በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች ስማቸውን እያወቅን አመሠራረታቸውን እና ታሪካቸውን በቅጡ የማናውቃቸው ብዙ አምራች እና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች አሉ:: ከእነዚህ ድርጅቶች አንዱ ሸዋ ዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካው ነው:: በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ቢጓዙ፣ የሸዋ ዳቦን ማከፋፈያ አያጡም:: አባ ኮራን፣ ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ፣ ቃሊቲ፣ ወይራ ሰፈር፣ አየር ጤና፣ ቦሌ፣ ገርጂ፣ ጀሞ፣ ቄራ የሸዋ ዳቦ ማከፋፈያ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች መካከል ዋነኞዎቹ ናቸው::
ሸዋ ዳቦ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፣ ከ64 ዓመት በፊት በ1951 ዓ.ም የተቋቋመ ነው:: በተለምዶ አባኮራን በመባል በሚጠራው ሰፈር፣ የመጀመሪያውን ዳቦ ቤት በመክፈት ሥራ የጀመሩት አቶ ዘሙይ ተክሉ፤ ባለሁለት አሃዝ ቁጥር ያለውን ቅርንጫፍ ለመክፈት የበቁት ጥራት እና ተመጣጣኝ ዋጋን ማዕከል አድርገው በማገልገላቸው ነበር:: አዲስ ዘመን በዛሬው የባለውለታ አምዱ እኚህን የዳቦ አባት በአገልግሎት ዘርፉ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እንደሚከተለው ሊዘክራቸው ወዷልና መልካም ንባብ ይሁንልዎ::
የሸዋ ዳቦ አመሠራረት ሲነሳ፤ በአዲስ አበባ በተለምዶ ጎጃም በረንዳ እየተባለ ከሚጠራው ሰፈር ዝቅ ብሎ፣ አባ ኮራን እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ካለው ቤንዚን ማደያ አጠገብ፣ የአንድ ኢጣሊያዊ ትንሽ ዳቦ ቤት ነበረች:: አቶ ዘሙይ ከአሥመራ እንደመጡ፣ እዚያች ዳቦ ቤት በኃላፊነት ተቀጥረው ይሠሩ ነበር:: ጣሊያኑ አርጅቶ መሥራት ሲያቅተው፣ አቶ ዘሙይ ያቺን ዳቦ ቤት ከጣሊያኑ ገዝተው ማምረት ጀመሩ::
በወቅቱ የገዙት ከ5 ሺህ ብር ጥቂት ከፍ ባለ ትንሽ ካፒታል ነበር:: እርሳቸው ሥራ በጀመሩበት ጊዜ፣ ዳቦ ቤቷን ከገዙበት ሌላ ተጨማሪ ገንዘብ አልነበራቸውም:: ሥራ ማካሄጃ ከዘመድ እና ከወዳጅ በብድር ተገኘ:: ሥራ ለመጀመር፣ ለዱቄት መግዣ የሚሆን ገንዘብ ስለቸገራቸው፣ አቶ ሰይድ አህመድ የተባሉ ወዳጃቸው አበደሯቸው:: ከዚያም ያለ ዕረፍት ለሊት እና ቀን ጥርሳቸውን ነክሰው በመሥራት ዕዳቸውን ከፈሏቸው::
