ረጃጅም ጉዞ በትራንስፓርት ውስጥ መጓዝ አሰልቺ ነው። ጉዞው ምቾት ባለው ሁኔታ ካልሆነ ደግሞ ይበልጥ አድካሚ ይሆናል። የመስታወት ጸሀይ፣ የመኪና ውስጥ ሙቀት አልፎ አልፎም ቢሆን የሚያጋጥም ግሳት ሀገር አቋራጭ መስመርን እንዳልመርጠው ያደርገኛል። ግን ደግሞ ወግ አዋቂ፣ ታሪክ ተራኪ ነገሮችን አጣፍጦ ነጋሪ ሰው ከጎን ካለ መንገዱ ‹ከምኔው!› እንድንል ያደርገናል። እናም እኔ ረጅሙን መንገድ ስጀምር በቅድሚያ የማስበው ጥሩ አጫዋች ከአጠገቤ እንዲኖር ነው። የያዝነውን ቆሎ በጋራ ቆርጠም፣ ውሃውንም ጎንጨት እያደረግን አብረን እንድንጓዝ ነው። ይሄው ምኞቴ ተሳክቶ የጀመርኩትን ረጅም መስመር በጨዋታ ተወጣሁት።
የጨዋታ ለዛ አዋቂ ናቸው ከጎኔ ያሉት አዛውንት። መቼም ዘንድሮ የሚወራ፣ የሚነሳ የሚወድቅ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ አይጠፋምና የፖለቲካ ወጋቸውን ጀመሩ። ጨዋታቸው የቀድሞውን ከአሁኑ እያዋሀዱ ደግሞ ለዛ ባለው ቋንቋቸው እያዋዙና ፈገግ እያሉ በመሆኑ ሙሉ ጆሮዬን አሳልፌ ሰጥቻለሁ። ደግሞ የራሳቸውን ብቻ አይደለም የሚያወሩት ተሳታፊ እንድሆንም የድሮውን ባይሆን የአሁኑን ታስታውሻለሽ አይደል እያሉ ጥያቄ ይጠይቁኛል ። የማውቀውን እመልሳለሁ፤ ግን ደግሞ አንዳንዱን የይለፈኝ አይነት ተወት አደርጋለሁ። እሳቸውም ይሄ የገባቸው ይመስላል ‹‹ሳታውቂው ቀርተሽ አይደለም! ነገሩ የዘንድሮ ሰዎች ነገር ቶሎ ትረሳላችሁ፤ ረስተሽው ካልሆነ ወይም ተወት አድርገሽ›› ይሉና ይቀጥላሉ። የራሳቸውን ጨዋታ የተዘለለውም መለስ ብለው እያስታወሱኝ ‹‹ይሄን አታውቂም?›› ይሉኛል።
‹‹የጊዜው ሰው ሁሉ ነገር አዲስ ይሆንበታል። ወይ አውቆ አያውቅ፤ ወይ ለማወቅ አይጠይቅ ብቻ ዝም ብሎ ታሪክ ማጥፋት፣ ክፋት ፣ ተንኮል፣ ልብላ ባይ ብቻ ምን…›› አሉና ቀጠሉ። በብዙ ሀገራዊ ጉዳዮች የተበሳጩ ይመስላሉ። ‹‹አሁን በሀገራችን አንዴ በብሄር፣ በጎሳ፣ በሀይማኖት እያልን፤ አንዴ በክልል ሌላ ጊዜ ሌላውን ነገር እያነሳን እንዲህ መጨካከን ነበረብን?›› ሲሉ ጠየቁ። መልስ አልሰጠሁም። ማለቴ በአንደበቴ እንጂ ጭንቅላቴን ነቅነቅ በማድረግ መመለስ አላቆምኩም።
‹‹አንድ ጨዋታ ላጫውትሽ›› ብለው ጉሮሯቸውን ለንግግር እንዲመቻቸው ሳል ሳል አደረጉ። ‹‹ታሪኩን በደንብ አድምጪ›› ሲሉም ትኩረት እንድሰጠው ጋበዙኝ። ፊቴን ወደፊታቸው መለስ ከማድረጌ ትረካውን ቀጠሉ። ‹‹ሶስት ሰዎች ናቸው፤ እንዲህ እንደእኛ ረጅም መንገድ የወጡ። የፈለጉበት ቦታ ሳይደርሱ የመሸባቸው ናቸው። መንገዱን በጭለማው ቀጥለው ቢሄዱ አውሬውን ፈሩ፤ ረጅም ጉዞ አድርገዋልና ርቧቸዋል፤ ውሃ ጥሙም ፈተኗቸዋል፤ እናም ‹የመሸበት መንገደኛ እንበል› ሲሉ ተመካከሩ። እንደምታውቂው ድሮ መንገደኛ መንገድ ሲጓዝ ውሎ ሲመሽበት፤ ወይም የቆሎ ተማሪ ወደ አንዱ ገዳም ሲጓዝ ውሎ ሲመሽበት ‹የደከመው …የራበው መንገደኛ› ብሎ ምጸዋት ይጠይቃል። አሳዳሪ ይለምናል ። ያን ጊዜ ባለቤቶቹ ይወጡና ‹ማነህ? ከየት መጥተህ ነው?› ብለው ጠይቀው ለእግሩ ውሃ፣ ለረሀቡ ማስታገሻ ምግብና የሚጠጣ ውሃ ሰጥተው፣ መኝታ መደብ አንጥፈው ያስተናግዳሉ። እንግዳውም በሚገባ ተስተናግዶ ማልዳ ተነስቶ ስላደረጉለት መልካም ነገር አመስግኖና መርቆ መንገዱን ይቀጥላል።›› በማለት በላብ የወረዛ ፊታቸውን በእጃቸው መዳፍ ዳሰስ አደረጉት።
