ትንሿ ኢትዮጵያ – በሳይንስ ሙዚየም

 ሠላም ልጆች እንዴት ናችሁ? ሳምንቱ ለእናንተ እንዴት ነበር? ትምህርታችሁን በሚገባ በማጥናት፤ ያልገባችሁን በመጠየቅ እንዳሳለፋችሁት ምንም ጥርጥር የለኝም። ልጆች ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በቅርስ፣ በባህል፣ በተፈጥሮ፣ በእደ ጥበብ እና በመሳሰሉት ነገሮች የታደለች ሀገር መሆናን ታውቃላችሁ አይደል? ‹‹በሚገባ።›› አላችሁ ጎበዞች። ስንቶቻችሁስ ናችሁ ስለሀገራችሁ ለማወቅ ፈልጋችሁ ቤተሰባችሁን እና መምህራኖቻችሁን የጠየቃችሁ? ስለዚህም ልጆች መልሳችሁን ወይም ኢትዮጵያን ማወቅ ከፈለጋችሁ ፤ የኢትዮጵያን የቱሪስት መስህቦችን በአንድ ሥፍራ የምታገኙበትን ቦታ እንጠቁማችኋለን።

ልጆች የሉሲ (ድንቅነሽ)፣ የሰላም እና አርዲ ቅሪተ አካል፣ የሶፍ ዑመር ዋሻ፣ የሀረር በር፣ በጎንደር አቢያተ መንግሥታት የፋሲል ግንብ፣ የአክሱም ሐውልቶች እና በሌሎች የሀገራችን ክፍል የሚገኙ የታሪክ፣ የተፈጥሮ፣ የባህል ሀብቶችን እንዲሁም የእደ ጥበብ ውጤቶችን ለመጎብኘት ከፈለጋችሁ የቱሪዝም ሚኒስቴር በአዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚገኘው የሳይንስ ሙዚየም በተዘጋጀው ‹‹የቱሪዝም እና ሆስፒታሊቲ ዐውደ ርዕይ›› ሄዳችሁ ብትጎበኙ ስለ ሀገራችሁ ብዙ ታውቃላችሁ።

እንዲሁም በዐውደ ርዕዩ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙ የቱሪዝም ምርት አቅራቢዎች ምርቶቻቸውን እያስጎበኙ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ታይተው የማይጠገቡ የባህል፣ የታሪክ ፣ የተፈጥሮ እና ሌሎች ሰው ሰራሽ መስህብ ሀብቶች ሀገር ባለቤት መሆኗን በሁለም የእድሜ ክልል ያሉ ሁሉ እንዲያውቁት ተደርጎ ተዘጋጅቷል።

በዐውደ ርዕዩ ስለ ክልሎች ዝርዝር መረጃዎችን፣ ስለ ፓርኮች እና የኢትዮጵያውያን የእጅ ሥራ ውጤቶች በአይነት የተገኙበት ሲሆን ፤ ከዐውደ ርዕዩ የሀገርን ነባር እወቀት እንዲረዱት ያስችላል። በርካታ ቁጥር ያላቸው የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ጨምሮ የተለያዩ ግለሰቦች እና ተቋማትም እየጎበኙትም ይገኛሉ።

እኛም ለእናንተ ለልጆች ወደ ተዘጋጀው ስፍራ አምርተን የተመለከትናቸውን ነገሮች እናጋራችሁ። ቦታው ‹‹የልጆች ስፍራ›› የሚል መጠሪያ ስያሜ ተሰጥቶታል። ስፍራው በቱሪስት መስህቦች፣ በተለያዩ እንስሳት እና ቀለማት ያሸበረቀ ነው። በኢትዮጵያ የቱሪዝም መስህቦች በተቀረጹ ካርታ፣ ዳርት እና መሰል ጨዋታዎችን በማዘጋጀት፤ ልጆች እየተጫወቱ ስለ ሀገራቸው እንዲያውቁ ስፍራው በጥሩ ሁኔታ መዘጋጀቱን ተመለክተናል። በስፍራው ህጻናት የእድሜ ክልላቸውን ያማከል ገለጻ ይደረግላቸዋል። በተለይም ንግግር (ተግባቦት) የሚችሉ ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ ነገሮች እነርሱ ሊገነዘቡት በሚችሉ መልኩ በማስረዳት ከአውደ ርዕዩ አንዳች ነገር እንዲቀስሙ ለማድረግ ዓላማ ያደረገ ነው።

