ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር እያከናወነች ባለችው ተግባር ለኢንዱስትሪ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች። በግሉ ዘርፍ በኢንዱስትሪው መስክ እየተከናወኑ ካሉ ተግባሮች ጎን ለጎን መንግስት እስከ አሁን 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብቶ ወደ ስራ አስገብቷል። በኢንዱስትሪ ፓርኮቹም ተዋቂ ዓለም አቀፍ የውጭ ባለሀብቶች ገብተው ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ እያቀረቡ ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ፓርኮቹ እየገቡ ይገኛሉ።
በአገሪቱ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ባለፈው ሳምንትም ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ለማምረት ፍላጎት ካላቸው ሦስት ኩባንያዎች ጋር ስምምነቶችን ተፈራርሟል።
ከኮርፖሬሽኑ ጋር ስምምነት የተፈራረሙት አምራቾች ‹‹ሎንግ ማርች ኤሌክትሪካል ኢኪዩፕመንት ማኑፋክቸሪንግ›› ኩባንያ (Long March Electrical Equipment Manufacturing PLC)፣ ‹‹ዋርቃ ትሬዲንግ›› ኩባንያ እና ‹‹ኤን ኬ ወርልድ ሜዲካል ኢኪዩፕመንት ማኑፋክቸሪንግ›› (NK World Equipment Manufacturing PLC) ሲሆኑ ሁለቱ አገር በቀል አምራቾች፣ አንዱ ደግሞ የውጭ ድርጅት ነው። አምራቾቹ ከ480 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ይዘው ወደ ሥራ ይገባሉ፤ ከ550 በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያንም የሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎም ይጠበቃል።
‹‹ሎንግ ማርች ኤሌክትሪካል ኢኪዩፕመንት ማኑፋክቸሪንግ›› ኩባንያ (Long March Electrical Equipment Manufacturing PLC) የውጭ ኩባንያ ሲሆን፣ በ240 ሚሊዮን ብር ካፒታል የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎችንና ሌሎች የኤሌክትሪክ መሳሪያዎችን በማምረት ተግባር ላይ ይሰማራል። ኩባንያው የምርት ሥራውን በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በሦስት ሺ ካሬ ሜትር የማምረቻ ሼድ ላይ የሚያከናውን ይሆናል። ምርቶቹን ለአገር ውስጥና ለውጭ አገራት ገበያዎች የማቅረብ እቅድ ያለው ይህ ድርጅት፣ ለ250 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ይጠበቃል። ኩባንያው በብዛት ከሰው ኃይል ይልቅ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን የሚጠቀም እንደሆነም ተገልጿል።
አገር በቀሉ ‹‹ዋርቃ ትሬዲንግ›› ኩባንያ ክር በማምረት ሥራ ላይ የሚሰማራ ሲሆን፤ በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 5500 ካሬ ሜትር መሬት በመከራየት ወደ ምርት ሥራ ይገባል። ኩባንያው የተለያዩ የክር ዓይነቶችን ያመርታል። ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በተጨማሪ በሌሎች ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ አምራቾችም የክር ምርቶችን የማቅረብ እቅድ አለው። ይህም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የግብዓት ትስስር በመፍጠርና በምርት ሂደት ላይ የሚፈጠር የግብዓት እጥረትን በመፍታት የምርት አቅርቦትንና የወጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግ ይረዳል።
የ‹‹ዋርቃ ትሬዲንግ›› ኩባንያ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ ምስጋናው ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብቶ ማምረት ብዙ ቢሮክራሲያዊ ውጣ ወረዶችን እንደሚያቃልል ይገልጻሉ። ‹‹መሬት ወስዶ ለማልማት ቢሮክራሲው ረጅም ጊዜ ይወስዳል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግን ሁሉንም አገልግሎት መስጠት ስለሚችሉ ወደ ፓርኮቹ ገብቶ መሥራት ተመራጭ ነው›› ይላሉ። ከተመሰረተ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው ‹‹ወርቃ ትሬዲንግ›› ክር በማምረት ላይ እንደሚሰማራ ጠቁመው፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ኩባንያዎችም ምርቶቹን እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ የአገሪቱን የክር ምርት ግብዓቶች ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ለማምረት ኩባንያቸው በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልሎች ጥጥ በማልማት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
