1933 ዓ.ም ዕለተ መስቀል። ለአቶ ገሰሰ ቤተሰብ አውደዓመት ሆኖ ብቻ አላለፈም። ከቀኑ መከበር ጋር ለጎጇቸው ሌላ የምሥራችን ይዞ ደረሰ። እማወራዋ ጌጤ ጉሩሙ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ መገላገላቸው በቤቱ ታላቅ ደስታን ፈጥሮ ዋለ። በዓሉ ለመላው ቤተሰብ ዕጥፍ ድርብ ሆኖም ቀኑ በተለየ ስሜት ታሰበ።
እነሆ በዚህ ቀን የተገኘው ፍሬ ለመላው ቤተሰብ የአዲሱ ዓመት ታላቅ ስጦታ ሆኖ ተበረከተ። በትዳር ለተጣመሩት ጥንዶች የዓይን ማረፊያ የሆነው ብላቴና ውሎ አድሮ መጠሪያ ስም ተቸረው። ጥላሁን ገሰሰ ተባለ።
ታዳጊው ጥላሁን አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ‹‹ጠበንጃ ያዥ›› ከተባለ አካባቢ እንደ እኩዮቹ ሆኖ አደገ። ለሚያዩት ሁሉ ልጅነቱ የሚያጓጓ፣ መልኩ የሚያምር፣ ቁመናው የሚማርክ ነበር። ጥላሁንና አዲስ አበባ በአብሮነት እምብዛም አልዘለቁም። አስራ አራተኛ ዓመቱን ባከበረ ማግስት ከተማውን ለቆ ወሊሶ ሊገባ ግድ ሆነ። ወሊሶ አያቱ ይኖራሉ። የጥላሁን ዕጣ ፈንታም በእሳቸው ቤት ሊሆን ተወስኗል። በወቅቱ የአዲስ አበባው ልጅ የመማር ዕድል አልተነፈገም። በአካባቢው ከሚገኝ የራስ ጎበና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፊደል እንዲቆጥር ተመዘገበ።
ጥላሁንና ትምህርት ወሊሶ ላይ በአካል ተገናኙ። የእሱ ፍላጎት ከቀለሙ አልሆነም። ውስጡ ያደረው የሙዚቃ ፍቅር ይታገል፣ ያሸንፈው ያዘ። ይህን ያስተዋሉት አያት ሁኔታውን አልወደዱም። በትምህርቱ ብቻ እንዲያተኩር መከሩ፣ ወተወቱ። የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ ሱዳናዊው ሼድድ ግን ጥላሁንን በተለየ አስተውሎት አይተው ትኩረት ቸሩት። ችሎታውን መዝነውም ወደ ሱዳን ሄዶ ሙዚቃ እንዲያጠና ምክር ለገሱት። ጥላሁን የተባለውን ባያደርግም ከራሱ ስሜት ሲታገል ሲሟገት ቆየ።
አንድ ቀን ግን የጥላሁንን ታሪክ ሊለውጥ የሚችል አጋጣሚ ተከሰተ። በወቅቱ የሀገር ፍቅር ቲያትር ባለሙያ የነበሩ ባለሙያዎች በትምህርት ቤታቸው የሙዚቃ ትዕይንት ለማሳየት ተገኙ። ይህ አጋጣሚ ለጥላሁን መልካም ሆነ። አቶ ኢዩኤል ዮሐንስን ቀረብ ብሎ ያለውን ችሎታና ፍላጎቱን አስረዳቸው። ኢዩኤል ጆሮ ሰጥተው አደመጡት። ፍላጎቱ ካለውም አዲስ አበባ መምጣት እንደሚችል ጠቆሙት። እንግዶቹ ከወሊሶ ከተሸኙ በኋላ ጥላሁን ዕንቅልፍ ይሉት አጣ። ትምህርቱን መማር፣ መከታተል ተሳነው።
አንድ ማለዳ የጥላሁን ልብ ቆርጦ ተነሳ። ማንም ሳያየው ከቤት ጠፍቶ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ጀመረ። ሁኔታውን ያወቁት አያት ለዘመድ ነግረው ሰላይ ላኩበት። አስራ አምስት ኪሎ ሜትር በእግሩ የተጓዘው ጥላሁን ቱሉ ቦሎ ሲደርስ አዳሩ ከአክስቱ ቤት ሆነ። ማግስቱን ጉዞ ከመቀጠሉ በፊት ግን ተይዞ ወደ ወሊሶ ተመለሰ።
