የመጀመሪያው የትምህርት ሳምንት እንዴት አለፈ?

ሠላም ልጆች እንዴት ናችሁ? ሳምንቱ እንዴት አለፈ? በጥሩ እንዳሳለፋችሁት ምንም ጥርጥር የለኝም።ትምህርት ቤቶች ማድረግ ያለባቸውን ዝግጅት ጨርሰው እናተን መቀበል ጀምረዋል።በዚህም ምክንያት አብዛኞቻችሁ ያለፈውን ሳምንት በትምህርት እንዳሳለፋችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። ከዚህ ጎን ለጎንም የናፈቃችኋቸውን ጓደኞቻችሁን፣ መምህራን እና በትምህርት ቤት ውስጥ የሚሠሩትን ሌሎች ሰዎች ዳግም በመገናኘታችሁ ደስ እንዳላችሁ ምንም አልጠራጠርም።

ልጆችዬ ከረዥም ጊዜ ረፍት በኋላ ትምህርት ስትጀምሩ ምን ተሰማችሁ? በርግጥ እናንተ ጎበዞች ስለሆናችሁ አልከበዳችሁም አይደል?።የክረምቱን ወቅት በንባብ እንዲሁም ትምህርታችሁን ላለመርሳት ደብተሮቻችሁን በማንበብ ጥረት ስታደርጉ እንደነበር እተማመናለሁ። ከዚህ በኋላም በክፍል ውስጥ በንቃት በመከታተል፣ በማጥናት እና መምህራኖቻችሁን በመጠየቅ በትምህርታችሁ መጠንከር ይኖርባችኋል፡፡

አንዳንዶቻችሁ ደግሞ ከዚህ ቀደም ከነበራችሁበት ትምህርት ቤት በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሌላ ትምህርት ቤት የገባችሁ ተማሪዎች ትኖራላችሁ። በተለይም ለእናንተ እንደ አዲስ ተማሪዎችን እና መምህራንን መተዋወቅ ግድ ይላችኋል።ነገሮች ለጊዜው አዲስ ሊሆንባችሁ እንደሚችል በመገመት፤ ከተማሪዎች፣ ከመምህራን ጋር በመላመድ፤ ትምህርታችሁን እየተከታተላችሁ ፣ እያጠናችሁ እና እየተጫወታችሁ የትምህርት ጊዜያችሁን በጥሩ መንገድ ማስኬድ ትችላላችሁ፡፡

ያለፈው ሳምንት ትምህርቱ አሰጣጥ ከሌላው ጊዜ ቀለል ያለ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።ከዚህ በኋላ ግን ወደ መደበኛው የመማር ማስተማሩ ሂደት በስፋት ስለሚገባ የክፍል እና የቤት ሥራዎችን በመሥራት፣ ያልገባችሁን በመጠየቅ፣ በማጥናት በክፍል ውስጥ ባለመረበሽ ትምህርታችሁን በንቃት ከተከታተላችሁ ጎበዝ ተማሪ እንድትሆኑ ይረዳችኋል።

ወደ ወላጆች ደግሞ እንለፍ። ወላጆች ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆቻቸውን ለሀገር፣ ለወገን እና ለራሳቸው እንዲጠቅሙ በማሰብ ስማችሁ መርቃችሁ ትሸኛላችሁ። በይበልጥ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ልጆቻችሁን ወደ ትምህርት ቤት የላካችሁ ወላጆች ስሜታችሁ ድብልቅልቅ (የደስታና የኀዘን) ያለ እንደሚሆን ይጠበቃል።ከዚህ ቀደም ልጆቹ አብረዋችሁ የሚውሉ ከሆነ እና ከነሱ ተይቶ ለመዋል ከባድ ሆኖባቸው ልጅም ወላጅም በጋራ ሲያልቅሱ ይታያሉ።ይሁን እንጂ ለልጆቻችሁ ለወደፊት ሕይወት እንደ አንድ ወሳኝ ምዕራፍ የሚታይ መሆኑን መዘንጋት የለባችሁም።እንዲህ አይነቱ ነገር በጊዜ ሒደት የሚለመድ ሲሆን፤ ልጆቻችሁ እናንተን አይተው እንዳይረበሹ ይህንን ወቅት በጥንካሬ ማሳለፍ ይኖርባችኋል።