አቶ ዘሙይ እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ውቧ ሀብተየስ፣ ከወዳጅና ከዘመድ የወሰዱትን ገንዘብ ከከፈሉ በኋላ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ጠንክረው ሥራቸውን ቀጠሉ:: አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት ማስፋፋት የጀመሩት ፒያሳ ከማዘጋጃ ቤት የኋለኛ በር በታች አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት አካባቢ ነበር:: ትጋታቸው በዚህ አላቆመም ከ2ኛው የሸዋ ዳቦ ቅርንጫፍ ቀጥለው አምስት ኪሎ ከቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት 3ኛውን ቅርንጫፍ ደገሙ::
በደጃዝማች በላይ መንገድ አካባቢ 4ኛውን ደገሙ:: እንደዚያ እያደረጉ የቅርንጫፎቻቸውን ቁጥር 7 አደረሱ:: አቶ ዘሙይ ሸዋ ዳቦን አሳድገው በርካታ ቅርንጫፎች ከመክፈታቸው ጎን ለጎን፣ ከ20 በማይበልጡ ሰራተኞች ሥራ የጀመረው ሸዋ ዳቦ የሠራተኛውን ቁጥርም እየጨመረ ቀጠለ::
ሸዋ ዳቦ በተጀመረበት በንጉሡ ዘመን በርካታ ሌሎች ዳቦ ቤቶች ተከፍተው በሥራ ላይ የነበሩ ቢሆንም ሸዋ ዳቦ በውድድር እያሸነፈ ገበያውን ሲመራ ሌሎች ግን ከገበያው ወጡ:: አቶ ዘሙይ ጥረታቸውን በመቀጠል ጠንክረው እየሠሩ ሀብት፣ የሠራተኞች ቁጥር እና የቅርንጫፎች ብዛትም በሚያስገርም መልኩ እየጨመረ ሄደ::
ከዚያም ደርግ ሥልጣን ሲይዝ በአዋጅ 47/67 ብዙ ንብረታቸው ተወረሰባቸው:: በዚያን ጊዜ አዳማ ላይ አቋቁመው የነበረው የዱቄት ፋብሪካ፣ በቦሌ መንገድ ከኦሎምፒያ ፊት ለፊት አሁን ጌቱ ኮሜርሻል ሕንፃ ካለበት ፊት ለፊት ያለው ዳቦ ቤት እና ሕንፃው የአቶ ዘሙይ ተክሉ ነበር:: ያ ሁሉ ተወረሰ:: እዚያ ያለው ዳቦ ቤት ሲመለስላቸው ሕንፃው ግን እንደተወረሰ ቀረ:: አባ ኮራን ሠፈር ያለውም ሕንፃ ተወረሰ፣ ይህ ብቻ አይደለም፤ ሌሎች በርካታ ንብረቶችም ተወረሰባቸው::
የኤርትራን አማፅያን ተገንጣይ ኃይሎችን ትደግፈለህ በሚል በደርግ ዘመነ መንግስት ለእስር ተዳርገው ነበር:: በዚህ ዓይነት ብዙ ፈተናዎች ተደቅነውባቸው፤ በተጨማሪ ደግሞ የባንክ ዕዳ ነበረባቸው:: ብዙ ችግር ቢወድቅባቸውም ብርቱ ናቸውና ለፈተና እጅ አልሰጡም:: ተስፋ ቆርጠው መቀመጥን አልመረጡም:: ያ ሁሉ ችግር አልበገራቸውም በዚያ ሁሉ በደል ሞራላቸው ሳይወድቅ እና ሳይጨናነቁ ሥራቸውን ቀጠሉ::
በ2005 ዓ.ም በደራሲ ተክሉ ጥላሁን ተዘጋጅቶ ‹‹ትናንትን_ሳስታውስ›› በሚል ርዕስ ለህትመት በበቃው እና የህይወት ታሪካቸውን በያዘው መፅሐፍ “ቅድመ ታሪክ” ላይ የሸዋ_ዳቦ_ባለቤት_ዘሙይ_ተክሉ ህልማቸውን እንዲህ ስሉ አስቀምጠዋል:: ‹‹ ከአንድ ጋራ ላይ ሆኜ ከአባቴ ቤት ጓሮ ያለውን ሰፊ ቦታ የማይ ይመስለኛል፤…‘ጓሯችን እንደዚህ ሰፊ እና ትልቅ ነው እንዴ?’ ብዬ በግርምት አየሁት:: ዐይኔ እጅግ ብዙ ርቆ ቢመለከትም ማብቂያ ጠርዙን ማየት ተሳነው::
