ምስጋና በዓድዋ ለተዋደቁ ጀግኖች እናት አባቶቻችን ይግባና፣ ኢትዮጵያን ነጻ አውጥተው ባያስረክቡን ኖሮ ዛሬ ላይ ሆነን የኢትዮጵያን ባህል.. የኢትዮጵያ ፋሽን እያልን ባላወራን ነበር። በጥቂቱ እየተበረዘ የሚያስቸግረን ይህ እሴታችን ዛሬ ምን አይነት ይሆን እንደነበር አስበነው እናውቃለን?፣ መቼስ ፈረጅ ፈረጅ እያለብን መላቅጣችንንም ባሳጣን ነበር። የባህል የበኩር ልጅ የሆነው ፉሽን፣ የቅንጦት ጉዳይ እየመሰለን ንቀን ችላ ካልነው የመጀመሪያውና ትልቁ ስህተታችን የሚጀምረው እዚህ ጋር ይሆናል። ለምን? የሚል ካለ ምክንያቱን እንመልከት። የአንዲት ሀገር ሉአላዊነት ከሚለካበት ሶስት መሰረታዊ ነገሮች ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ባህል ዋነኞቹ ናቸው። ፋሽን ደግሞ ከሁለቱ መሰረታዊ ነገሮች ጋር ቁርኝት አለው። ከኢኮኖሚና ባህል ጋር። የፋሽን ኢንዱስትሪያቸውን ያዘመኑ አገራት ያላቸውን ለአለም እያስተዋወቁና ምርታቸውን በባለቤትነት እየሸጡ ዛሬ ላይ ኢኮኖሚያቸውን ከፍ ማድረግ ችለዋል።
ሌላው ደግሞ የልዩ ልዩ ባህሎች መገኛ የሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ባህላቸውን ለማስተዋወቅ መጀመሪያ የሚከተሉት ባህላዊ ፋሽኖቻቸውን ነው። የእኛ የፋሽን መገለጫዎች ከተቀረው አለም ለየት ባይሉና ባህላችን ከወረራ ባይድን ኖሮ ዛሬ ላይ ቱሪስቶች እዚህ ድረስ እየመጡ የሚጎበኙበት ምንም ምክንያት አይኖርም ነበር። በዛሬ የፋሽን አምዳችን የዓድዋ ድል ካጎናፀፈን ትልቅ እድል መካከል አንዱ በሆነውና ትኩረት ባልሰጠነው የፋሽን እሴታችን ዙሪያ ይሆናል። ለዚህም ከአንዲት እንግዳ ጋር የስልክ ቃለምልልስ አድርገናል። ማርታ ሳምሶን ትባላለች፣ ከአመታት በፊት በምትኖርበት የካናዳ አገር በፋሽንና ዲዛይን ሙያ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀብላለች። በአሁኑ ሰዓትም በሀዋሳ ከተማ የራሷ የሆኑ የባህል አልባሳትን ዲዛይን በማድረግና በማዘጋጀት ለገበያ ታቀርባለች። ለባለሙያዋ ያነሳነው የመጀመሪያ ጥያቄ ከባህል ወረራ ጋር ተያይዞ በፋሽን ላይ የሚፈጠር ተፅእኖን የተመለከተ ነው።
ባለሙያዋ ለዚህ ሃሳብ ምላሽ ስትሰጥ፣ የባህል ወረራ ከፋሽን አንፃር ትርጉሙ እጅግ በጣም ሰፊ ነው ትላለች። ይህን ስታብራራም፣ ሁለት ምሳሌዎችን ታስቀምጣለች። የመጀመሪያውን ከአልባሳት አንጻር በሁለት መልኩ ልንከፍለው እንችላለን። የመጀመሪያው የእኛ ቱባ የባህል መገለጫ የሆኑ አልባሳት ያለ እኛ ፈቃድና እውቅና ሌሎች በዚያው ዲዛይንና መልክ አዘጋጅተው እንደራሳቸው በማድረግ የሚለብሱት ከሆነ የባህል ወይም የፋሽን ወረራ አካሄዱብን ማለት እንችላለን። ሁለተኛው ደግሞ የራሳችንን ወደጎን ጥለን በተለያዩ ሚዲያዎችም ሆነ መሰል መንገዶች ተመልክተን ብቻ፣ ከእኛ የባህል ስርዓት ጋር የማይሄዱ ፋሽኖችን ስናዘወትር የፋሽን ወረራ እንለዋለን። ፋሽን በባህሪው በቶሎ የሚዛመት በመሆኑ ባየናቸው ነገሮች በሙሉ አይናችንን የምንጥል ከሆነ ሳናስበው ወደዚያው እንገባና የእኛ የሆነውን እንረሳለን ስትል ታስረዳለች።
“ልዩ ልዩ የፋሽንና ባህል መገለጫዎች ባሏት እንደ ኢትዮጵያ ያለች አገር ውስጥ የባህል ወረራ ፋሽን ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ አሉታዊ ጎኑ እጅግ በጣም የከፋ ነው” የምትለው ማርታ፣ የባህል ወረራ ከፋሽን አኳያ የእኛ የሆነውን ነገር አስትቶ ፍላጎታችንን በመቀነስ በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች እየጠፋ እንዲሄዱ ያደርጋል የሚል እምነት አላት። በሌላ መልኩም አገር በቀሉን ፋሽን በሂደት ያጠፋዋል፣ባህሉም ይመናመናል ባይ ነች።
መነሻቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረ እኛ ግን የረሳናቸው በጣም ብዙ ፋሽኖች አሁን አሁን በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች እንደ አዲስ እየታዩና በእኛ ፋሽን እነርሱ ሲታወቁበት እንመለከታለን። ባህሎቻችን ሰፊ ከመሆናቸው አንጻር ኢትዮጵያዊ ሆነን እንኳን ይህን ስንመለከት የእኛ ስለመሆኑ ፈጽሞ አናስተውለውም ወይም ደግሞ ከነ ጭራሹ አናውቀውም። ታዲያ የእኛ ነው ብለን ብንከራከር ማን ይሰማናል?። ቱሪስቶች ወደአገራችን በሚመጡበት ወቅት ከከተማው ይልቅ ወጣ ብለው ባህላዊ በሆኑ ነገሮቻችን ላይ ማተኮር የሚወዱት ለምን ድነው? በማለት ሃሳቧን በጥያቄ የምታብራራው ማርታ፣ ለዚህ ምክንያቱ ለእኛ ከእጅ ያለ ወርቅ ሆኑና ከምንም ያልቆጠርናቸውን ነገሮች በመውሰድ የራሳቸው ለማድረግ ስለሚፈልጉም ጭምር ነው ትላለች። ይህን ደግሞ በተግባርም እያየን መሆኑን በቁጭት ትናገራለች።
ማርታ የዓድዋ ጦርነት ላይ የተገኘው ድል ለባህልና ፋሽን አለም ተምሳሌት ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አላት። ጀግኖች አባቶቻችን በደህናው ጊዜ ቀርቶ ያኔ ለጦርነቱ ከየአቅጣጫው ሲጎርፉ እንኳን የለበሱት የወታደር ልብስ አልነበረም። ለብሰው የዘመቱት ነጭ ተነፋነፍ ሱሪና በረባሶ ጫማ አልያም ባዶ እግራቸውን መሆኑ ለዚህ ማሳያ እንደሚሆን ትናገራለች። “በረባሶውን ምናልባት በወቅቱ ጫማ ስላልነበረ ነው ልንል እንችል ይሆናል። ያንን ልብስ የለበሱት ግን እነርሱ አገራቸውን የሚገልጹበትና የእነርሱ ብቻ የሆነ ባህላዊ መገለጫቸው ስለነበረ ነው። ፋሽን ትልቁ አላማው የማይታየውን የውስጥ ማንነት በሚታይ ነገር መግለጽ ነው። ልቡሱ ወኔያቸውን የሚቀሰቅስ የሞራል ስንቃቸው ነበር። እንደዚያ ለነብሳቸው ሳይሳሱ የተዋጉት ለአፈሩና ለጋራ ሸንተረሩ ብቻ ነው ካልን ሞኝነት ነው። ከዚያም በላይ እኛ ያላየናቸው ብዙ ነገሮችን አሻግረው አይተዋል። በነጻነቷ ውስጥ የራሷ ባህል፣ የራሷ ቋንቋ እንዲኖራት እንዲሁም ያሏት እሴቶች በሙሉ እንዳይወረሩና እንዳይጠፋ ነው” በማለትም ሃሳቧን ታጠናክራለች።
ፋሽን ስንል አልባሳቶቻችንን ብቻ አይደሉም። በፋሽን ውስጥ ያሉ በርካታ እሴቶች አሉን። ፋሽኖቻችን በወረራ ከጠፉ ብዙ ነገሮቻችን ከእኛ መውጣት ይጀምራሉ። ዛሬ ይህን ችላ ብለን የራሳችንን ነገሮች እየተውን በፋሽን ወረራ ውስጥ ከገባን የዓድዋንም ሚስጥር ከንቱ እናደርገዋለን ስትልም ታብራራለች። ‘የፋሽን ወረራ ዘመናዊነት ነው ልንለው እንችላለን? ትውልዱስ እነዚህን ሁለት ነገሮች በምን መልኩ አስታርቆ መሄድ ይችላል?’ ለባለሙያዋ የሰነዘርነው የመጨረሻ ጥያቄ ነው። የእሷም ምላሽ እንዲህ የሚል ነበር፣ “የፋሽን ወረራ በፍጹም የዘመናዊነት መገለጫ አይሆንም። ዘመናዊነትማ የራስን ጥሎ የሌላን መስረቅ አይደለም። በዘመናዊነት ውስጥ ትልቅ ስልጣኔ አለ። ይህ ስልጣኔ ደግሞ ያለንን ነገር እንድናዘምን የሌለንንም ነገር እንድንፈጥር ያደርገናል። አንድ ሰው መጽሀፍ ሲገዛ ስላየን ብቻ የተማረ ነው ልንል አንችልም፤ የተማረ ነው የምንለው መጽሀፉን ማንበብ ሲችል ነው።
የሰለጠኑ ሰዎች የለበሱትን ስለለበስን ብቻ የሰለጠነ አሊያም ዘመናዊ አያስብለንም። መዘመንም የሌላውን እንደወረደ አምጥተን መከናነብ አይደለም። መዘመን የነበረውን ማሻሻልና ከጊዜው ጋር እንደሚሄድ ማድረግ እንጂ ምንም ታሪክ እንደሌለው ትውልድ የነበረውን በዜሮ አባዝቶ አንድ ብሎ መጀመር አይደለምና ዘመናዊ ነኝ ብሎ የሚያስብ ትውልድ መሰረቱን መትከል ያለበት በድሮው ላይ ነው። አባት እናቶቻችን የሄዱበት መንገድ የማይጠቅም ቢሆን ኖሮ ዛሬ ከዘመናት በኋላ ነጮቹ ባልፈለጉት ነበር። ዘመናዊነትን እየሰበኩን አሞኝተው የእጃችንን እያስለቀቁን መሆኑን ልናስተውል የግድ ነው።”እኛም የራሳችንን ዓድዋ በድል ደግመን ታሪካችንን በቀጣዩ ትውልድ ማህደር ላይ እናስፍር! ስንል የባለሙያዋ ሃሳብ ላይ አከልንበት።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም