ወፈፌው ይልቃል አዲሴ፣ ዛሬም በለሊት ተነስቶ በሰፈራችን ከሚገኘው ዋርካ ስር ቆሞ ይጮሃል:: የዛሬው ጩኸት በውዝዋዜ የታጀበ በመሆኑ ግራ የገባቸው የሰፈራችን ሰዎች ከመቅጽበት ወደዋርካው ተሰብስበው በዋርካው ስር ባሉ ድንጋዮች ላይ ተኮለኮሉ:: የሰፈራችን ሰዎች በመሰብሰብ ላይ እያሉ ይልቃል አዲሴም “ሃይማኖት እንተ አልባቲ ምግባረ ሠናይ፤ ምውት እይቲ” በጎ ስራ ያልተሰራባት ሃይማኖት የሞተች ናት:: ወይም ጾለት ያለ ፍቅር ሃይማኖት ያለ ግብር አይረባም:: ” እያለ ይጮህ ነበር::
የሰፈራችን ሰዎች ወደ ዋርካው ተሰባስበው ቦታቸውን መያዛቸውን ከተመለከተ በኋላ ይልቃል አዲሴ፣ ራሱን ለንግግር እያዘጋጀ ‹እህ..እህ…› ብሎ ጉሮሮውን ጠራረገ። ንግግሩንም እንዲህ ሲል ጀመረ፤ “ እመ ብከ ጥበብ ጸሐፍ፤ ወልደ ሕይወት እንፍራንዛዊ ወይም መነገድ ለማትረፍ፤ መማር ለመጻፍ መሆኑን አውቃለሁ:: በእኛ ሰፈር ያለው ንግድ ግን ለማትረፍ ሳይሆን መዝረፍን ያማከለ ይመስለኛል:: ”
ወፈፌው ይልቃል ንግግሩን ቀጥሎም፤ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰፈራችን እና በእድራችን እየተስተዋለ ያለው የኑሮ ውድነት እጅጉን ፈታኝ እየሆነ የመጣ ይመስላል:: ምናልባትም ከዚህ ቀደም ባሉት ጊዜያት ከተስተዋሉ የኑሮ ውድነቶች ጋር ሲነጻጸር የአሁኑ ትንሽ የከፋ ይመስላል::
ከዚህ ቀደም የኑሮ መወደድ ጋር በተየያዘ ያለ አግባብ ትርፍ ለማጋበስ የፈለጉ ነጋዴዎች ከምግብ ጋር ባዕድ ነገሮችን ቀላቅለው ሲሸጡ ስለመታየታቸው በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሲነገር ስንሰማ በአግራሞት ጉንጫችን ይዘን ነበር:: ምግብ ቤት ገብተን እንጀራው ጤናማ ነው? እያልን ሁሉ እንጠይቅ ነበር::
አሁን ላይ ግን እንጀራው ጄሶ ይኑረው፤ ሳጋቱራ መጨነቁን ትተነዋል:: ብቻ እንጀራ ሆኖ ይምጣ እንጂ ሌላው ነገር ግድ ሲሰጠን አይስተዋልም:: ይህን ስመለከት በአንድ ጊዜ የሌላ አገር ተወላጅ የሆንኩ ያህል ይሰማኛል ወደፊት እነ አሞራ እና እነ እህያ ጉድ ሊሆኑ ይችላሉ ስል ለራሴ እነግረዋለሁ::
የሰፈራችን ሰዎች እና የዕድራችን አባላት የኑሮ ውድነቱን መሸከም ከሚችሉት በላይ ሆኖ ሳለ የእኛ “ገራዳዎች” ግን የሚያስጨንቃቸው የሰፈራችን ሰዎች እና የዕድራችን አባላት ጎሳ እና ማንነት ሆኖ ስመለከት ውስጤ ሲጤስ ይሰማኛል::
ጢሶ አንጀቴ ቢሸተው ጉበቴ፤
ስጋ ጠብሷል ብሎ አማኝ ጎረቤቴ::
የሚለው የጋሽ ባህሩ ቃኜ ፉከራ እና ሽለላ እውነት መሆኑን ያረጋግጥልኛል::
