የአንድ ሺህ 444 ተኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ከተከበረ ከስድስተኛው ቀን በኋላ በሃረሪ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት “የሹዋሊድ” ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስነ ስርዓት ይካሄዳል። የዘንድሮው የሸዋሊድ በዓልም ካሳለፍነው ሃሙስ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ተከብሮ ዛሬ በደማቅ ዝግጅት ይጠናቀቃል። ሹዋሊድን በሐረር የሚኖሩ የብሔረሰቡ አባላት ብቻ ሳይሆኑ፣ በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ሐረሪዎች ጭምር የበዓሉን ቀን ጠብቀው ከያሉበት በመሰባሰብ ያከብሩታል።
የዝግጅት ክፍላችንም ይህንን ደማቅ ስነስርዓት በተመለከተ የክልሉን የባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወልዳ አብዶሽን አነጋግሮ ስለ“ሸዋሊድ” በአል ምንነት፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እና ስለበአሉ አከባበር ስነ ስርዓት የሚከተለውን ዳሰሳ ይዞላችሁ ቀርቧል።
የሹዋሊድ ክብረ በዓል
አቶ ተወልዳ አብዶሽ እንደሚናገሩት፤ በእስልምና ሃይማኖት ያሉ አጽዋማትን (የጾም ወቅቶችን) ለአቅመ አዳምና ሄዋን የደረሰ የእምነቱ ተከታይ ሁሉ መጾም ሃይማኖታዊ ግዴታው ነው። ከእነዚህም መካከል ዋናው የጾም ወቅት የረመዳን ወር ጾም ነው። የሹዋሊድ ፆም በእስልምና እምነት የረመዳን ወር ጾም እንደተጠናቀቀ ነው የሚጀመረው። በሹዋል ወር የመጀመሪያው ቀን የዒድ አልፈጥር በዓል ይከበራል። ከሹዋል ወር ሁለተኛው ቀን ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ስድስት ቀናት ደግሞ የሹዋሊድ ጾም ይጾማል። ይህ ጾም በሹዋል ወር የሚጾም በመሆኑ ስያሜውንም ያገኘው ከወሩ ስያሜ ነው።
የሹዋሊድ ጾምን ነብዩ መሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) በህይወት ዘመናቸው ሲጾሙት የነበረ ጾምና በሹዋል ወር ስድስት ቀናትን የጾመ ዓመቱን በሙሉ እንደጾመ ይቆጠራል የሚል አስተምህሮት ያላቸው በመሆኑ የሹዋሊድ ጾም በዚሁ መነሻነት በሐረሪዎች ዘንድ ከጥንት ጀምሮ መጾም እንደተጀመረ የቢሮ ኃላፊው ገልፀውልናል።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የሹዋሊድ ጾም በፍላጎት የሚጾም የሱና ጾም ነው። ሱና ስንል የነብዩ መሐመድ ወይም የረሱልን አስተምህሮ የተከተለ፣ አጅር ወይም ምንዳ የሚገኝበት፣ በረመዳን ጾም በምክንያት የተፈታን ጾም ለማሟላትና ሃይማኖታዊ አስተምህሮትን መተግበርን ሁሉ ያካትታል። በሃይማኖቱ የሹዋልን ጾም በተከታታይም ሆነ ነጣጥሎ መጾም ይቻላል። ሁለቱም የአጿጿም ስልት ደረጃቸው እኩል ነው።
ይሁንና ከዒድ አልፈጥር በኋላ ያሉትን ስድስት ቀናት በተከታታይ መጾም ግን የበለጠ ዋጋ አለው። ሴቶች በተፈጥሮ አስገዳጅነት ምክንያት በረመዳን የጾም ወቅት የወር አበባ በሚያዩባቸው ቀናት ጾሙን ለማቋረጥ መገደዳቸው አይቀሬ ነው። በዚህ ምክንያት ያቋረጧቸውን ወይም ያጓደሏቸውን የጾም ቀናት በሹዋል ጾም ማካካስ ይጠበቅባቸዋል።
