ጊዜው በዱላ ቅብብሎሽ እየሮጠ አንዱ ሌላውን ለመተካት በማኮብኮብ ላይ ናቸው። 2015 ግብሩን አጠናቆ ለ2016 ለመስጠት በማቀዝቀዝ፤ 2016ም በማሟሟቅ ስለመሆኑ ባወራ ለቀባሪ መርዶ እንደማርዳት ነውና ነገር ግን ከበስተጀርባ በአዲስ ዓመት አዲስ ነገር መኖሩ የማይቀር ነው። ምን አለ ካላችሁኝ እኔም ልንገራችሁ። ጥበብ ድግሷን ደግሳ በሙዚቃ አውቶብስ ከተዋበው የሸራተን አዲስ ደጅ ላይ ለመድረስ አስባለች።
በየዓመቱ የአዲስ ዓመት ዋዜማ በደረሰ ቁጥር ለበዓሉ ማድመቂያ እንቁጣጣሽን ተከትሎ እንቁ ስጦታዋን እንናፍቃለንና ዘንድሮም አልቦዘንኩም ትለናለች። በአሁናዊው የሀገራችን ሁኔታ ብዙዎች በጭንቅና በምጥ፣ በሰላም ማጣት፣ ስደት የበዛበት እንደመሆኑ የሰላም አርማ በሆነው ሙዚቃ ሰላምን እናወርድ ዘንድ በ2016 ዓ.ም ዋዜማ ላይ “ሰላም” በተሰኘ የሙዚቃ ኮንሰርት ከመልካም ምኞት ጋር ብቅ ብላለች። የ2015 መጥፎ ትዝታዎቻችንን ለመሻር አንድም በተማጽኖ፤ አንድም በፍቅር ጥበብን በሙዚቃ፣ ሙዚቃን ለሰላም በዋዜማው ምሽት።
በዘንድሮው የአዲስ ዓመት ዋዜማ አብረን አምሽተን አብረን በማንጋት የሀገራችንን የሰላም ንጋት በአንድነት እንመልከት የሚል መልዕክት ያለው የሙዚቃ ኮንሰርት በዋዜማው ምሽት ሊሰናዳ ስለመሆኑ ተገልጿል። “ከወዴት?” ከተባለ ደግሞ መንገዱ ወደ ሸራተን ይዞን ሳይነጉድ አልቀረም። ይህ ኮንሰርት ለ25 ዓመታት ያህል በየዓመቱ በዋዜማው ሲዘጋጅ የነበረ በሳል የሙዚቃ ኮንሰርት ቢሆንም የዘንድሮው ግን በሁሉም ነገሩ ለየት ያለ ነው ሲሉ አዘጋጆቹ ባሳለፍነው ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል። በእለቱ በርካታ የሚዲያ ጋዜጠኞች ከሸራተን አዲስ በመገኘት ካሜራቸውን ከኮንሰርቱ አዘጋጆች ፊት ደግነው፣ የተባለውን ሰምተው በተራቸው የተሰማቸውንም ብለዋል። ለመሆኑ አዘጋጆቹ ስለ ኮንሰርቱ ምን አሉ?