በሰፈራችን ጎሳን የመረጠ የኑሮ ውድነት የተከሰተ ይመስል ነጋም ጠባም ሥራችን ከጎሳ ጋር፤ ምን አይነት ልክፍት ነው? በነገራችን ላይ ከበፊት ጀምሮ ነጋዴዎች ኑሮ ውድነቱ የሚሰጡት ምክንያት ተመሳሳይ እና እጅጉ የሚያናድድ ነው:: ሁሌም ነዳጅ እና ዶላር ጨምሯል::
ነጋዴዎች ለኑሮ ውድነቱ የነዳጅ መጨመርን እና የዶላር መጥፋትን እንደምክንያት ሲያነሱ ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ያደረጉ እና በድህነት የሚፈተኑ እናትን የተመለከተ የተስፋዬ ካሳን ቀልድ ያስታውሰኛል::
ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ የሆኑት እና በድህነት የሚፈተኑ እናት የኑሮ ውድነቱ እሳት ሆኖ አላስኖር፤ አላስቀምጥ ብሏቸው እየተጨነቁ እያለ በእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ እንዲሉ ከክፍለ አገር እንግዳ ይመጣባቸዋል:: ያውም የመጣው ጥቁር እንግዳ ነው::
ለጥቁሩ እንግዳ ስጋ እንዳይገዙለት ብር የላቸውም:: እንዲሁ ሽሮ አያቀርቡለት ጥቁር እንግዳ ነው:: በዚህ የተጨነቁት እናት ስጋ ማቅረብ ባልችል እንኳን እንቁላል ሰርቼ ላቅርብ ይሉና ሰፈራቸው ወደምትገኝ ትንሽዬ ሱቅ ያመራሉ:: “ባለሱቁንም እንቁላል አለ?” ሲሉ ይጠይቁታል:: ባለሱቅም አንገቱን ላይ እና ታች እያወዛወዘ እንቁላል መኖሩን ይንገራቸዋል:: “ስንት ነው ?” ሲሉም ይጠይቁታል:: ባለሱቁም እጅጉን የተጋነነ ዋጋ ይነግራቸዋል:: “እንቁላል ደግሞ ይሄን ያህል መወደዱ ምነው?” ሲሉ ባለ ሱቁን ይጠይቁታል:: ባለሱቅም ፣ “እማማ ነዳጅ ስለጨመረ ነው” ሲል ይመልሳል:: በነጋዴው መልስ የተበሳጩት እናትም “እኔ እምለው እንቁላሉን የሚጥለው ሞቢል እና ቶታል ነው ?” ሲሉ ጠየቁት ይባላል::
የኑሮ ውድነቱ ከሸቀጣ ሸቀጦች እና ለምግብነት ከሚውሉ ፍጆታዎች አልፎ በአገልግሎቶች ላይም እየተስተዋለ ነው:: ይሄው በትምህርት ቤቶችም ደርሶ ወላጆች እና ትምህርት ቤቶች ወታደር እና አውዳሚ ከባድ መሳሪያ የሌለው ጦርነት ውስጥ ገብተዋል:: ጉዳዩም የአደባባይ አጀንዳ ከሆነም ውሎ አድሯል::
ትምህርት ቤቶች እንደ ሸቀጥ ነጋዴዎች ሁሉ ለክፍያ መጨመራቸው የሚያነሱት ምክንያት ከበፊት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ተመሳሳይ ነው:: የመምህራን ደምወዝ እና የህንጻ ኪራይ ጉዳይን ነው:: ከትምህርት ቤት ክፍያ ጋር ተያይዞ ወላጆች እና ትምህርት ቤቶች ተደራደሩ እና ተስማሙ የሚባለው ነገር ተገቢ አይደለም:: እዚህ ላይ ቁርጥ ያለ አስተዳደራዊ ውሳኔ ያስፈልጋል:: ተደራደሩ መባል ያለበት ለሸቀጥ ሽያጭ ነው! ያውም ላልተጋነነ የሸቀጥ ዋጋ ነው::