“ምንም እንኳ ይህን ያቋረጠ በሃይማኖቱ በወሩ በማንኛውም ጊዜ ማካካስ እንደሚችል ቢጠቀስም በሐረሪዎች ዘንድ ከጥንት ጀምሮ በተከታታይ መጾሙ እንደ ባህል ተይዞ የመጣ ነው” የሚሉት የቢሮ ሃላፊው፤ ለዚህም መነሻቸው የሴቶችን ጫና ከመቀነስ አንፃር፣ ሴቶች ለብቻቸው ከሚጾሙ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት በጋራ መጾሙ አብሮነትን፣ መተሳሰብንና መደጋገፍን ያጎለብታል በሚል አስተሳሰብ እንደሆነ ያብራራሉ። ከዚያም ባለፈ በመጾማችን ከአላህ ወይም ፈጣሪ የምናገኘው አጅሪ ወይንም ምንዳ ከፍተኛ ነው በማለት ያምናሉ። በዚህም መሠረት ጾሙን ከስራ ባህላቸው ጋር እንዲስማማ አድርገው ባህልና ወጋቸውን በጠበቀ መልኩ ስድስቱን ቀናት በተከታታይ በመጾም የሹዋሊድ በዓል ያለምንም የጾታ፣ ዕድሜና ማኅበራዊ ደረጃ ገደብ ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ በደመቀ ሁኔታና ባህላዊ እሴቶቻቸውን በሚያንጸባርቅ መልኩ ይከበራል። ይህም ባህላዊ ቅርሱን የብሄረሰቡ አባላት የብሔረሰቡ ህያው ሀብትና የማንነት መገለጫው አድርውታል።
“ሹዋሊድን በሐረር የሚኖሩ የብሔረሰቡ አባላት ብቻ ሳይሆኑ በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ሐረሪዎች ጭምር የበዓሉን ቀን ጠብቀው ከያሉበት በመሰባሰብ ያከብሩታል” የሚሉት አቶ ተወልዳ፤ ክብረ በዓሉ በድሬዳዋ፣ በጉርሱም በተለይ ካለፉት ሁለት አስርተ አመታት ወዲህ በአዲስ አበባም በብሔረሰቡ ተወላጆች ዘንድ እየተከበረ የሚገኝ የሐረሪ ብሔረሰብ ትልቅ የማንነት መገለጫ እሴት መሆኑን ይገልፃሉ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ምንም እንኳን የሹዋሊድ ጾምን የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ ሕዝቦች የሚጾሙት ቢሆንም የሹዋሊድን በዓል እንደ ሐረሪዎች የሚያከብሩት አለመሆኑ ነው።
የሹዋሊድ በዓል አከባበር ሂደት
“የሹዋሊድ በዓል በሐረሪ የሚከበረው ለሶስት ተከታታይ ቀናት ነው” የሚሉት አቶ ተወልዳ አብዶሽ፣ ሐረሪዎች በዓሉ የማንነታቸው መገለጫ ባህላቸው መሆኑን ለመግለጽ ዚኢኛ ኢድ (የኛ በዓል)፣ አዳ ኢድ (የባህል በዓል ወይም ባህላዊ ይዘት ያለው በዓል)፣ ሹዋሊድ በማለት ይጠሩታል። በሹዋሊድ የበዓል አከባበር ወቅት በሚዜሙ ዜማዎች ውስጥ ዚኢኛ ኢድ፣ ሹዋል ኢዴ የሚሉትን ሐረጋት ይደጋግሙታል። በሌላ በኩል አዳ ኢድ (የኛ የሐረሪዎች በዓል) እያሉም ያዜሙበታል።
ሹዋሊድ መሠረቱ ሃይማኖት ቢሆንም እንደ ሐረሪ በዓሉ በባህላዊ ክንዋኔዎችና ሥነ ሥርዓቶች ታጅቦ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል (ዙሄር)። ሹዋሊድን ከሐረሪዎች በተጨማሪ ሌሎች በሐረርና በአካባቢዋ የሚኖሩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ወደ ከተማዋ በመምጣትና በበዓሉ ላይ በመሳተፍ በጋራ የሚተገብሩት የማይዳሰስ ቅርስ ነው።
“አንዳንዶች አብሮ በመኖርና የአካባቢውን ባህል ከመልመድ የተነሳ የበዓል ሥነ ሥርዓቱን ከመሳተፍ ባለፈ በአንዳንድ ሥርዓተ ክዋኔዎች ላይ በትግበራ የሚሳተፉበት ሁኔታም አለ” የሚሉት የቢሮ ሃላፊው፤ ለምሳሌ ዝክሪ በማውጣት፣ ከበሮ በመምታትና በመሳሰሉት ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ይገልፃሉ። የሹዋሊድ በዓል የአካባበር ሥነ ሥርዓት የሚጀምረው ከሁለት ቀናት ቀደም ብሎ ማለትም ከሹዋል ወር ስድስተኛው ቀን ምሽት ላይ ነው፤ ይህም እስከ የሹዋሊድ በአል እስከሚውልበት ስምንተኛው ቀን ድረስ ይቀጥላል። በስድስተኛው ቀን ምሽት ሶስት ሰዓት ላይ አባቶችና እናቶች ዝክሪ በማድረግ ማለትም ፈጣሪያቸውን አላህን፣ ነብዩ መሐመድን በማስታወስና በማወደስ በዓሉን ያከብራሉ። በሚቀጥለውም ምሽት ይኸው ሥነ ሥርዓት ይቀጥላል።
