የመስዋዕትነት ቀንዲል

ለዛሬው ብዕራችን የምትሆነዋን ቄጤማ ከመስዋዕትነት ላይ ቆርጠን ከኪነ ጥበብ ደጅ ላይ እየነሰነስን እንጎዝጉዛት። ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገሪያ ከሆኑት እንቡጦቹ የጳጉሜ ቀናት መካከልም የዛሬዋ ጳጉሜያችን ይህንን የመስዋዕትነት የብዕር ጠብታ እናቀርብላት ዘንድ ትወዳለች። የዛሬዋ ዕለት የመስዋዕት ቀን ተብላ ተሰይማለችና፡፡ ታዲያ እኛም ይህን ማለታችን በምክንያት ነውና ዕለቷን በብዕራችን ልንካድማት ወደድን። ሙሽራ ያለ ሚዜ፤ ሠርግም ያለ አጃቢ ድምቀት የለውም። እናም የዛሬዋ ልዩ የጳጉሜ ቀን በመስዋዕትነት ቀን ከመሰየሟም በላይ ካስተዋልናቸው ከሥር መሠረታቸው አንስቶ ሁሉም የጳጉሜ ቀናት በመስዋዕትነት የተመሰሉ ናቸው። ብዙኀኑ ጊዜና ጉልበት፣ እውቀቱን ሰውቶ ሀገርና ሕዝቡን በነፃ የሚያገለግልባቸው ናቸው። የመንግሥት ሠራተኛውም ነፃ አገልግሎቱን ከነፃ ፈቃዱ ጋር ለሀገሩ የሚሰጥበት ነው፡፡ ይህን የተረዱ ሀገር ወዳድና ቅን የሆኑ የቤት አከራዮችም የነዚህን ቀናት የቤት ኪራይ አይጠይቁም። መሰል አገልግሎቶችን በተመሳሳይ መልኩ የሚሰጡ ሌሎችም አሉ። ታዲያ መስዋዕትነት ማለት የራስን ጥቅም ትቶ የሌሎችን ማስቀደም እስከሆነ ድረስ መላው የጳጉሜ ቀናት ጥንቱን የመስዋዕትነት ናቸው ብንል ስህተት አይሆንም፡፡ መስዋዕትነት የምትለዋን ቃል እንዲያው እንደዋዛ እንዲህ ናት እንዲያ ናት ለማለት ከቶ አታስደፍርም ትርጓሜዋ ሰፊ ሀሳቧም እጅጉን እረቂቅ ነውና። እኛ ግን ለዛሬው ከኪነ ጥበቡ አኳያ ከርሰ ምድሯን እየቆፈርን የቻልነውን ያህል ጠልቀን እንገባለን።

መስዋዕትነትን በኪነ ጥበባዊ መነጽራችን ስንመለከት ምናልባትም ለአንዳንዶቻችን ምስሉ ፈዞና ደብዝዞ ይታየን ይሆናል፤ እውነታው ግን ኪነ ጥበብ ያለመስዋዕትነት ሻይ በጨው እንደማለት ነው። የጥበብ ሰው ሥራው መስዋዕት፤ ሕይወቱም የመስዋዕትነት ነው። በጣም ለምንወደው ሰው ያለችንን ነገር ያለ ስስት ብንሰጠው ይሄ የፍቅር ስጦታ ነው፤ ነገር ግን ከምንሰጠው ነገር ጋር እራሳችንንም ጨምረን ብነሰጠው ይሄ ደግሞ የመስዋዕትነት ስጦታ ይባላል። መስዋዕትነት መስጠትን ብቻ ሳይሆን መሰጠትንም ይጠይቃል። ኪነ ጥበብ ደግሞ ይህንን አብዝቶ ይሻል። በሀገራችን ውስጥ በተለይ ደግሞ ቀደም ባሉት ጊዜያት የጥበብ ሰዎች ብቻም ሳይሆኑ ኪነ ጥበብ እራሷ መስዋዕትነትን ስትከፍል ቆይታለች። በመጥፎ የፖለቲካ ጥላሸት መልኳ እየጠቋቆረ፣ ልቧ እየተሰበረ ልጆቿ ተበትነውባታል። ከሙዚቀኛ እስከ ገጣሚ፣ ከሀያሲ እስከ ደራሲ፣ ከቲያትር አዘጋጅ እስከ ተዋናይ መስዋዕት እየሆኑ ለእስርና ለእንግልት አልፎም ለሞት ድግስ በቅተዋል። ‘ማን ያውራ የነበረ፤ማን ያርዳ የቀበረ’ ቢሉ ለዚህ ምስክሩ ብዙ ነው። ያለ ኪነ ጥበብና የጥበብ ሰዎች የሚሰፋ ቀዳዳም ሆነ የሚዘውር መርፌ የለምና እያንዳንዱን ቀዳዳ ለመሸፈን በሮጡ ቁጥር ከበስተኋላ የሚግትለተለው የዱላ መዓትም በዚያው ልክ ነው።

