አስባለው..ባለማሰብ ውስጥ። ላለማሰብ አስባለው..ለማሰብ አስባለው። ላለማሰብ ማሰብ ለማሰብ ከማሰብ በላይ አስጨናቂ እንደሆነ በእለት ተእለት ኑሮዬ ተለማምጄዋለው።
አልጫ በጨው ይጣፍጣል፣ ቡና በስኳር ይጥማል የህይወት ማጣፈጫ ምንድነው? ህይወት ምን ጠብ ቢደረግባት ነው ስኳርና ጨው እንደገባበት አልጫና ቡና የምትጥመው? ስል አስባለው። በተለይ የተሰራ እየበላ፣ የተሰፋ እየለበሰ፣ እግሩ መሬት ሳይረግጥ በማርቼዲስ እየሄደ ሰላም ያጣውን የሰፈራችንን ባለስልጣን ሳስብ..በተለይ እንደ ሀገር በሰፋ ግቢ ውስጥ፣ ቤተ መንግስት በሚመስል ቤት ውስጥ፣ የተለያዩ ዘመናዊ መኪናዎችን እየቀያየረ ደስታ የራቀውን ባለጸጋ አጎቴን በየነን ሳይ..በተለይ ለገነት በቀረበ ተድላ ውስጥ እየኖረ፣ ባየሁት ቁጥር ምራቄን እየዋጥኩ መች ነው እንደሱ የምሆነው የምልለት፣ አንድም ቀን ፊቱ በፈገግታ ሲፈግ ያላየሁትን ጎረቤታችንን ፍሰሀን ሳስብ ህይወት ታመራምረኛለች። ከሁሉ በላይ ላለማሰብ የማስበውን እኔን ሳስበው ህይወት ያሳስበኛል። ላለማሰብ በማሰቤ ውስጥ ከመኖር ጋር ትግል የገጠምኩ ይመስለኛል። ህይወት የሚጀምረው ከማሰብ እንደሆነ አውቃለው። አለማሰብን ማሰብ ግን በመኖር ላይ ሌላ ጣጣ መጨመር ነው እላለው። እኔም ለመኖር ባልጠና ጫንቃዬ ላይ ብዙ እንቶፈንቶ የተሸከምኩ ነኝ። ርካብ በሳተ በህይወት ቼቼ ላይ በሀሳብ አንቀልባ ተይዞ መኖር እንዴት ይቻላል? ይሄም ያልመለስኩት ሌላው ጥያቄዬ ነው።
ህይወት ሙሉ ነገር የላትም። ቀዳዳ እና ጨምዳዳ ናት። ሙሉ ነው ባልከው ነገሯ ላይ ሸራፋ ሆና ታገኛታለህ። እናም እጠይቃለው..‹ህይወት የምትጥመው እንዴትና መቼ ነው? እያልኩ። የህይወት ጣዕም አሜን እያሉ መኖር ይመስለኛል። ለሆነውና ለሚሆነው ተመስጌን እያሉ ማንጋጠጥ። ህይወት አስር ጊዜ መትረን አንድ ጊዜ የምንቆርጣት የማሰብና የማድረግ ቀመር ናትብዬ በማመንኩበት ማግስት ባለማሰቤ ውስጥ ማሰብ ይፈጠራል። እንዲህ የሚል ‹ህይወት መራራ ናት..እንደ እሬት የጎመዘዘች፣ እንደ ሀሞት የመረረች። ስኳር መሆን የማይችሉ የማይቀምሷት..የማይታገሷት። ስኳር መሆን የቻሉ የሚያጣጥሟት›።
