የቱሪዝም ሚኒስቴር በታህሳስና በያዝነው የጥር ወራት ውስጥ በተለይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በድምቀት የሚከበሩት “ገናን በላሊበላ” እንዲሁም “ጥምቀትን በጎንደር” በዓላት ላይ የሃይማኖቱ ተከታዮችና የመስህብ ስፍራውን ለመመልከት የሚሹ ኢትዮጵያውያንና የውጪ አገር ጎብኚዎች እንዲታደሙ የማስተዋወቅ ስራ እየሰራ ይገኛል። የልደት በዓልን ለማክበርና ታሪካዊዎቹን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና በዙሪያው የሚገኙ የመስህብ ሃብቶችን ለመጎብኘት በርካታ ቁጥር ያለው ህዝብ በስፍራው መገኘቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከጥር 10 ጀምሮ በሚከበረው የከተራ በዓልና “ጥምቀትን በጎንደር” በዓል ላይም ተመሳሳይ ውጤት እንደሚጠበቅ ሁነቱን የሚያስተባብሩት አካላት እየገለፁ ይገኛሉ።
የዝግጅት ክፍላችን በ“ገናን በላሊበላ” ክብረ በዓል ላይ የተመዘገበውን ውጤትና “ጥምቀትን በጎንደር” ክብረ በዓል ላይ የሚጠበቁትን ሁነቶች አስመልክቶ ከቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት ጋር ያደረገውን አጭር ቃለ ምልልስ በዛሬው የባህልና ቱሪዝም አምዱ ይዞ ቀርቧል፡፡ መልካም ንባብ!
አዲስ ዘመን፦ በ“ገናን በላሊበላ” ክብረ በዓል ላይ ምን ያህል ህዝብ ተገኘ?
ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት፦ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ጎብኚዎችና በሃይማኖታዊ ስርዓቱ ላይ መታደም የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ደማቅ ስነስርዓት ወዳለበት ላሊበላ ሄደው እንዲያከብሩና የመስህብ ስፍራዎችን እንዲጎበኙ ከሶስት ወራት በፊት ጀምሮ የቱሪዝም ሚኒስቴር የማስተዋወቅና የቅስቀሳ ስራ ሲሰራ ቆይቷል። በዚህ ምክንያት ከአገር ውስጥም ከውጪም ጎብኚዎች ወደ ስፍራው እንዲሄዱ ማድረግ ተችሏል። “ገናን በላሊበላ” ለማክበር አንድ ነጥብ 8 ሚሊዮን ህዝብ በእለቱ ተገኝቶ በዓሉን ታድሟል።
አዲስ ዘመን፦“ገናን በላል ይበላ” ማክበር ከሌላው አካባቢ በምን መልኩ ይለያል? የቱሪዝም ሚኒስቴርስ ትኩረቱን በዚያ ላይ ማድረግ ለምን አስፈለገው?
ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት፦ ገናን በላል ይበላ ማክበር ለየት የሚያደርገው ላል ይበላ የአገራችንም ሆነ የዓለም ቅርስና መስህብ በመሆኑ ነው። በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ እውቅና ተወዳጅ ቅርስ ነው። ከዚህ ባሻገር በገና በአል በልዩ ሁኔታ ደማቅ ሃይማኖታዊ ስርዓት የሚፈፀምበትና ይበልጥ ደማቅ የሚሆንበት ጊዜ ነው። ይህ ከኢትዮጵያም ሆነ ከመላው ዓለም በሚመጡ ጎብኚዎች በስፍራው መገኘትና መታደም ልዩ ስሜትን ይፈጥራል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማሳደግና ይህንን ታላቅ ክብረ በዓል ይበልጥ ታዋቂ ለማድረግ “ገናን በላል ይበላ” የሚል መሪ ርእስ በማውጣት ሰፊ የማስተዋወቅ ስራ ሰርቷል።
አዲስ ዘመን፦ ክብረ በዓሉ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ምን የተለየ ነገር ታይቶበታል?
ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት፦ የቱሪዝም ሚኒስቴር ባከናወነው ተግባር ባሳለፍነው ዓመት “ ገናን በላል ይበላ” በተመሳሳይ ተከብሯል። ሆኖም ግን በነበረው የፀጥታ ችግርና ሙሉ ለሙሉ ተወግዶ ባልነበረው የኮቪድ ወረርሽኝ ሳቢያ ብዙ ጎብኚዎችና የሃይማኖቱ ተከታዮች ወደ ስፍራው ሳይጓዙ በመቅረታቸው የጎብኚዎች ቁጥር አመርቂ የሚባል አልነበረም።
የዘንድሮው ገናን በላል ይበላ ግን በጣም በደማቅ ስነስርአት ተከብሯል። በርካታ ቱሪስቶች፣ ዲያስፖራዎች እንዲሁም ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በዓሉን ለማክበር በእግር፣ በትራንስፖርትና በአየር ትራንስፖርት ጭምር ተጉዘው አክብረውታል፡፡ ይህም ከአንድ ነጥብ 8 እስከ ሁለት ሚሊዮን ታዳሚዎች የነበሩበትና መልካም ውጤት የተመዘገበበት ነው።
አዲስ ዘመን፦ በበዓሉ ምን ያህል የውጪ ቱሪስቶች ተገኝተዋል? ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ ምን እየተሰራ ነው?
ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት፦ በዘንድሮው በዓል ላይ የተገኙት የውጪ ቱሪስቶች ከ500 ይበልጣሉ። በዘንድሮው በዓል ካለፉት ዓመታት ለየት ባለ መልኩ ጎብኚዎች ቆይታ እንዲኖራቸው አርገናል፡፡ ከዚህ ቀደም ግማሽ ቀን ብቻ በስነስርዓቱ ላይ ይታደሙ ነበር፤ ዘንድሮ ግን የጉብኝት ቆይታቸውን ወደ ሁለት ቀን ከግማሽ እንዲያራዝሙ አድርገናል። በአካባቢው ያሉ አብያተ ክርስቲያናት እንዲጎበኙና ከገና አንድ ቀን ቀደም ብለው እንዲመጡና የተለያዩ የመስህብ ሰፍራዎችን እንዲመለከቱ አመቻችተናል። በተለይ የቱሪዝም ምርት የሆኑና በአካባቢው ማህበረሰብ የሚሰሩ ባህላዊ አልባሳት፣ ጌጣጌጦች እና ሌሎች ምርቶችን እንዲሸምቱ እድሉ ተመቻችቶላቸዋል።
አዲስ ዘመን፦ በዘንድሮው በዓል ላይ በርካታ በኢትዮጵያ የሚገኙ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በላልይበላ ተገኝተዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ከቱሪዝም ዲፕሎማሲው አኳያ ሲታይስ ምን ይመስላል?
ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት፦ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በበዓሉ ላይ ጎብኚዎች እንዲታደሙ ከማስተዋወቅ ባሻገር ዝግጅት አሰናድቶ በአዲስ አበባ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቦችን፣ አምባሳደሮችን ጋብዟል። ዲፕሎማቶቹ ግን ወጪያቸውን ራሳቸው ሸፍነው ነው በስፍራው የተገኙት። የደህንነትና የተለያዩ አስፈላጊ ሁኔታዎችን ደግሞ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሸፍኗል። በዚህም ከ10 በላይ አምባሳደሮች ከ20 በላይ ዲፕሎማቶችና የኢምባሲ ተወካዮች በበአሉ ላይ ተገኝተዋል።
በሰላም መደፍረሱ ምክንያት የተለያዩ አገራት ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ አስጠንቅቀው ነበር። አሁን አምባሳደሮቹና ዲፕሎማቶቹ ገናን በላል ይበላ ተገኝተው ሁነቱን መከታተል ቢፈልጉ በቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችና በመዲናችን የፀጥታ ጉዳይ እንደማያሰጋ እንዲረዱና ክልከላው እንዲነሳ እንዲያግዙ ያለመ ነበር። እንግዶቹም በቀጥታ ስፍራው ላይ ተገኝተዋል፤ ሁነቱ ልዩ የደስታ ስሜት እንደተፈጠረባቸውም መገንዘብ ችለናል። ይህ ለኛ ትልቅ ድል ነው። በተለይ የሰላም ስምምነቱ ከተካሄደ በኋላ መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መመልከት መቻላቸው ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል አለው።
አዲስ ዘመን፦ በገናን በላል ይበላ ክብረ በዓል ላይ ይህን ያህል ብዛት ያለው ሰው እንደሚመጣ ተገምቶ ነበር? ምን አይነት ዝግጅቶችስ ተካሂደዋል?
ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት፦ በዚህ ደረጃ ብዛት ያለው ታዳሚ እንደሚገኝ ገምተናል። ምክንያቱም የማስተዋወቅ ስራዎችን ሰርተናል። በደቡብ አፍሪካ በመንግስት እና በሕወሓት መካከል የሰላም ስምምነት መፈረሙና ይህም በዓለም አቀፍም ሆነ በመላው አገሪቱ እውቅና ማግኘቱም ሌሎች ለታዳሚዎች በእዚህ ልክ መገኘት አስተዋጽኦ ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ከዚያ በተጨማሪ በአካባቢው የመብራትና ሌሎች የመሰረተ ልማት አቅርቦቶች መኖራቸው በበአሉ ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ታዳሚ እንዲገኝ የራሳቸውን አስተዋፆኦ አድርገዋል።
ሆቴሎችም ተደራጅተውና ተዘጋጅተው መጠበቃቸው ቱር ኦፕሬተርና ሌሎች ባለድርሻዎች የየራሳቸውን የቤት ስራ መስራታቸውም ለተገኘው ውጤት ድርሻ አለው። በዚህ ምክንያት ከአምናው በተሻለ ሁኔታ የህዝብ ብዛት ሊኖር እንደሚችልና ስነስርአቱም ደማቅ እንደሚሆን ግምቶች ነበሩን። የክልሉ አስተዳደርም ፀጥታውን በማስጠበቅ ጎብኚዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ረገድ የበኩሉን በመወጣት የሚያስመሰግን ተግባር አከናውኗል። የባህልና ቱሪዝም ቢሮው እና የከተማው አስተዳደርም በቱሪዝም ሚኒስቴር ስም ላመሰግናቸው እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፦ በቀጣይ ቀናት በመላው ኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል ይከበራል። በልዩ ሁኔታ በሚከበረው “ጥምቀትን በጎንደር” በአል ላይ በተመሳሳይ በርካታ የውጪና የአገር ውስጥ ጎብኚዎች እንደሚገኙበት ይጠበቃል። በዚህ ረገድስ ምን ዝግጅቶች አድርጋችኋል?
ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት፦ የጥምቀት በዓል በተለየ መልኩ በጎንደር፣ በኢራምቡቲና በሌሎች ልዩ ልዩ የአገሪቱ ክፍሎች በድምቀት እንደሚከበር ይጠበቃል። በዓሉ በመላው ኢትዮጵያ የሚከበር ቢሆንም በልዩ ሁኔታ በእነዚህ አካባቢዎች ይከበራል። በእነዚህ ስፍራዎች የውጭ አገር ጎብኚዎችም ሆኑ የአገሪቱ ዜጎች ሄደው እንዲያከብሩ አገልግሎት ሰጪዎች አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ አስቀድመን ስንሰራ ቆይተናል።
ሃይማኖታዊ ስርዓትና ባህላዊ ይዘት ያላቸው በዓላት በቱሪዝሙና በኢኮኖሚው ላይ አዎንታዊ ተፅእኖ ማሳደር የሚችሉት ተጓዦች በአሉን አንድ ቀን በማክበራቸው ብቻ ሳይሆን፣ ቆይታቸውን ማራዘም ሲችሉ ነው። ስለዚህ በዘንድሮው ጥምቀት በአል ላይም በጎንደርና በልዩ ሁኔታ ጥምቀት በሚከበርባቸው አካባቢዎች ጎብኚዎች ቆይታቸውን ሁለትና ሶስት ቀን አራዝመው ሌሎች የመስህብ ስፍራዎችን አይተው እንዲመለሱ ሰፊ የቅስቀሳና ማስተዋወቅ ስራዎችን እያከናወንን እንገኛለን።
ጎንደር ላይ ሁሌም በየዓመቱ “ጥምቀትን በጎንደር” ፕሮጀክት አለን። የውጪ ጎብኚዎችም ሆኑ የአገር ውስጥ ዜጎች በእነዚህ ልዩ ስፍራዎች ላይ በሚካሄደው ደማቅ ስነስርዓት የሚከበረውን በአል እንዲታደሙ የምናበረታታው ለዚህ ነው። በተለይ የውጪ ዜጎች መስህቦቹን እያዩና በፌስቲቫሉ እየተዝናኑ ጥሩ ቆይታ እንዲኖራቸው እንደ ሁልጊዜውም ዘንድሮም እየሰራን ነው።
ጥምቀትን በጎንደር ከማክበር ባሻገር በዚያው የሚገኘውን የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ቱሪስቶች እንዲጎበኙ፣ የዱር እንስሳትን እንዲመለከቱና ልዩ መስህብ የሆነውን የተፈጥሮ መልከአምድር እንዲያዩ እያስተዋወቅን እንገኛለን። በባህርዳርም ሆነ በጎርጎራ በኩል እግረ መንገዳቸውን ጣና ሃይቅንና ልዩ ልዩ የተፈጥሮ ሃብቶችን እንዲጎበኙም በመርሃ ግብሩ ውስጥ አካተናል።
በዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ጋር በጋራ ይሰራል። ባሳለፍነው ዓመት ጎንደር የነበረው የፀጥታም ሆነ የኮቪድ ድብታ ውስጥም ሆኖ በነበረው “ጥምቀትን” በጎንደር ፕሮጀክት አየር መንገዱ በአንድ ቀን ብቻ 22 በረራዎችን ማድረግ ችሏል። ዘንድሮ ደግሞ ከዚያ በተሻለ ሁኔታ የተጓዡም ቁጥር ይጨምራል የሚል ግምትና ዝግጅት አድርገናል። ዋናው ምክንያታችን የሰላም ስምምነት መካሄዱና የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ መኖሩ ነው።
ዘንድሮ ከፍተኛ ቁጥር ይገኛል ብለን የምንጠብቀው በጎንደር፣ በዝዋይ፣ በአራንቡቲ በልዩ ሁኔታ ከሚከበረው የጥምቀት ባህል ባሻገር ቆይታን አራዝሞ የተፈጥሮ፣ የባህል፣ የታሪክና የቅርስ መስህቦችን መጎብኘት የሚቻልባቸው አጋጣሚዎች ስላሉ ጭምር ነው። ለዚህ ደግሞ ሰፊ የማስተዋወቅና አገልግሎት አቅራቢዎችም ራሳቸውን አዘጋጅተው እንግዶቻቸውን እንዲቀበሉ ስራዎች ተከናውነዋል። በአጠቃላይ ጎብኚዎች ቆይታቸውን የሚያራዝሙበት፣ የቱሪዝም ምርቶቸን የሚገዙበትና በኢኮኖሚው ላይ መነቃቃት የሚፈጠርበት ልዩ ክብረ በዓል እንዲሆን አርገን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን። በገና የታየውን ስኬት በጥምቀት ላይም ለመድገም እንሰራለን።
አዲስ ዘመን፦ የጥምቀት በዓልን በማስመልከት አገልግሎት ሰጪዎች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ያደርጋሉ የሚል ስጋት አለ። ይሄ ገና በላል ይበላ በተከበረ ወቅትም ይነሳ ነበር። ይህ እንዳይሆን ምን እየተሰራ ነው?
ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት፦ ልክ ነው። አገራችን ውድና የተጋነነ የቱሪዝም መዳረሻ እንዳትሆን ዋጋ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ከሆነ ማንም አይፈልገንም። እዚህ አጠገባችን ያሉት ጎረቤቶቻችን ኬኒያ፣ ጅቡቲ ያሉትን የአገልግሎት ክፍያዎች ስናይ በጣም ዝቅተኛ ነው። ስለዚህ ይህንን ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል። ጎብኚዎች አንዴ ብቻ አይመጡም። በየጊዜው ነው የሚመጡት። ስለዚህ ደረጃ አስቀምጦ በዚያ መሰረት ፍትሃዊና ቱሪስቱን የማያርቅ ዋጋ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ሲቻል ነገ ቱሪስቱ ተመልሶ እንዲመጣና ሌሎችንም እንዲያስተዋውቅ ስለሚያደርግ በዚህ አግባብ ማየት ያስፈልጋል። ዋጋ የምንቆልል ከሆነ ግን ተመልሶ እንዳይመጣና ሌሎች አማራጮችን እንዲያይ አንደሚያስገድደው መታወቅ አለበት። ዘንድሮም ይህ እንዳይፈጠር በማስተማርና አንዳንዴም በመቆጣጠር ጭምር ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን። ገናን በላል ይበላ ክብረ በዓል ተሞክሮም ይህንኑ ነው የሚያሳየን።
አዲስ ዘመን፦ በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ እድሉን ልስጥዎት?
ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት፦ ቱሪዝም ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ በጣም ከፍተኛ የሆነ አቅም አላት። በባህል፣ በተፈጥሮ፣ በታሪክ በአርኪዎሎጂ ጨምሮ ሁሉንም አይነት የቱሪዝም አማራጮች የያዘች አገር ነች። ስለዚህ ያለንን አቅም አውቀን አውጥተን በማስተዋወቅና በመሸጥ መጠቀም ይኖርብናል። የሚያስደንቅ ታሪክ፣ የሚያስደንቁ መስህቦች አሉን። እነዚህን ግን ዓለም ሊያውቃቸው ይገባል። እኛም ማወቅ ይኖርብናል።
እነዚህን መስቦች ዓለም ሊያውቃቸው የሚችለው እኛ ካወቅን በኋላ ነው። አውቀን፣ ጠብቀን፣ ተንከባክበን ማቆየትን እንደ ዋና ጉዳይ መውሰድ ይኖርብናል። ይህንን ለልጆቻችን ማሳወቅ አለብን። “የማያቁት አገር አይናፍቅም” እንደሚባለው የማየት፣ የማወቅ፣ የመረዳትና ያንንም የመጠበቅ ባህል ሊኖረን ይገባል የሚል መልእክት አለኝ።
መጎብኘት ባህላችን ሊሆን ይገባል። ክልሎችም ያላቸውን አቅም ተጠቅመው በዚህ ላይ መስራት አለባቸው እላለሁ። ይህ ከሆነ አገራችን ከቱሪዝም ምናልባት ትላልቅ ከሆኑ ዘርፎች በተሻለ ገቢ ልታገኝበት የምትችልበት ዘርፍ እንደሚሆን አያጠራጥርም። በመጨረሻም እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሰን ለማለት እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ለትብብርዎ እናመሰግናለን!!
ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት፦ እኔም አመሰግናለሁ!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥር 7 ቀን 2015 ዓ.ም