ፍቅር ጌታ

ፀሐይ ውበታም ሴት ናት፡፡ ተፈጥሮ የአንዲትን ውብ ሴት ፈገግታ ፀሐይ አድርጎ ህዋ ላይ የሰቀላት ይመስለኛል፡፡ ዓለም የደመቀችው በፀሐይ በተሳለችው የሴት ልጅ ፈገግታ ነው፡፡ እሷን ሳይ እንዲህ ብቻ ነው የማስበው፡፡

የምሠራበት ቦታ ሰርቪስ መጠበቂያዋ ነው፡፡ እዚያ ቦታ ሊስትሮ ሆኜ መሥራት ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ በሴት ውበት ነፍሴ ስትደክም እሷን ነው የማውቀው፡፡ ቦርሳዋን በእጇ አንጠልጥላ ማስቲካዋን እያላመጠች ወዳለሁበት ትመጣና የምሠራበት ወንበር ላይ አረፍ ትላለች፡፡ ለአምስት አመታት ጫማ ስጠርግ እንደ እሷ እግር ደልቶኝ እና ወድጄ የምጠርገው ጫማ የለም፡፡ ጫማዎቿ ያማምራሉ፡፡ ንጹህ ናቸው፡፡ በአየር ላይ የምትንሳፈፍ እንጂ መሬት የምትረግጥ አትመስልም፡፡ ጥረግልኝ ብላ ሊስትሮ ዕቃዬ ላይ እግሮቿን ስታስቀምጣቸው አበላሽልኝ ብላ የመጣች ነው የሚመስለኝ፡፡ እንደዚያ ንጹህ ሆነው ለምን ጥረግልኝ እንደምትለኝ ግራ ይገባኛል፡፡ በእሷ ጫማ ላይ ልዩነት ፈጥሬ አላውቅም፡፡ በሳሙናና በብሩሽ ፈትጌ አጥቤላት እንኳን ውበታቸው እንደበፊቱ ነው፡፡ እንዴትም ባጸዳላት የልቤ ደርሶ አያውቅም፡፡ ገንዘቧን ዝም ብላ የምትከሰክስ ሞኝ መሰለችኝ፡፡

ጫማዎቿ በብዛት ነጭ ናቸው፡፡ ነጭ ቀለም እንደምትወድ በጫማዎቿ ማወቅ ቻልኩ፡፡ ክፍት ጫማ ስታደርግ አይቻት አላውቅም፡፡ ማንም ሳይነግረኝ እግሯ ላይ ችግር እንዳለባት ደረስኩበት፡፡ እንደዚያ ባይሆን እማ ይሄን ሁሉ ጊዜ በሽፍን ጫማ አላያትም ነበር ስል ለራሴ ጥያቄ መልስ ሰጠሁ፡፡

ብዙ አታወራም..ትመጣና እግሯን ሊስትሮ ዕቃዬ ላይ ታስቀምጥና እንድጠርግላት ዓይን ዓይኔን ታስተውለኛለች። ስታየኝ በልቧ ነው፡፡ በልብ ማየት ከአእምሮ ርቆ ነው፡፡ እንባ ባንጠለጠሉ ዓይኖች..ሊወርድ የሚታገል እንባን አምቆ፣ የኀዘን ደመና ባጠላበት ፊት፡፡ የእናት መሳይ ዓይን አላት፡፡ እያዩ የሚያልባቸው…እያስተዋሉ የሚቃትቱ ዓይኖች፡፡

‹ለምን ታዝንልኛለች..? ከእይታዋ ጋር አብሮ የሚነሳ ጥያቄዬ ነው፡፡ ስታየኝ ሰንብታ ወደ ሰርቪሱ ትገባለች፡፡ መልካም ቀን ሳትመኝልኝ ሄዳ አታውቅም፡፡ ከሠራሁበት በለጥ ያለ ገንዘብ አስጨብጣኝ ‹መልካም ቀን› ትለኛለች፡፡ ከዚያ መልካም ምኞት በኋላ ቀኖቼ የተባረኩ ነበሩ፡፡ ቀን ሙሉ አስባታለሁ…የቀኔ ትልቁ ሃሳቤ እሷና ሀሳቧ ናቸው፡፡