መንግስት ግብር ኃይል አቋቁሞ ያስተጋባው፤ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች እና የቤት አከራዮች ላይ የእርምት እርምጃ እየወሰደ ባለበት ሰፈር እና እድር ስለምን ትምህርት እንደ ሸቀጥ እንዲሆን ተደራደሩ ይባላል? ትክክል አይደለም:: … ” ብሎ ይልቃል አዲሴ እየተናገረ እያለ፤ ሁሌም ሳይፈቀድለት የሚናገረው አብሿሙ ክንፈ ጉደታ እንደተለመደው ዛሬም የይልቃልን ንግግር አቋረጠው::
አብሿሙ ክንፈ ጉደታ፣ የይልቃልን ንግግር ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፈው ገልጾ፤ ንግግሩን እንዲህ ቀጠለ… “ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ለትምህርት ቤት ዋጋ ጭማሪ በዋናነት እየተነሳ ያለው ምክንያት ለመምህራን ደሞዝ እና ለህንጻ ኪራይ የሚል ነው:: እውነት የተጨመረው ክፍያ ለመምህራን ደምወዝ ይውላል ወይ? የሚለውን አጽዕኖት ሰጥቶ መመልከት ይገባል::
ለእኔ ግን ነገሩ ..በልጅ አመካኝቶ
ይበላሉ አንጉቶ ነው::
በወላጆች ላይ የሚጨመረው ክፍያ በአካፋ ለመምህራን የሚሰጠው ክፍያ ደግሞ በማንኪያ መሆኑን ሁሉም ሰው የሚያውቀው ነው::
ከዚህ በፊት በጉሊት ገበያ ሽንኩርት እና ድንች፤ በሱቅ በደረቴ የተለያዩ ሸቀጦችን ሽጠው ልጆቻቸውን በግል ትምህትር ቤት ያስተማሩ ሰዎች በርካታ ነበሩ:: አሁን ላይ ግን የኑሮ ውድነቱ አልቀመስ በማለቱ ወላጆች ሁሉም ነገር ከቁጥጥራቸው ውጭ እየወጣ ስለመጣ እንኳንስ የግል ትምህርት ቤት ከፍሎ ማስተማር ይቅርና የልጆቻቸውን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት የተቸገሩ መሆናቸውን እያየን ነው::
ፈላስፎች እንዲህ ይላሉ… “ሰዎችን በምክር የሚገስጹ ሽማግሌዎች ራሳቸው ሲቆጡ እና ሲበሳጩ እብዶች ናቸው:: አስታራቂም ሆነ ሽማግሌ መቆጣት እና መበሳጨት አይገባውም:: ” በሸቀጦች ላይ ያለአግባብ ዋጋ የሚጨምር ነጋዴ የትምህርት ቤት ዋጋ ተወደደብኝ ብሎ እሮሮ ሊያሰማ አይገባውም፤ የትምህርት ቤት ክፍያ ያለአግባብ የሚጨምር ትምህርት ቤትም የጽህፈት መሳሪያ ተወደደ ብሎ ሊያማርር አይገባውም:: እኛ ላይ ሲሆን የምንጨረጨረው ለምንድን ነው?