መስዋዕትነት፤ ያለ ደም ስርየት የለም! እንደሚባለው ዓይነት በአራት ነጥብ ተዘግቶ በቃለ አጋኖ የተከረቸመ ጉዳይ አይደለም። መስዋዕትነት ደረጃዋ ከፍ ሲል ሞት እንደ ጅብራ ከፊታችን ተደንቅሮ ይበላን ይሆናል፤ ነገር ግን አንዳንዶች እንደሚያስቡት በደም ተለውሰን ወደ መቃብር ካልገሰገስን መስዋዕትነት አይባልም ካልን ግዙፍ ስህተት ነው። የምንወደውን ለምንወደው ስንል ከተውን፣ ለሙያችን ታምነን የሚመጣውን ሁሉ ከተጋፈጥን፣ ከግል ጥቅማችን ይልቅ ሀገርና ሕዝብን ማስቀደም ከቻልን መስዋዕትነት ነው። በየትኛውም ዘመን ኪነ ጥበብ ያለ መስዋዕትነት ኖራ አታውቅም። ያለዚህ ካስማ መቆም ትችላለች ብሎ የሚሞግት ካለም አውቆ የተጋደመ ሃሳቡም የተወላገደ ብቻ ነው። አንድ የጥበብ ሰው የመጀመሪያውን የመስዋዕትነት ጉዞውን የሚጀምረው የራሱን ሕይወት ቁጥብ በማድረግ ነው። ታዋቂነቱና ዝናው በጨመረ ቁጥር ማኅበራዊ ኃላፊነቱም ይጨምራል። እርሱን የሚያይና የሚሰማ ብዙኃኑ እንደመሆኑ እንደማንኛውም ሰው ሀገርና ሕዝብ ባህል እሴቱ ጥንቅር ይበሉ እያለ ያሻኝን ተናግሬ፣ እንዳሻኝ ተሰባብሬ ልኑር ማለት አይችልም። ይልቁንስ ሁለንተናውን ለማኅበረሰቡ ዓይንና ጆሮ የማይጎረብጥ፤ ተምሳሌትነቱም የማያዳልጥ ማድረግ ይጠበቅበታል። ከራሱ ደስታ የሌላውን አስበልጦ የሚወደውን ነገር ለሚወደው ሕዝብ ሲል መተው ከቻለ ይህም ትልቅ መስዋዕትነት ነው።

