ነቀምት፡- አገራዊ አንድነትን ማስጠበቅ የተወረሰው ከአባቶች መሆኑን በማስታወስ፤ ልምዱን በመከተል የተገኘውን ነፃነት በአንድነት በመጠበቅ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ጠቅ ላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት በነቀምት ከተማ ተገኝተው የወለጋ ስታዲየምን በመረቁበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ላይ እንደተናገሩት፤ አገራዊ አንድነትን በማስጠበቅ ለአገራቸው ድል ያስመዘገቡ እና ስማቸው በትውልድ እየተወሳ የሚኖረውን እንደአብዲሳ አጋ ያሉ አባቶችን ፈለግ በመከተል
እና የእነሱን ልምድ በመቀበል ለትውልድ ማስተ ላለፍ ይገባል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኦሮሞ እንደትናንቱ አንድነቱን ጠብቆ ከቆመ፤ ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያ አልፎም ለመላው አፍሪካ ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል። ትናንት ያለጥይት የተገኘው ነፃነት ነገም ያለጥይት የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አለበት ካሉ በኋላ፤ ይህ እንዲሆን እርስ በዕርስ መደማመጥ እና መግባባት ያስፈልጋል ብለዋል።
አመራሮች ስልጣን ሲይዙ ወዲያው ውጤት ያመጣሉ ተብሎ አይጠበቅም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ማህበረሰቡ ጥያቄዎቹ እንዲመለሱለት በትእግስት መጠበቅ እንዳለበት ጠቁመዋል። የወለጋ ህዝብ ጥያቄ እና ፍላጎት በመሪዎች ደረጃ እንደሚታወቅ እና ይህም በጊዜ ሂደት እንደሚፈታ አመልክተው፤ ህዝቡም በትዕግስት መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።
በችግር ጊዜ የወሎ እና የትግራይ ማህበረሰቦች ወደ ወለጋ መጥተው ማረፋቸውን በማስታወስ፤ ወለጋን ማልማት ማለት ሌላውንም አካባቢ ማልማት መሆኑን ጠቁመዋል።
‹‹የኦሮሞ ህዝብ ባህሉን እና ማንነቱን ሲጠብቅ ቆይቷል። ነገ እኛም የበኩላችንን ሰርተን እናልፋለን፤ ሥራችንም ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ ለትውልድ ማስተላለፍ አለብን›› ብለዋል። በተለይ በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ አመራሮች ከራሳቸው አልፈው የአገሪቷን አንድነት ለመጠበቅ ሌት ተቀን በመስራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዕለቱ ከምስራቅ ወለጋ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፤ በተለይ በፍትህ፤ በአካባቢው ያሉ የመሰረተ ልማት ችግሮች ላይ እና በወጣቶች ሥራ አጥነት ዙሪያ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ እና ለእዚህም ማህበረሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትዕግስት መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት በነቀምት ከተማ ተገኝተው የወለጋ ስታዲየምን በመረቁበት ወቅት፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2011
በአዲሱ ገረመው