ዋናው የበዓሉ ሥነ ሥርዓት የሚጀምረው በዋዜማው ምሽት እና በሹዋሊድ በዓል ዕለት ነው። በዓሉ በዋነኝነት በሁለቱ የጁገል መግቢያ በሮች በሚገኙ አዋቾች ይከበራል። ይኸውም ከሐረር ከተማ በስተምስራቅ የሚገኘው አርጎ በሪ (ኤረር በር) አጠገብ በሚገኘው አው ሹሉም አህመድ አዋች ላይ እና በሐረር በስተሰሜን በኩል አስሱም በሪ (ፈላና በር) አቅራቢያ በሚገኘው አውዋቅበራ አዋች ላይ በጋራ ይከበራል (አብዱልሰመድ ኢድሪስ)።
አርጎ በሪ (ኤረር በር) አጠገብ የሚገኘው አው ሹሉም አህመድ አዋች መጠሪያውን ያገኘው በወቅቱ በአዋቹ በሙሪድነት ወይም መሪነት እያገለገሉ ይኖሩ ከነበሩ ትልቅ ሼኽ ሲሆን፣ እኚህ ትልቅ ሰው ሲሞቱም አስከሬናቸው በአዋቹ ቅጥር ግቢ እንዳረፈ ይነገራል። በአዋቹ ቅጥር ግቢም መታሰቢያ መቃብራቸው እንዳለ ጥናታዊ ጽሑፍች አረጋግጠዋል።
የሹዋሊድ ክብረ በዓል ፋይዳዎች
“የሹዋሊድ ክብረ በዓል በርካታ ፋይዳዎች አሉት” የሚሉት የክልሉ የባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ፤ እነዚህም ባህላዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቡናዊ ፋይዳዎች መሆናቸውን በመናገር እንደሚከተለው በቅደም ተከተል ያቀርቡታል።
የሹዋሊድ በዓል ከብሔረሰቡ ባለፈ ከተወላጆቹ ውጪ ያሉትንም ሌሎች ሕዝቦች በነጻነት የሚያሳትፍ በመሆኑ ለባህል ልውውጥና እድገት፣ ለሕዝቦች ትስስርና ግንኙነት መጎልበት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። በበዓሉ ላይ የብሔረሰቡን ባህልና ወግ የጠበቁ ባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች ወጥተው የሚለበሱበት፣ በየደረጃው ያሉ የብሔረሰቡ አባላትም በአልባሳቱና ጌጣጌጡ ደምቀውና አሸብርቀው የሚታደሙበት በመሆኑ ለባህል ትውውቅ እንደሚረዳ አቶ ተወልዳ አብዶሽ ይናገራሉ። አንዱ የሌላውን ባህል እንዲያውቅ እንደሚያደርግም ይገልፃሉ። ለተወላጆቹም ቢሆን ከልጅነታቸው ጀምሮ ባህላቸውን እያወቁ እንዲያድጉ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ይገልፃሉ። ህጻናት እና ልጆች ባህላቸውን ማወቅ ብቻ ሳይሆን በባህላቸውና በማንነታቸው እንዲኮሩ ያደርጋል ሲሉ ያብራራሉ።
“አንዱ የሌላውን ባህል ማወቁ ለባህል ትስስሩ፣ ለርስ በርስ ግንኙነቱ፣ ባህልን ለማጋራትና ለማሳደግ ባህል እንዳይረሳና እንዲቀጥል በማድረግ ረገድም ትልቅ አሰተዋጽኦ ይኖረዋል” የሚሉት አቶ ተወልዳ አብዶሽ፤ ወጣቶች የሹዋሊድ በዓል ማከናወኛ ባህላዊ ሥፍራዎችንና ከቅርሱ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን አልባሳትና የበዓሉ መተግበሪያ ቁሳቁስን /ለምሳሌ ከበሮ እና ከበል ወይም ማጨብጨቢያ የመሳሳሉትን/ ከመሰረቱ ማወቃቸው አገልግሎታቸውን እየተረዱ እንዲሄዱ ያደርጋል ይላሉ። ይህ ሁኔታም ትውልዱ ባህሉን ወይም ማንነቱን ጠያቂ ሳይሆን አስረጂ እንዲሆን ያደርገዋል በሚል ፋይዳው የጎላ መሆኑን ይገልፃሉ።
