ተሰማ መንግስቴን፤ ዘውዴ መታፈሪያና ገብረየስ ገብረማሪያም ከምን ጊዜውም በላይ ተደስተዋል። ሰላም መስፈኑ ብቻ ሳይሆን የየልባቸውን ሊተነፍሱ አካታች አገራዊ የምክክር መድረክ እንደሚኖር ሲያስቡ መሸታ ቤት ተገናኝተው ሲነጋገሩ የነበሩባቸውን ሁሉ አደባባይ አውጥተው ተንፍሰው ለመገላገል ጓጉተዋል።
ዛሬ የመሸታ ቤት ውይይታቸው ከምን ጊዜውም የተለየ ነው። ማንም እንደልቡ ገብቶ እንደሚንቦራጨቅበት ግልፅ የፖለቲካ ንትርክ ላይ ያተኮረ አልነበረም። እነዘውዴ መንግስቴ ውይይት ላይ የፖለቲካ ጉዳይ የተነሳው ውስጠ ወይራ በመሰለ መልኩ በስሱ ነበር።
ዘውዴ መታፈሪያ እንደቀልድ ‹‹ ኢትዮጵያውያን ልዩነታችን ላይ ብቻ በማተኮር የጋራ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ በመስራት ከድህነት የምንወጣው መቼ ነው?›› ሲል እንደቀልድ በመጠየቅ አጀንዳውን ከፈተ ። ተስፈኛው ተሰማ ከተል አድርጎ ‹‹ አትጠራጠር የዛሬ አምስት ዓመት ከድህነት መውጣታችን አይቀርም፡፡›› አለ። ዘውዴ እየሳቀ ‹‹ ታዳጊ አገር የምንባልበት ጊዜስ የሚያበቃው መቼ ነው ›› ሲል በድጋሚ ጠየቀ።
ተሰማ በድጋሚ ‹‹ ከአምስት አመት በኋላ ወይም መጀመረያ አሁን የጀመርነው ስራ መሰረት ከያዘ በኋላ፤›› ሲል፤ ዘውዴ ሳቁን መቆጣጠር አቃተው። በሳቅ ሞተ፤ ‹‹ አይ ተሰማ ጥሩ ተስፈኛ ነህ። ኢትዮጵያ ማን ፈቅዶላት ነው የምትበለፅገው ?›› ሲል ሶስተኛ ጥያቄውን ዘውዴ አቀረበ። ተሰማ በበኩሉ መልሱን ከመመለስ ይልቅ እርሱም ዘውዴን መጠየቅ ጀመረ። ‹‹ ከድህነት ለመውጣት ስለልዩነት ላለማውራ ፤ ለብዙሃንነት ቦታ በመስጠት አንድነት ላይ አተኩሮ ከድህነት ለመውጣት የማን ፈቃድ ያስፈልጋል?›› ሲል ጥያቄውን በጥያቄ መለሰ።
ዘውዴ ‹‹ አየህ ተሴ የማይገባችሁ ይሔ ነው። በዓለም እያንዳንዱ የኢትዮጵያ እንቅስቃሴ የሚመራው በሌሎች ፈቃድ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡›› ሲለው፤ የሁለቱን ምልልስ ሲከታተል የነበረው ገብረየስ ለዘውዴ ‹‹ ምን ጉዳዩን ታወሳስበዋለህ ? ›› ሲል ጥያቄ አቀረበ። ዘውዴ በበኩሉ ‹‹ አንተ ደግሞ ተራ አዳማጭ አትሁን ወሬ ሲነግሩህ ሃሳብ ጨምርበት›› አለው። ዘውዴ ትንሽ ቆየት ብሎ የሚጠጣውን ተጎንጭቶ አየር ከወሰደ በኋላ በረዥሙ ተንፍሶ ‹‹ነገሩ ይገባኛል፤ እኔ ስናገር ጭንቅላታችሁ እንደእግር ዞሮ ዞሮ እንደሚደክመው በቀደምም አስተውያለሁ። ግን እስኪ ጭንቅላታችሁን አሰሩት፤ እየዞረ እየተነተነ መፍትሔ ያመንጭ እንጂ፤ አለበለዚያም የሚደገስልን ድግስ ይበታተናል፡፡›› ሲል የዘውዴ ገለፃ ተሰማን ፈገግ አሰኘው።