ኮንሰርቱን ለማዘጋጀት በሀገራችን ውስጥ የሚገኙ ትላልቅ ኩባንያዎችና ድርጅቶች በአንድነት በመዋሃድ አንድነትን ለማምጣት በሰላም ኮንሰርት ላይ አንድ ሆነዋል። በርካቶች የኮንሰርቱ አጋር ቢሆኑም በኢትዮጵያ ታሪክ አዳዲስ የመዝናኛ ስራዎችን ለሀገራችን በማበርከት ፊተኛ የሆነው ይሳካል ኢንተርቴይመንትና ሸራተን አዲስ በባለቤትነት የሚመሩት ስለመሆኑ ገልጸዋል። በዚህ ኮንሰርት ላይ አንድ ዝነኛና ዓለም አቀፍ አቀንቃኝ ስለመጋበዙም አውስተዋል። በመድረክ ስሙ “ሬማ” በመባል የሚታወቀው ናይጄሪያዊው የአፍሮ ቢት አቀንቃኝ በኢትዮጵያ ሰማይ በሮ በሸራተን አዲስ ኮንሰርት ላይ ሊገኝ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የኮንሰርቱ ስያሜ ሰላም የሚል ስያሜ የተሰጠው መሆኑን የገለጹት የይሳካል ኢንተርቴይመንት ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ኢዮብ “ሰላም ለሀገርና ለህዝብ ህልውና መሰረት ቢሆንም አሁን አሁን በሀገራችን ያለው ሁኔታ ግን አሳሳቢ ነው። የሀገራችን ህዝብ ሁሉ ሰላምን ይናፍቃል። እኛም ይህን ኮንሰርት “ሰላም” ብለን ስነሰይመው ሰላምን ለሀገራችን በመመኘት ነው። ሙዚቃ ደግሞ የሰላም መግለጫ መሳሪያ እንደመሆኑ በዚህ ኮንሰርት አንድነትን በማስፈን የሰላምን ግብዣ ለማድረግ ጭምር ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
እውነት ነው ሙዚቃ የሰላምና የፍቅር መለፈፊያ ጥሩምባ ነው። የሙዚቃን ድምጽ መስማት ለቻለ ከሀዘን ድባብ፣ ከጥላቻ መንገድ፣ ከልዩነት ባህር ተሸክሞ የማውጣት ኃይል አለው። የጦር መሳሪያ ጆሮን ያደነቁራል፣ ልብንም ይሰብራል፤ የሙዚቃ መሳሪያ ግን የደነቆረውን የመክፈት፣ የተሰበረውን የመጠገን ኃይል አለው። በጥላቻና ቁርሾ፣ በዘርና በጎሳ የነደደውን ልባችንን እያረሰረሰ ማርኮ የሰላምና የፍቅር ምርኮኞች የማድረግ እምቅ ኃይል አለው። ለዚህ ደግሞ በአፍሪካ መሪዎች ፊት ፍቅርን ሰብከው ሰላምን ያወረዱት የቦብ ማርሌይ የጊታር አውታሮች ምስክር ናቸው። የሙዚቃን ታላቅነት የመረዳት ልብ ያለው የጦር መሳሪያውን እየጣለ የሙዚቃ መሳሪያውን ድምጽ ተከትሎ ወደ ሰላሙ ደጅ ያመራል።
በእለቱ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አዘጋጆቹ ብቻ መግለጫውን ሰጥተው “በሉ ደህና ሰንብቱ” አላሉም። ከፊት ለፊታቸው ካሜራውን ደግኖ የተኮለኮለው ጋዜጠኛም በተራው ጥያቄዎቹን በሉ መልሱልን ሲል አቅርቧል። ከቀረቡት ጥያቄዎች አንዱ “አሁን አሁን ከወደ ሀገራችን የምናደምጣቸው ከባህልና ከወግ የራቁ አንዳንድ መጥፎ ጭምጭምታዎች አሉና እናንተስ ኮንሰርቱ ከዚህ የጸዳ እንዲሆን ምን እየሰራችሁ ነው?” የሚል ነበር። አዘጋጆቹም እንዲህ በማለት መልሰውታል፤ “እንደዚያ አይነት አስቀያሚ ነገሮች በጭራሽ እንዲስተዋል አንፈልግም።
በኮንሰርቱ መድረክ ላይ ብቻም ሳይሆን ፈጽሞ ወደ ሀገራችን እንዲገባ አንፈልግም። በተቻለን አቅም ሁሉ ኢትዮጵያዊ የጨዋነት መንፈስን ለማስፈን እንሰራለን” ብለዋል። ሌላኛው ጥያቄም ተከተለ፤ “አዲስ ዓመት ሲመጣ አንጋፋዎቹ የሀገራችን አርቲስቶች ሙዚቃዎቻቸው ከነድምጻቸው በጆሮዋችን ላይ ያቃጭላል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ደግሞ ይህን ይናፍቃልና እነርሱን በመድረኩ ላይ ስለመጋበዝስ አላሰባችሁም?” ለሚለውም “እነርሱን በዚህ መድረክ ማየት የኛም ምኞት ነው። ነገር ግን ጉዳዩ በሂደት ላይ ነውና እድሜና ጤና ሰጥቶን በጊዜው የምናየው ይሆናል” ሲሉ ምናልባት ይገኙም ይሆናል በማለት በመንታ ሃሳብ አስቀምጠውታል።