በሌላኛው የኪነ ጥበብ ጫፍ የምትገኘዋ የመስዋዕትነት ሰበዝ ደግሞ ሙያዊ ግብርን ትቋጥራለች። እሬት መራራነቱ፤ ማርም ጣፋጭነቱ ሳይቀመስ እንዴት ይሆናል። የምንሠራው ለማኅበረሰባችን መሆኑን ካወቅን ማኅበረሰባችንን ከሥር መሠረቱ ማወቅ፣ ማጤን ከዚያም በላይ የሚወጣውን ዳገት ወጥተን የሚወርደውን ቁልቁለት ወርደን የሚኖረውንም ኑሮ ቀምሰን ማየት አለብን። ሥራዎቻችንን ሠርተን የምናቀርበው በስማ በለው የስሚ ስሚ እሩጫ ከሆነ ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ መፈታቱ አይቀርም። ያልኖረውንና የማያውቀውን ሕይወት የሚጽፍ ደራሲ ያልበላውን እንደሚያክ ሰው ነውና በብዕር ጥፍር እራሱን ከማድማት በቀር ስሜት አይሰጥም። የሚሞነጫጭረው ሁሉ መቦጫጨር ይሆንበታል። ታሪክ ይፋለሳል፤ እውነትም ይደበቃል። ከምናባዊ እይታችን ባሻገር ስለምናነሳቸው ታሪኮች ወርደን አይተን የእያንዳንዱን ገጸ ባህሪያት እውነታ በዚያው ውሃ ልክ መሥራት ይኖርብናል። ኪነ ጥበብ ሠርቶ በማሳየት ሆኖ በመኖር የበለጸገች ናት፡፡ ይህን የሚያደርጉ ለሙያና ለሕዝባቸው የሚጨነቁ ምስጉኖችም በርካቶች ናቸው። አንዳንድ ጊዜ በሙዚቃው፣ በመጽሐፍቱና በፊልሙ ዓለም በይሆናል ግምት ተካተው ትችትና ወቀሳን የተስተናገዱባቸው አጋጣሚዎችም ቀላል አይደሉም። ለሙያው ክብር ስንል በትዕግስትና ጽናት በብዙ ውጣወረዶች መሃከል እያለፍን ለሥራችን ግብዓት ለሚሆነን እውነት በመስዋዕትነት ስንዳክር ፍሬውም ያማረና የሚጣፍጥ ይሆናል። ይሄ እውነታ ያልገባው የጥበብ ሰውም ልጓም እንደሌለው ደንባራ ፈረስ መሆኑ አይቀሬ ነው። በፈረጠጠና በደነበረ ቁጥር አዝሎ የተሸከመውን ሀገርና ሕዝብ አንገት እየረገጠ ብዙኃኑን ከመሬት ጋር ማላተም ይጀምራል።

በጥበብ ቤት ስንሰነብት አንድ እግራችን የእኛ አንድ እግራችን የሕዝብ፣ አንድ እጃችን የእኛ ሌላኛውም የሕዝብ ነው። በልባችን ማህደር ውስጥ ያለው መሪ ቃልም ለእኔና ለሕዝቤ፣ለእኔና ለሀገሬ እንጂ፤ ከራስ በላይ ንፋስ እያልን ለእኔ ለእኔ ካበዛን ሳንሞቅ እንገነፍላለን። የጥበብ ሰው ሁሌም ከማኅበረሰቡ ዓይን ሥር ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ዝነኛ ፖለቲከኛ ከማኅበረሰቡ ጎን ባይቆም ማኅበረሰቡ ላይሞቀው ላይበርደው ይችል ይሆናል፤ አንድ ዝነኛ የኪነ ጥበብ ሰው በችግሩ ጊዜ ከጎኑ አለመቆሙን ሲያውቅ ግን ሕመሙ እስከ አጥንቱ ዘልቆ ይገባል። ቁጣውም በደም ሥሩ ይዘዋወራል፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሳይቀር የሚወርደው የቁጣ መዓት አይጣል አያድርስ ነው። ሕዝቡ እንዲህ የሚሆነው ስለሚጠላው ሳይሆን ከማንም በላይ የእኔና ለእኔ የቆመ ነው ብሎ ስለሚያስብ ነው። ፖለቲካና ፖለቲከኛው በፖለቲካ ሲወድቅ፣ መንግሥትም በመንግሥት ሲሻር፣ ኪነ ጥበብና የጥበብ ሰው ውልደትና ሞታቸው በማኅበረሰቡ ውስጥ ነው።