ሥራ ስፈታ ወደማነበው ጋዜጣ እጄን ሰድጄ አንድ መዘዝኩ። ከሃሳቤ ጋር የተጣጣመ አንድ መልዕክት ተመለከትኩ፡፡ ከዚያች ሴት መልካም ቀን በኋላ ሁሉም ነገር አገልጋዬ ሆኗል፡፡ ጋዜጣው ላይ እንዲህ ተጽፏል..ልብ የፍቅር ቦታ ነው፡፡ ፍቅር ባህሪው እዝነት ነው፡፡ የሚያዝኑ ሁሉ ለፍቅር የተረቱ ናቸው..› ከጋዜጣው ላይ ዓይኔንም ሃሳቤንም ሰብስቤ ‹ለማያውቁት ዝም ብሎ ማዘን ይቻላል? ስል ራሴን ጠየኩ፡፡ መልሱ ሲያቅተኝ ወደጋዜጣው ማተርኩ፡፡ ከእኔ እውነት እጅግ የራቀ መልስ ጋዜጣው ርቃን ላይ ተከትቦ አነበብኩ፡፡ እንዲህ ይላል ‹ልብ የእውነት ዙፋን ነው። ዙፋኑ ለመውደድና ለማፍቀር ሰው አይመርጥም..ዝም ብሎ ማፍቀር የዚህ ዙፋንና ልብ ባህሪዎች ናቸው›

በሃሳቤ ያቺን ሴት ተከተልኳት..እኔን ባየችበት የእዝነት እይታ ሌሎችን እያየች መሆኗን ሳስብ፣ ለእኔ ባቀረሩ እናታዊ ዓይኖቿ ለሌሎች ማቅረሯን ስረዳ ልጠላት ከአፋፍ ደረስኩ። እንደእሷ መሆን ተመኘሁኝም ፈራሁም፡፡ እንደእሷ መሆን ይናፍቃል እንጂ አይደረስም የሚለው መደምደሚያ ሃሳቤ ነበር፡፡

ወደጋዜጣው ቀልቤን ሰደድኩ..ከሌላ ሃሳብ እና እምነት ጋር አላተመኝ፡፡ ‹እግዜር ሲኦልን አልሠራም፡፡ ሲኦል የሰው ልጆች የሃሳብ፣ የምኞት፣ የድርጊት መዳረሻ ነው፡፡ የላይኛው ንጉሥ ልጆቹን ይቅር እያለ የሚኖር አባት ነው፡፡ ንጹህ እጁ በሲኦል አትቆሽሽም፡፡ ሲኦል ከእግዜር የሸሹ አእምሮና ልቦች የሚገኙበት የቅጽበት ድሎት ነው፡፡ ሌሎችን አለማፍቀር የሚፈጥረው የህመም ውጋት የነዚህ አእምሮና ልቦች ዘላለማዊ እዬዬ ነው›

chaep find more are making a special effort to accomplish new records in slimness.

ዝም አልኩ..በጽኑ፡፡ አንድ የጫማ ደንበኛዬ ፊቴ ቆሞ እስካስደነበረኝ ጊዜ ድረስ ከነዝምታዬ ነበርኩ፡፡ ለማታውቀው ለእኔ እንባ ያቀረሩ ዓይኖች ያሏትን ሴት በብርቱ ናፈኩ፡፡ ፍቅሬን ከዚህ ደንበኛዬ በመጀመር ልቤን የእዝነት ዙፋን ለማድረግ ማንም አልቀደመኝም ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥርስ በጥርስ ሆኜ የወዳጄን ጫማ ጠረኩ፡ ፈገግታዬ ደንበኛዬን ያስገረመ ይመስላል።

‹ዛሬ ደስተኛ ሆነሀል ምን ተገኘ?

