የሙዚቃ ታሪክ ከሰው ልጅ ታሪክ ጋር የተቆራኘ ነው። ብዙ ጊዜ የሚነገርለት ታሪክ ከሸክላ ዘመን በኋላ ያለው ቢሆንም ሙዚቃ ግን ከሰዎች የዋሻ ውስጥ ኑሮ ጀምሮ በኢመደበኛ ደረጃ ሲንጎራጎር የቆየ ነው።
በሸክላ መታተም ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ ያለው የሙዚቃ ታሪክ ግን መደበኛ የሙዚቃ አይነት ስለሆነ ብዙ ተብሎለታል። የሰው ልጅ የሥልጣኔ ደረጃ እያደገ እና እየዘመነ በመጣ ቁጥር የሙዚቃ ማጫወቻ አይነቶችም እየተለወጡና እያደጉ መጡ።
አሁን ላይ ባለው ወጣት ትውልድ የልጅነት ትዝታ ያለው ደግሞ ካሴት ነው። የካሴት ቅጂ የተጀመረው በአውሮፓ አገራት ውስጥ በ1960ዎቹ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። በእነዚህ ዓመታት የነበሩ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች የሚታወቁት በሸክላ ሥራዎች ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የካሴት ቅጂ የተጀመረበትን ትክክለኛ ጊዜ ባናገኝም ከ1970ዎቹ እና 1980ዎቹ ጀምሮ ግን የካሴት ሥራዎች አሉ። በተለይም በአሁኑ ወጣት ትውልድ ዘንድ ከፍተኛ የልጅነት ትዝታ ያላቸው ደግሞ የ1990ዎቹ የሙዚቃ ሥራዎች የሚታወቁት በካሴት ነው።
የሰው ልጅ የሥልጣኔ ደረጃ አይነቱንና መልኩን እየቀየረ መሄዱን ቀጥሏል። ብዙ ባህላዊና ልማዳዊ አሰራሮች በዘመናዊና ረቂቅ ቴክኖሎጂዎች ተተኩ። ከእነዚህም አንዱ የሙዚቃው ዘርፍ ነው። በአገራችን በተለይም ከሚሊኒየም በኋላ የሲዲ እና ዲ ቪ ዲ ማጫዎቻዎች ፋሽን ሆነው መጡ።
እነዚህ ማጫወቻዎች ከካሴት ጋር ጎን ለጎን አብረው የተወሰኑ ጊዜያት ቢሄዱም የካሴት ነገር ግን ልክ እንደ ሸክላ ሁሉ እየተረሳ መጣ። እነዚህን የሲዲ እና ዲ ቪ ዲ ማጫወቻዎችን በቴሌቭዥን ማጫወት ተለመደ። በድምጽ ብቻ ይሰሙ የነበሩ ዘፈኖችን በተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) ማየት ጭምር ተለመደ። አዳዲስ ሙዚቃዎች ሲሰሩ በቪዲዮ ጭምር እየሆነ መጣ።
ቴክኖሎጂ ወለድ የሆኑት እንደ ፍላሽ እና የእጅ ስልኮች ሚሞሪ ካርድ ደግሞ ተጨማሪ የሙዚቃ ማጫወቻዎች ሆነው መጡ። ዳሩ ግን እነዚህ ነገሮች ለሙዚቃው ኢንዱስትሪ ደግሞ ትልቅ ፈተና አስከተሉ። ‹‹ፍላሽ ክላሽ›› እስከሚባል ድረስ የፈጠራ ሥራዎችን በሕገ ወጥ መንገድ በማባዛት ለሌብነት በር ከፈቱ።
የቴክኖሎጂው ዕድገትና ለውጥ ቀጥሏል። በአገራችን ከ10 ዓመታት በፊት ጀምሮ ደግሞ የ‹‹ዩ ትዩብ›› አማራጮች ሌላ የሙዚቃ መስሚያ አማራጭ ሆነው መጡ። በቀጥታ ከበይነ መረቡ ዓለም ላይ በማውረድ ሰዎች በራሳቸው የእጅ ስልኮች ወይም በቴሌቭዥን እና በሌሎች የማጫዎቻ አማራጮች መስማት ጀመሩ።