በተጨማሪም ልጆቻችሁ ትምህርት እንዲወዱ ስለ ትምህርት ጥሩ ነገር በመንገር እና በትምህርት ቤት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ምን እንደሚመስል በዝርዝር በመንገር የጀመሩትን ትምህርት በተሻለ መንገድ እንዲቀጥሉ በሥነ ልቦና ዝግጁ ማድረግ ከወላጅ ወይም አሳዳጊ የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው።

ከትምህርት ቤት ሲመለሱም ትምህርታቸውን እንዲያጠኑ ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ለምሳሌ የማጥኛ ሥፍራ በማዘጋጀት፣ እንደ ቴሌቪዥን፣ ታብሌት፣ የእጅ ስልክ (ሞባይል) ያሉ እና መሰል የልጆችን ትኩረት በቀላሉ ሊስቡ የሚችሉ ነገሮችን ማራቅ ይገባል።እንዲሁም ወደ የመኝታ (እንቅልፍ የሚተኙበትን እና የሚነሱበትን) ሰዓት እና የጥናት ሰዓታቸውን በማውጣት፣ የትምህርት ቤት ውሏቸው ምን እንደሚመስል በመጠየቅ፤ ልጆች የትምህርት ቤት ውሏቸውን እንዲወዱት ማለማመድ ይገባል።

ታዲያ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትምህርት ቤት የገቡ ልጆችን ተጨንቀው እንዲያጠኑ ከማድረግ ይልቅ በማጫወት እና ዘና እንዲሉ በማድረግ ትምህርት ቤት ገብቶ መማር ቀላል እንጂ ከባድ አይደለም የሚለውን ነገር እንዲስቡ ያደርጋቸዋል።ሁኔታዎች የተመቻቸላችሁ ከሆነም እነርሱን ለማበረታታት ከልጆቻችሁ ጋር በጋራ በማንበብ እና በመጻፍ ብታለማምዱ የትምህርት ፍላጎታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ለማነሳሳት ያግዛቸዋል።ገና ማንበብ ያልጀመሩ ወይም የማይችሉ ልጆቻችሁን ደግሞ ተረት በማንበብ፤ የማንበብ ልምድ እንዲኖራቸው ከወዲሁ ከማለማመድ ባሻገር ከልጆቻችሁ ጋር ደስተኛ ጊዜ እንድታሳልፉ ይረዳችኋል።

ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ማሰብ ያለባችሁ ነገር ቢኖር፤ አንዳንድ ተማሪዎች ደፋር፣ ተግባቢ… ሲሆኑ፤ አንዳዶቹ ደግሞ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ለመላመድ ጊዜ የሚፈጅባቸው፣ ቁጡ፣ አኩራፊ ወይም የሚፈሩ እና መሰል ጸባይ ያላቸው መሆኑን በማጤን፤ ልጆቻችሁን የምክር እና የሥነ ልቦና ድጋፍ ልታደርጉላቸው ይገባል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ይሁን ከዚህ ቀደም ወደ ትምህርት ቤት የገቡ ልጆች ትምህርታቸውን ያለ አንዳች እንከን እና ለቀጣዩ ቀን ደስ ብሏቸው እንዲሄዱ በማድረጉ በኩል የመምህራን ድርሻ ላቅ ያለ ነው።የነገ ሀገር ተረካቢውን ዜጋ በሥነ ምግባር የታነጸ እንዲሆን በማድረግ መምህራኑ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።ስለሆነም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትምህርት ቤት የሚመጡ ልጆች እንግዳ ነገር ሊያሳዩ የሚችሉ መሆኑን በማሰብ ሂደቱን እስኪለማመዱት ድረስ በትዕግስት መወጣት ይኖርባችኋል፡፡

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን መስከረም 13/2016

Recommended For You