“በዓሉ ከሐረር ውጪ በድሬዳዋ፣ በአዲስ አበባና በባህር ማዶም ጭምር በብሔረሰቡ ተወላጆች እንደሚከበር ይታወቃል” የሚሉት የቢሮ ሃላፊው፤ ይህ ሁኔታ ባህሉ እንዳይረሳና እንዲቀጥል በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል። ይሁንና በበዓል ማክበሪያው ዋና ማዕከል ሐረር ላይ ሁሉም መሰባሰባቸውና ማክበራቸው የበዓል ሥነ ሥርዓቱን ሙሉ ገጽታ እንዲረዱ፣ መሰረተ ዐውዱን እንዲያውቁ ያደርጋል ይላሉ። ምንም እንኳን ባህል አዳጊ፣ ተለዋዋጭ የእያንዳንዱ ትውልድ አሻራ እያረፈበት የሚመጣ ቢሆንም፣ ነባር የሆነው ትውፊት መሰረቱን ሳይለቅ ባለው ላይ እየጎለበተ እንዲሄድ እንደሚረዳም ይገልፃሉ። ከዚህ አንጻር ባህላዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ነግረውናለ።
የሹዋሊድ በዓል ለብዙዎች በተለያየ ምክንያት ለምሳሌ በስራ፣ በትዳር ህይወት፣ በሌላም ምክንያት ለተራራቁ ቤተሰቦች፣ ዘመድ አዝማድ እና ጓደኛማቾች የመገናኛና የመሰባሰቢያ መድረክ ነው። በዚህም ምክንያት የተነፋፈቁ ናፍቆታቸውን የሚወጡበት፣ የተራራቁ የሚቀራረቡበት፣ የተቸገሩ ተመልካች የሚያገኙበትና የሚረዱበት ሆኖ ያገለግላል።
ይህም ሁኔታ በሁሉም የብሔረሰቡ አባላት ዘንድ በዓሉን ተናፋቂና አይረሴ እንዲሆን አድርጎታል። ሹዋሊድን ከብሔረሰቡ ተወላጆች ባሻገር ሌሎች በከተማዋና አካባቢዋ የሚኖሩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች አብሮ ከመኖርና ባህሉን ከመልመድ የተነሳ እንዲሁም በከተማዋና ዙሪያዋ ባሉ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ የተለያየ ባህልና ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ተማሪዎች ሳይቀሩ የሚሳተፉበትና በጋራ የሚያከብሩት በመሆኑ በእነሱም ዘንድ የሚናፈቅና የሚታሰብ እየሆነ መጥቷል። ይህ በመሆኑም በዓሉ ለእርስ በርስ መስተጋብር፣ ለአብሮነት ህይወትና ለማኅበራዊ ግንኙነነት መጠናከር ከፍተኛ አሰተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
የሹዋሊድ በዓል ተሳታፊዎች በበዓሉ መታደም ብቻ ሳይሆን አብሮነትን የሚያጠናክሩበት፣ በተለይ ልጃገረዶች ከአቻዎቻቸው ጋር ቤት ለቤት እየተጠራሩ የሚገባበዙበት፣ አብረው የሚጫወቱበት፣ የሚዝናኑበትና ጥሩ ጊዜ የሚሳልፉበት በመሆኑ የብሔረሰቡ ትልቁ እሴት እየሆነ መጥቷል።
ይህ ሁኔታም በኅብረተሰቡ የዕለት ተዕለት የህይወት እንቅስቃሴ ላይ በጎ ተጽዕኖ እየፈጠረ ይገኛል። መግባባቱ፣ በሀዘንና በደስታ መደጋገፉና መተሳሰቡ ጨምሯል። ሁሉም ለባህሉ ተቆርቋሪ እንዲሆን አድርጓል። የርስ በርስ መስተጋብሩ መጠናከርና መግባባት ለአካባቢው እድገት መፋጠን፣ ለመሰረተ ልማቶች መስፋፋትና መጎልበት የአካባቢውን ማኅበረሰብ በተለያየ መልኩ ተጠቃሚነቱን እያሳደገው ይገኛል።
ሌላው ሹዋሊድ ‹‹ዋሓቺ ዋ ደርማ ዒድ›› በዋናነት የወጣቶችና ልጃገረዶች የወደፊት የትዳር ህይወት መጠንሰሻ ወይም መተጫጫ መድረክ ሆኖ የሚያገለግል ነው። በዚህ ዕለት ወጣቱ ከምንጊዜውም በላይ ቁመናውንና አለባበሱን አሳምሮ ከጓደኞቹ ጋር የሚታደምበት ሲሆን ወጣቷም በብሔረሰቡ አልባሳትና ጌጣጌጥ ተውባና ደምቃ በበዓሉ ላይ የምትሳተፍበት ይሆናል። ሹዋሊድ በዚህና ከላይ በተለያየ መልኩ በተጠቀሰው ገጽታው አይረሴነቱ ከፍተኛ በመሆኑ ማኅበራዊ ፋይዳው የላቀ ነው።
ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ
“የሹዋሊድ በዓል በየዓመቱ በደማቅ ሥነ ሥርዓት የሚከበር ነው” የሚሉት አቶ አቶ ተወልዳ አብዶሽ፤ ይህ በዓል ከዓመት ዓመት በከፍተኛ የተሳታፊዎች ቁጥር የሚከበር ነው። በዓሉን የብሔረሰቡ ተወላጆች በብሔረሰቡ ባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች ደምቀውና አሸብርቀው እንደሚታደሙበት ይናገራሉ። ይህ ሁኔታ በአልባሳትና በጌጣጌጦች የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ሰዎችን ለአዳዲስ የፈጠራና የዲዛይን ስራ በማነሳሳት አዳዲስ ስራዎችን በማቅረብ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን የገበያ እድል መፍጠሩን ይገልፃሉ። በቀላል ወጪና አቀራረብ ባለሙያዎችን ውጤታማ እያደረገ ይገኛል ይላሉ።
በአሉ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ማስገኛ መንገድ እየሆነም መጥቷል። በበዓሉ ላይ የብሔረሰቡ ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ፣ ሌሎችም ተወላጅ ያልሆኑትም ጭምር በተለያዩ ኅብረ ቀለማትና ዲዛይኖች ያሸበረቁ የብሔረሰቡን አልባሳት እና ጌጣጌጦች ለብሶ መታደም፣ ካልሆነም በማስታወሻነት መግዛት በስፋት እየተለመደ መጥቷል። ለዚህም ሲባል በስፋት የማዘጋጀቱና የማምረቱ ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
ይህ ሁኔታም የሙያውን ባለቤቶች ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ የብሔረሰቡን ባህል በማስተዋወቅ፣ ባለሙያዎቹን በማበረታታትና ለተሻለ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያተጋ እየሆነ ነው። ሌላው በበዓሉ ላይ ከብሔረሰቡ ተወላጆች ባለፈ ሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች በነጻነት የሚሳተፉበት በመሆኑ አካባቢውን ለመጎብኘት የሚመጡ ሰዎች የአካባቢውን ባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች እንዲሁም የዕደ ጥበባት ውጤቶች ለመግዛት መነሳሳትን ጨምሯል። ይህ ሁኔታም አካባቢውን የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን አድርጎታል። ከፍተኛ የሆነ የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን ፍሰት እንዲጨምር አድርጓል። በተለያየ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ለአዳዲስ የፈጠራ ስራዎች እያነሳሳ ይገኛል። የተፈጠረው መልካም አጋጣሚ ባለሙያዎችን እያበረታታ፣ የአካባቢውን ገጽታ እየገነባ፣ ባህልን እያስተዋወቀ፣ በአጠቃላይ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት በተለያየ መልኩ እያሳደገ ይገኛል። ከዚህ አንጻር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል በማለት የቢሮ ኃላፊው ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22ቀን 2015 ዓ.ም