የዓለም አቀፍ ሰዎች ዝና እንዲህ ነው። የሕንዱ ማህተመ ጋንዲ የመብት ተሟጋች ስለነበሩ በየትኛውም የዓለም አገር ይታወቃሉ። በአገራችን ኢትዮጵያም በተደጋጋሚ ስማቸው ይነሳል። ሆስፒታል ሁሉ ተሰይሞላቸዋል።
በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ከ75 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 22 ቀን 1940 ዓ.ም የተገደሉትን ማሕተመ ጋንዲን እናስታውሳለን።
ማሕተመ ጋንዲ የተወለዱት መስከረም 23 ቀን 1862 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ ኦክቶበር 2፣ 1869) ነው። ማሕተመ ጋንዲ ‹‹የሕንድ አባት›› በመባል የሚታወቁ የሰላማዊ ትግል መሪ እና የፀረ ቅኝ አገዛዝ አብዮተኛ ናቸው።
‹‹ፍልስምና›› በተሰኘው የቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው፤ ጋንዲ እንግሊዞችን ፍጹም ሰላማዊ በሆነና ለእነርሱ ጨርሶ ሊገባቸው በማይችል እምነትና መንገድ የታገላቸው ነው። ከምዕተ ዓመታት ቅኝ ግዛታቸው ለማስወጣት የሕንድን ሕዝብ እያንቀሳቀሰ ስለሚፈታተናቸው ብዙ ጊዜ እስር ቤት ይከቱት ነበር።
ወደ መጨረሻው አስከፊ እስር ቤት በወረወሩበት ጊዜ ‹‹እናንተ አውሮፓውያን ወዳጆቼ ሆይ! የሰው ልጅ እኮ በአራት ግድግዳ የሚታሰር ግዑዝ ነገር አለዚያም እንሰሳ አይደለም። የሰው ልጅ መንፈስ ነው። እዚህ በእስር ሳለሁ ጽናቱን እምነቴ ሕንዳውያን ወገኖቼን ያንቀሳቅሳል፤ እስር ቤት ክፉ የሚሆነው በመንፈስ ሊታሰሩና በግድግዳ ለሚወሰኑ እውነተኞቹ እስረኞች እንጂ መንፈሳቸውን ከፍርሃትና ከጥላቻ ነጻ ላወጡ መንፈሳውያን እስራት አያስጨንቃቸውም፤ አያሸብራቸውም›› ብሏቸዋል።
በሌላ ጊዜ ደግሞ ጋንዲን የመጨረሻዎቹ ዱርዬዎችና ነፍሰ ገዳዮች መካከል ይከቱታል። ጋንዲ ወደዚያ ሲገባ ‹‹እነሆ ወንድሞቼ መሐል ገባሁ። ከዛሬ ጀምሮ የዚህ ቤተሰብ አካል ነኝ›› ይላቸው ነበር። ሐዘን ቢሰማው እንኳ ሐዘኑን በተስፋና በፍቅር ሊታገለው ይጀምራል እንጂ ቅሬታና ማጉረምረምን አያሰማም ይሉታል። በእነዚህ የማይጠቅሙ ተብለው በተጣሉ ዱርዬዎች ውስጥ ፍቅርና መልካምነት እንዳሉ ያውቃል ብቻ ሳይሆን ያምናል። እናም ኃላፊነት ይወስዳል። የእስር ቤቱን ቆሻሻ ማጽዳት ይጀምራል። እነዚያን አይጠቅሙም እንደውም ማኅበራዊ አደጋ ናቸው ተብለው የተጣሉ ነፍሰ ገዳዮችን በማክበር አክብሮት ከሚሰጠው መልካም ስሜት ያስተዋውቃቸዋል። ከእግዚአብሔር ያስተዋውቃቸዋል። ጤና አጠባበቅን፣ አብሮ መኖርን ያስተምራቸዋል። ታሪክ የማያውቁትን ታሪክ፣ ማይማኑን ማንበብ መፃፍ ያስተምራቸዋል። እንዲህ በመልካም ተግባር ተጠምዶ ሲውል ስለ እስር የሚያስብበት ጊዜ አልነበረውም። እንግዲህ ስለ ነጻነታቸው ሲል የራሱን ነጻነት ያጣላቸው ሕንዳውያን ማለት እነዚህን ወህኒ የተጣሉትንም እንደሚጨምር ያውቃል። እናም የብርሃን ተስፋውን በወህኒ ጨለማ ውስጥ ሳለ ይበልጡኑ ጸንቶና አምኖ እየታገለለት ነው ማለት ነው።