በእነዚህ ሁሉ የቴክኖሎጂ ቅብብሎሽ ውስጥ ሙዚቃዎችን ለማግኘትና ለመስማት ምቹ ሁኔታ ቢፈጠርም ባለቤቶችን ግን አመድ አፋሽ አደረገ። የሙዚቃ ባለሙያው ከሥራው ተጠቃሚ መሆን አልቻለም።
ይህን ችግር ለመቅረፍ ነው እንግዲህ የሙዚቃ ባለሙዎች አንድ ዘዴ የፈጠሩ። ይሄውም የራሱ የሙዚቃ መተግበሪያ መፍጠር ማለት ነው። ይህ የሙዚቃ የሞባይል መተግበሪያ ‹‹ሰዋሰው›› የሚባል ሲሆን ባለፈው ሐሙስ ኅዳር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በስከይላይት ሆቴል ከሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር መሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።
አንጋፋዋን ድምጻዊት ማሪቱ ለገሰን ጨምሮ፤ ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ ካሙዙ ካሳ፣ አብነት አጎናፍር፣ ግርማ ተፈራ፣ ሔኖክ አበበ፣ ራሄል ጌቱ፣ ያሙሉ ሞላ፣ ለምለም ኃይለሚካኤል፣ ብሌን ዮሴፍ፣ ዘሩባቤል ሞላ እና ሌሎች ከ80 በላይ የሚሆኑ አንጋፋና ወጣት የሙዚቃ ባለሙያዎች ከሰዋሰው መልቲ ሚዲያ ጋር ለመስራት የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል።
ሰዋሰው መልቲ ሚዲያ ሙዚቃን በቀላሉ በኦንላይን ለመገበያት የሚያስችል የመተግበሪያ ዘዴ ሲሆን ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት 300 ሚሊዮን ብር ካፒታል ይዞ ነው ሥራ የጀመረው።
በዕለቱ ባለሙያዎቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ እንደተነገረው፤ መተግበሪያው የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች ድንበር ተሻጋሪ ታዳሚ እንዲያገኙ ያደርጋል። ባለተሰጥኦዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል፣ የሙዚቃ ሥራዎች የአከፋፋይ እጥረት ሳይገድባቸው በየትኛውም ቦታ እንዲደመጡ ያደርጋል።
በሙዚቃ ሥራዎች ግብይት ላይ የሚሰራው ሰዋሰው መልቲ ሚዲያ፤ ተሰርተው የተጠናቀቁ ሙዚቃዎችን ገዝቶ በተመጣጣኝ ዋጋ ለታዳሚዎች ከማድረስ በተጨማሪ ባለተሰጥኦዎች ችሎታቸውን የሚያወጡበት ዕድል ይፈጥራል።
ሰዋሰው መተግበሪያ ሕገ ወጥ ቅጂ ይበዛበት የነበረውን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ የባለተሰጥኦዎችን የባለቤትነት መብት ባስከበረ የቴክኖሎጂ አሰራር ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ነው ተብሏል። ይሄውም፤ ለባለፈጠራዎቹ ጠቀም ያለ ክፍያ በመክፈል ሙዚቃውን ራሱ ይሸጣል ማለት ነው። ባለፈጠራዎቹ ውል ከተፈራረሙ በኋላ ሥራቸውን ማስረከብ ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ አከሰረውም አተረፈውም ሥራው የሰዋሰው ነው።