‹ሲኦል ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ? አልኩት ከነሳቄ፡፡

‹አላውቅም..ግን የመከራ ቦታ፣ የክፉ ነፍሶች ማረፊያ› ይመስለኛል፡፡

ከመናገሬ በፊት ዝምታ ቀደመኝ፡፡ በደንበኛዬ ንግግር ‹ሰው ሁሉ ገብቶት የሚኖር ነው አልኩ፡፡ ግን የገባውን ያክል የሚኖር ሰው ባለማግኘቴ ግርምቴ ጣሪያ ተሻግሮ ሰማይ ነካ። ብዙዎቻችን ብዙ እናውቃለን ያወቅነውን ስንኖር ግን አንታይም፡፡ ማወቅ እውነትን ካልሰጠን ካለማወቅ የበረታ ስቃይ ነው የሚል አባባል ታወሰኝ፡፡

‹ምነው ዝም አልክ? ›የደንበኛዬ ድምጽ ተሰማኝ፡፡

‹አይ እንዲሁ ነው› አልኩት፡፡ ሁሉንም ትቼ ወደሳቄ ተመለስኩ፡፡ የማውቀውን ልኖር፣ ያላወኩትን ልጠይቅ አሁንን መረጥኩ፡፡ አንዲት ነፍስ ከነሃሳቧ ናፈቀችኝ፡፡

ከመቀመጫው እየተነሳ ‹ሁለት ብር ይጎድለኛል ሌላ ጊዜ እሞላልሃለሁ› ሲለኝ ከዝምታዬ እየባነንኩ ነበር፡፡ በዚህ ሰው ዛሬ ከነጋ..ከነጋ አልኩ ከመጣ ሦስት ጊዜ መበርገጌ ነው። ለማስደንገጥ የተፈጠረ መሰለኝ፡፡ ነው እኔ እሆን ለመደንገጥ የቀረብኩት? ጣቶቼን ወደሌሎች መቀሰሬን ትቼ ራሱን መፈተሽ ጀመርኩ፡፡ እውነት ነው እኔ ነኝ ለመደንገጥ የቀረብኩት፡፡ በዝምታ ተለጉሜ ራሴን ለድንጋጤ ባላመቻች ኖሮ በዚህ ሰው ንግግር ባልደነገጥኩ ነበር፡፡ እናም ጥፋቱ የኔ ነው አልኩ፡፡ የማውቀውን ለመኖር ቃል ገብቼ የለ? ራሱን ተጠያቄ በማድረግ እውነትን ጀመርኩ፡፡

ሁለት ብር የጎደለውን ፍራንክ ዘረጋልኝ፡፡

‹ዛሬ በእኔ ወጪ ነው..ዘና በል አልኩት..

‹ምን ተገኘ? አለኝ፡፡

‹ሰዎችን ለማስደሰት አዲስ ነገር አያስፈልግም፡፡ ያለኝን ስቆጥር የሊስትሮ ባለሙያ ሆኜ ራሴን አገኘሁት እናም ባለኝ ነገር ሰዎችን ላስደስት ተነሳሁ፡፡

‹አመሰግናለሁ..› አለኝ፡፡

በሳቄ እጅ ነሳሁት፡፡

‹መልካም ቀን› ብሎኝ ሲሄድ ግን በታላቅ መገረም ውስጥ ነበርኩ፡፡ እስከዛሬ ወደእኔ በተመላለሰባቸው ማለዳዎች እና ከሰዓቶች ውስጥ አንድም ቀን ‹መልካም ቀን› ብሎኝ አያውቅም ነበር፡፡ ሳቄ በፊቴ ላይ ጎመራ፡፡ በሰማይ ርቃን ላይ እንደሚጥመለመል የመብረቅ ፍላጻ ፊቴ በብዙ ፈገግታ ፈካ። ተቀይሬ የቀየርኩት መሰለኝ፡፡ መሰለኝ አይደለም ነው ስል ደመደምኩ፡፡ ለዘላለም በማውቀው ፊቱ ላይ ያላስተዋልኩት ፈገግታና በጎ ቃል በእኔ ካልሆነ በማን መጣ? ያ በምንም የሚፈግ የማይመስለው ቁጡ መሳይ ፊቱ ርህራሄን ለብሶ ሲሄድ ከእኔ ውጪ ማን ተጠያቂ ሊሆን ይችላል? ለመጀመሪያ ጊዜ በራሴ ኮራሁ፡፡

ጀምበር ሸሸች..ጠዋት ሆነ..

