ኢትዮጵያ በርካታ የቀንድ ከብት ሀብት ካላቸው አገራት መካከል ተጠቃሽ ናት። ይህ የቀንድ ከብት ሀብት ባለቤትነቷ በቆዳ ልማት ዘርፍ ትልቅ አቅም እንዲኖራት አስችሏታል። አገሪቱ ወደ አስራ አራት የሚሆኑ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች እንዳሏት መረጃዎች ያመለክታሉ። ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉት ከዘርፉ የሚገኙት ብዙዎቹ ምርቶች ከአገር ውስጥ ገበያ ተሻግረው በውጭ አገራት ገበያዎችም ተፈላጊ ናቸው።
ቆዳና ሌጦ ወደ ውጭ እየተላከ ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ይታወቅም ነበር፤ የቆዳ ልማት ዘርፍ ባለፉት 20 ዓመታት፣ በተለይም የተጨማሪ እሴት ታክስ (Value Added Tax) አሰራርን ተግባራዊ ካደረገ ወዲህ፣ በርካታ አወንታዊ ለውጦችን እንዳስመዘገበና ትልቅ እመርታ አሳይቶ እንደነበርም ይገለፃል። ከዘርፉ እስከ 133 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ የተገኘበትም ሁኔታም እንደነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ያም ቢሆን ታዲያ አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘው ጥቅም በቆዳ ልማት ዘርፍ ካላት እምቅ አቅም አንጻር ሲታይ ብዙ የሚባል አልነበረም። ይህን ሁኔታ በመቀየር ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት ሲሰራ እንደነበር ይታወቃል። ስራዎቹን ተከትሎ ከዘርፉ መገኘት ያለበት ጥቅም መገኘት ሲገባው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። 133 ሚሊዮን ዶላር ያስገኘ ዘርፍ 40 ሚሊየን ዶላር ያስገኘበት ሁኔታም ይህንኑ በሚገባ ያስረዳል።
ከአገሪቱ የዘርፉ አቅም አንፃር የቆዳ ልማት ዘርፍ ከፍተኛ እድገት ማስመዝገብ የሚችልበት እድል እንዳለው ቢታመንም በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ማምረት ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች ግን በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው በተደጋጋሚ ይገለፃል። የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ዋና ጸሐፊ አቶ ሰለሞን ጌቱ የኢትዮጵያ የቆዳ ልማት ዘርፍ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ችግር እንደገጠመው ያስረዳሉ።
እርሳቸው እንደሚገልፁት፤ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረትና የግብዓት ችግሮች በዘርፉ ህልውናና እድገት ላይ ከፍተኛ አደጋ ደቅነዋል። ከአምስት ዓመታት በፊት በዓመት 133 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ያስገኝ የነበረው ይህ ዘርፍ፣ ባለፈው ዓመት ከዘርፉ የተገኘው የወጪ ንግድ ገቢ 40 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው። ከውጪ ንግድ ገቢው መቀነስ በተጨማሪ በዘርፉ የተሰማሩ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል፤ አንዳንዶቹ በዝቅተኛ አቅም እያመረቱ ሲሆን፣ ብዙ አምራቾች ደግሞ የምርት ስራቸውን ለማቆም ተገድደዋል።
እንደዋና ፀሐፊው ገለፃ፣ በቆዳ ማልፋትና ማለስለስ እንዲሁም የቆዳ ውጤቶችን በማምረት ላይ የተሰማሩ አምራቾች አብዛኛው ስራቸው ከውጭ በሚገቡ ግብዓቶች ላይ የተመሰረተ ነው። ብዙዎቹ ፋብሪካዎች የገበያ ስምምነታቸውን መሰረት በማድረግ ለመስራት የሚያስችላቸው ሁኔታ የለም። የመንግሥትና የአምራቾች የውጭ ምንዛሬ መጋራት የድርሻ አሰራር 50/50 እንዲሆን በተደጋጋሚ ቢጠየቅም 20/80 ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ይህ አሰራር ደግሞ ግብዓቶችና መለዋወጫዎችን በበቂ ሁኔታ ለማግኘት መሰናክል ሆኗል። መንግሥት ለአምራቾች ግብዓቶችን ለማቅረብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ የቀረበ ቢሆንም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።