‹‹ይሄ በሁሉም የሀገራችን ክፍል የተለመደ ነው። የማን ዘር ነህ? የትኛው ሀይማኖት ተከታይ ነህ? ብሎ ጥየቃ የለም። ብቻ ሰው የተቸገረ ሰው መሆኑን ከተረጋገጠ በቂ ነው። እንግዳ ደራሽ ተብሎ በክብር ተስተናግዶ ይሸኛል። እነዚያም ሶስት ሰዎች ይሄን ያውቁ ነበርና ሁሎችም አንድ ቦታ ከመግባት ብለው ‹አንተ ሂድና እዚህ ጠይቅ› ይሉታል፤ ‹ማነህ ካሉኝ ማነኝ ልበል?› ይላቸዋል። ሁሉም የመሰላቸውን ነገሩት። አዋጪ ምክር ያሉትን ለገሱት። እርሱ ግን ‹አይ በጣም አድርገው እንዲያከብሩኝ፣ እንዲፈሩኝ የምላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉልኝ እግዚአብሄር ነኝ እላቸዋለሁ› ብሎ ወደፊት ሄደ። እንዳለው ለተጠየቀው ጥያቄ ‹እግዚአብሄር ነኝ› ብሎ መለሰላቸው ። ሰዎቹ ግን እጅግ በጣም ተናደዱ፤ ፊታቸው ሁሉ በአንዴ ተለዋወጠ። ያን ግዜ እንግዳውም ደነገጠ። ‹ጌታን ተፈታተንከው› ብለው ይሆን ብሎ የሚሆነውን ሁሉ በጸጋ መጠበቁን ቀጠለ።
የቤቱ ጌታ ተናደውና ተበሳጭተው ‹በሀገር ላይ ይሄ ሁሉ ደም ሲፈስ ያሁሉ ነፍስ ሲጠፋ ልጅ በአባቱ ወንድም በወንድሙ ላይ ሲጨካከን ስንጠራህ! ስንጮህ! የት ነበርክ ? አሁን ብቅ ያልከው። አንተማ የፍጥረትህን ድምጽ የማትሰማ በመሆንህ አናሳድርህም› ብለው መለሱት። እሱም ወደ ጓደኞቹ ሄዶ የሆነውን ሁሉ በጣም አዝኖ ነገራቸው ። እንዴት እግዜአብሄር ነኝ ላላቸው ይሄ ሁሉ ባይሆን ወደፊት ስቃያችንን ተመልከት፤ ጥሪያችንን ተቀበል ብለው ማለት ሲገባቸው ብሎ መሬቱን እየቆረቆረ የተሰማውን ሁሉ ገለጸ።
ሌላው ደግሞ ቀበል አድርጎ እኔ ደግሞ ሌላኛው ቤት ሄጄ እድሌን ልሞክር አለ። እንዴት በዚህ ጨለማ አውሬ እንዲበላን እንፈቅዳለን ብሎ ተነሳ። ‹ማነህ ስትባል ማነኝ ትላለህ ? › አሉት እሱም አውጥቶ አውርዶ ከምንም በላይ ጥሩ ነገር ‹‹ፍቅር›› ነው። ፍርቅር ነኝ ብዬ እላቸዋለሁ አለ። የመረጠውን የገበሬ ቤት አንኳኳ። ብቅ ብለው ማነው አሉ ። እኔ ነኝ የመሸብኝ መንገደኛ አሳድሩኝ ብዬ እየለመንኩ ነው አለ። እንደተለመደው ጥያቄ ቀረበለት፤ እሱም ፍቅር መሆኑን ነገራቸው። በአጋጣሚ ብቅ ብለው የጠየቁት የቤቱ አባወራ ናቸው።
