አዲስ አበባ፡- የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ሚያዚያ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ ሶስት ሰዓት በመላው አገሪቱ «ዘረኝነትን እንፀየፍ ከተማችንን እናፅዳ» በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የጽዳት ዘመቻ ላይ መላው ህዝብ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቧል።
አገራዊ የጽዳት ዘመቻውን ተከትሎ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የባህል ቱሪዝምና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን መግለጫ ሰጥተዋል። የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ‹‹ጽዳታችን ለጤናችን›› በሚል ቁልፍ መልዕክት በሁሉም የጤና ቢሮዎች፣ ፅህፈት ቤቶች እና የጤና ተቋማት እንዲሁም ኤጀንሲዎች ይካሄዳል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ‹‹በመጪው እሁድ የተጠራው የጽዳት ዘመቻ አንዱ ሲሰራ ሌላው ቁጭ ብሎ የሚመለከትበት ሳይሆን በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘን አካባቢያችንንና ከተሞቻችንን በማጽዳት ጤናችንን ከመጠበቅ ባለፈ ለአገር ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና የምንጫወትበት ነው።›› ካሉ በኋላ፤ መላው ህዝብ በአንድነት እንዲያፀዳ ጠይቀዋል። አክለውም ከአሁን ጀምሮ ልዩነትን ወደ ጎን በመተው በአንድነት በመቆም በጋራ አካባቢን ማጽዳት ላይ መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጽዳት ዘመቻው የአካባቢን ጽዳት ለመጠበቅ መልካም አጋጣሚ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት የጽዳት ዘመቻውን ቀጣይነት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ገልጸዋል። ፅዳት መልካም ባህል ሆኖ እንዲቀጥል እንደሚሰራና ቀደም ብሎ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሀይጅንና በአካባቢ ጥበቃ ለማከናዋን ላቀዳቸው
ስራዎች መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረለት ተናግረዋል።
የሀይጅንና የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ዳይሬ ክተር ወይዘሮ ኢክራም ሬድዋን በበኩላቸው፤ የሀይጅንና የአካባቢ ጤና አጠባበቅ የስራ ሂደት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
አደረጃጀቱን ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ በማውረድ የሀይጅንና የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ስራዎች የተሳካ እንዲሆን እየተሰራ ባለበት በዚህ ወቅት እንደዚህ አይነት የልማት ዘመቻ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መጠራቱ እቅዳቸውን ወደታች ወርደው ለመተግበርና የጽዳት ስራውንም በዘላቂነት ለማስቀጠል ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና የባህል ቱሪዝምና ስፖርት ሚኒስቴር ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ ሚያዚያ 6 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄደውን የጽዳት ዘመቻ አስመልክተው ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ዘመቻውን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊደግፈው እና ሊሳተፍበት ይገባል። ዘረኝነት የኢትዮጵያውያን ባህል አይደለም፤ በመሆኑም መልካም በማሰብ፣ በመናገርና በመስራት አገሪቷን አንድ ማድረግ ያስፈልጋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ ዕሑድ ዕለት ሁሉም አካባቢውን ሲያፀዳ ውስጡ ያለውንም ዘረኝነት በማፅዳት ኢትዮጵያ ለህጻናት፣ ለሴቶች፣ ለአረጋ ውያን በአጠቃላይ ለህዝቡ የተመቸችና አንድነቷ የተረጋገጠባት አገር እንድትሆን በማሰ ብም ጭምር መሆን እንደሚኖርበት ጠቁመዋል።
«ዘረኝነት ቆሻሻ ነው አይጠቅምም» ያሉት ሚኒስትሯ፤ ከሚሰበሰበው ቆሻሻ ጋር በማቃጠል አልያም በመቅበር ከአገሪቷ ይህን ቆሻሻ ማጥፋት እንደሚገባ ጠቁመዋል። በቆሻሻ ምክንያት የሚከሰቱ በሽታዎች በቀላሉ ህክምና ይድናሉ፤ ዘረኝነት ግን የሚያስተላልቅ አደጋውም ብዙ ዎችን የሚጨርስ በመሆኑ እንደማያስፈልግ ከመናገር ጀምሮ፤ ተፀይፎ ተግባራዊ ስራን በመስራት ማሳየት ይገባል ብለዋል።
ዘረኝነት አስተሳሰብ ከውጭ የመጣ በመሆኑ አካባቢው ሲጸዳ በዛው የተጫነውን አላስፈላጊ የዘረኝነት አስተሳሰብም ጠራርጎ ማፅዳት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘረኝነት ምክንያተ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች ከአቅም በላይ አይደሉም፤ ያሉት ሚኒስትሯ ‹‹የፈጠረው የራሳችን አስተሳሰብ በመሆኑ እሁድ ጠዋት አካባቢያችንን ስናጸዳ አብረን ማጽዳት አለብን›› ብለዋል። አያይዘውም ከሰኞ ጀምሮ አዲስ አስተሳሰብ መልካም ስራና አገርን አንድ ወደ ማድረግ ማተኮር እንደሚያስፈልግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በላከልን መግለጫ እንደገለጸው፤ የክረምት ወራትን ተከትሎ ሊከሰት በሚችል ጎርፍ ምክንያት የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች ቱቦዎችን እንዳይደፍኑ፣ ለጤናና አካባቢያዊ ችግሮች መነሻ እንዳይሆኑ ይህ ሀገራዊ የጽዳት ዘመቻ ንቅናቄ መፈጠሩ አስፈላጊ መሆኑን በመጠቆም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርቧል።
‹‹የመኖሪያ አካባቢያችንን ንጹህና ጽዱ የማድረግ እና የአካባቢ ብክለት የመታደግ ስራ የሁሉም ዜጎቻችን የአካባቢ ተቆርቋሪነትና ተግባራዊ ምላሽ ያስፈልጋል።›› ያለው መግለ ጫው፤ ይህ እንዲሆን ኮምሽኑ ዜጎች የአካባቢ ጽዳትና ጥበቃ አምባሳደር እንዲሆኑ ጥሪ አቅ ርቧል።
በሀገሪቷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንድነት በመንቀሳቀስ መሰረታዊ ሊባሉ የሚችሉ አገራዊ ሪፎርሞች ተግባራዊ መደረግ በመጀመራቸው በርካታ ውጤቶችን ተመዝግቧል የሚለው ይኸው መግለጫ፤ ከፊታችን እሁድ ጀምሮ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት የሚለኮሰው የአካባቢ ጽዳት ዘመቻ ሁሉም ዜጋ በንቃት እንዲሳተፍና ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲተገብረው ኮምሽኑ ጥሪውን አስተላልፏል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2011
በበጋዜጣው ሪፖርተር