‹‹የኢትዮጵያ የቆዳ ሀብት በብዛት ከመገኘቱ በተጨማሪ በርካታ ልዩ ባህርያት ያሉበት ነው። የቆዳው የተፈጥሮ ጥራት ዋጋው ውድ እንዲሆን በማድረግ ከፍ ያለ ገቢ ለማግኘት ይረዳል። ዘርፉ ከፍተኛ የመልማት እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ በስራ እድልና በሀብት ፈጠራ ለአገራዊ ምጣኔ ሀብት ትልቅ አስተዋፅኦ የማበርከት አቅም ያለው ቢሆንም፣ አሁን ያለበት ሁኔታ ግን አሳሳቢ ነው።
መንግሥት ዘርፉ ግብዓት እንዲያገኝ የጀመራቸው ስራዎች በፍጥነት መጠናቀቅ አለባቸው። አምራቾች ከወጪ ንግድ ከሚያገኙት ገቢ 50 በመቶውን ለግብዓትና ለመለዋወጫ ግዢ መጠቀም እንዲችሉ ሊፈቀድላቸው ይገባል። ዘርፉ ሙሉ በሙሉ ከመቆሙ በፊት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ ሊያበጅለት ይገባል›› ይላሉ።
በቆዳ ልማት ዘርፍ የተሰማሩት አቶ አየለ በየነም ዘርፉ ብዙ ችግሮች እንዳሉበት ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ የቆዳ ዋጋ በየጊዜው የተለያየ መሆኑን ጨምሮ ለመሸጫ የሚሆን አማካይ ቦታ አለመኖርና ለሰራተኛ የሚከፈለው ዋጋ ውድ መሆኑ የቆዳ ልማት እድገት በሚፈለገው ልክ እንዳይሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ። ይህም አምራቾችን፣ በተለይም የአገር ውስጥ ድርጅቶችን ከገበያ ውጭ እንዲሆኑ እያደረገ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም በህገ ወጥ መንገድ (በኮንትሮባንድ) ወደ ውጭ የሚወጣው ቆዳና ሌጦም ቀላል የማይባል ኪሳራ ያስከትላል።
የጥሬ ቆዳና ሌጦ ጥራት ጉድለት፣ በተለይም እየተባባሰ የመጣው የቆዳ መቀደድና የቅርፅ መበላሻት፣ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚፈልግም አቶ ሰለሞን ይጠቁማሉ። የጥራት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የጥሬ ቆዳና ሌጦ ምርት ባለሙያዎችን በቴክኒክና ሙያ ደረጃ ለማስተማር እንዲሁም የሙያና የሥራ ደረጃ ለማውጣት ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ይገልጻሉ። ከዚህ በተጨማሪም ለዘርፉ አምራቾች ስልጠናዎችን ለመስጠት ጥረቶች እንዳሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው እርድ የሚከናወነው በቤት ውስጥ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሰለሞን፤ ይህም ጥራቱን የጠበቀ ቆዳና ሌጦ ለማግኘት የሚከናወነውን ተግባር አስቸጋሪ እንዳደረገው ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም የጥሬ ቆዳና ሌጦ ግብይት አዋጅ ተግባራዊ አለመሆኑ በዘርፉ እድገት ላይ ትልቅ ችግር እንዳስከተለ ያስረዳሉ። «አዋጁ ስለቆዳና ሌጦ ምርት አጠቃላይ አስተዳደርና አመራር ያሳያል። አዋጁ ክፍተት ካለበት ማስተካከያ ተደርጎበት ተግባራዊ እንዲደረግ በተደጋጋሚ ብናሳስብም እስካሁን ግን ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም። በ2004 ዓ.ም ዘርፉ የሚመራበት ፍኖተ ካርታና ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም፣ ተግባራዊነቱ ግን በሚፈለገው ልክ አልሆነም» ሲሉ ያብራራሉ።
የማህበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ሰለሞን በቆዳ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ገልፀው፣ የዘርፉን ችግሮች በተደጋጋሚ ለመንግሥት ማቅረባቸውንም ይናገራሉ። ‹‹የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ጥያቄ ካቀረብን አንድ ዓመት ቢሆነንም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። በኮቪድ ምክንያት የተዳከመውን ይህን ዘርፍ ለማነቃቃት ከመንግሥት ድጋፍ እንፈልግ ነበር›› ነው ያሉት።
መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሄ እርምጃዎች መካከል በቅርቡ ይፋ የተደረገው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› አገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው። የአገራዊ ንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የስራ ባህል ማሻሻል ብሎም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሻሻል ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ ናቸው። ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ብሎም የዘርፉን ልማት ለመደገፍ እንዲሁም አምራች ኢንዱስትሪዎችን በጥራትና በቁጥር ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት የሚከናወኑበት ሲሆን የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከተለመደው አሰራር በማሻገር ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያግዝ ታምኖበታል። በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪዎች ለአገር ውስጥ ምርት እድገት እያበረከቱት ያለውን አነስተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያሳድግም ተስፋ ተጥሎበታል።
በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር የዘርፉን የማምረት አቅም ማሳደግ፣ ለዜጎች ተጨማሪ የስራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ እና ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማዳን ከ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› መርሃ ግብር የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ኢንዱስትሪዎች የገጠሟቸውን ችግሮች በመፍታትና ለምርታማነታቸው ማደግ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የኢንዱስትሪው ዘርፍ በሀገራዊ ኢኮኖሚ የሚኖረውን ድርሻ ለማሻሻል ታቅዶ መተግበር እንደተጀመረ በንቅናቄው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ መግለፃቸው ይታወሳል።
አቶ ሰለሞን ‹‹የቆዳ ልማት ዘርፍን ሊያነቃቃ በሚችለው በ‹ኢትዮጵያ ታምርት› ንቅናቄ ላይም ያሉብንን ችግሮች አሳውቀናል። ንቅናቄው በስራ እድል ፈጠራም ሆነ በገበያ ተወዳዳሪነት በተለይ ለቆዳ ልማት ዘርፍ ትልቅ ለውጥ ይዞ የሚመጣ ነው›› በማለት ያስረዳሉ።
አቶ ሰለሞን ችግሩን በሌላ ወገን ከማሳበብ ይልቅ የአምራቾችን አቅም መፈተሽ እንደሚያስፈልግ ታምኖበት አምራቾች ከአደረጃጀትና ከሌሎች ጉዳዮች አንፃር ያሉባቸውን ችግሮች በመለየት ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀርቡ የሚያስችሉ ተግባራዊ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። ማኅበሩ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ በማዘጋጀት የቆዳ አምራቾችን ተወዳዳሪነትና የዘርፉን እድገት ለማሻሻል እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረው፣ ከሌሎች አገራት ልምድ ለመቅሰምና መልካም ተሞክሮዎችን ለማምጣት ምክረ ሃሳቦችን አቅርቧል ይላሉ። የቆዳ ዘርፍ አምራቾች በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ ቦታ እንዲያገኙ መደረጉንም ያመለክታሉ።
አምራቾች ምርቶቻቸውን ለገበያ ሲያቀርቡ ከተናጠላዊ አካሄድ ይልቅ እንደአገር እንዲያቀርቡ የሚደግፋቸው ተቋም ሊኖር ይገባል። በመጪው የካቲት ወር በኢትዮጵያ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቆዳ ንግድ ትርኢት ለቆዳው ዘርፍ ችግሮች መፍትሄ የሚሆኑ አማራጮች የሚመላከቱበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
