ብዙ ነገሮች “ድሮ ቀረ” ሆነዋል። “ድሮ ቀረ” የሚለው አባባል ለሁሉም ነገር ሊባል በሚችል መልኩ ጥቅም ላይ ሲውል መስማት ከመለመድ አልፎ ተሰልችቷል። ምግብ፣መጠጥ፣ ቁርጡ፣ ቂቤው፣ ጠላው ጠጁ… ዘፈን፣ ፍቅር፣ ምን የቀረ ነገር አለ? ሁሉም ድሮ ቀረ ሆኗል። በእርግጥም ነገሩ አባባል ብቻ አይደለም። መሬት ላይ ያለው እውነታ እንደዛው በመሆኑ ነው “ድሮ ቀረ” የሚለው አባባል የበዛው። የሚበላው፣ የሚጠጣው… ኑሮው እንደድሮው አይደለም። ሰው እንደድሮው እርስ በእርሱ አይተሳሰብም፣ አይተዛዘንም፣ አይደጋገፍም፣ አይዋደድም። የራስና የገንዘብ እንጂ እንደድሮው የሰውና የሀገር ፍቅር የለም። ዕውቀት፣ ጥበብ፣ ሥነ ምግባር፣ ዕምነት፣ ሞራል…በማደግ ፋንታ ከድሮው በእጅጉ እየቀነሰ መጥቷል።
ለዚህ ሁሉ ድሮን ናፋቂነት መንስኤው ደግሞ የአሁኑ ትውልድ ካለፈው ትውልድ በብዙ ነገር ወደኋላ መቅረቱ ነው። በሀገራችን በብዙ ነገሮች ያለው የዕድገት ጉዞ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ካለው፤ ከራሱ ከዕድገት ተፈጥሯዊ ሕግም በተቃራኒው በመጓዙ ነው። እናም ዕድገታችን፣ ለውጣችን፣ ኑሯችን ሁሉ “ሁሉም ድሮ ቀረ” እያልን ድሯችንን እንድንናፍቅ የሚያደርግ ሆኗል።
በዚህ ረገድ ዓይነተኛ ማሳያዎች የሚሆኑን ደግሞ በአሁኑ ሰዓት በተለይም ከዘጠናዎቹ መጨረሻና ከሁለት ሺዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ባለፉት አሥር ዓመታት በሀገራችን እየወጡ የሚገኙ የሙዚቃ ሥራዎች ናቸው። እነኚህ “ሙዚቃዎች” ዜማቸው የሙዚቃ ጥበብ ከተሰጣቸው ዜመኛ አዕምሮዎች ሳይሆን ምንነታቸውና ማንነታቸው ከማይታወቁ የኢንተርኔት ድረ ገጾች የሚቀዳ፣ “ሙዚቀኛው” ካልሆነ በቀር የሙዚቃ ምታቸው እንደሳሙና ከአንድ ምንጭ ተጠፍጥፎ የሚሠራ ተመሳሳይና አሰልች የሆኑ እጅጉን የወረዱ በመሆናቸው ነው። ግጥሞቻቸውና የግጥሞቻቸው ይዘት እጅግ ግልብ፣ መናኛና አንዳች ርባና ያለው መልዕክት የማያስተላልፉ፤ ለረጅም ጊዜያት በአድማጭ ጆሮ ውስጥ የማይቆዩ፣ ገና ከመውጣታቸው የሚያልፍባቸውና እንኳንስ ትውልድን ቀናትን የማይሻገሩ ባዶ እንቶፈንቶ ጩኸቶች ናቸው።
ይህንን በሚመለከት በብዙዎች ዘንድ “የወግ ጠበብት” በመባል የሚታወቁት አንጋፋው ወግ ጸሐፊ መስፍን ሀብተማርያም ዘፈኖቻችንና ዘፋኞቻችንን በሚመለከት አንድ መጣጥፋቸው ውስጥ ከዛሬ 32 ዓመት በፊት እንዲህ ብለው ጽፈው ነበር። “የመሣሪያዎቹን ድምጽ ለይቶ እንዳይሰማ የሚያደርግ መሣሪያ ቢኖር ኖሮ ዜማው ከነግጥሙ የዓረፍተ ነገር ንባብ ሊመስል ይችላል። ያውም በተለያየ መልክ የቁጣ፣ የልመና፣ የዛቻና የምሬት ዓይነት ድምፀት ያለው” የሚሉት ደራሲ መስፍን ሀብተማርያም በጊዜው አንዳንድ ዘፋኞች ለዘፈን በማይሆን ዜማ አድማጭን ከማዝናናት ይልቅ ያሳዝኑ እንደነበር ጽፈዋል። ያኔ በእነሱ ዘመን የነበሩ ዘፋኞች እንዲያ ከነበሩ ዛሬ ደግሞ የኔ ዘመን ወጣቶች የሚዘፍኗቸውን ዘፈኖች ቢሰሙ መስፍን ሀብተማርያም ምን ይሉ ነበር?
ግጥምን በሚመለከትም “የግጥሙ ጉዳይ ካሁኑ ካልታሰበበት ፈረንጅኛ አይሉት ኢትዮጵያዊኛ መላ ቅጡ የጠፋ ሁኔታ ላይ እንዳይደርስ እሰጋለሁ(ለአፅንዖት የተስተካከለ)። እንደሚታወቀው ዘመነኛ ከሚባሉ አነጋገሮች መካከል ጥቂቶቹን እንጥቀስ ብንል ʻአለ አይደል፤ ማውረድ፤ መቀላጠፍʼ የሚሉትን እናገኛለን። አሁን እነዚህ በጊታር ታጅበው ብቅ ቢሉ የማን ያለህ ሊባል ነው?!” ብለው ነበር ታዋቂው የወግ ጸሐፊ መስፍን ሀብተማርያም። እነሆ ዛሬን ትናንትና ላይ ሆነው የተመለከቱት አርቆ አስተዋዩ የጥበብ ሰው እንደሰጉት ʻአለ አይደል፤ ማውረድ፤ መቀላጠፍʼ ብቻ ሳይሆን “ረገጣ፣ ፈታ ፈታ፣ ሊፒስቲካ ቻፕስቲካ፣ እንች እንካ እንች እንካ፣ በሚለው በሚለው፣ ልባል ፋራው…” እየተባለ ይዘፈንልናል።
ስለሆነም እኔና አብዛኞቹ የዘመን ተጋሪዎቼ በዘመናችን በየቀኑ በርካታ “ሙዚቃዎች” እየወጡልን ቢሆንም የምናዳምጠው ሙዚቃ አጥተናል። እናም “ሙዚቃ ድሮ ቀረ” በማለት የምናዳምጠው ሙዚቃ ፍለጋ ወደአባቶቻችን ዘመን ለመመለስ ተገደናል። በዚያም እድሜ ለእነርሱ ዘመን ዜማቸው አካልን አልፎ ነፍስን የሚያረፈርፍ፣ ግጥማቸው ተመንዝሮ የማያልቅ ጥልቅ መልዕክትን የተሸከመ፣ ተደምጠው የማይጠገቡ ሁሌም አዲስ የሆኑ ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዎችን አግኝተን የሙዚቃ ጥማችንን እንቆርጣለን።
እናም የሀገራችን ሙዚቃ በማደግና የበለጠ በመሻሻል ፋንታ እየቀነሰና እየተበላሸ መጥቶ በእኛ ዘመን እጅጉን የወረደ ደረጃ ላይ በመድረሱ በራሳችን ዘመን ሙዚቃ ለመደሰት ባንታደልም ወደኋላ ተመልሰን ከትውልድ ቀዳሚዎቻችን የላቀውን የሙዚቃ ጥበብ አግኝተን መደሰት መቻላችን ዕድለኝነት ነው። የእኛን ዘመን “ሙዚቃዎች” ለሚወርሰው፣ እርሱም እንደ እኛ ዘመን ተሻጋሪ ምርጥ ሙዚቃዎችን መሥራት ባይችል እንኳን “ሙዚቃ ድሮ ቀረ” ብሎ ወደኋላ ተመልሶ የበቃ የሙዚቃ ጥበብን ማግኘት ለማይችለው ይብላኝ ለቀጣዩ ትውልድ። ከእኛው ዘመን ለእኛ የሚመጥን ሙዚቃ ለማግኘት ባንታደልም “ድሮ ቀረ” ብለን ከዘመናችን ያላገኘነውን በድሮ መዝገብ ውስጥ የምንፈልገውን ማግኘት ችለናልና እኛማ ዕድለኞች ነን!