በየዓመቱ የአዲስ ዓመት ዋዜማ በሚዘጋጀው በዚህ ኮንሰርት ላይ አያሌ የዓለማችን እውቅ አርቲስቶች የኢትዮጵያን አፈር ረግጠው ከገጸ በረከቷ ተቋድሰዋል። መቼም ታዲያ ከቦሌ አየር ማረፊያ ደርሶ በዚያው የሚመለስ የውጭ ሀገር ዜጋ የለምና ከመድረኩ በስተጀርባ ይህቺን ብዙ የሚወራላትን የሀገራችንን ጓዳ ጎድጓዳውን ሳያስሱ አይሄዱም። አብዛኛውን ቆይታቸውን ለማለት በሚቻል መልኩ የሚያሳልፉት ታሪካዊና አስደናቂ በሆኑ ስፍራዎቿ ጉብኝት በማድረግ ነው። ይህ ታዲያ በቀጥታ ለቱሪዝም ዘርፉ የሚሰጠው ፋይዳ ቀላል አይደለም። ሙዚቃ በሁሉም ዘርፍ፤ ለሁሉም እንደ ጨው ማጣፈጫ ነው። መልከ ብዙና ዘርፈ ብዙ በሆነው ወዘናው ያለው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። የዚህ ኮንሰርት ዋነኛ ዓላማም የሙዚቃ አፍቃሪያንን ማዝናናት ብቻም አይደለም፤ ይልቅስ በዚህ የሙዚቃ ድግስ የዓለምን አይኖች ወደ ሀገራችን በማዞር የኢትዮጵያን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ከፍ ማድረግም ጭምር ነው።
አርቲስቶቹ በየዓመቱ ወደ ሀገራችን ብቅ ማለታቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለመደ መጥቷል። ለዚህ ምክንያት የሆነው ደግሞ ይሄው ኮንሰርት ነው። ዝግጅቱ የብዙዎችን ቀልብ እየሳበም የናፍቆት እሳትን በልብ የሚያጭር እየሆነ መጥቷል። በተለያዩ ጊዜያት በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሉ የተባሉ ስመ ጥር አርቲስቶችን በመጋበዝ የኢትዮጵያን ገጽታ በዓለም ደረጃ ከፍ አድርጎታል። የነበራትን የሙዚቃ ኢንዱስትሪም መልኩን ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ አሳድጎታል። ወደ ሀገራችን የሚመጡት ተጋባዥ ሙዚቀኞች ብቻ ሳይሆኑ አድናቂዎቻቸውም ጭምር ነውና እነርሱን የሚከተሉ አይኖች ሁሉ ትኩረታቸውን ወደ ሀገራችን ማድረጋቸው አይቀርም።
ሀገራችንን በማስተዋወቅ ረገድም ይህ ነው የማይባል ትልቅ ሚና ይጫወታል። ታላላቅ የሙዚቃ ፈርጦች ወደዚህ መድረክ የተጋበዙ ስለመሆኑ አውስተናል። ከእነዚህም መሃከል አንደኛዋ ቢዮንሴ እንደነበረች የቅርብ ዓመታት ትውስታችን ነው። በዘንድሮው የአዲስ ዓመት የጥሪ ካርዱ ደርሶት ከመድረኩ ባሻገር ያለችውን ኢትዮጵያና ሕዝቦችዋን ለመገናኘት በናፍቆት የሚጠባበቀው ደግሞ ታዋቂው የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ናይጄሪያዊው ሬማ ሆኗል።
የሚመጣው ሬማ ማን ነው? የ23 ዓመቱ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ሬማ (ዲቫን ኢክቡር) በ16 ዓመቱ ከዝነኞቹ የናይጄሪያ ሙዚቀኞች ተርታ መሰለፍ የቻለ ሲሆን ከሀገሩ አልፎም በርካታ ዓለም ዓቀፍ ሽልማቶችን ለማግኘት ችሏል። ሬማ ወደ ዓለም ዓቀፉ መድረክ ለመቀላቀል የቻለው በፈረንጆቹ 2019 ቢሆንም ስሙ ገኖ ለመውጣት የቻለው ግን በ2022 ዓ.ም ‘Calm Down’ የተሰኘውን ነጠላ ዜማ ከለቀቀ በኋላ ነበር። በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች እየዞረ ስራዎቹን በማቅረብም በብዙ መድረኮች ላይ አድናቆትን እየተቸረው ዓለም አቀፍ አድናቂዎቹን ለማፍራት ችሏል። አሁን ደግሞ በተራ መዳረሻውን ከኢትዮጵያ የሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ አድርጓል።