ከዚህ በተጨማሪም ‹‹የቆዳ ልማት ዘርፍ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ነው። የአስር ዓመቱ አገራዊ የልማት እቅድም የቆዳ ልማት ዘርፍ ያለውን አቅምና በአገራዊ ምጣኔ ሀብቱ ላይ የሚኖረውን ድርሻ በግልጽ አመላክቷል። እቅዱ ተኪ ምርቶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ስለሚያበረታታ ለዘርፉ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። በመሆኑም ዘርፉ ካለው አቅምና ፍላጎት አንፃር የተቃኘ እቅድ በማዘጋጀት በልማት እቅዱ ትግበራ ላይ ለመሳተፍ እየተዘጋጀን ነው›› በማለት የዘርፉ ባለሀብቶች በቀጣይ ዓመታት ሊኖራቸው ስለታሰበው እቅድ ይገልፃሉ።
አቶ ሰለሞን የዘርፉ ችግር በዘላቂነት የሚፈታው በመዋቅራዊ ሽግግር እንደሆነ ይገልፃሉ። ‹‹ኢንዱስትሪው መዋቅራዊ ለውጥ ያስፈልገዋል። በዚህም ቆዳ አምራቾች አዋጭ በሆነ መልኩ በአንድ ቦታ ተሰብስበው እንዲሰሩ ማድረግ (Clustering) ያስፈልጋል። ይህም ተረፈ ምርቶች ወደ ገንዘብ የሚቀየሩበትን እድል እንዲሁም ለአካባቢ ጥበቃና ለተወዳዳሪነትም ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። የትልልቅ ብራንዶች ወደ ገበያው መግባትም በቆዳ ኢንዱስትሪዎች አንድ አካባቢ መሰባሰብ ላይ የተመሰረተ ነው›› ይላሉ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ አገሪቱ ብዙ የቆዳ ሃብት እንዳላት ጠቅሰው፣ ከመጀመሪያው አንስቶ የቆዳው ጥራት ተጠብቆ ባለመምጣቱ ምክንያት እና ‹‹ፕሮሰስ›› በሚደረግበት ወቅት ጥራትን የማረጋገጥ ችግሮች ስላሉ ኢትዮጵያ ከቆዳው ዘርፍ የሚገባትን ያህል ጥቅም ማግኘት እንዳልቻለች ተናግረዋል።
አቶ መላኩ በቆዳው ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዘርፎችም ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና አምራቾችን፣ ተጠቃሚዎችንና አምራች ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃት ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የተሰኘ ንቅናቄ መጀመሩንና ይህም በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
አገሪቱ በዘርፉ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ ሽግግር እውን ለማድረግ ባለፉት ዓመታት በርካታ ተግባራትን ማከናወኗ ይታወቃል፤ ይሁንና በቁጥርም በዓይነትም የበዙትን የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት ተጨማሪ ጥረቶች ያስፈልጋሉ። የአገሪቱን የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪዎችን ልማትና ሽግግርን በማፋጠን ኢንዱስትሪዎቹ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና ፈጣን ልማት እንዲያስመዘግቡ ማብቃትን ዓላማ አድርገው እስካሁን ድረስ የተከናወኑት ተግባራትን ማጠናከር ይገባል። አምራቾቹ የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች መፈተሽና ምላሽ ማግኘት ላለባቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በፍጥነት መስጠት ከመንግስት ይጠበቃል።
የቆዳና ሌጦ ዋጋ መውደቁ ይታወቃል፤ ይህ የሆነው ከዋጋ መቀነስ ጋር በተያያዘ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ማህበሩ በበኩሉ የቆዳ ጥራት ችግርን ይጠቅሳል። በአንድ በኩል ለቆዳ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ሊሆን የሚችል የአገር ሀብት እየተጣለ በሌላ በኩል ደግሞ ስለግብዓት እጥረት እየተገለጸ ነው።ለውጭ ገበያ እየቀረበ ከቡና ቀጥሎ ለአገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስገኝ የነበረው ቆዳና ሌጦ በአገር ውስጥ የሚገዛው ያጣበትን ሁኔታም አምራቾቹ መፈተሽና ለመፍትሄው መስራትም ይኖርባቸዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ህዳር 22/2014