በመሆኑም ታላቁ የወግ ጸሐፊ መስፍን ሀብተማርያም እንዳሉት ፈረንጅኛ ይሁን አገርኛ የት መጤያቸውን የማናውቃቸው ቃላት በጊታር ታጅበው ዘፈን ሆነው ሲመጡ ለቀጣዩ ትውልድ ስንል “የማን ያለህ?” ማለት ይጠበቅብናል። ነገር ግን ግራ ተጋብተው ግራ የሚያጋቡት ዘፋኞቻችን ወይም በሽታቸው ተጋብቶብን እኛም እንደ እነርሱ ግራ ገብቶን ፈዘናል፤ ደንዝዘናል፤ ዝም ብለናል። ትርጉማቸውን በማናውቃቸው እንግዳ ቃላት የተሞላው ግራ አጋቢው ግጥማቸውና ዘፈናቸው ተመችቶናል ማለት ነው። ካልሆነማ የሆነ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ፈልገን “አቤት” ማለት ነበረብን እኮ።
በእርግጥ ሙዚቃን መግደል መብት ከተባለ ዘፋኞቻችን የፈለጉትን መዝፈን መብታቸው ቢሆንም፤ እኛም ከፈለግን እነርሱ የሚዘፍኑልን መስማት ካልፈለግን ደግሞ ከሚዘፍኑብን ጋር ከመስማማት በቀር መዝፈን አትችሉም ማለት አንችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ ሁላችንንም የሚመለከት፣ የሀገራችንን ኪነ ጥበብ የሚመለከት የጋራችን ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን እንደ ደራሲ መስፍን ሀብተማርያም “መላ ቅጡ የጠፋ ሁኔታ ላይ ሳይደርስ ካሁኑ ይታሰብበት” የሚል እውነተኛ የጥበብ ሞግዚት ያስፈልገናል።
እኛ ግን ዘፈን እና ዘፋኝ ብቻ አይደለም ያጣነው፣ ዘፈንና የዘፈን ጥበብ መላ ቅጡን ሲያጣ፣ ሙዚቃ የስሜት ማነቃቂያ፣ የመንፈስ ማደሻ፣ የልብ ደስታ፣ የመንፈስ እርካታ መሆኑ ቀርቶ፣ ማንነቱን አጥቶ፣ የቀደመ ክብሩን ተገፎ፣ ተዋርዶ እርቃኑን አደባባይ ሲወጣ ጥበብን ከሚያረክሱ ጠበኞች የሚጠብቁ፣ ለጥበብ ክብር የሚሟገቱ ጥበበኞችም አጥተናል። ጥበብ ስትዋረድ የሚቆጩ፣ ስለ ክብሯ የሚጨነቁ፣ ስለ እርሷ ከፍታ ድምጻቸውን በአደባባይ ከፍ አድርገው የሚያሰሙ እንደነ መስፍን ሀብተማርያም ዓይነት የጥበብ ዘበኞች በእኛ ዘመን የሉም። ካሉም ድምጻቸውን አላሰሙንም ወይም እኛ አልሰማናቸውም።
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 /2015