ምንም አይነት አስተሳሰብ ያለው ግለሰብ ወይም ቡድን የፖለቲካ ፍላጎት ቢኖረውም ባይኖረውም የተለያዩ አይነት የመገናኛ ዘዴዎችን ተጠቅሞ በሚያሰራጫቸው ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎች ሳቢያ በሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች እና ግጭቶች በቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ዋነኛ ሰለባዎቹ ንጹሐን ዜጎች ናቸው፡፡
ሀሰተኛ መረጃን በማሰራጨት ዜጎችን ማታለል፣ ማደናገርና ለጉዳት ማጋለጥ፣ የህብረተሰቡን የአንድነት፣ የወንድማማችነትና የመቻቻል ባህልን ማዳከም፣ የብሔርና የሃይማኖት ግጭቶች እንዲፈጠሩ ፅንፈኛ አጀንዳዎችን ማቀንቀን ማህበረሰብ ይቅር የማይለው ወንጀል እንጂ በየትኛውም መመዘኛ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተደርጎ ሊታሰብ አይችልም፡፡
የተዛባ እና ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ሕዝብን እርስ በእርስ ማጋጨት ወይም በመንግሥትና በሕዝብ መካከል አለመግባባትን እንዲፈጠር ማድረግ ሀገር ወዳድነትን ወይም ለሕዝብ ጥቅም መስራት ሊሆን እንደማይችል ግልፅ ነው። ለየትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ለግጭት ማነሳሳት የጥፋት እንጂ የመፍትሄ መንገድ አይሆንም።
በመሆኑም ሀሰተኛና የተዛባ መረጃ የሚያሰራጩ ግለሰቦችንም ሆነ ቡድኖችን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማድረግ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት የመከላከልና ሀገርን መታደግ ከመሆኑ ባሻገር የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከሚደረጉት እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ መንግሥታዊ ግዴታና ተግባር ነው፡፡
ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ሽፋን አድርገው ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ሕዝብን የሚያደናግሩና የተለየ ዓላማ ለማሳካት ታች ላይ የሚሉ ሀሰተኞችን አደብ ለማስያዝ እንደ ሕዝብ ውሸትን ያለማዳመጥ መፍትሄ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።
አንድ ሃይማኖት በሌላ ሃይማኖት ላይ እንዲነሳ፤ በብሔርና ብሔር መካከል ግጭት በመፍጠር የማህበረሰብን አብሮነት የሚያጠለሹ የጥላቻ ንግግሮችን የሚናገሩ፤ በተዛባ መረጃ ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያስነሱ፤ መንግስትና ሕዝብ እንዳይተማመኑ የሚያደርጉትስ የመናገር ነፃነታቸውን ተጠቀመው ነው? የመናገር እና የሚዲያ ነፃነትስ እስከምን ድረስ ነው? ስንል የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመረጃ ነፃነት ዳይሬክተር አቶ ማናዬ አለሙን፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ አቶ ሰለሞን ጎሹን እና የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ፍሬዘር እጅጉን አነጋግረናል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመረጃ ነፃነት ዳይሬክተር አቶ ማናዬ አለሙ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት መሰረቱ ህገ መንግስቱ ነው ይላሉ። የህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 ማንኛውም ሰው የፈለገውን ሀሳብ የማዳመጥ፤ የፈለገውን ሀሳብ የመያዝ፤ የፈለገውን ሀሳብ የማስተላለፈ መብቱ በህገ መንግስቱ ተቀምጧል። በዛው ልክ መብቱ ፍፁም መብት ተደርጎ ያልተቀመጠ ሲሆን ሁልጊዜ ከመብቱ እኩል ታሳቢ የሚደረጉ ነገሮች ይኖራሉ። ታሳቢ ከሚደረጉ ጉዳዮች ውስጥ የሕዝብ መብት፤ የወጣቶች ደህንነት፤ የሀገር ደህንነት፤ የግለሰቦች ክብር ወይም ግላዊነትን ታሳቢ በማድረግ ገደቦች ይጣላሉ።