‹የልጆች ሥፍራ› ተቆጣጣሪ አቶ ኃይለኢየሱስ ደበሽ እንደገለጹት፤ ልጆች እንዲጫወቱ ከተዘጋጁት መካከል ገበጣ አንዱ ሲሆን፤ ልጆች ገበጣ እንዲጫወቱ፣ ለማያውቁት ደግሞ እንዲለማመዱ እና እንዲያውቁት ይደረጋል። ሌላው ጨዋታ ደግሞ ጂንጋ ይባላል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ የቱሪስት መስህቦች በተቀረጹ እና አነስተኛ መጠን ያላቸውን ጣውላዎችን ወደላይ ደርድረው እንዲጫወቱ በማድረግ ልጆች ታሪካቸውን እንዲያውቁ ይደረጋል። ጨዋታዎቹ ለልጆች ብቻ ሳይሆን ለአዋቂዎች ጭምር እንዲሆን በመዘጋጀታቸው ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በጋራ እንዲጫወቱ እና ስለሀገራቸው በስፋት እንዲያውቁ ያስችላል።

ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ከመጫወት በሻገር ስለ ገበጣ፣ ስለ ቱሪስት መስህቦች ሲነጋገሩ ማየታቸውን ያደነቁት ኃይለኢየሱስ፤ በዚህም ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚያደርጉትን ንግግር እንደ ጥሩ ልምድ መገንዘባቸውን ያስረዳሉ። ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመምህራኖቻቸው አስተባባሪነት አውደ ርዕዩን እንዲጎብኙ በማድረግ ስለ ኢትዮጵያ እንዲያውቁ ሁኔታዎች መመቻቸቱንም አድንቀዋል።

አቶ ኃይለኢየሱስ እንደሚሉት፤ ልጆች ከአዋቂዎች የሚማሩበት መንገድ የተለየ ነው። እነርሱን በተለየ መንገድ መረዳት እና እገዛ ማድረግ ይገባል። በርካታ የከተማ ልጆች የሚጫወቱት በስክሪን (በቴሌቪዥን፣ ሞባይል፣ ታብሌት፣ ኮምፒውተር…) ወይም ዲጂታል ጨዋታዎችን ነው። ይህ ጨዋታ የጎንዮሽ ጉዳት ያለው መሆኑን በመረዳት በእጅ በሚነካኩ፣ ትምህርቶችን በሚሰጡ እና የጎንዮሽ ጉዳታቸው አናሳ ናቸው የሚባሉ ጨዋታዎች ማጫወት ይገባል።

ህፃናት ተማሪዎች ስለአገራቸው ታሪክ፣ ተፈጥሮ፣ ባህል በአጠቃላይ ስለቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች ጥልቅ እውቀት እንዲኖራቸው ለማስቻል በሳይንስ ሙዚየም በተዘጋጀው የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ ተገኝተው እንዲጎበኙ የተደረገ ሲሆን፤ ‹‹እርስዎም የነገ ሀገር ተረካቢ ህፃናትን ይዘው ይምጡና ያስጎብኟቸው፤ ስለሀገራቸው ትምህርት ቀስመው ይመለሳሉ›› ሲል የቱሪዝም ሚኒስቴር መልዕክቱን አስተላልፏል። ዐውደ ርዕዩ ከመስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የተከፈተ ሲሆን እስከ ጥቅምት 28 ቀን 2016 ዓ.ም ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናል።

 እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You