እንግዲህ ይህቺን የመስዋዕትነት ቀን በኪነ ጥበብ ደጅ አስቀምጠን በገረፍታም በጨረፍታም ካነሳናት አይቀር ከወዲሁ ደግሞ፤

አትሮኖሱን ያዙ አንድ ታሪክ አለ፣

በጨርቅ ተሸፍኖ የተጠቀለለ

በጉንጉን ሳይደምቅ ካፈር የተጣለ፣

ሞትም እንደ ምስጢር በጉም ተሰቀለ።

ፋኖሱን ለኩሱ ላባውንም አብሩ፣

ቀንዲሏን ይዛችሁ ማዶ ተሻገሩ፣

እናም ይቺን እውነት እስቲ ተናገሩ፣

ለጥበብ ከሞቱት እነማን ነበሩ?

ብለን ስንጠይቅ በኪነ ጥበቡ ዓለም በሥራው ምክንያት በመስዋዕትነት ቆመጥ ስለተቀጨ አንድ ሰው ጥቂት ማንሳት የግድ ይለናል። በ20ኛው ክፍለ ዘመን በሀገራችን ውስጥ ከነበሩ ታላላቅ ደራሲያን መሃከል ስለሆነው በዓሉ ግርማ፤

እውነት ነው በሀገራችን ኪነ ጥበብ ውስጥ በርካቶች ለቆሙለት አላማ ሲሉ እራሳቸውን የመስዋዕት በግ አድርገው አቅርበዋል። በመስዋዕትነት እሳት እንደ ሻማ ቀልጠው ለእኛ ብርሃን ለሰጡንና እንደ ወርቅ ነደው የእንቁ ፈርጥ ማንነታቸውን ከሥራዎቻቸው ጋር ትተውልን የሄዱ ብዙዎችን አልቅሰን ቀብረናቸዋል። ከመቃብራቸው በላይ ባለው የድንጋይ ሐውልታቸው ላይም ሕያውነታቸውን ቀርጸን አኑረንበታል። ግራ ቀኝ እየነፈሰ ግራ ገብቶን ዘመናትን በዝምታ የቆዘምንበት የበዓሉ ግርማ ዓይነት ሌላ ታሪክም አለን። በ1975 ዓ.ም በዓሉ ግርማ ኦሮማይን ጻፈ። የአንድ እናት ልጆች በነበሩት የኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝቦች መሃከል የሚካሄደው የበረሀ ላይ ጦርነት የፖለቲካው ዳፋ እንጂ የሕዝብ ለሕዝብ ጥላቻ አልነበረም። ይህን ሴራ የቅርብ ሆኖ ሲከታተል የነበረው ደራሲውም በኦሮማይ ገለጠው። የመጽሐፉ አርእስት እንዳዘለው ፍቺም አበቃ፤ አከተመ ፍጻሜውም ተቃርቧል ሲል የማንቂያ ደወሏ ከብዕሩ ጫፍ አቃጨለች። ድምጿን የሰማው የደርግ መንግሥትም እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ በንዴት ጸጉሩን አቁሞ ወደ በዓሉ ግርማ ገሰገሰ። ታላቁ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ እውነትን በመስዋዕትነት ካቆማት ወዲያ እርሱ ግን የለም። ከኦሮማይ ዋሻ የወጣ አንዳች ጅብ በልቶት የሥጋን ሞት ሞተ። በዓሉን የበላውን ጅብ ጥልቅ ምስጢር በኦሮማይ መጽሐፉ ውስጥ ካለው ከጋዜጠኛው ጸጋዬ ወይንም ደግሞ ከውቧ ፊያሜታ ዘንድ ያገኘን እንደሆን እንጂ ሌላ ማንም ሊፈታው አልቻለም። ጅቡም ቢሆን አንተ ነህ ወይ የበላኸው ተብሎ አይጠየቅ ነገር የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ። ጥበበኛውን እንጂ ጥበብን ማን ደፍሮ ይገድላታል? ሕዝባዊ እውነታውን በተዋበ ብዕሩ የከተበው የጥበብ ሰው በማይመለሰው ሞገደኛ ጅረት ውስጥ ተጥሎ እስከወዲያኛው ቢያልፍም፤ጥበብ ግን ለዘለዓለሙ ትዘክረዋለች።