በአስገዳጅነት ተመልሶ ወሊሶ የገባው ጥላሁን በሆነበት ሁሉ አዘነ። እልህና ቁጭት ያዘው። በውስጡ ያደረውን የሙዚቃ ፍቅር ያደናቀፉበትን በሙሉ በክፉ ዓይን አያቸው። በቤቱ ከአንድ ቀን በላይ አልቆየም። በጭነት መኪና ተሳፍሮ ዳግም ጉዞ ጀመረ። አዲስ አበባ ያደረሰው እግሩ ከአገር ፍቅር ቲያትር አገናኘው። የጥላሁን ምኞት ዕውን ሆነ። የውስጡ ፍላጎትና የሙዚቃው ፍቅር ገጠሙለት።
የትናንትናው የወሊሶ ጉብል አዲስ አበባ ላይ ታዋቂ ለመሆን አልዘገየም። እንዳሻው የሚታዘዝለት ድንቅ ጉሮሮው የሰጡትን ግጥምና ዜማ እያንቆረቆረ በርካቶችን ይማርክ ያዘ። ጥላሁን ገሰሰ የዘመኑ ተወዳጅ ድምጻዊ በመሆን ቀዳሚው ሆነ። ጥቂት ጊዜያትን በሀገር ፍቅር የቆየው ጥላሁን ለሌላ ዕድል መታጨቱ አልቀረም። ወደ ክቡር ዘበኛ ተዛውሮ ከአንጋፋና ታዋቂ የሙዚቃ ሰዎች ጎን ተሰለፈ።
የላቀ ዝነኝነቱን ተከትሎ ግን ፈተና አላጣውም። በታኅሣሥ ግርግር ሰሞን ዘፍኖታል የተባለ ዜማ ትርጉም ተሰጥቶት ለእስር ዳረገው። ጥላሁን ገሰሰ ያልነካው የሕይወት ጫፍ፣ ያላነሳው የዓለም እውነታ የለም። ክፋትና ደግነት ፣ ኀዘን ደስታ፣ ሕይወትና ሞት፣ በጥላሁን አንደበት ተዳሰዋል። ገንዘብ፣ ማግኘት ማጣት፣ ሀብትና ድህነት፣ በዜማዎቹ ተነስተዋል።
ስለጥላሁን ገሰሰ ዜማዎች አንድ በአንድ መዘርዘር ‹‹ዓባይን በማንኪያ›› እንደሚሉት ይሆናል። ጥላሁን ያላነሳቸው የሕይወት እውነታዎች የሉምና አንዱን ከሌላው አወዳድሮ መለየቱ በእጅጉ አስቸጋሪ ነው። በዛሬው ዳሰሳችን ጥላሁን በምክንያትና በሰበብ አዚሟቸዋል ተብለው ከሚታወቁት መካከል እጅግ ጥቂቶቹን ብቻ በወፍ በረር እንዳስሳለን።
ዋይ! ዋይ! ሲሉ
ወቅቱ ኢትዮጵያ አገራችን ባጋጠማት ድርቅና ርሀብ የከፋ ችግር ላይ የወደቀችበት ዘመን ነበር። ይህ ጊዜ መላው ዓለም ኢትዮጵያን ርዕስ አድርጎ ስለከፋው ርሀቧ፣ በየዕለቱ እንደ ቅጠል ስለሚረግፈው ምስኪን ሕዝቧ በእጅጉ የሚያወራበት፣ አስከፊው 1967 ዓ.ም። ጥላሁን ገሰሰ እና የሙያ አጋሮቹ በሙያቸው ሕዝቡን ለመድረሰ ወደሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተጉዘዋል። በስፍራው ሲደርሱ ግን ያዩት እውነት ከተባለውና ከተነገረለት በላይ እጅግ አስከፊ ነበር። ጥላሁን ታዲያ ይህን አይደበቄ ገጽታ በዓይኑ አይቶ፣ በውስጡ አንብቶ ብቻ አላለፈውም። በእጁ የገባውን ግጥም ከዜማ አዋህዶ ለሁሉም ‹‹ይድረስልኝ›› ሲል በታላቅ ኀዘንና ለቅሶ አንጎራጎረው።
ዋይ !ዋይ ሲሉ፣
የርሀብን ጉንፋን ሲስሉ።
እያዘንኩ በዓይኔ አይቼ፣