ሰርቪስ ከሚጠብቁ ሴቶች መሀል ቦርሳዋን በእጇ ያንጠለጠለች አንድ ሴት ፈለኩ አላገኘሁም፡፡ እንዲህ የምታረፍድበት አንዳንድ ጊዜዎች አሉ፡፡ ከነጋ አልቆየም የቀደመኝ ለማኝ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ሌሊት ቀረች ብዬ መስጋቴ ራሴን እንድጠራጠረው አደረገኝ፡፡ እንዲህ አስቤ አላቆየሁም። ተሻግሮ ካለው አስፓልት መኪና ለማሳለፍ ቆማ አየኋት፡፡ የጀመርኩትን ጫማ ለመጨረስ ዝቅ ባልኩበት ሰሞን ‹ከእንዴት አደርክ ጋር አንድ ሂል ያደረገ እግር ሊስትሮ ዕቃዬ ላይ ሲያርፍ አንድ ሆነ። ቀና ስል እሷ ናት..የቋጠርኩት ፈገግታ ያለ ይመስል እንዳየኋት ደስታዬን ለቀኩት፡፡ እሷን በተመለከተ ብዙ የተሳሳትኩት ነገር እንዳለ በእግሮቿ ውበት ነበር ያመንኩት፡፡ ከትናንት በፊት ያለው እኔ አሳቀኝ፡፡ ዛሬ ብቻ አይደለም ሁሌም የምስቅበትን እኔ አሻግሬ ተመለከትኩት፡፡ ሳያይ የሚፈርድ፣ በይሆናል የሚኖር ሆኖ አገኘሁት፡፡

በውበት ያጌጡ እግሮቿን ሊስትሮ ዕቃዬ ላይ ሳያቸው ልታርፍ መስሎኝ ዝም አልኩ፡፡

‹ሰርቪስ እንዳያመልጠኝ..›

ስትለኝ..እንድጠርግላት የፈለገች መሰለኝ፡፡ ምኑን እንደምጠርግ ግራ ገባኝ፡፡ እግሮቿም ጫማዎቿም ንጹህ ናቸው። ለመጥረግ እንዲመቸኝ ይመስለኛል..ነው እንጂ ከዚች ደግ ሴት ልብ ውስጥ ከዚህ ወዲያ ምን ይታሰባል? ቁርጭምጭሚቷ ላይ ያረፈ ሱሪዋን ወደ ላይ ሳበችልኝ፡፡ ከማልቋቋመው ባቷ ጋር ተፋጠጥኩ። በጥልፍልፍ ሂል ውስጥ ጣቶቿን አየኋቸው። በውበት እና በማማር የአራስ ልጅ ጣቶች ይመስላሉ..፡፡ ቀይ ባት..ከረጃጅም ጣቶች እና ከተስተካከሉ ጥፍሮች ጋር..የቀኔ ምርጥ ገጠመኝ ሆኖ አለፈ፡፡

‹ካላፈቀሩበት ልብ ሲኦል ነው..ሞቶ የሚገል› የሚል ከየት እንደመጣ የማላውቀው ሃሳብ ወደአእምሮዬ ሰተት አለ። ቀና ብዬ አየኋት በነዛ ፊቴ ሲቀርቡ በሚያዩኝ አዛኝ ዓይኖቿ ስታስተውለኝ እጅ ከፍንጅ ያዝኳት፡፡

አንድ ጥያቄ አለመጠየቅ አልቻልኩም..፡፡ ልጠይቃት አፌን ሳሞጠሙጥ ወዲያው መልሱ ልቤ ውስጥ ተፈጠረ፡፡

ጥያቄዬ..

‹ጉድፍ ያልነካቸውን አዲስ ጫማዎችሽን እንድጠርግልሽ ወደእኔ የምትመጪው ስለምን ነው?

መልሱ..

የገባህ ስለገባኝ..

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን  መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You