‹‹ኤን ኬ ወርልድ ሜዲካል ኢኪዩፕመንት ማኑፋክቸሪንግ›› (NK World Equipment Manufacturing PLC) ከኮርፖሬሽኑ ጋር ስምምነት የተፈራረመው ሌላኛው አገር በቀል ኩባንያ ነው። ኩባንያው በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ አንድ ሄክታር የለማ መሬት ተረክቦ በ250 ሚሊዮን ብር ካፒታል የሕክምና ቁሳቁስን የሚያመርት ሲሆን፤ ከ210 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል። በ279 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የፋማሲዩቲካል ምርቶችን የሚያመርቱ ባለሀብቶች የተሰማሩበት የኢንዱስትሪ ፓርክ እንደሆነ ይታወቃል።
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሕክምና መሳሪያዎች ፍላጎትና እጥረት አለ። አብዛኛው የሕክምና ቁሳቁስ ከውጭ የሚገባ ነው። ‹‹ኤን ኬ ወርልድ ሜዲካል ኢኪዩፕመንት ማኑፋክቸሪንግ›› የሚያመርታቸው የህክምና ቁሳቁስ አሁን አገሪቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታስገባቸውና ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸው ናቸው። ኩባንያው የሕክምና ቁሳቁስን በማምረት ላይ ስለሚሰማራ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች ተክቶ የአገሪቱን ፍላጎት በማሟላትና ምርቶቹን ለውጭ ገበያ አቅርቦ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። ምርቶቹ በአገር ውስጥ ሲመረቱ ለምርቶቹ ግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ማዳንም ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪም አገሪቱ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 60 በመቶ የሚሆነውን የመድሃኒትና የሕክምና መሳሪያዎች ፍላጎቶቿን በአገር ውስጥ ለማምረት የያዘችውን እቅድ ለማሳከት የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ስምምነት የተፈራረሙት ኩባንያዎች ለሥራ እድል ፈጠራ ከሚያበረክቱት አስተዋፅኦ በተጨማሪ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግርን እውን በማድረግ የሚኖራቸው ሚናም የላቀ እንደሚሆን ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው የሚያለሙ ኩባንያዎች ለዜጎች የሥራ እድል የመፍጠር ፋይዳቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖርና የምርት ተግባራት በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። በዚህም የምርት ሥራዎች ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆኑ እገዛ ያደርጋሉ።
‹‹አገር በቀል ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሲገቡ ያስደስታል›› የሚሉት አቶ አክሊሉ፤ ‹‹አገር በቀል ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው በምርት ሥራ ላይ ለመሰማራት የሚያሳዩት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱ የኩባንያዎቹ የማምረት አቅማቸው አድጎ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ተወዳዳሪ የመሆን አቅማቸው ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነ ያመለክታል። ከዚህ በተጨማሪም የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች በሽርክና (Joint Venture) የሚሰሩበት የቢዝነስ ሞዴል እድገት እያሳየ እንደሆነም ጠቋሚ ነው›› ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ አቶ አክሊሉ ማብራሪያ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን የሚያመርቱ በርካታ ኩባንያዎች አሉ። ከእነዚህ ኩባንያዎች መካከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመ ጥር የሆኑ ትልልቅ አምራቾች ይገኛሉ። እነዚህ አምራቾች ክርና ሌሎች ጥሬ እቃዎችን የሚያገኙት ከውጭ ገበያ ነው። ይህ ደግሞ አገሪቱ ካላት ውስን የውጭ ምንዛሬ አንፃር በምርቱም ላይ ሆነ በአገሪቱ ላይ ጫና እንደሚያሳድር ይታወቃል። ‹‹ወርቃ ትሬዲንግ›› የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ግብዓት የሆነውን ክር የሚያመርት በመሆኑ የግብዓት እና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለማቃለል እንዲሁም ምርቶቹን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ይረዳል።
በሌላ በኩል የ‹‹ኤን ኬ ወርልድ ሜዲካል ኢኪዩፕመንት ማኑፋክቸሪንግ›› ወደ ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብቶ በምርት ሥራ ላይ መሰማራቱ በኢትዮጵያ ጤናው የተጠበቀ ዜጋ እንዲኖር የተቀመጠው ማኅበራዊ ፖሊሲ እንዲሳካ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አቶ አክሊሉ ያስረዳሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ‹‹የኢንቨስትመንት ዘርፍን ለማሳደግ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ጥራቱን የጠበቀና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያለው አገልግሎት እየተሰጠ ነው›› የሚሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ አክሊሉ ታደሰ፤ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው እንዲያመርቱ ኮርፖሬሽኑ በትኩረት ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ይናገራሉ። ባለሀብቶች በርካታ ጥቅሞችንና እድሎችን ወደያዙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ እንዲሰማሩም ጥሪ አቅርበዋል።
ባለሀብቶችን ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመሳብ በሚደረገው ጥረት ለዘላቂ የአገር ልማትና እድገት አስተማማኝ ዋስትና መሆን የሚችሉትን የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ዐቢይ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል።
የምጣኔ ሀብት ጥናቶች እንደሚያስረዱት፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ለዘላቂ የአገር ልማትና እድገት አስተማማኝ ዋስትና መሆን የሚችሉ የልማት አንቀሳቃሾች ናቸው። በአሁኑ ወቅት በምጣኔ ሀብታቸውና በፖለቲካ ተፅዕኗቸው የዓለም ኃያላን የሆኑት አገራት የአገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸውን በመደገፍ ረገድ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል። እነዚህ አገራት ባለሀብቶቻቸውን በማገዝና በመጠበቅ የሰሩት ሥራ የአምራችነት አቅማቸውን አሳድጎ የምጣኔ ሀብት እድገታቸው ዘላቂ እንዲሆን አስችሏቸዋል።
የበለፀጉት አገራት የአገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸውን ቀደም ባሉት ጊዜያት ብቻም ሳይሆን አሁንም ከፍተኛ ድጋፍና ጥበቃ ያደርጉላቸዋል። አገራቱ በፋይናንስ አቅርቦትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ለባለሀብቶቻቸው የተለየ የድጋፍ መርሃ ግብር አላቸው። የበለጸጉት አገራት ለአገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸው የሚያደርጉት ድጋፍ፣ ገና በማደግ ላይ ያሉ አገራት ከሚያደርጉት ድጋፍ ቢበልጥ እንጂ አያንስም። ለአሁኑ የምጣኔ ሀብት ኃያልነታቸው መሰረት የሆናቸውና ከውጭ ጥገኛነት ያላቀቃቸው የውስጥ አምራችነት አቅማቸው ማደግ እንደሆነ ይታወቃል።
በጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር እና የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ጥናትና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ግርማ፤ ‹‹መንግሥት ኢኮኖሚውን ነፃ አድርጎ ችግሮች ሲያጋጥሙ ድጋፍ/ድጎማ በማድረግ ባለሀብቶችን ማገዝ ይኖርበታል። የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚው ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር በመሆኑ ይህን ዘርፍ በተደራጀና ተቋማዊ በሆነ መልኩ መምራትና መደገፍ ይገባል›› ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍ ጥረት በብዙ መልኮች ሊገለፅ ይችላል። የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን የሚያበረታቱ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችን በመቅረፅ፣ ፋይናንስን ጨምሮ ግብዓቶችን በማቅረብ፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦትን በማሟላት እንዲሁም ቢሮክራሲያዊ የአሰራር ውጣ ውረዶችን በማቃለል ለባለሀብቶቹ ድጋፍ ማድረግ ይቻላል። ባለሀብቶቹ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በማቅረብ ከሚኖራቸው ሚና ባሻገር ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር፣ ገቢ ምርቶችን በመተካት እና የወጪ ንግድን በመጨመር ትልቅ አስተዋፅዖ ስለሚኖራቸው ይህን ሚናቸውን የበለጠ እንዲያሳድጉ በመንግሥት ድጋፍ መደረግ ይኖርበታል።
በተለይ ኢትዮጵያ በሥራ አጥነትና በዋጋ ንረት እየተፈተነች ባለችበት በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ እጅግ አስፈላጊ ተግባር ነው። መንግሥት ለባለሀብቶቹ የሚያደርገው ድጋፍ ምጣኔ ሀብቱን በማነቃቃት፣ የሥራ እድል በመፍጠር፣ የገቢ ንግድ እቃዎችን በመተካት፣ የወጪ ንግድን በማሳደግ ጥቅል አገራዊ ምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴው ዘርፈ ብዙ ለውጥ እንዲኖረው ያደርጋል። የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ አገር በራሷ አምራቾች ላይ እንድትተማመን ያስችላል። ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ፖለቲካ ምክንያት በሚፈጠሩ ችግሮች ከሚከሰት አደጋ ለመዳንም ይረዳል።
ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ፤ ኢኮኖሚያዊ የሆኑትን አብዛኞቹን አስፈላጊ የኢንቨስትመንት ግብዓቶች ባለሀብቶቹ በራሳቸው ለማሟላት ጥረት እንደሚያደርጉ አመልክተው፣ መንግሥት ቢሮክራሲያዊ የአሰራር ውጣ ውረዶችን በማቃለል ረገድ ትልቅ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ ይናገራሉ። ለአብነትም መንግሥት አሰልቺ የሆኑ የአሰራር ሰንሰለቶችን በማሳጠርና አገልግሎትን በማቀላጠፍ እንዲሁም የንብረት ጥበቃ በማድረግ ለባለሀብቶቹ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል። በተጨማሪም ባለሀብቶቹ በኢንቨስትመንት ላይ የሚኖራቸው ተሳትፎ ዘላቂ እንዲሆን መንግሥት የኃይል አቅርቦትን፣ የመንገድና የሎጂስቲክስ አገልግሎቶችን ጨምሮ ለሌሎች የመሰረተ ልማት ችግሮችም መፍትሄዎችን ማበጀት ይጠበቅበታል። የውጭ ምንዛሬን በፍትሐዊነት ማቅረብም የመንግሥት ኃላፊነት ነው ይላሉ።
የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከእርሻ መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና እድሎች አሉ። ይሁን እንጂ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት አገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ አይደሉም። ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ለማሳካት አምራች ዘርፉ አሁን ካለው አፈፃፀም በብዙ እጥፍ እንዲጨምርና እንዲሻሻል ማድረግ ያስፈልጋል። የአምራች ዘርፉ እድገት ሊሻሻል የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ናቸው።
መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግሩን ለማሳካት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን አፈፃፀም ማሻሻል ይገባል። ይህም ባለሀብቶች ወደ ፓርኮቹ ገብተው ለማምረት የሚያስችሏቸውን የመሰረተ ልማት ግብዓቶች፣ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የፋይናንስ አቅርቦት ማሟላትን እንደሚያካትት ሊታወቅ ይገባል። ኢትዮጵያውያን የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎና ድርሻ በየጊዜው እየተሻሻለ እንደመጣ ባይካድም በቂ የሚባል ግን አይደለም። ስለሆነም ለዘላቂ የአገር ልማትና እድገት አስተማማኝ ዋስትና መሆን የሚችሉትን የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2015