ምን ላድርግ አለፍኳቸው ትቼ።
ወይ እማማ ወይ አባባ፣
ብለው ሲሉ ሆዴ ባባ።
አስጨነቀኝ ጭንቀታቸው፣
ምንስ ሆኜ ምን ላርጋቸው።
ሳያቸው ዓይኔ አፍጥጦ፣
ተለየኝ ልቤ ደንግጦ፣
ተብረከረከ ጉልበቴ፣
ምን ላድርግ ዋ! ድህነቴ»
በርሀብ ስቃይ ቸነፈር፣
ግማሹ ጎኔ ሲቸገር።
ክው ብሎ ደርቆ አፋቸው፣
የእግዜር ውሀ ሲጠማቸው።
ጥላሁን በዚህ ዜማው አገር ቤትን ጨምሮ በባህር ማዶ ያሉ ወገኖችን ለእርዳታ አንቅቷል። ወገን ለወገኑ እንዲደርስ፣ አስከፊው የርሀብ ጊዜ እንዲታውስ አድርጓል። ይህ አይረሴ ዜማ ለመላው ኢትዮጵያውያን የክፉ ቀን ማስታወሻ እንደሆነ ዓመታትን ተሻግሯል።
አልማዝን አይቼ
ይህ ሙዚቃ በዘመነ ደርግ በነበረው የሥልጣን ሹምሽር ጊዜ የወጣ ዜማ ነበር። ይሁን እንጂ ግጥሙ የያዘው መልዕክት በዘመኑ ለነበሩ ባለሥልጣናት የተመቸ አልነበረም ይባላል። አድማጩም ቢሆን ሦስቱን አልማዞች ከወቅቱ ሦስት የደርግ ባሥልጣናት ጋር አመሳስሎ የራሱን ትርጓሜ መስጠት ይዞ ነበር። ታሪክ እንደሚነግረን ደግሞ እነዚህ ሦስት ሰዎች የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታሪክ የመቀየር ገጽታን ተላብሰው ነበር። ሰፊ ትርጉም የተቸራቸው የጥላሁን ገሰሰ ሦስቱ አልማዞች ደግሞ እንዲህ ተዚመዋል።
አልማዝን አይቼ፣አልማዝን ባያት፣
ሦስተኛዋ አልማዝ ብትመጣ ድንገት።
ሁለቱን አልማዞች ስላስረሳችኝ ፣
ምርጫዬ በምርጫ ተበላሸብኝ።
ሦስቱንም አልማዞች ባያቸው ባያቸው፣
እቺም፣ያቺም አልማዝ- አልማዝ አልማዝ ናቸው።
ሰው የተቸገረው በሌላ ሌላ ነው፣
እኔን ያስቸገረኝ የአልማዞች ምርጫ ነው።
በዚህ ዜማው ላይ ጥላሁን ሦስቱንም አልማዞች በወጉ አይቶ፣ ፈትሾ እንዳላዋጡት ይገልጻል። እንዲህ መሆኑ ደግሞ ምርጫው ወደሌላ እንዲያደላና በመጨረሻ ጥሩወርቅ ከተባለችው ላይ እንዲያርፍ መገደዱን ጭምር ይነግረናል። በወቅቱ ሦስቱ አልማዞች እነማን ናቸው? ጥሩወርቅስ ? ለሚለው ትርጉሙ እንደተባለው ፖለቲካ ፣ አልያም የተለመደው ጸጉር ስንጠቃ ሊሆን ይችላል። ጥላሁን ግን ያለውን ብሎ የውስጡን ስሜት ተነፍሷል።
ጃፓኗን ወድጄ
ይህ ሙዚቃ የባህር ማዶን የፍቅር ታሪክ ያስታውሳል። ጥላሁን በዜማው እንደገለጸውም አንድ ኢትዮጵያዊ ሩቅ ምሥራቅ ሳለ ከአንዲት የጃፓን ወጣት ጋር በፍቅር መውደቁን የሚያሳይ ሀቅ አለው። ይህ በዜማ የተገለጸው ስንኝ የአርቲስት ሃምሳ አለቃ ሸዋንዳኝ ወልደየስ እውነተኛ ታሪክ ነው።
ሸዋንዳኝ ለሥራ ሩቅ ምሥራቅ በሄዱበት አጋጣሚ ከአንዲት ጃፓናዊት ጋር ፍቅር ይጀምራሉ። ቆይታቸው አልዘለቀም። ወደመጡበት መመለስ ነበረባቸው። ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ አገርቤት ሲገቡ ግን ያሳለፉት የፍቅር ጊዜ አይረሴ ትዝታ ይጥልባቸዋል። ይህኔ ግጥሙን ጽፈው ዜማውን ከሌሎች ጋር ተባብረው ያዘጋጁታል። ጥላሁን ገሰሰ አሳምሮ እንደሚጫወተው እርግጠኛ ነበሩ። ጥላሁን አላሳፈራቸውም። በሚያምር ተስራቅራቂ ድምጹ ጃፓኗን ወድጄ ሲል እንዲህ አንጎራጎረው።