እሳቸው ከሚስታቸው ጋር በነበረባቸው መጋጨት በፍቅር ማጣት ተጣልተው ከተለያየ አጭር ጊዜያቸው ነው። ቤተሰባቸው ፍቅር አጥቶ ጸብ በቤቱ ነግሶ ኑሮው ሁሉ ተደበላልቆ ባቸዋል ። እኚህ ሰው ‹‹ፍቅር›› የሚለውን ቃል ፈጽሞ መስማት አይፈልጉም ፤እንዳው ቢሆንላቸው በጉልበት፣ በሀይል፣ በደሉኝ አስከፉኝ ቤቴን በጠበጡ ያሉትን ሁሉ መበቀል የሚፈልጉ ናቸው። እናም ውጣ ከቤቴ አንተን የማሳድርበት ምክንያት የለኝም ብለው አመናጭቀው መለሱት ። እሱም እያዘነና እየተከዘ ወደ ጓደኞቹ ሄዶ የሆነው ሁሉ ነገራቸው። ሁሉም አዘኑ የአንዳችንም ሳይሳካ እዚሁ አውሬ ሊበላን ነው ብለው ተጨነቁ ።
ሶስተኛው ሰው እኔ ደግሞ እድሌን ልሞክር ብሎ ተነሳ ፤ሁሉም በጸሎት ሸኙት። እርሱም ሁለቱ ያላንኳኩት ቤት ሄዶ የመሸበት መንገደኛ አለ። ማነህ የሚለው የተለመደው ጥያቄ ቀረበለት። እሱም መላዕከ ሞት መሆኑን ተናግሮ መንገድ እየሄደ መሽቶበት መሆኑን አስረዳ ፤እንድታሳድሩኝ ብዬ ነው ብሎ ጠየቀ። የቤቱ ጌታ ከመቀመጫቸው ተነሱ። ግባ ብለው እግሩ ላይ ወደቁ ።አንተማ ሁሉን እኩል የምታደርግ፣ ደሀ ከሀብታም የማትለይ ፣ ልጅ አዋቂ ፣ ምሁር መሀይም የማትመርጥ ፣ የእጅ መንሻ ምናምን የማትል ሀቀኛ አንተን ያላሳደርን ማንን እናሳድራለን ። ግባ ከእልፍኙ ብለው የሚበላ የሚጠጣውን የሚተኛበትን ሁሉ ለደከመው እግሩ የሙቅ ውሀ ጭምር ሰጥተው አስተናገዱት። እሱም በጥሩ መስተንግዶ ተስተናግዶና አድሮ ሲነጋጋ ስንቅ ተቋጥሮለት ከአደረበት ወጣ አሉ፤ ብለው በጣፋጭ አንደበታቸው ተረቱን ነገሩኝ። ትልቅ ሰው ተረቴን መልሱ አይባልም እንጂ ተረቴን መልሱ ብላቸው ደስ ባለኝ ነበር።
‹‹ይሄ ተረት አሁን ገብቶሻል›› ሲሉ ፈጠን ብለው መልስ እየሻቱ ጥያቄ አቀረቡ ። እናም ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ አፍ አፌን ተመለከቱ ። የመሰለኝን ነገርኳቸው ስህተት አላሉም ራሳቸውን ነቀነቁ። ትክክል ነኝ ብዬ ደስ አለኝ። እሳቸው ግን ይሄንን ሁሉ ወግ ያመጡት ከሀገራዊ ሁኔታው ጋር አገናኝተው ነው። በሀገራችን አሁን ያለው ሁኔታ ከምንጠብቀውና ከምንፈልገው የተለየ ነው። ፍቅር እየጠፋ ጸብ እየነገሰ፤ ርህራሄ እየጠፋ ጭካኔ እያየለ ነው። መረዳዳት ሳይሆን መቀማማት የበዛበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ሹመኛው ማንን ላገልግል ሳይሆን እንዴት ልገልገል ብሎ ነው የሚያስበው። ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል ብሎ ነው የሚነሳው፤ እኔን ምረጡ አገለግላችሁለሁብሎ ገብቶ ህዝብ ያስለቅሳል አገልግሎት በገንዘብ ግዛ ይላል።… ቀጠሉ ድሮም እኮ ጉቦ አለ፤ እጅ መነሻ ።አሁን ያ አይደለም አድጎ ገዝፎ ንጥቂያ ሆኗል። እኛ እንኑር ሀገር ይጥፋ ነው ነገሩ ሁሉ። መሬቱን ፣ ሀብቱን፣ ፕሮጀክቱን ሁሉ ዘራፊ እንጂ አልሚ አልገጠመውም። ብቻ አስፈሪ ደረጃ ላይ ደርሰናል።