ተሰማ ‹‹ እውነትም ጭንቅላታችንን እግር አደረግከው። ሰሞኑን የተናገርከውን አስበን ለመረዳት ብዙ መጓዝን እንደግዴታ ቆጠርክብን እኮ! አንዳንዴ ቀለል ብታደርገው ይሻላል። ›› አለው። ዘውዴ በበኩሉ ‹‹እንኳን ቀለል ብሎ አክብደነውም ሚስጥራችንን መደበቅ አልቻልንም። እናቅልለው ካልን ደግሞ ሁሉ ነገር ግልፅ ይሆናል። ደግሞም ‹የቁም ነገር ስልቻ ለብቻ› እንደሚባለው እራሳችንን እንደሚገባን አወሳስበን መነጋገርን ካልለመድን ሚስጥራችንን ጠላት ያውቅብን እና ከአሁኑ የበለጠ ያራርቀናል፡፡
ሁሉም ነገር ከተገለጠ ያቀድነው ሁሉ ይሰናከላል። ምክንያቱም እሳት እንጨት ካልነሱት እንደማይጠፋው ሁሉ ማንኛውም ነገር የሚፈልገውን ካገኘ መፈለጉን ስለማያቋርጥ በኢትዮጵያ መደብዘዝ ዛሬም እየተጠቀሙ ያሉ፤ ነገ የኢትዮጵያ መጥፋት ደግሞ የበለጠ ተጠቃሚ ያደርገናል ብለው የሚያስቡ ስግብግቦች በሞሉባት ዓለም ጭንቅላታችን ለአገራዊ መግባባት ካልሰላ፤ እግራችን እና እጃችን ብቻ ሳይሆኑ መላው ሰውነታችን በሥራ ካልተወጠረ እንኳን ኢትዮጵያን መበልፀግ ቀርቶ
፤ የህዝብን አንድነት ማጠናከር እና ኢትዮጵያ እንደአገር እንደምትቀጥል ማረጋገጥ ያዳግታል፤ በካርታ ላይ ስማችን የሚጠራበት ጊዜም ሊያከትም ይችላል። ›› አለ።
ዘውዴ ንግግሩን አላበቃም ቀጠል አድርጎ ‹‹ የሰውን ሃሳብ አለመቀበል፤ በተለይ በራስ ላይ አንዱ የሚለውን ካልተቀበልነው ክንዋኔው የተሳካ አይሆንም። እሳት የላስኩ ፈጣን፣ ጮሌ ወይም በጣም ንቁ ሰው ልሆን ብችልም፤ ጭንቅላቱን በተደጋጋሚ ሲያሰራ የኖረው የዓለም ቀጣፊ ሊያወናብደኝ ይችላል። በእርግጥ አንዳንዴ ደግሞ አማራጭ ይጠፋል። ነገር ግን ደግሞ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ሚስቱን ገድሎ ዓማት ቤት መሸሸግ የማይታሰብ እንደሚሆነው ሁሉ፤ እያንዳንዱ ጥፋትም ሆነ እያንዳንዱ መሸሸጊያ የተሰላ ካልሆነ ውጤቱ አደገኛ ነው። አህያ በሞተ በዓመቱ ‹‹ና ኩር›› አለ ባለቤቱ፤ እንደሚባለው ከሆነ ያው እንግዲህ በእኛው ሰበብ ሀገር ፈረሰች ይባላል፡፡›› ሲል ሃሳቡን ጠቀለለ።
ተሰማ በበኩሉ ‹‹ የምር የዛሬው ንግግርህ ትንሽም ቢሆን ጭንቅላቴን እያደከመው ነው። ከመጠጡ ጋር ያንተ የተወሳሰብ ንግግር ታክሎበት ጭንቅላቴ በጉዞ ታከተ፤ ግን አሁንም ምን ለማለት እንደፈለግክ በደንብ አልገባኝም? ›› ሲል ጠየቀ። ዘውዴ በበኩሉ ‹‹ ዛሬ የአንተ ጥያቄ እና ነገር በፍጥነት የማይገባህ መሆኑ እኔን እያደከመኝ ነው። ግን ጥያቄህን ለመመለስ ያህል ልንገርህ። ኢትዮጵያን የመሰለች አገር ብዙዎች ለዘመናት እንድትፈርስ ቢመኙላትም ህልማቸው እውን መሆን የለበትም። ይህ ህልማቸው ለዘመናት ሲጨናገፍ ኖሯል። አሁንም እየተጨናገፈ ይገኛል።