ማንኛውም ሰው ሀሳቡን መግለፅ ይችላል ሲባል እንደፈለገ ያወራል ማለት አይደለም፡፡ በህግ አግባብ የተጣሉ ገደቦችን ጠብቆ በዛ መልኩ የሚናገረውን ሀሳብ የሚገልፅበት ስርዓት ነው። በህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 ንዑስ አንቀጽ 6 ላይ ገደቦቹ በግልፅ ተቀምጠዋል። የወጣቶችን ደህንነት የሚነካ፤ መልካም አስተዳደር ላይ ተጽእኖ የሚፈጠር፤ የሀገር ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥል፤ የግለሰቦችን ክብር በሚነካ መልኩ ማንቋሸሽ አይቻልም የሚሉ ገደቦች ተቀምጧል። በእነዚህም መስረት የሀሰተኛ መረጃና ጥላቻ ንግግርን ለመከላከል አዋጅ ቁጥር 11/85 ታውጇል፡፡
ማንነትን፤ ብሔርን፤ ቋንቋን መሰረት አድርጎ በሌሎች ዘንድ በጥላቻና በጥርጣሬ እንዲታይ ማድረግ ወንጀል መሆኑን ያመለክታል። ሌላው ሀሰተኛ መረጃን ሀሰተኛ መሆኑን እያወቀ ሶሰተኛ ወገንን ለመጉዳት በማሰብ ሀሰተኛ መረጃን በማሰራጨት ላይ መገኘት ወንጀል ነው። ለዚህም ለማስተማርና ፍትህ ለማሰጠትም የተለያዩ ተቋማት ሀላፊነቱን ወስደዋል ይላሉ።
የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ አቶ ሰለሞን ጎሹ በበኩላቸው ማንኛውም ሰው ሰው በመሆኑ የተሰጠው መሰረታዊ መብት አለው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ግዴታ አለበት። ሀሳብን በነፃነት የመግልፅ መብት የግለሰቦች ነፃነት ይሆንና በተቋማዊ አደረጃጀታቸው በተቋማዊ ይዞታቸው የመገናኛ ብዙሃን ደግሞ ተቋማዊ የሆነውን ነፃነታቸውን የሚመለክት ነው። እንደ ሰው እንደ ጋዜጠኛ ሲሰራ በግለሰብ ደረጃ የሚሰጠው ሀሳብን የመግለፅ መብት በጣም ሰፊ ሲሆን፤ የፕሬስ ነፃነት ግን ፕሬስ ባለው ተቋማዊ ይዘቱ መሰረት ጥበቃ አለው። ይህም ከህገ መንግስቱ ጀምሮ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ስምምነቶችና የተለያዩ የህግ ማእቀፎች የሰጣቸው ነፃነቶች ላይ የተቀመጠ ነው።
ግለሰቦች ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ መብታቸውን በሙሉ እንዲጠቀሙ የተቋማት አደረጃጀት ያስፈልጋል። አንድ መረጃ ለሁሉም እንዲዳረስ መገናኛ ብዙሃን ያስፈልጋሉ። ይህ ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ብዙሃኑ ጋር እንደመድረሳቸው ገደብ ቢኖራቸውም፤ ለፕሬስ ነፃነት ሰፊ የሆነ ጥበቃና ሰፊ የሆነ መብት እንዲሰጠው ሆኗል።
መገናኛ ብዙሃን ነፃ በመሆናቸው የተነሳ መረጃዎችን የመቀበል፣ መረጃዎችን የማድረስ፣ ሀሳብን ለሌሎች የመካፈል ደግሞም ከሌሎች የመቀበል መብት እና ሃላፊነት አለባቸው፡፡ በዚህ ሂደት ሀሳብን መያዝ መቀበልና ማስተላለፍ በተቋማዊ ቅርፁ ጥበቃ እየተደረገለት የሚሰራ ሲሆን የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት ይባላል።
የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ቢኖራቸውም ነፃነታቸው እስከምን ደረስ ነው? ሲባል መገናኛ ብዙሃን ገደብ አለባቸው። ከላይ እንዳልነው ከተቋማዊ ጥበቃ አንፃር የተሻሉ ጥበቃዎች ሊሰጣቸው ይችላል እንጂ፤ ሀሳብን በነፃነት መስጠት በራሱ ገደብ አለው።
ገደቦቹም በዓለም አቀፍ ህግ መሰረትም ሆነ ኢትዮጵያ እነዛን የዓለም አቀፍ ህጎች ተቀብላ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 ንዑስ አንቀፅ 6 ላይ ምን ሲሆን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ገደብ ይኖረዋል? የሚለውን ለመመልከት ከሌሎች ተነፃፃሪ መብቶች አንፃር ጉዳዩ ይመረመራል። ለነፃነትም ገደብ ሲቀመጥ እንዲሁ አይደለም፡፡ ማንም ዝም ብሎ ገደብ ሊያበጅለት አይችልም። ህግ የማውጣት ስልጣን የተሰጠው አግባብነት ያለው ኃይል በሚያወጣቸው ህጎች አማካኝነት ገደብ ሊደረግ ይችላል። ሁለተኛው እነዛ ገደቦች የሚደረጉት ከተነፃፃሪ መብት ጋር ታይተው ነው።