ከሀሳብ ለመገላገል እንጠራራለው..አዛጋለሁ። ከሀሳብ ለመገላገል የማደርገው ጥረት ግን መና ነበር..ወዳልደረስኩበት የሀሳብ ባህር ነው የሚወረውረኝ። ሀሳብ ከጣለኝ እንጦሮጦስ ውስጥ ቧጥጬና ተንፈራግጬ አፈር ልሼ እነሳለው። አዲስ ነገር በሌለባት አለም ላይ አዲስ ለመሆን እሞክራለው። ጥረቴ ሁሉ ከንቱ ነበር..ከማሰብ የራቀውን እኔን አላገኘውም። እናም ወደነበርኩበት ተመልሼ በአዲስ ሀይል ባለማሰብ ውስጥ አስባለው። ‹በህይወት ውስጥ አዲስ ነገር የለም። የሆነው የሚሆነው ነው። እየሆነ ያለው ከዚህ በፊት የሆነው ነው። እየሄድንበት ያለው መንገድ ያለፈው ትውልድ የሄደበት ነው። ወደፊትም የሚመጣው ትውልድ በዚህ መንገድ ላይ ነው የሚሄደው። ለእኛ ተብሎ የተሰራ የተለየ መንገድ የለም። አለም ሁሌም አንድ አይነት ናት። መኖር በራሱ መደጋገም ነው። ከዚህ በኋላ ሰው ሆነው የሚፈጠሩ ነፍሶች ዛሬ እኔና እናንተ የሆንውን መሆን እጣ ፈንታቸው ነው። ሲመጣ አዲስ ይመስለናል እንጂ አለም ለሰው ልጅ አዲስ ነገር የላትም። ያኛው ትውልድ ያለፈበትን እየደገምነው ነው።
መኖር አዲስ ነገር የለውም። አለም ዛሬም ድረስ እየሰጠችን ያለው ለመጀመሪያው ልጇ አዳምና ቤተሰቡ የሰጠችውን ነው። ሰው በራሱ ውስጥ አዲስ ነገርን ካላገኘ በአለም ውስጥ አያገኝም..› እዚህ ሀሳቤ ጋ ቆምኩ..እስከዛሬ የሚያቆም ሀሳብ አልገጠመኝም ነበር። ይሄ በእስካሁን ማሰቤ ውስጥ ያሰብኩት ምርጡ ሀሳቤ ሆኖ ልቤ ተቀመጠ። በተመስጦ አሰብኩት ‹ሰው በራሱ ውስጥ አዲስ ነገር ካላገኘ በአለም ውስጥ አያገኝም› ሀሳቤ ብርቅ ሆኖብኝ ደገምኩት።
እናም አልኩኝ ህይወት አንድ አይነት ናት..በተደገመና በተደጋገመ፣ በሚደጋገምም ህይወት ውስጥ ነን። አዲስ ነገር በሌላት አለም ውስጥ በመከራዋ ለምን አጽናኝ እስካጣ አለቅሳለው? ደስታዋንስ ለምን የማያልቅ አደርገዋለው? እያልኩ አሰብኩ። ማሰብን መርታት አቅቶኝ ባለማሰቤ ውስጥ ብዙ አሰብኩ።
ሞትን መግደያ..ሀዘንን ማብረጃ ጥበብ አለን። ብርጭቆና ስኒ ውስጥ ጨምረን እንደምናሟሟው ስኳርና ጨው ህይወት እንድትጥመን ማድረግ የእኛ ፈንታ ነው። ፍቅር የህይወት ጨው ነው። የነፍስ ስኳር ነው። መራራውን እንዳጣፈጥንበት አልጫና ቡና መኖርን የምናጣብጥበት። ፍቅር የሰውነት እጣን ነው..የመኖር ጠጅ ሳር ነው። የአለምን ግማትና ጥንባት የምንሽርበት መጽናኛችን።
እንዲህ ያለኝ ህሊናዬ ወዲያው ያድፍብኛል። ፍቅርን አለቃ ብሎ የተቀበለ ሀሳቤ አፍታ ቆይቶ ያብልብኛል። ‹አዲስ ነገር በሌላት አለም ላይ ፍቅርን የህይወት አዲስ ነገር አድርጌ አልቀበልም› ሲል ይሞግተኛል። በሀሳቤ እሸንፋለው..ለሀሳቤ እጅ ሰጥቼ እኔም እንዲህ ማለት እጀምራለው ‹ሀሳቤ ሆይ ልክ ነህ..በአሮጌ አለም ውስጥ ፍቅር አዲስ ሊሆን አይችልም› ስል ሀሳቤ ይሰማኝ ይመስል ድምጼን ከፍ አድርጌ እናገራለው። በራስ ላይ ማመጽ ይሄ አይደል?