የአባቴ ቤት ጓሮ የቱንም ያህል ሰፊ ቢሆን፣ አሁን እንደማየው ወሰኑ እጅግ የሰፋ አልነበረም:: በግምት ግማሽ ጋሻ መሬት ቢሆን ነው:: ‘ታዲያ ምን እንደዚህ ትልቅ አደረገው?’ ስል አሰብኩ፤ በጣም ያስገረመኝ ነገር ቢኖር ስፋቱ ብቻ አልነበረም- ሙሉ በሙሉ መሬቱ በስጋ የተሸፈነ መሆኑ እንጂ:: አልፎ አልፎ አይኔ ውስጥ ገባ ካለው ቀይ ስጋ በቀር በሙሉ ምራቅ የሚያስውጥ፣ ዓይን የሚያጥበረብር ቅልጥ ያለ ጮማ ነው::
‘እንዴት የአባቴ ጓሮ ጮማ ስጋ ማብቀያ ይሆናል?’ ብዬ ግራ ተጋባሁ:: ይሄ ቅዠት መሆን አለበት እንጂ አንድ የእርሻ ቦታ እንዲህ ሊሆን አይችልም በማለት በጣም ተጠራጠርኩ:: በእግሬ ረግጬ ምንነቱን ማወቅ ፈለግኩ:: እናም ስፈራ ስቸር አንድ እግሬን አንስቼ ቀስ ብዬ ጮማ ስጋው ላይ አሳረፍኩት:: ከአሁን አሁን አንሸራቶኝ እወድቅ ይሆናል በሚል ስጋት ውስጥ ሆኜ ሌላኛውን እግሬን መሬት ላይ አድርጌ በመጠባበቅ አቆየሁት:: ጮማ ስጋውን የረገጠው እግሬ ምንም አልሆነም:: ልክ ትቡምክ የሚል የፋርስ ወለል ንጣፍ ላይ ያረፈ ያህል በምቾት ስምጥ አለ::
ከጋራው አፋፍ መለስ ብዬ ራሴን ካረጋጋሁ በኋላ በድጋሚ እንዳልወድቅ ተጠንቅቄ አንገቴን አስግጌ ለመመልከት ወደ ጫፉ ስጠጋ ባልጠበቅኩት ሁኔታ ጋራው ተንዶ ሰውነቴ እየተምዘገዘገ ወደ ታች ሲወርድ ታወቀኝ:: እናም ከመሬት ስደርስ አይሆኑ አኳኋን እንደምሆን አወቅኩና ደነገጥኩ:: አጥንቴ እንኳን አይገኝም::
‘እናቴ፣ ወንድምና እህቶቼ ተከስክሼ የወደቅኩበትን ስፍራ ካላወቁ ምን ይውጣቸው ይሆን?’ እያልኩ ሰውነቴ ተምዘግዝጎ ከመሬት ሲፈጠፈጥ ነፍሴ ከስጋዬ ትለያለች ብዬ መጠበቅ ጀመርኩ፤ ነገሩ ሁሉ ግን ከግምቴ ውጪ ሆኖ አገኘሁት::
ከመሬት ወድቄ በመከስከስ ፈንታ ልክ እንደ አውሮፕላን በአየር ላይ፣ ያውም በሚያምረው የጮማ ስጋ ላይ እየተንሳፈፍኩ ነበር:: እጆቼን እንደ አውሮፕላን ክንፍ ዘርግቼ አየሩን እየቀዘፍኩ ወደ ጮማ ስጋው ቀረብ ብዬ ሳየው ለካንስ የሚያምር የስንዴ ማሳ ኖሯል:: በዚያ ውብ በሆነው የስንዴ ማሳ ላይ ስፍፍ… አልኩበት::
ከዳር እስከ ዳር፣ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ሰፈፍኩበት:: ምንም ገላጣ መሬት ማግኘትና ማየት ባለመቻሌ እንዲሁ እንደተንሳፈፍኩ የስንዴ ማሳው መሀል ለማረፍ ወደ ታች ዝቅ አልኩ:: አውሮፕላን ሲያርፍ ጎማዎቹን ከብብቱ ስር ወጣ ወጣ እንደሚያደርገው ሁሉ እግሮቼ ከታጠፉበት ዝርግት ብለው ከስንዴ ማሳው ላይ ለማረፍ ተሽቀዳደሙ:: ገጭ፣ ጓ የሚል ድምጽ ሳላሰማ በስንዴ ማሳው መሀል አረፍኩ::