በዋዜማው ምሽት ሬማ ብቻውን አይደለም። በዚሁ መድረክ ላይ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ኢትዮጵያውያን የሙዚቃ ፈርጦችም ተካተውበታል። የኢትዮጵያ ሂፓፕ ሙዚቃ ንጉስ የሆነው ልጅ ሚካኤል ሌላኛው የምሽቱ ድምቀት ሆኖ ያመሻል። የልጅ ሚካኤል ሙዚቃዎች የሂፓፕ ስልት ያላቸው ይሁኑ እንጂ ሙዚቃዎቹ ኢትዮጵያዊ ለዛ እንዲኖራቸው በማድረጉ የሚታማ አይደለም። የሙዚቃ ግጥሞቹም ቢሆኑ ኢትዮጵያዊ ለመምሰል ጉልበታቸው አይዝልም። በተለይ ደግሞ ከሁለት ዓመታት በፊት የሰራው የአልበም ስራ ይህንኑ አጉልተው ያሳያሉ። በዚህ መድረክ ላይ ደግሞ የዘመናዊ ሙዚቃዎቻችንን ልክ ለማሳየት ሚናው የጎላ ነው።
ከእነዚህ ፈርጦች በስተጀርባ ደግሞ ሁለት ክዋክብት ይገኙበታል። ባለፉት ዓመታት የብዙ ሙዚቃ አፍቃሪያን የልብ ምት የሆነችው ተወዳጅዋ ድምጻዊት ብሩክታዊት ጌታሁን “ቤቲ ጂ” የመድረኩን እሳት ታቀጣጥለዋለች። እንዲሁም ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ አድናቆትን እያተረፉ እየመጡ ካሉ አዳዲስ ድምጻውያን መሃከል ብቅ ያለው አዲሱ ለገሰ ከዝነኞቹ አብሮ በመድረኩ ያቀነቅናል። በምሽቱ መድረኩን የሚዘውረው ‘ዲጄ’ም ማን እንደሆን ባይገለጽም እሱም ባህር ተሻግሮ የሚመጣ መሆኑ ታውቋል።
መቼም ከአንድ ሬስቶራንት ገብተው ከበሉና ከጠጡ በኋላ እጅን በሳሙና ታጥበው እግዜር ይስጥልኝ ብሎ መሄድ የለምና “የመግቢያው ዋጋስ እንዴት ነው?” በማለት ከጋዜጠኞች ለቀረበው ጥያቄ ምላሹ በኑሮው ውድነት ለደቀቀው ብዙሃኑ ቆንጠጥ የሚያደርግ ነው። እናም እንደተባለው ከሆነ ከ15 እስከ 20ሺህ የኢትዮጵያ ብር ይሆናል ማለት ነው። የኮንሰርቱ አላማና ዝግጅቱ መልካም ሆኖ ሳለ የመግቢያ ዋጋው ለአብዛኛው የሙዚቃ አፍቃሪ እንደ ገነት በር የጠበበ መሆኑ ግን ትንሽ ቅር የሚያሰኝ ነው። ሰላም የሚል ስያሜ ይዞ ለሰላም ዓላማ እስከመጣ ድረስ ሰላም ናፋቂውን ማህበረሰብ በሚያካትት መልኩ ቢሆን መልካም ነበር የምትል ምክር አዘል ሃሳብ ቢጤ ጣል ለማድረግ እንወዳለን።
እንግዲህ ኮንሰርቱን ለመቀላቀል እየፈለግን “እስኪ ኪሳችን ትገባ እንደሆን አይሃለሁ” እያለ ለሚዝትብን ከኮንሰርቱ በረከት ይድረሰን። ከምንም በላይ ሀገር ሰላም ውላ ሰላም ትግባ። ጥላቻና ጦርነት የሰላም እጦት በ2015 አጋሰስ ላይ ጭነን ወደ’ማይመለስበት በረሃ ለመሸኘት ያብቃን። ስደት ለምጥፎ ትዝታዎቻችን እንጂ ለዜጎች አይሁን። ጥበብ ብዙ ትውልድ እንደ ሰማይ ክዋክብት፣ እንደ ምድርም አሸዋ፤ ሀገራችንንም በሰላም ዘር ልባችንንም በፍቅር አውታር ትቀኘው እንደ ሙዚቃው። የ2016 የሰላምን የዘንባባ ዝንጣፊ እያውለበለብን እንቀበል ዘንድ መልዕክታችን ይሁን ብለን አበቃን።
መልካም አዲስ ዓመት !!!
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 4/2015