ወዲያው ከምስቅልቅል ሀሳቦቼ መሀል ‹ግን እኮ ፍቅር አሮጌ ሆኖ አያውቅም። የሚል ድምጽ ይሰማኛል። የቱን እንደማምን በገዛ ሀሳቦቼ ግራ እጋባለው። የሀሳቦቼ ፈጣሪ እኔው ሆኜ እንደ ፈለጉ የሚያደርጉኝ ግን እነሱ ናቸው። ወደመጀመሪያው ሀሳቤ አደላው..ፍቅርን አሮጌ ብሎ ወደታበየውና ወደተመጻደቀው ሀሳቤ። ሀሳቤን ሳስበው ልክ ነው..እቅል አስቶ በደስታ የሚያሰክርን ፍቅር የነፍስ ጣዕም አድርጌ መቀበል አልተቻለኝም። ለምን ላለኝ እንዲህ የሚል መልስ አለኝ..‹ያፈቀረን እያለ የማያፈቅረንን እየተከተልን፣ የሚወደን እያለ ለሚጠሉን እያጎበደድን ፍቅርን የህይወት ራስ አድርጎ መቀበል አቃተኝ።
ተስፋን ፈራሁት..ፍቅር በሌለበት ልብና ህይወት ውስጥ ተስፋን የሙጥኝ ማለቴ ሞኝነት መሰለኝ። ‹ለምን ሰው ሆንኩ? ከሆንኩኝስ በኋላ ስኳር መሆን ለምን አቃተኝ? ራሴን ጠየኩ..። ምንም እንደማላመጣ ሳይገባኝ ያለስራው ራሴን ኮነንኩት።
ህይወት አሮጌ ከሆነች፣ መኖር ድግግሞሽ ከሆነ፣ አለም አዲስ ነገር ከሌላት፣ ፍቅር ከእስራታችን ነጻ ካላወጣን መኖር ምንድነው? ህይወት ምንድነው? ሰው መሆን ምንድነው? አልኩ። ለነዚህ ሁሉ መልስ አልባ ጥያቄዬ አእምሮዬ ያቀበለኝ አንድ ነገር ብቻ ነበር..መኖር ባይኖር ሲል። ሀሳቤን ተከትዬ እኔም መኖር ባይኖር አልኩ። መኖር ባይኖር እኚህ ሁሉ ውጣ ውረዶች በማን ላይ ይስተናገዱ ነበር? በማን ላይ ነፍስ ይዘሩ ነበር? ማንን ያስለቅሱ፣ ማንን ያሳዝኑ ነበር? ስል ግራ በገባችኝ ህይወት ላይ አምባ ገነን ሆንኩባት። አፍታ አልቆየሁም ሀሳቤ ከዳኝ..‹መኖር ባይኖር እኮ ምንም ነበርኩ። መኖር ስላለ ነው ባለማሰብ ውስጥ አሳቢ የሆንከው›። ሲል የገዛ ሀሳቤ አብጠለጠለኝ።
ባለማሰብ ውስጥ ያሰብኩት፣ በማሰብ ውስጥ የተረዳሁት፣ በማየትና በመስማት በመኖርም የተገነዘብኩት ህይወትና አለም፣ ፍቅርና መኖር ጣዕሙ ካልገባኝ አለመኖር በስንት ጣሙ ልል ከጀለኝ። ግን አላልኩም ሞጋች ሀሳብ አለኝና። ውሸት መሆኔን ሳስብ ፈራሁ። ያሰብኩት፣ የኖርኩት ዘመን ሀሰት መሆኑ ሲገባኝ መኖር አሰጋኝ። ማሰቤ፣ ባለማሰብ ውስጥ ማሰቤ፣ ራሱ ሀሳቤ አሁን ላለው እኔ ምን ፈየደልኝ? ይሄ ሁሉ ካልሆነ ህይወት መዳረሻዋ የት ነው? ከየት ተጀምራ የት ነው ያቆመችው? አላውቀውም። የህግ ፍጻሜ በሆነው ፍቅር ውስጥ ህይወት ሙሉዕነት ከሌለው፣ ጥማ ካላገኘኋት፣ እምነትና እውነት፣ ተስፋና ጽናት ከተፍረከረኩ መኖር ቅሉ ምንድነው?
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ኅዳር 16/ 2015 ዓ.ም