ከዚህም በላይ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ከኦሮማይ መጽሐፍ ሥር ህያው ሆኖ የቆየውን የበዓሉ ግርማ ዳግመ ትንሳኤው በሚመስል መልኩ የዛሬ ሁለት ወር ገደማ ጸሐፊ ተውኔትና የቲያትር አዘጋጁ ውድነህ ክፍሌ እንደገና አካል አልብሶና ሕይወት ዘርቶ በቲያትር መድረክ ላይ አቁሞት አየን። ቲያትሩን ለተመለከተም እውነትም በዓሉ ግርማ አልሞተም የሚያስብል ነበር። ኪነ ጥበብ በመስዋዕትነት ያለፈውን ሰው ትናንትና ነበር ብሎ ብቻ ሳይሆን ዛሬም አለ ብሎ ማሳየትን ይችልበታል ያልነው ለዚህ ነው። ታሪክ በግርድፉ በቃላት የቆመ እውነት ነው፤ ኪነ ጥበብ ግን በእውነት ላይ አካላዊ አምሳል ለብሶ የቆመ ማንነትና ምንነት ነው፡፡ ታሪክ ቢረሳው እንኳን ኪነ ጥበብ ግን ፈጽሞ አይረሳውም። «ስለ ልዑላኑ ማውራት ከአንገት ያሳጥራል» የሚል የአንድ የጥንት ፈላስፋ አባባል ነበር፤ በበዓሉ ግርማ የሆነውም እንደዚሁ ነው። ይሄም ለሚወዷት ሀገርና ሙያ ሲባል በራስ ላይ የተከረቸመ ትልቁ የመስዋዕትነት በር ነው።

ሀገር በጦርነት ቅርቃር ተሰንቅራ ለነፃነት ትግሏ ከጠላቶቿ ጋር አንገት ላንገት ስትተናነቀ ኪነ ጥበብ መች ሸሽታ ታውቃለች..ወታደሩ ጋሻና ጃግሬውን ይዞ ዘራፍ እያለ ሲወጣ በለው! እያለ የጠላቱን አንገት ሲያስቀላ የነበረው የኋላኛው ደጀን የኪነ ጥበቡ ትንታግ ነበር። ከፊቱ የሚገኘውን አርበኛ በቃላት እየቆሰቆሰ እሳት አስታጥቆ ጠላትን ድባቅ ያስመታባቸውን የድል ታሪኮች የጦርነት አውድማዎቹ ይመሰክሩታል። አንዴ በሙዚቃና ግጥም፣ ሌላ ጊዜ በሽለላና ፉከራ እንዲሁም በቀረርቶው የሠራዊቱን ልብ በእናት ሀገሩ የመስዋዕትነት እስትንፋስ እየሞላው በወኔ የድል ጫፍ ማስነካቱ አይካድም። የጥበቡ ዓለም ሰዎች በእናት ሀገራቸው ጥሪ ጀግናውን አርበኛ እየተከተሉ ያልተሳተፉበት የጦርነት አውድማ ከቶ ከወዴት አለ? ለነብሳቸው ሳይራሩ በጥበባዊ ወኔና በሀገራዊ ፍቅር በመስዋዕትነት ሕይወታቸውን ገብረዋል። ኪነ ጥበብ በመስዋዕትነት ጀግናን ይወልዳል፤ የሞተውንም ታሪክ ይቀሰቅሳል፡፡ ብዕርም በጠብታዋ የሥርየት ቀንዲል ታበራለች፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን    ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You