አዲስ ዘመን ድሮ እንዴትና ምን ይመስል ነበር? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በዛሬው የአዲስ ዘመን ድሮ አምዳችን ትኩረታችንን በ60ዎቹና በ70ዎቹ በጋዜጣው የወጡ ዜናዎች ላይ አድርጓል። አንዳንዶቹ ፈገግታን የሚያጭሩ ቢሆኑም ጋዜጣው ምን ያህል ለማህበረሰቡ ቅርብ እንደነበረም የሚያመላክቱ ናቸው። ሲጃራ ተደብቆ ያጨሰው ግለሰብ ለፍርድ መቅረብ፣ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ጥቂት አዋቂዎች በነበሩበት ዘመን ማንበብና መጻፍ ስለቻለችው አስገራሚዋ የአራት አመት ህጻን፣በሞስኮ አሎምፒክ ለሀገሩና ለአህጉሩ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ስላስገኘው ጀግና አትሌት፣ስለመጀመሪያው የሳታላይት ጣቢያ መከፈት እና ሰዎች ሲሞቱ ስለዳነው እንስራ እንዲሁም ከህብረተሰቡ ውስጥ ከሚላኩት ደብዳቤዎች መሃከል ሁለቱን ለትውስታ ያህል አካተን አቅርበንላችኋል።
ሲጃራ ተደብቆ ያጨሰው ተከሰሰ
ከሲጃራ ፋብሪካ ውስጥ ሰራተኛ ሆኖ ሳይፈቀድለት ከሽንት ቤት ውስጥ ተደብቆ ሲያጨስ የተገኘው በልሁ ተሰማ ተከሶ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀረበ።
ተከሳሹ የካቲት ፲፫ ቀን ፩፱፻፷፪ዓ.ም ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት በቀረበ ጊዜ ያለመስሪያ ቤቱ ፈቃድ 5 ሲጋራዎች ተደብቆ ማጨሱን አምኗል።
የቀረበበት የአቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያመለክተው ከሆነ ተከሳሹ ከአዲስ አበባ ትምባሆ ፋብሪካ ወስዷል የተባለው የሲጃራ ፓኬት በርከት ያለ መሆኑን ያመለክታል። ጉዳዩ እስኪጣራ ተከሳሹ በ፵፪ ብር ዋስትና እንዲለቀቅ ፍርድ ቤቱ አዟል። (ህዳር 9/1962ዓ.ም)
የአራት አመት ሕጻን ማንበብና መጻፍ ቻለች
ጅማ፣(ኢ-ዜ-አ) ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ በከፋ ክፍለ ሀገር በመካሄድ ላይ በሚገኘው በሦስተኛው ዙር የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ትምህርት በመቀበል እጅግ ፈጣንና ብሩህ አእምሮ ያላት የአራት አመት ልጅ ተገኘች።
በጅማ አውራጃ በቀርሳ ወረዳ በኩሳዬ ቡሬ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነዋሪ ከሆኑ ገበሬ ቤተሰብ የተወለደችው ራውዳ አባቦር የተባለችው ይህችው ሕጻን ፈጣንና ብሩህ አእምሮ ያላት መሆኑን የታወቀው በአከባቢው በተከፈተው የመሰረተ ትምህርት መስጪያ ጣቢያ በመሄድ ከእናቷ ጋር ተቀምጣ በመማር በሁለት ወር ውስጥ የፊደልን ዘር ለይታ መጻፍና ማንበብ በመቻሏ ነው። (ነሀሴ 7/1972ዓ.ም)
ሊቀመንበሩ ሳተላይት ጣቢያ መርቀው ከፈቱ
አዲስ አበባ፣(አ-ዜ-አ) ጓድ ሊቀመንበር መንግስቱ ኃ/ማርያም የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሊቀመንበር የሚንስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢና የአብዮታዊ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ከትላንት በስቲያ በመናገሻ አውራጃ በሱሉልታ ወረዳ በ14 ሚሊዮን 72 ሺህ ብር ወጪ የተሰራውን የሳተላይት የምድር መገናኛ ጣቢያ መርቀው ከፍተዋል። (ሰኔ 14/1972ዓ.ም)
ጎመንና ቅቤ ሰርቆ 18 ወር ታሰረ
በእምነት ከቤት እንዲያደርስ የተሰጠውን ጎመንና ቅቤ ለግል ጥቅሙ ያዋለው ዓለሙ ዋጭላ ተከሶ በ ፲፰ወር እስራት ተቀጣ።