ሩቅ ምሥራቅ ሳለሁ ጃፓኗን ወድጄ፣
ትዝ ትለኛለች በፍቅሯ ነድጄ።
የወይን ዘለላ አበባ የመሰለች፣
ውበቷ ግሩም ነው ሲያይዋት ታፈዛለች።
ማክበር ልማዷ ነው እናትና አባቷን፣
በፍቅር ታንጿል እዩት ሰውነቷን።
መች እጠግባት ይሆን ናፍቆቷን ተርቤ፣
በሕይወቴ እስካለሁ አትወጣም ከልቤ።
ጥላሁን ይህን ዜማ ሲጫወተው በውስጡ ናፍቆትን ብቻ አልገለጸበትም። አድማጭን በሀሳብ ከባህር ማዶ አድርሶ ከጃፓኖች ባህልና ወግ ጋር አጨባብጧል። በአገሬው የሙዚቃ ቃና በፍቅር አስምጦ እውነተኛውን ትዝታ አሳይቷል።
ስትሄድ ስከተላት…
በጥለሁን ገሰሰ ድንቅ አንደበት ከተዜሙት መሀል ስትሄድ ስከተላት የሚለው ሙዚቃ አንዱ ነው። ይህ ታሪክም የሃምሳ አለቃ ሸዋንዳኝ ወልደየስን ታሪክ የሚነካ እንደሆነ ይነገራል። አርቲስት ሸዋንዳኝ ከአሁኗ ባለቤታቸው የልጆቻቸው እናት ጋር ከመጋባታቸው በፊት መልካም ይሉት የፍቅር ጊዜን አሳልፈዋል። ሁልጊዜም ትዝታ እየተመላለሰ የሚፈትናቸው ሸዋንዳኝ ታዲያ ጥላሁን ባማረ ድምጹ የልባቸውን ሀሳብ እንዲገልጽላቸው፣ ትዝታውን እያስታወሰ እንዲያዜምላቸው ግጥሙን እነሆ! አሉት። ጥላሁንም እንዲህ ብሎ የልባቸውን ሀሳብ ሞላው።
ይገርማል! ስትሄድ ስከተላት፣
በጎን እያየችኝ፣
አማላጅም ብልክ፣
ጨክና እምቢ አለችኝ።
ተሞኘሁ! ተሞኘሁ፣
ደግ ነሽ እያልኩኝ፣
ባንቺ ላይ ስመካ፣
አኝጀት የምትቆርጪ፣
ጨካኝ ሴት ነሽ ለካ።
ጥላሁን የሚታይባቸው መድረኮች ሁሌም የደመቁ ሆነው ይውላሉ። የእሱ አድናቂና ወዳጆች በእጅጉ የበረከቱ ናቸውና ፍቅርና አክብሮታቸውን ያሳዩታል። ከዚህ ባሻገር ደግሞ ጥላሁን በትግል ሜዳ አዋጊ ጀግና በመሆን ይታወቃል።
በተገኘባቸው የጦር አውድማዎች ጀግናን ማወደስ፣ ወታደሩን ማጀገን ያውቅበታል። በጦርነት መሀል ተገኝቶ ወደፊት በሉለት ይለይለትን አዚሟል። የጀግና ሰው ክብሩ ዳር ድንበሩ ሲል አነቃቅቷል ዘማች ነኝን ዘፍኗል። ከሁሉም ግን የውትድርና ሕይወትን መሠረት አድርጎ ለጀግኖች ኢትዮጵያውያንና ቤተሰቦቻቸው መታሰቢያነት ያንጎራጎረው ይህ ዜማ ፍጹም አይረሴነትን እንደያዘ እስከዛሬ ቀጥሏል።
ለአገሬ ስታገል ለድንበሯ
ከአገሬ ስታገል ለድንበሯ፣
ተኝቻለሁ እኔ ከአፈሯ።
ስለድል ታሪኬን ስታወሱ፣
ቤተሰቦቼን ግን እንዳትረሱ።
እንዳይራቡብኝ አስታውሱልኝ፣
እንዳይራቆቱ አልብሱልኝ።
እንዳይቸገሩብኝ ልጆቼ፣
አደራ ብያለሁ ወገኖቼ።