ፈሪሀ እግዚአብሄር ጠፍቷል። የሀይማኖት አባት ፣ የጎሳ መሪ ፣ታላቅ ታናሽ መባባሉ ተረስቷል። ማን ማንን አዳምጦ! ብቻ ህገወጥነት ሰፍቷል። እናም ሁሉም የመረጠው፣ መላከ ሞትን ሆኗል። ይሄ ያልኩሽ የነገርኩሽ ሁሉ ተረት ተረት አይደለም፤ የእኛው የኢትዮጵያውያን አሁናዊ ገጽታ ነው። ባይጥምሽም…። ሁሉ እኛኑ የሚገልጽ ነው። ኢትዮጵያውያን ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ሁላችንም በመጠፋፋት አዙሪት ውስጥ ነን። ፖለቲካው ስልጣኔው ሁሉ የሚያፋቅር የሚያዋድድ ሳይሆን ቂም ቁርሾ መወጣጫ ሆኗል። በህይወት ባሉት ብቻ ሳይሆን በስም ባሉት ሁሉ መከራ ተቀበሉ በዝቷል›› እያሉ የተሰማቸውን ሁሉ ዘረዘሩ። መራር ቢሆንም በዘመናችሁ በዘመናችን የምናየው የምንቀምሰው እውነት ስለሆነ ተቀበይ አሉ። ይህን መከራከር አልፈለኩም። ደጋግሜ ራሴን ነቀነቅኩ።
እርሳቸው ግን አላቆሙም ‹‹አይተሽ የለ ያን ሰሞን ያ ሸኔ የምትሉት ጨካኝ በወለጋ አካባቢ የፈጸመውን ግፍ። የጨረሳቸውን ህጻናት ሴቶች አይተሽ የለ!? ››ሲሉ ጠየቁ፤ መልስ ሲያጡ መቼም ሰምተሻል ብለው ለጥያቄው ራሳቸው መልስ ሰጡ ። እሱማ ብዙ ሰምተናል። የሰው ልጆች ሞት ቁጥር እስኪመስለን ድረስ አድምጠናል። ኦሮሞው፣ አማራው፣ ሙስሊሙ፣ ክርስቲያኑ ሳይለዩ አልቀው አንድ ላይ ተቀብረው ሰምተናል። አሰቃቂ የሚባሉ ግድያዎችን አይተን ይሄ በኢትዮጵያ ውስጥ የሀይማኖተኞች መኖሪያ ሀገር በምትባለው ሀገራችን በራሳችን ወገኖቸ የሆነ ነው ብለን እግዚኦ ብለናል።
አሁንም ግን ገና አልተማርንም ። አሁንም ገና ፈጣሪን ፍጡሩን እያጠፋን መሆናችን ገብቶን ፈጣሪ ይፈርድብናል ብለን ከጥፋት አልተመለስንም። አሁን ከሁሉም ነገር በላይ ፍቅር ይበልጥ ጥፋትን በይቅርታ፤ ጸብን በፍቅር እንተካው ብለን ለንሰሀ አልተዘጋጀንም። አሁንም በቃን ብለን በህብረት በአንድነት ለመኖር አልተነሳሳንም ።አሁንም በውስጥ ክፋትን አዳፍነን ነው ያለነው። ትንሽ ነገር ብቅ ስትል የተዳፈነውን ረመጥ ገለጥለጥ ከማድረግ አልቦዘንም። ዛሬም እናስገባው እንጋብዘው እናክብረው ብለን ያለነው መላከ ሞትን ነው።
ግን ደግሞ ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል። የኖርንበትን ታሪክ ማስታወስ ያስፈልጋል። የማይጠቅመንን ትተን የሚሆነን ይዘን ሀገራችንን ሀገር ማድረግ እንደ ህዝብም ታሪካችንን ማስቀጠል ይሻለናል። ይሄንን ማን ይጀምር? ይሄንን ማን ያድርግ? ይሄንን ማን ያዳምጥ? በይ እንግዲህ ለአንቺም እንደ አቅምሽ የቤት ስራ ሰጥቼሻለሁ። ሁሉም የአቅሙን ከሰራ በሆነውና በሚሆነው ነገር ተጸጽቶ ከተመለሰ መጥፎው ሁሉ በጥሩ ይገለጣል። እኔ አበቃሁ፤ አቦ እንዴት አደከምሽን፤ የመንገዱን መርዘም ወሬው አሳጠረው እንጂ መቼም ይደክመን ነበር›› ብለው በረጅሙ የድካም አየር ተነፈሱ። በእውነት ትልቅ መልዕክት ትልቅም ትምህርት ረጅም መንገድ ከጥሩ ማወራረጃ ጋር እንዲህ የጣፈጠና ያጠረ ነው። ኬር…..ኬር ይሁን ብለን ተሰነባበትን።
አልማዝ አያሌው
አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 13 ቀን 2015 ዓ.ም