ነገር ግን ምንም እንኳ ኢትዮጵያን የማፍረስ ዕቅድ በተደጋጋሚ ቢጨናገፍም አሁንም ከድህነት መውጣት፣ ማደግ፤ መመንደግ አልቻልንም፤ አሁን ልብ ብለህ አዳምጠኝ በኋላ ስጠይቅህ ጭንቅላቴን አደከምከው ምናምን እንዳትለኝ። ›› ብሎ ካስጠነቀቀ በኋላ ዘውዴ መዘርዘሩን ቀጠለ። ‹‹ እንደውም ለሁለታችሁም አንድ ጥያቄ አለኝ። ጭንቅላታችሁን በደንብ አሰሩትና መልስ ስጡኝ በትክክል ኢትዮጵያን ታውቋታላችሁ?›› በማለት ዘውዴ ጥያቄውን ቀጠለ።
ገብረየስ ‹‹ እኔ እንደሚመስለኝ ኢትዮጵያ ሀገሬ ናት። ተንከባክባ በስነስርዓት አሳድጋናለች፤ እኛ ደግሞ ዳር ድንበሯን አስከብረን እንኳን ለራሳችን ለጎረቤቶቻችን እንተርፋለን፤ ብለን እየሰራን ነው። ደግሞስ አገር እንዴት ትገለፃለች? ትንሽ ለመግለፅ ከበደኝ ›› ብሎ ግራ በመጋባት ራሱ ላይ አሳበቀ። ዘውዴ ፈገግ ብሎ ከተሰማም ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን በመጠቆም ፊቱን ወደ ተሰማ አዞረ። ተሰማ በበኩሉ ‹‹ እኔም ኢትዮጵያ ሀገሬ ናት። ለምለም ናት። አሁን ያለኝን ማንነት ማግኘት የቻልኩት ኢትዮጵያዊ በመሆኔ ነው ፤ በዚህ ደስተኛ ነኝ›› አለ።
ዘውዴ ሁለቱም ንግግራቸውን ሲጨርሱ ፈገግ ብሎ ‹‹ ሁለታችሁም ኢትዮጵያ ሀገሬ ናት ማለታችሁ አስደስቶኛል። ከብሔራችው በፊት ኢትዮጵያዊነታችሁ ሲታወሳችሁ ማስተዋል ራሱ ደስ ያሰኛል። በእርግጥም ብሔራችሁ እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያዊነታችሁ ደግሞ አንድ ያደርጋችኋል። ኢትዮጵያዊነታችሁ ቀስ በቀስ እያደገ ማየት በጣም ያስደስታል፤ ከሀገራችን ውጪ የትኛው ሀገር ብንሄድ የምንጠየቀው ዜግነታችንን እንጂ ብሄራችንን አይደለም። ከየት ነህ ለሚል ሁሉ መልሱ ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ከአፍሪካ ነው የመጣሁት ነው የምንመልሰው›› ሲል ተሰማ በስጨት አለ።
‹‹ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ብለን እናውቃለን እንዴ ? ›› ሲል ተቆጣ። ዘውዴ ግን ተረጋግቶ ንግግሩን ቀጠለ። ‹‹ በየዘመኑ የነበሩ ልጆቿ ድንበሯን ከመጠበቅ ይልቅ አንዳንዶቹ ከጠላቶቿ ጋር በማበር እና የዕለት ስልጣናቸውን መጠበቅ ላይ ብቻ በማተኮር ስትሸራረፍ ቆመን ተመልክተዋል። መሸራረፍ ደግሞ ቀስ በቀስ መሔድ በመጨረሻም መጥፋት ነው። ኢትዮጵያ ስፋቷ እና በመንግስቷ የምታስተዳድረው አካባቢ ምን ያህል ሰፊ እንደነበር ታሪክ አገላብጡ። የትኛው የኢትዮጵያ ክፍል መቼ ከኢትዮጵያ ተነጠለ የሚለውን በደንብ አጢኑ፤ እኛ እያወቅንም ኢትዮጵያ ተሸርፋለች። ከዚህ በላይ ተሸራርፋ እንዳትጠፋ እንደምንም ተፍጨርጭረን አገራችንን ማዳን አለብን። ነገር ግን አገር ማዳን በቃል ብቻ ሳይሆን ትርጉም በሚያመጣ ተግባር ላይ መመስረት የግድ ነው። አስፈላጊ ከሆነ አገር ለማዳን የምንሰዋው ስልጣን እስከመልቀቅም ሊደረስ ይችላል። የሀገርን አንድነት ለማስጠበቅ መሞትም ካለብን መሞት አለብን›› ሲል በዘውዴ ንግግር ተሰማ ሳቁ መጣ። ከትከት ብሎ ሳቀ።
‹‹ አይ ዘውዴ ስልጣን መልቀቅን የሀገርን ህልውና ከማቆየት በላይ አገዘፍከው እኮ!›› አለው። ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹እያየን ያለነው ተመሳሳይ ነው። ሰዎች ስልጣን ከሚለቁ ቢሞቱ ይመርጣሉ። አንድ ሰው ምንም እንኳን አገር እና ህዝብ ላይ ትልቅ ጥፋት የሚያስከትል ውሳኔን ቢያስተላልፍም ከስልጣኑ አይነሳም። ስልጣን ህይወትን ከመሰዋት በላይ እንደትልቅ ጉዳይ በመታየቱ ይህንን ለማለት ተገድጃለሁ፡፡›› ብሎ ሳቀ።
ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹ኢትዮጵያ ዛሬ ከመሬት የተፈጠረች አገር አይደለችም። ለዘመናት ኖራለች፤ አሁንም እየኖረች ነው፤ ወደ ፊትም ትኖራለች። ለዘመናት መኖሯን በታሪክ እናውቃለን። አሁን እንዳለች በተጨባጭ ኖረንባት እያረጋገጥን ነው። ወደ ፊትም ለዘላለም እንደአገር እንደምትኖር መተንበይ ብቻ ሳይሆን እጅግ በጣም እርግጠኛ ነኝ። ግን ከድህነት ለመውጣት ልዩነታችን ላይ ሳይሆን ብዝሃነትን ባከበረ መልኩ አንድነታችን ላይ በመመስረት ፖለቲካውንም ሆነ ኢኮኖሚውን በቅጡ መምራት ይጠበቅብናል፡፡›› አለ።
ዘውዴ አላቆመም ንግግሩን ቀጠለ፤ ‹‹ የሰዎች የመናገር ነፃነት መረጋገጥ አለበት። ሰዎች በእኩል አይን ሊታዩ ይገባል። ዕድሎች ሁሉ ለሁሉም እኩል ክፍት መሆን አለባቸው። ዜጎች በፍፁም ኢትዮጵያዊነታቸው ጥያቄ ውስጥ መግባት የለበትም። ሁሉም ኢትዮጵያዊነቱ አስደስቶት መኖር አለበት። ባለፈው ታሪክ ከመቆጨት ይልቅ በሚያስደስተው ኮርቶ፤ በሚያበሳጨው ጉዳይ ተምሮ፤ ታሪክን እንደታሪክ ለነገ ትቶ፤ አንዱ ብሔር ሌላውን እንደጨቆነ ከማሰብ ይልቅ ለአንድነቱ ቅድሚያ ሰጥቶ በጋራ አገር ለማበልፀግ ቢነሳ መልካም ነው፡፡›› ብሎ እንደለመደው ለአስተናጋጁ ይርጋ የጠጣበተን እነርሱ እንደሚከፍሉለት ገልፆ ሳይሰናበታቸው ከመሸታ ቤቱ ወጣ።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥር 11 /2015