ጥላሁን ገሰሰና የአገር ፍቅር ፈጽሞ አይነጣጠሉም። ጥላሁን ተፈጥሮው ሆነና ሆደ ቡቡ የሚሉት ዓይነት ነው። ስለአገሩ ካሉት ደግሞ የዕንባው ነገር ይለያል። አገሩን እያነሳ አልቅሶ ታዳሚውን ጭምር ያስለቀሰባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው። ከጥላሁን የዕንባ ዜማዎች መካከል ስለነፃነት ያዜመው ስንኝ እንዲህ ይታወሳል።
ነፃነት
እንኳንስ ደስታዬን -የሰውነቴን ሰው፣
እንኳን ነፃነቴን- ጸጋ ክብሬን ትቼው።
በእናት አገር ምድር – በሚያውቀኝ፣
በማውቀው ፣
ስቃይ መከራዬን ካንቺው ዘንድ ያድርገው።
ጥላሁን ገሰሰ በአማርኛ ከተጫወታቸው እጅግ በርካታ ዜማዎች በተጨማሪ በኦሮምኛና ሱዳንኛ ዘፈኖቹ ጭምር ይታወቃል። ሁሉም በሚባል መልኩም ዜማዎቹ ተወዳጅና ተደማጭ እንደሆኑ ዓመታትን ተሻግረዋል።
የኢትዮጵያ የሙዚቃ ንጉሥ የሚባለው ጥላሁን በሕይወት ዘመኑ በርካታ ውጣውረዶችን አልፏል። በ1985 ዓ.ም በአንገቱ ላይ የደረሰበትን ጉዳት ጨምሮ በስኳር ህመሙ መነሻ ባጋጠመው ህመም አንድ እግሩን እስከመቆረጥ ደርሷል። እንዲያም ሆኖ ከመድረክ የመለየት ፍላጎት አልነበረውም። ሁሌም ቢሆን ሙያውን ማሳየት፣ ለአድናቂዎቹም ፍቅሩን መግለጽ ይሻል። ጥላሁን በሕይወት ካለፈ በኋላ በአገር እንዲታወስና በሙያው እንዳይረሳ እንዲህ ሲል አዚሞ ነበር።
ትንፋሼ ተቀርፆ
ትንፋሼ ተቀርፆ ይቀመጥ ማልቀሻ፣
ይህ ነው የሞትኩኝለት የእኔ ማስታወሻ።
ውበቷን ሳሞግስ -የለምለም አገሬን፣
ማንም አይዘነጋው በጩኸት መኖሬን።
ዜማ እንጉርጉሮዬን የግሌን ቅላጼ፣
ተቀርፆ ይቀመጥ ታሪኬ ነው ድምጼ።
ድምጻዊ ዘፋኝ ነኝ አንጎራጉራለሁ፣
ይኸው ነው ታሪኬ ሌላ ምን አውቃለሁ።
ጥላሁን ገሰሰ ዕድሜውን ሙሉ ለአገሩ ባበረከተው የኪነጥበብ ሥራዎች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት አግኝቷል። እንዲሁም ከኢትዮጵያ የኪነጥበብና የብዙኃን መገናኛ ሽልማት ድርጅት የሙሉ ዘመን ተሸላሚ ለመሆን ችሏል። ጥላሁን ገሰሰ ከሚወዳት አገሩ፣ ከሚያከብረው መድረክና በፍቅር ከተንበረከከለት ሙያው በድንገት የተለየው ሚያዝያ 11 ቀን 2001 ዓ.ም በዕለተ ፋሲካ ሌሊት ነበር።
‹‹ከመሞት አልድንም፣ መለያየት ሞት ነው›› ባለበት አንደበቱ በአይቀሬው ሞት በተነጠቀ ጊዜ የብዙኃን አድናቂዎቹ ልብ በታላቅ ኀዘን ተሰብሯል። ጥላሁን ከመሞቱ አስቀድሞ አገሩን ሊያመሰግንበት የነበረው ድንቅ ዜማ በሥርዓተ ቀብሩ ላይ በሙያ አጋሮቹ ተቀንቅኗል። እነሆ! በጥቂቱ።
ቆሜ ልመርቅሽ
ቆሜ ልመርቅሽ – ተቀበይኝ እማ
ሕይወትን መርቀሽ -ሰጥተሸኝ እኔማ
ይህ ቀረኝ የምለው- የሚቆጨኝ በዓለም
ኢትዮጵያ ዕድሜ ላንቺ- ያላየሁት የለም
አንገትሽ ራስሽን – ችሎ ልየውና
ማግስቱን ይውሰደኝ- አስር ሞት ይምጣና
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 26/2015