እዚህ ላይ መብቱ የሚገደበው የሌላውን መብት ለመጠበቅ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ገደቡን የወቅቱ መንግስት ወይም ጉዳዩን ተፈፃሚ የሚያደርገው አካል ተቀባይነት ያለው መሆን አለበት፡፡ እዚህ ላይ በዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ተቀባይነት ያለው መስፈርት መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
በመስፈርትነት የተቀመጡ ገደቦች ጥቅም ላይ ይውላሉ። በሀገራችን የህግ አግባብ የወጣቶችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል፤ የጦርነት ፕሮፖጋንዳን ለመጠበቅ ሲባል እና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ታሳቢ በማድረግ ገደብ ይደረጋል ይላሉ።
የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል መምህር ፍሬዘር እጅጉ በበኩላቸው በሀገራችን የመረጃ ነፃነትንም ሆነ የመገናኛ ብዙሃን ነፃነትን የሚጠብቅ አዋጅ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 ላይ ተቀምጧል። እዚህ አንቀፅ ላይ ዋናው መሰረታዊ ነገር አንድ ግለሰብ ሀሳቡን በማንኛውም መገናኛ ብዙሃን ተጠቅሞ ሀሳቡን መግለፅ መብቱ እንደሆነ ተቀምጧል። መገናኛ ብዙሃንም እንደተቋም ሀሳብን የማንሸራሸር መብታቸው በግልፅ ተቀምጧል።
ሀሳብን የመግለፅ መብት ሰብዓዊ መብት ከመሆኑ አንፃር ገደብ ሊጣልበት ባይገባም ለሀገር ደህንነት ለሕዝብ ሰላም ሲባል በህገ መንግስት ላይ ገደብ ሊጣልበት እንደሚችልም ተቀምጧል። ሀሳብን የመግለፅ መብት ገደብ ሊጣልበት እንደሚችል መቀመጡን ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት በሀገሪቱ የወጡ አዋጆች ላይ የተለያዩ ገደቦች ሰፍረዋል። ለአብነት ያህል የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል በወጣው አዋጅ 1185/2012 ላይ በግልፅ አንድን ግለሰብ ወይም ቡድን በብሔሩ፣ በፆታ፣ በሃይማኖት፣ በአካል ጎዳኝነት ወይም በመገለጫዎቹ ጥላቻን የሚቀሰቅሱ መድሎን ሊያመጡ የሚችሉ ንግግሮች ገደብ የተጣለባቸው ናቸው፡፡ ይህንን ጉዳት ሲፈፅሙ የተገኙ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ቅጣት ተጥሎባቸዋል።
ሀገሪቱ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንን ለማስተዳደርና ለመምራት የተቋቋመ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የተባለ ተቋም አለ። ይህ ባለስልጣን በሀገሪቱ ያሉ መገናኛ ብዙሃን በተሻለ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ መደላድል የሚፈጥር እንዲሁም በህግ የተቀመጡ ጉዳዮችን አልፈው ሲገኙ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን እንደሚወስድ በአዋጁ ስልጣን ተሰጥቶታል።
ሀገሪቱ በጦርነት ወቅት በነበረችበት ጊዜ የህግ ማእቀፍ ተጥሷል ተብሎ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ሲወሰድባቸው የታየ ሲሆን፤ በቅርብ ጊዜ ግን የጥላቻ ንግግርን በመናገር ሕዝብን በማነሳሳት የተጠየቁ አካላት እንዲህ ነው የሚባሉ እርምጃዎች ሲወሰድባቸው አይታይም።
ይህ ግን ሀሰተኛ መረጃም ሆነ የጥላቻ ንግግርን በመደበኛ መገናኛ ብዙሃንም ሆነ በማህበራዊ ድህረ ገጾች የሚነገሩ የጥላቻ ንግግሮች እንዳሉ እየታወቀ፤ ተጠያቂነት ኖሮ ቅጣት ተሰጥቷቸው ሌሎች ትምህርት እንዲወስዱ ሲደረግ አለመታየቱ ጉዳዩ እንዳይቀንስ ያደረገው ይመሰለኛል።
ለዚህ ችግር መፍትሄ ይሆናል ያሉትን አቶ ማናዬ አለሙ ሲጠቅሱ፤ ሀገሪቱ ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት በሬ ወለደ አይነት ዜናዎችን መስማት የጥላቻ ንግግሮችን ማየት የተለመደ ነው። ለዚህም ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃኑ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። ዋናዎቹ ሚዲያዎችም ግን ከዚህ የፀዱ አለመሆናቸው ይታያል።
ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንን የተጠያቂነት ሁኔታ እጅግ አናሳ ነው። የት እንዳሉ አይታወቅም፤ ስለዚህም ማህበራዊ ሚዲያውን የማዘጋት ስራ የተሻለ አማራጭ በመሆኑ መንግስት ከልክ በላይ ማህበራዊ ሚዲያዎችን የማዘጋት ሰራ ይሰራል። ከዚህ ይልቅ ዋናዎች መገናኛ ብዙሃን ከእነዚህ ተግባራት የፀዱ እንዲሆኑ ማድረግ፤ መንግስት ለመረጃ ክፍት በመሆን የሚፈበረኩ ሀሰተኛ ዜናዎች እንዳይኖሩ ማስቻል ጉዳዩን ቀላል ያደርገዋል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
አዋጁም ተጠያቂነቱም በግልፅ ተቀምጦ ሲፈለግ ተግባራዊ የሚደረግ ሳይፈልግ የሚተው መሆን አይገባውም፤ በወጥነት ማስተማሪያ የሚሆን ቅጣት መተላለፍ አለበት። በተጨማሪ የማይፈፀም ህግ መውጣት የለበትም አዋጁ በአላማ በመውጣቱ አላማውን ማስፈፀም የግድ ነው። ይህም መንግስት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው ብለዋል።
አቶ ሰለሞን ጎሹ በበኩላቸው፤ የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት ገደቦች እንዳይጣሱ፤ የጥላቻ ንግግሮች እንዳይሰራጩ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የቅድመ መከላከል ሀላፊነት ተሰጥቷል። የጥላቻ ንግግርን ከስሩ ለማድረቅ ለእነዚህ ሁለት ተቋማት የማስተማር ስራ እንዲሰራ ተደርጓል። አቃቤ ህግ ደግሞ ማንኛውንም የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትሉ ጉዳዮችን ይከታተላል፤ ማንንም ሳያስፈቅድ ይከሳል። ፍትህ ሚኒስቴርም የመጨረሻ ውሳኔውን የሚያደርግ አካል ነው። ስለዚህ ተጠያቂነቱ እንዳለ ሆኖ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ይህንን አድርገው የተገኙ ሰዎች አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ይወሰድባቸዋል።
መፍትሄው ጉዳዩ የመብት ጉዳይ እንደመሆኑ ተጠያቂነትን ለማንሳት ገደቦቹ እስከምን ድረስ እንደሆኑ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ቅጣት ቢኖርም ቅጣት የተሰጠበትን አግባብ ህብረተሰቡ እንዲያውቅ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
መምህር ፍሬዘር እጅጉ የመገናኛ ብዙሃን በአጠቃላይ ከተለያየ ተፅእኖ ራሳቸውን ገለልተኛ አድርገው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል። መገናኛ ብዙሃን ተቋማዊ ነፃነት ሊኖራቸው ይገባል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን በልዩ ሁኔታ እንዲፈቀድላቸው ተደርጓል። እነዚህ ተቋማት አሰራራቸው በምን መልኩ እንደሚቃኝ ባይታወቅም፤ በአዋጁ ላይ የተቀመጠው ግን ማንኛውም ሃይማኖት ተኮር ፕሮግራም በሃይማኖቶች መካከል ግጭት ማነሳሳት የሌሎችን ሃይማኖቶች ወይም እምነት ማንኳሰስ በሌሎች ሃይማኖቶች መካከል አለመቻቻል እንዲፈጠር ማድረግ የለበትም።
ይህን ገደብ በመከተል የሃይማኖቶች ልዩነት ላይ ግጭት እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ሊወሰድ ይገባል። ህግ ላይም በተቀመጠው ልክ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን በመፍጠር ሃይማኖታዊ መገናኛ ብዙሃን በህግና በስርዓት እንዲመሩ ማድረግ ተገቢ ነው።
ሌላው መፍትሄ ማህበረሰቡ የመገናኛ ብዙሃን እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ይህ ማለት በማንኛውም መገናኛ ብዙሃን የተላለፉ መረጃዎችን በተለያዩ መመዘኛዎች ውስጥ ከቶ ማህበረሰቡ በተገቢው መልኩ በግንዛቤ በመመራት ከግጭት የፀዳ ማህበረሰብ እንዲኖር መደረግ አለበት።
ይህም ህፃናት ከልጅነታቸው ጀምሮ የመገናኛ ብዙሃን እውቀት ኖሯቸው፤ በእውቀት የተመራ ማህበረሰብ መረጃን መዝኖ አንጥሮ እንዲቀበልና እንደ ማህበረሰብ እሴቱን ጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ ተገቢ ነው ሲሉ የመፍትሄ ሀሳብ ያሉትን አጋርተዋል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 18 /2015