ይህን ስል በሰፈራችን የሚገኙ የአንድ ታዋቂ ሃይማኖት አባት አድራጎት አስታወሰኝ ብሎ ንግግሩን ቀጠለ … እኝህ የሃይማኖት አባት ሁሌም በእርሳቸው ስር ያሉ ምዕመናን ቤተሰቦች ሲሞቱ “ተው እንዳታለቅሱ:: ፈጣሪ እሱ ፈጠረ እሱ ወሰደ:: በሱ ስራ መግባት ትክክል አይደለም:: መጽሐፉም ቢሆን ፈጣሪ ባመጣው ሞት ማልቀስን አጥብቆ ይከለክላል” እያሉ ብዙ ሰዎችን ይቆጡ እና ይገስጹ ነበር::
ከሁሉም በላይ የማልረሳው በሰፈራችን መከራ አይለፍሽ ተብሎ የተፈረደባት የምትመስለውን ወይዘሮ አማረችን ያጽናኑበትን መንገድ ነው:: ወይዘሮ አማረች መጀመሪያ እናት እና አባቷ ይሞታሉ:: ቀጥሎም ባለቤቷ፣ ልጆቿ እና ዘመዶቿ ያልቃሉ:: ይህን ተከትሎ መከራ በመከራ የተደራረበባት ወይዘሮ አማረች ለቀናት እርር ኩርምት ብላ ማልቀሷን ተያያዘችው:: ይህን የተመለከቱት የነፍስ አባትም፤ “አንች ሰው ምን ብየሽ ነበር ? ፈጣሪ ፈጠረ ወሰደ ! በእርሱ ስልጣን እና ኃይል አንች ስለምን ትገቢያለሽ? መጽሐፉም ቢሆን እንዲዚህ እንድታዝኚ አይፍቅድም:: ከአሁን በኋላ ስታለቅሺ እንዳላይሽ! ገዝቼሻለሁ” ይሏታል::
ወይዘሮ አማረችም የነፍስ አባቷን ምክር እና ተግሳጽ ሰምታ ለቅሶዋን እርግፍ አድርጋ ትታ ፈጣሪዋን “አንተ ፈጠረክ አንተ ወሰድክ:: በአንተ ስራ ገብቼ አለቀስኩ፤ አንተንም አስቀየምኩ፤ እባክህ የሞቱትን ነፍሳቸውን በገነት አኑር” እያለች ትጸልይ ገባች::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከእለታት በአንድ ቀን የነፍስ አባት ብቸኛው እና ያለእናት ያሳደጉት ልጃቸው በድንገት ይሞታል:: በዚህ እርር ድብን ያሉት የነፍስ አባት አገር ይያዝልኝ አሉ፤ ጩኸታቸውን አቀለጡት፤ ከመጠን በላይም አለቀሱ:: በዚህ ወቅት ሙሉ ቤተሰቧን በሞት ያጣችውና በነፍስ አባት ተይ አታልቅሺ ! ፈጣሪ ራሱ ፈጠረ ራሱ ወሰደ፤ መጽሐፉም ቢሆን ይህን ያህል ማዘንን እና መተከዝን እንደማይፈቅድ የተነገራት ወይዘሮ አማረች የነፍስ አባቷን ለማጽናናት በማሰብ “አባቴ አያልቅሱ፤ ፈጣሪ ራሱ ፈጠረ ራሱ ወሰደ፤ ይህን ያህል ማልቀስና መተከዝንም መጽሐፉ አይወደውም!” ስትል የነፍስ አባት ምን ቢሉ ጥሩ ነው … “እኔ ስለመፅሐፉ አያገባኝም! የእኔን ጉዳት የማውቀው እኔ ነኝ” ሲሊ መለሱ ይባላል::
አዋቂ ሰው በዕውቀት ከሚበልጠው ሰው ቢማር እና ቢጠይቅ ነውር የለበትም:: አንድ አሮጌ ሽማግሌ ሰው አንዱን ፈላስፋ እኔ ያረጀሁ ሽማግሌ ስሆን በዚህ ዕድሜዬ መማር ይገባኛል ቢለው አዎ በድንቁርና ከመኖር እስከሞት ድረስ እውቀትን በመሻት ብዙ መኖር ይሻላል አለው:: በእኛ ሰፈርም ያሉ ነጋዴዎች ንግድ ከጀመሩ በርካታ ጊዜያትን አስቆጥሯል:: የግል ትምህርት ቤቶችም ለዜጎች የእውቀት እሸትን ማብላት ከጀመሩ እንዲሁ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል::
ነገር ግን ንግድ ማለት እንዲሁ ትርፍ ማጋበስን ብቻ የሚመስላቸው በርካታ ናቸው:: ይህ ትክክል አይደለም:: ንግድ ምንድንው ? እንዴትስ ይከናወናል? ማንንስ መሰረት ያደረገ ነው ? ወዘተ የሚለውን ከውጪ ዓለም ቢማሩ መልካም ነው:: የግል ትምህርት ቤቶች የመቋቋማቸውን ዓላማ በቅጡ የተረዱት አይመስለኝም:: ስለሆነም ለትፍር ከመራኮት ባለፈ በውጩ ዓለም የግል ትምህርት ቤቶች የተቋቋሙለትን ዓላማ እንዴት እንደሚተገብሩ ትምህርት ውሰዱ:: ከዚያ ዜጎቻችሁን ለማስተማር ተዘጋጁ:: ምክንያቱም ፈላስፎች እንዳሉት ሌላውን የማያስተምር ለራሱ አይማርም::
በእኛ ሰፈር እና እድር በስግብግብ ነጋዴዎች የሚደረገውን እንዲሁ ሀብትን የማጋበስ ልክፍት እና ኢሰብዓዊ ድርጊት ስመለከት በውጩ ዓለም የተደረገን አንድን ሁነት ተሞክሮ ለነጋዴዎቻችን ማስተማር እንዳለብኝ ይሰማኛል::
በውጭ አገር የምትኖር አንድ ድሃ ሴት ነበረች:: ከእለታት በአንድ ቀን በዚህች ሰው ቤት እሳት ተነሳ:: የድረሱልኝ ጩኸት አሰማች:: ከመቅጽበት የሰፈር ሰዎች ተሰብስበው እሳቱን ለማጥፍት ተሯሯጡ:: ነገር ግን እሳቱ ከአቅማቸው በላይ ሆኖ ቤቱ እና በቤቱ ውስጥ የነበረ ንብረት በሙሉ አንድም ሳይተርፉ ወደሙ::
የሰፈር ሰዎች የሴትየዋን ቤት እና ንብረት ባለማትረፋቸው እጅጉን አዘኑ:: የተቃጠለውን ቤት ለመስራት እና ሴትየዋንም ወደነበረችበት ህይወት ለመመለስ በማሰብ የሰፈር ሰዎች ወዲያውኑ ብር ያለው ብር፤ ብር የሌለው ብር ሊያወጡ የሚችሉ ጌጣጌጦችን አሰባሰቡና ለሴትየዋ ሰጧት::
ሴትየዋም በተሰጣት ገንዘብ ተጠቅማ በአጭር ቀናት ውስጥ ቤቷን ወደነበረበት መለሰችው:: የተወሰነ ገንዘብም ተረፋት:: ነገር ግን የቤቱ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ የተረፋትን ገንዘብ ለራሷ ጥቅም ከማዋል ይልቅ ለእርዳታ ድርጅት አበረከተች:: ይህ የሴትየዋ ድርጊት የአገሩ ባህል መሆኑን ተረዳሁ:: ምነው እንዲህ አይነት መተዛዘን በእኛ ሰፈር ነጋዴዎች ልቦና ቢጋባ ስል ተመኘሁ:: ”
አብሿሙ ከንፈ ጉደታ ንግግሩን ሲያጠቃልል “ጎበዝ በሰፈራችን እና በእድራችን የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ ይህ ተሰብሳቢ መፍትሔ ማበጀት ይገባዋል” ብሎ ወደ መቀመጫው ተመለሰ::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከስንዴ መሀል እንክርዳድ እንዲሉ በሰፈራችን የሚኖር አንድ ግብዝ ሰው ተነስቶ “የኑሮ ውድነቱን ያለምንም ስጋት በዘላቂነት ለማለፍ በማሰብ ጠንክሬ እየሰራሁ ነው:: ምናልባትም ጥሩ ተሞክሮ ስለሆነ ከእኔ እንድትማሩ በማሰብ የእኔን ተሞክሮ ልንገራችሁ” ብሎ ንግግሩን ቀጠለ….