የሰዋሰው መልቲ ሚዲያ የሙዚቃ ዲፓርትመት ኃላፊ ሀብቱ ነጋሽ እንደገለጸው፤ ሰዋሰው መልቲ ሚዲያ የሙዚቃ ስራዎችን ሲገዛ ሁለት አይነት አሰራሮችን ይከተላል። አንደኛው፤ ታዋቂና የራሳቸውን ስራ ራሳቸው ወጪውን ችለው ሙሉ አልበም የሚሰሩ ድምጻውያን ሥራ የሚቀርብበት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ይህ አቅም የሌላቸው ነገር ግን የሙዚቃው ተሰጥኦና ችሎታው ያላቸውን ወጣት ድምጻውያን ከባለሙያ ጋር በማገናኘት፣ የግጥምንና ዜማ እንዲሁም ሌሎች ወጪዎችን በመሸፈን ሙሉ አልበም የሚሰሩበትን መንገድ ያመቻቻል።
ሐብቱ ነጋሽ ለቁም ነገር መጽሔት በሰጠው መረጃ፤ ከእያንዳንዱ ድምጻዊ ጋር የሚደረገው ስምምነት እንደ አርቲስቱ ይለያያል። አርቲስቶች ከአልበማቸው ጋር አንድ የሙዚቃ ኮንሰርት እንዲሰሩ ስምምነት የሚያደርጉ ሲሆን ከአልበሙ ላይ ሶስት ዘፈኖችን ክሊፕ መስራት እንደ አንድ መስፈርት ተቀምጧል፤ የክሊፑን ወጪ በሰዋሰው አልያም በአርቲስቱ የሚሸፈን ሲሆን በሰዋሰው የዩቲዩብ ቻናል ላይ ብቻ ነው የሚጫነው።
የፊርማ ስምምነቱ በተደረገበት ዕለት ባለሙያዎቹ ለጋዜጠኞች በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ስምምነት ከተደረገ በኋላ ሙሉ ኃላፊነቱን ወስዶ የሚሰራው ሰዋሰው ነው። ባለሙያዎቹ ሥራቸውን ለሰዋሰው አንዴ ከሸጡ በኋላ ቢያንስ ለአምስት ዓመታት ከገቢው ላይ መብት መጠየቅ አይችሉም። ሰዋሰው ሙሉ ወጪውን ሸፍኖ የገዛ በመሆኑ አርቲስቶቹ በራሳቸው የዩቲዩብ ቻናል ላይም ሆነ የሮያሊቲ ክፍያ በሚሰበሰብበት የብሮድካስት ሚዲያ ላይ ስራዎቻቸውን አሳልፈው የመስጠት መብት አይኖራቸውም።
ሰዋሰው የሙዚቀኞቹን ስራ አድማጭ ጋር ለማድረስ የማስተዋወቅ ስራውን ሙሉ ኃላፊነት ወስዶ የሚሰራ ሲሆን ከቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር አማካይነት የሚሰበሰበው የሮያሊቲ ክፍያ አዋጁ ለፕሮውዲውሰሩ የሚፈቅደውን መብት ጨምሮ ለ5 ዓመታት ማስተዳደር የሰዋሰው መብት ይሆናል ማለት ነው።
በዚሁ ዕለት (ኅዳር 29 ቀን ማለት ነው) አሥር ድምፃውያን የተሳተፉበት ‹‹ሻኩራ›› የተሰኘ አልበም በሰዋሰው መልቲ ሚዲያ ቀርቦ ተመርቋል።
በዚህ አልበም ውስጥ፤ ጃሉድ አወል፣ ዘቢባ ግርማ፣ ራስ ዳጊ፣ ኒና ግርማ፣ ዳግማዊ ታምራትን ጨምሮ አሥር አርቲስቶች የተሳተፉበት አልበም ተመርቋል።
