰላማዊ ሕይወት ሊተጉ እንደሚገባ ያሳሰቡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ ሰዎች ከቂምና ከጥላቻ ይልቅ በፍቅር እና በአብሮነት መኖርን ሀብታቸው እንዲያደርጉም አባታዊ ጥሪ አቅርበዋል።

በተያያዘ ዜና፣ በእለቱ በሥፍራው በመገኘት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው፤ የጥምቀት በዓል ለቱሪዝም እድገቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው፤ መንግሥት ባህላዊና ቁሳዊ ቅርሶችን በመጠበቅ ለዓለም ሕዝብ የማስተዋወቅ ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ለዚህም ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመቀራረብ እየሠሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የበርካታ እሴቶች ባለቤት፣ በርካታ የአደባባይ በዓላትም ያሏት መሆኗን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱንና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በአደባባይ የሚከበር እና በማይዳሰስ ቅርስነት በዓለም ቅርስ መዝገብ መመዝገብ የቻለ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ የሆኑት አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፤ በዓሉ በቅርስነት በመመዝገቡ ሀገራዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ይሄን በዓል ከፍ አድርጎ ለማስተዋወቅና ለመጠበቅም ሁሉም ዜጋ የአምባሳደርነት ሚናውን መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል።

የጥምቀት በዓል ከመንፈሳዊ ይዘቱ ባሻገር ለቱሪዝም መስህብ እየዋለ መሆኑን የሚናገሩት ምክትል ከንቲባው፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያለ ልዩነት በጋር የሚያከብሩት የደስታ በዓል እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የጥምቀት በዓል ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ የትምህርትና የሳይንስ ድርጅት (ዩኔስኮ) ካስመዘገበቻቸው በርካታ ቅርሶች መካከል አንዱ ሲሆን፤ በዓሉ በቅርስነት የተመዘገበውም የማይዳሰስ ቅርስ በሚል ነው።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You