ዐይኖቼ ዙሪያውን ሲያማትሩ በማሳው መሀል ልክ ገበሬ እህሉን ከወፎች ለመከላከል የሚያቆመውን ሰው መሰል እንጨት ሆኖ ራሴን አየሁት:: ‘ይሄ ነገር ምንድነው?’ ብዬ ባስብም ምንም ምላሽ ሳላገኝ ከእንቅልፌ ነቃሁ:: በማግስቱ ጠዋት ያየሁትን ሕልም ለእናቴ ነገርኳት:: ‹ነገሩስ ጥሩ ነው… ፍቺውን ግን እንጃ› አለችኝ:: ይህንኑ ሕልም እንደገና ለሁለተኛና ለሶስተኛ ጊዜ ደጋግሜ በማየቴ ግራ ተጋባሁ:: ይሄኔ ለአያቴ ሕልሙን ለመንገር ወሰንኩ::
አያቴ ‹‹ልጄ ያየኸው ጮማ ስጋ ሀብት ነው:: ስንዴው ደግሞ ሀብትህ የሚገኝበት መንገድ ነው… ሩቅ መጓዝህ ደግሞ ሀብትህ ያለው እዚህ ሳይሆን ሩቅ ቦታ እንደሆነ የሚያሳይ ነው… እንደ አውሮፕላን ቀስ ብለህ ማረፍህ ደግሞ ጸጋ፣ በረከትና እድሜ ነው›› አለችኝ:: እውን እንደ ሕልሜ ፍቺ እኖር ይሆን? ሲሉ ያስቀምጣሉ::
እኝህ ጉምቱ የንግድ ሰው አቶ ዘሙይ ተክሉ ቅስሙ ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተካሄደው አምስተኛው ዙር የበጎ ሰው ሽልማት መርሐ ግብር በአገልግሎት ዘርፍ ለማኅበረሰቡ ታላቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱ በሚል ተሸላሚ ሆኖዋል::
ከብዙ ዓመታት በፊት በትንሽ ካፒታል እና ጥቂት የሰው ኃይል ሥራውን የጀመረው ሸዋ ዳቦ ዛሬ ላይ በስሩ በአዲስ አበባ እና በአዳማ ከ20 በለይ ቅርንጫፎች እና 52 ማከፋፈያዎች በቃሊቲ ትልቅ የዳቦ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በአዳማ የዱቄት ፋብሪካ እንዲሁም ሴንትራል ማተሚያ ቤት ጨምሮ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ – እህት ኩባንያዎችን ማፍራት ችሏል:: የሸዋ ዳቦን ሲመሠርቱ ከነበራቸው 20 የሠራተኛ ቁጥር አሁን ላይ ከአንድ ሺህ 200 በላይ ሠራተኞችን መቅጠር እና ማሠራት ችለዋል::
አቶ ዘሙይ ተክሉ ከአባታቸው ተክሉ ቅስሙ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ለተሥላሴ ወልደአብ በ1921 ዓ.ም በአሥመራ ከተማ ነበር የተወለዱት:: የኤርትራ መሠረት ያላቸው ኢትዮጵያዊ አቶ ዘሙይ ወደ አዲስ አበባ ዘልቀው ያቋቋሙት ሸዋ ዳቦ ለ70 ዓመታት ለአዲስ አበቤዎች ዳቦ ሲያቀርብ የቆየ ነው።
እኝህ አንጋፋ የንግድ ሰው በተወለዱ በ94 አመታቸው ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል:: ስርዓተ ቀብረቸውም ዊንጌት በሚገኛው የካቶሊክ መካነ መቀብር ተፈፅሟል:: እኛም በአገልግሎት ዘርፉ የአገር ባለውለታ የሆኑትን እኚህን ሰው እንዲህ አስታውሰናቸዋለን:: ሰላም!
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2015