በሙዚቃ አቀናባሪና ፕሮዲውሰር ካሙዙ ካሳ የተዘጋጀው ‹‹ሻኩራ›› የተሰኘው ይህ አልበም በዕለቱ ተለቋል። የሙዚቃ አቀናባሪው ካሙዙ ካሳ በዕለቱ እንደተናገረው፤ አልበሙ ወጣት ድምፃውያን የተሳተፉበትና ዳንሶል፣ ሬጌና ሌሎችም የሙዚቃ ሥልቶች ያካተተ ነው።
ይህ የሙዚቃ ባለሙያዎች የፊርማ ስምምነት መደረግ ለአንጋፋ ድምጻውያን ሥራዎችም እንደገና ዕድል ፈጥሯል። ዝርዝሩ ወደፊት ይነገራል ቢሉም የተወዳጇ ድምጻዊት ማሪቱ ለገሠ ኮንሰርት እንደሚዘጋጅም ሰዋሰው መልቲ ሚዲያ በዕለቱ አሳውቋል።
ከ23 ዓመታት በኋላ ወደ አገሯ ትገባለች ተብሎ የምትጠበቀው አንጋፋዋ ድምፃዊት ማሪቱ ለገሠ በአራት ከተሞች ሥራዎቿን እንደምታቀርብ ነው የተነገረው። አቶ ሀብቱ ነጋሽ በዕለቱ እንደተናገሩት፣ አንጋፋዋ ድምፃዊ ማሪቱ ለገሠ በቅርብ ቀናት ወደ አገሯ ትገባለች። ከ23 ዓመታት በኋላ ወደ አገሯ የምትመጣው ማሪቱ፤ በደሴ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከተሞች ሥራዎቿን ታቀርባለች።
በነገራችን ላይ ሰዋሰው መልቲ ሚዲያ የሙዚቃ ሥራዎችን የሚገዛው በአልበም ደረጃ ያሉትን ነው። ነጠላ ዜማን እንደማያበረታታ በዕለቱ ተነግሯል። በሌላ በኩል ደግሞ የሙዚቃው ይዘቶችም እንደሚታዩ ነው በመግለጫው የተናገሩት።
ሰዋሰው መልቲ ሚዲያ፤ ግጭትን የሚፈጥሩ እና ጥላቻን የሚሰብክ መልዕክት ያላቸው ዘፈኖች ያሉበትን አልበም አይገዛም። ፍቅርና አንድነትን እንዲሁም አገራዊ መልዕክት ያላቸውን ዘፈኖች ነው የሚገዛው ተብሏል።
ሰዋሰው መልቲ ሚዲያ የሰው ልጅ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ ታሳቢ በማድረግ ‹‹ሙዚቃ ድሮ ቀረ›› እንዳይባል የአሁኑም ትውልድ የራሱን አሻራ ሰንዶ የሚያስቀምጥበት ዓውድ ፈጥሯል። በፍላሽ እና የእጅ ስልኮች ሚሞሪ ካርድ ላይ የባለሙያዎችን ታሪክ አናገኝም ነበር። የካሴት ዘመን ላይ የዘፋኙ ስምና ፎቶ፣ የዜማና ግጥም ደራሲ፣ አቃናባሪ፣ በአጠቃላይ በሥራው ውስጥ የተሳተፉ ሰዎች እና የእያንዳንዱ ዘፈን ርዕሶ ተፅፈው በካሴቱ ማቀፊያ ውስጥ ይቀመጡ ነበር።
ሰዋሰው መተግበሪያ ይህን ማንነት ሳይለቅ ቴክኖሎጂው በፈጠረው ዕድል በሙዚቃ ሥራው ውስጥ ለተሳተፉ ሰዎች ዕውቅና ይሰጣል። በአጭር ቪዲዮም ራሳቸው ማብራሪያ ይሰጣሉ። በጽሑፍ እና በምስልም ይቀመጣል።
በአጠቃላይ መተግበሪያው የሰው ልጅ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ዘመን ታሳቢ በማድረግ የሙዚቃ ትዝታን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ፣ ዕድሉን ላላገኙ ባለተሰጥኦዎች ከባለሙያ ጋር የሚያገናኝ እና አድማጩንም ተደብቀው ከሚቀሩ ሥራዎች ጋር የሚያገናኝ ስለሚሆን ተጠናክረው ይቀጥሉ እንላለን።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2015