የትግሉ መንገድ ግን ጥላቻን በጥላቻ ማሸነፍ እንደማይቻል ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ጥላቻን በፍቅር መፈተን ነው። ስለዚህ መታሰሩ አስጨንቆ ዓላማውን ጥሎ እጁን እንዲሰጥ አያስገድደውም። ይልቁንም በዚያ ጨለማ ውስጥ ሕይወትን ይጀምራል። እናም መታሰሩን ይረሳዋል። በዚህ ጊዜ እነሱው አሳሪዎቹ ራሳቸው አስታውሰው ነው የሚፈቱት። ‹‹የረገጥኳትን መሬት ለመባረክ ሥልጣን ተሰጥቶኛል›› ነው የሚለው።
ማህተመ ጋንዲ በዚህ የሕይወት መንገዱ ያስተማረኝ ትልቅ እውነት ‹‹በዙሪያህ የሚታይህን ክፋት መቋቋም ካቃተህ ‹እኔን ምን ነካኝ?› እንጂ ‹ዓለም ምን ነካት?› ብለህ አትጠይቅ›› የሚል ትምህርት ነው። እንዲህ ብለህ ብትጠይቅም መልስ አታገኝም። ዓለም ክፉ ናት ብትል ራስህ ክፉ ናት ካልካት ከዓለም በእጥፉ የከፋህ ትሆናለህ። በምትጠላው ነገር ውስጥ ያለውን መልካም ነገር የምታስተውልበት ዓይኖች ቢኖሩህ ክፉውን መልካም ታደርገዋለህ። እርሱን ፈውሰህ አንተም ትፈወሳለህ›› ይላል።
ማሕተመ ጋንዲ በዚህ ባሕሪው ራሳቸው እንግሊዛውያኑ ቅኝ ግዢዎች፣ ሙስሊሙ፣ ክርስቲያኑ፣ የሌላ እምነት ተከታዮቹ ሳይቀሩ ይወዱት፤ ይከተሉትና ያምኑት ነበር። እንግሊዞቹ ተብትበው በወጡት መከፋፈልና ጥላቻ ምክንያት በተፈጠረው እርስ በእርስ የመጠፋፋት ጦርነት ውስጥ ሙስሊሞቹ ሂንዱዎቹን እያባረሩ በቆንጨራ በሚጨፈጭፉ ሰዓት እንኳ ማሕተመ ጋንዲን ግን ይሰሙት ነበር። ይከተሉት ነበር፤ እርሱ ዘንድ ሲደርሱ በፍቅሩ ጭካኔያቸውንና ቂም በቀላቸውን አሸንፎ ያንበረክካቸው ነበር።
የሁሉንም እምነት መጻሕፍት እየገለጠ በየዕለቱ ከሁሉም ሕንዳውያን ጋር አብሯቸው ይጸልይ ነበር። እናም ጋንዲ የቱንም መጥፎ የተባለን ቦታና ሃሳብ ወደ መልካም የመለወጥ ምሳሌ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በመሸ ጊዜ ንጋትን በማሰብ ተስፋህን አምነህ ጉዞህን ጀምር የሚል እምነት አለው። የክፉ ነገር መጨረሻ ጥፋት ነው። መልካሙን የሚያመጣው የግለሰቦች ጽናት ነው። በመጨረሻው ጨለማ ውስጥ ወደ ብርሃንህ መመልከት የማሕተመ ጋንዲ እምነት ነው።
ይህ የነፃነትና የሰብዓዊ መብት ታጋይ ናታሁራም ቪናያክ ጎድሴ በሚባል ግለሰብ በጥይት ተገድሏል። ገዳዩም የሞት ቅጣት ተፈርዶበት በስቅላት ተገድሏል። እነሆ የማሕተመ ጋንዲ ስምና ሥራ ግን በዓለም ዙሪያ ሲወሰድ ይኖራል።
አዲስ ዘመን ጥር 28 ቀን 2015 ዓ.ም