“ትምርትን ለመማር ሰው ካሰበ በእውነት፤
እድሜው ቢገፋ ቢሆነው ሀምሳ ዓመት ፤
የእኔ ሽመግልና አይሆንም እንቅፋት:: ”
ብለን እኔ እና ሚስቴ ትምህርት ከሰባት ልጆቻችን ጋር ቤት ገብተናል::
ይህን ተከትሎ የግብዙ ሰው ሃሳብ ያልገባው መድረኩን የሚመራው ይልቃል አዲሴ ነገሩን እንዲያብራራለት ግብዙን ሰው ጠየቀው:: ግብዙ ሰውየም እኔ እና ሚስቴ የኑሮ ውድነቱ የሚያስከትለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት፤ ለማወቅ ሳይሆን ለመብላት በማቀድ ከሰባት ልጆቻችን ጋር የመንግስት ትምህርት ቤት ገብተናል::
እንደሚታወቀው በመንስግት ትምህርት ቤት ምግብ እና ልብስ የሚሰጠው በነጻ ነው:: በመሆኑም በመንግስት ትምህርት ቤት በነጻ መመገብ እና መልበስ ሳለ ስለምን ለምግብና ለልብስ ወጭ እናስባለን?” በሚል ትምህርት ቤት ገብተናል ሲል ለስብሰባ ታዳሚው ተናገረ::
ንግግሩን ቀጥሎም ….:: “ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እኔ ሚስቴ እንዲሁም ልጆቼ የትምህርት ቤት ህጎችን ከማክበር ውጭ ሁሌም ተገኝተን የምንሰራው ከክፍል ከፍል ላለማለፍ ነው:: በዚህም እኔም ሚስቴም አንደኛ ክፍልን ለመጨረስ በትንሹ አራት ጊዜ መደጋገም እንዳለብን ስትራቴጂ ነድፈን እየሰራን ነው:: ልጆቼም ይህንኑ መመሪያ ተቀብለው በተገቢው መንገድ ትንሽም ሳያዛንፉ እየፈጸሙት ይገኛሉ” ሲል ተሰብሳቢውም በተቃውሞ በጩኸት ንግግሩን አቋረጠው::
ይህን ተከትሎ ለስብሰባው ማጠቃለያ ለመስጠት ይልቃል አዲሴ ከመቀመጫው ተነሳ:: በመጨረሻም ሲል ንግግሩን ጀመረ:: “ተበአለ በእንተ ጽድቅ እስከ ለሞት ..ለእውነት እስከሞት ድረስ ተጋደል…እውነት እውነቱን ተናግሬ እሞታለሁ! እውነቱንም እነግራችኋላሁ! ……ንግግሩንም ቀጠለ ሐንካስ በእግረ ዕውር ሖረ፤ ዕውርኒ በዐይነ ሐነካስ ነጸረ (አንካሰው በእውሩ እግር ሄደ እውሩ በአንካሳው አይን አየ:: ) እባካችሁ ነጋዴዎች ከሸማቹ ህዝብ ጋር ብትተባባሩ ይሻላችኋል:: ሸማቹ ህዝብ ሞቶ አናንተ የምትተረፉ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል” ብሎ ንግግሩን ሲጨርስ የሰፈራችን ሰዎችም ለይልቃል ያላቸውን አድናቆት በጭብጨባ ገልጸው ስብሰባው ተበተነ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2015