ዓለሙ ታህሳስ ፳፪ ቀን ፩፱፻፷፩ዓ.ም ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ የእመት አሚና ጂቢሊን ቅቤና ጎመን ይዞ መጥፋቱንና በፖሊስ መያዙ ታውቋል። አዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ ቅጣቱንም ተቀብሏል። (ሰኔ 10/1972ዓ.ም)
ሰዎች ሲሞቱ እንስራው ዳነ
ቁጥሩ 647 የሆነ ሴይቼንቶ ኅዳር ፬ ቀን ፩፱፻፷፩ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ስድስት ሰዎች አሳፍሮ ከአዲስ አበባ ወደ አለም ጤና ሲጓዝ ከሞጆ አቅራቢያ ካለው ድልድይ በስተግራ በኩል የመገልበጥ አደጋ ደርሶበታል።
በዚሁ መኪና ውስጥ ተሳፍረው ከነበሩት ስድስት ሰዎች ውስጥ ሁለቱ ወዲያውኑ ሲሞቱ ሁለቱ ደግሞ ክፋኛ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። እንዲሁ ሁለቱ ቀላል መቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው የሸዋ ፖሊስ ትራፊክ ክፍል ገልጦአል።
በዚሁ አደጋ ወቅት የመኪናው ባለቤትና ሾፌሩ ያልተገኙ መሆናቸው ታውቋል። በመኪና ውስጥ ባሉት ሰዎች ላይ አደጋ ሲደርስ ተጭኖ በነበረው እንስራ ላይ ግን ምንም ጉዳት ያልደረሰበት ሆኖ መገኘቱን የትራፊክ ክፍሉ በድጋሚ አስረድቷል። (ህዳር 10/1962ዓ.ም)
በሞስኮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ለማግኘት የመጀመሪያዋ የአፍሪካ ሀገር ሆነች
በሶቪየት ህብረት ሞስኮ ከተማ በመካሄድ ላይ ባለው የ፳፪ኛው የኦሎምፒክ ውድድር የ፲ሺህ ፍጻሜ ባለፈው እሑድ ተደርጎ ጀግናው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር አንደኛ በመውጣት ለአብዮታዊት ኢትዮጵያና ለአፍሪካ አህጉርም ጭምር የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቷል።(ሀምሌ 22/1972ዓ.ም)
ከደብዳቤዎች
“ወንበሩ የኔ አይደለም”
‘ወንበሩ የኔ አይደለም ባለወንበሯን እዘዝ’ የሚሉ ቃላት በአሁኑ ጊዜ በየቡና ቤት ሰራተኞች ተዘውትረው ይነገራሉ።
ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ ያነሳሳኝ በ፲፩ -፲ -፸፪ ዓ/ም ከምሽቱ ሁለት ሰዓት መርካቶ ውስጥ በሚገኘው አዲስ ከተማ ቡና ቤት ውስጥ ቡና አዝዤ ቀርቦልኝ ስኳር በማነሱ አንዷን የቡና ቤቱ ሰራተኛ ስኳር እንድትጨምርልኝ ብጠይቃት ‘ወንበሩ የኔ አይደለም ባለ ወንበሯን እዘዝ’፣ የሚል መልስ ሰጠችኝ። እንግዳን ማስተናገድ ለድርጅቱ ዕድገት ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ በዚሁ አንጻር የሠራተኞችም ኑሮ ሊያድግ ስለሚችል ተባብሮ መስራት የሚሻል መሆኑ አይጠረጠርም። ይህ ካልሆነ ግን ድርጅቱ ብቻ ሳይሆን፣ በራስ ላይም ውድቀት ሊያስከትል ይችላልና ይታሰብበት።
ልሳነወርቅ አስፋው
ከፍተኛ 5 አዲስ አበባ
ሰኔ 15/1972ዓ.ም
ጥንቃቄ ይደረግ
ቅዳሜ ሰኔ ፳፰ ቀን ፩፱፻፸፪ዓ.ም ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ በአዲስ ከተማና በተክለሃይማኖት አከባቢ በጣለው ዝናብ በከፍተኛ ፫ ቀበሌ ፴፩ ክልል ውስጥ አንዳንድ አሮጌ ቤቶች በጎርፍ ተሞልተው ነበር። ነዋሪዎችም እቃዎቻቸውን ከጎርፍ ብልሽት ለማትረፍ ቢጥሩም ብዙ ዕቃዎች መበላሸታቸውን ተመልክቻለሁ።
በዚያ ቀበሌ በርከት ያሉ አሮጌ ቤቶች ስለአሉ አሁንም የነዋሪዎች ንብረት እንዳይበላሽ ጥንቃቄ ይደረግ።
ወታደር ተዘራ አስፋው
ነሀሴ 9/1971ዓ.ም
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 25 /2015