ይድረስ ጠላቴም፤ ወዳጄም ለነበርከው «ሞረሽ»፤ ዛሬ የጻፍኩልህ ደብዳቤ በህልሜ ከአንድ ፈላስፋ ጋር ስለአንተ እና ስለቤተሰቦቻችን ያወራነውን ነው። አንተ ማን ነህ? ካልከኝ የእኔም ስም ሞረሽ ነው።
ማድረግ የማይችሉትን አደርገዋለሁ እያሉ ለሰዎች ተስፋ መስጠት ከባድ ደዌ መሆኑን በህልሜ ያወራሁት ፈላስፋ ነገረኝ። እውነቱን ነው! ሞረሽ ወንድሜ አንተ እና እኔም መርዝ ወጊው ሃኪም እና ምስር የገቡልንን ቃል መሰረት አድርገን ለዓመታት በማይጨበጥ ተስፋ ውስጥ ተዘፈቅን፤ ተቀዝፎ በማያልቅ የተስፋ ውቂያኖስ ውስጥ ስንዋኝ ኖርን። በከባድ የተስፋ ደዌም ተበላን። እኛ በተስፋ ደዌ መበላታችን ሳያንስ ለሰፈራችን ሰዎችም ሊተገበር የማይችል የተስፋ ቃል እየገባን የተስፋ ደዌ ታማሚ አደረግናቸው።
የተገባልንን ቃል አምነን እና ተስፋ አድርገን መርዝ ወጊው ሃኪም እና ምስር የሚሰጡንን ትዕዛዝ እየተቀበልን ወንድም እና እህቶቻችንን እንዲሁም እናታችንን ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል ከጀርባቸው ስንወጋ ኖርን :: በተላላኪነትም ወደር የማይገኝልን ሎሌዎች ነበርን ።
እናታችን አንተንም ሆነ እኔን ያለመሰልቸት ጡት አጥብታ ከማሳደጓ ባሻገር እንደ ልጅ ምንም ሳይጎድልብን ተንከባክባ እንዳሳደገችን ታውቃለህ! ይሁን እንጂ የምስርን እና የመርዝ ወጊውን ሃኪም ምክር ሰምተን ይሁዳ ከፈጸመው ክህደት ቢበልጥ እንጂ የማያንስ ክህደት በእናታችን ላይ ፈጸመ። መሬት ላይ አሉ የተባሉ በርካታ ግፎችንም ፈጸምንባት ።
በተለይ እኔ ያወቅኩኝ እና ከእኔ በላይ ጠንካራ የሌለ መስሎኝ መላ ቤተሰቤን ወጋሁ ፡ ፡ ጠብቼ ያደኩበትን የእናቴን ጡት ለመቁረጥ ያለ የሌለኝን ሃይል እና ዘዴ ተጠቀምኩ። ወንድሞቼ እና እህቶቼ ግን የእናታቸው ጡት እዳይቆረጥ እጅ ለእጅ ተያያዙ። የተሰጠኝን ተልዕኮ አንዱንም ሳልፈጽም እንደዱቄት በተኑኝ ።
መርፌ ወጊው ሃኪም እና ምስር የቱንም ያህል ቢረዱኝ እንኳን የታሰበውን የእናታችን ጡት መቁረጥ ሳልችል ቀረሁ ። የነበረኝ ሃይል ሙሉ በሙሉ በወንድሞቼ ጡጫ እንዳይሆን ሆነ ።
ጠላቴም ወዳጄም የነበርከው ሞረሽ አሁንም «እኛም ተኩለን ባል አላገባን! » አለች ዝንጀሮ የሚለውን አባባል ደግሜ ላስታውስህ እወዳለሁ ። ምክንያቱም እኔም የቱንም ያህል ከመርፌ ወጊው ሃኪም እና ምስር የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገልኝ ብሰራም እንኳን ማንም ከወንድሞቼ ጡጫ ሊያስጥለኝ አልቻለም። የተረፈኝ ውርደት ብቻ ነው ።
ውርደት ስል ፈላስፋው የነገረኝ አንድ ነገር ትዝ አለኝ ። በእርግጥ አንተ የፈላስፋም ሆነ የአወቂ ንግግር አይገባህም ። ምናልባት ከገባህ ግን ፈላስፋው በተደጋጋሚ ከሚለው አንድ አባባል ልንገርህ በሚል እንጂ። «የትህትና ፍሬዋ ፍቅር ነው ። የትዕቢዕት ግን ፍሬዋ ጥላቻ እና ውርደት ነው።» እኔም በጥላቻና በትዕቢት ታውሬ ቤተሰቦቼን ላጠፋ ተነሳሁ። ግን ምን አገኘሁ! ውርደት ብቻ።
እናም! ሞረሽ ወንድሜ አሁኑኑ በጊዜ ከእኔ ስህተት ተምረህ ለፍቅር እና ለትህትና ቦታ ስጥ። መሬት ከስህተታቸው የማይማሩ ግብዞችን የምትቀጣ ፍርድ ቤት ስትሆን ፤ ከስህተታቸው ለሚማሩት ደግሞ የንስሃ ስፍራ መሆኗንም በደንብ ልትገነዘብ ይገባል ።
ሞረሽ ወንድሜ፣ አሁንም «እኛም ተኩለን ባል አላገባን» አለች ዝንጀሮ የሚለውን አባባል ደግሜ እነግርሃለሁ። ከ80 ዓመታት በፊት ለምጣሞች የእናታችንን ቤት በማን አለብኝነት በወረሩበት ጊዜ አባቴ የለምጣሞች ፓስታ ቀቃይ ሆኖ ተቀጠረ። ከፓስታ መቀቀሉ ጎን ለጎን የባንዳነት ስራ ይሰራ ነበር። በወቅቱ የነበሩ የአባቶችን ወንድም እና እህቶች ለምጣሞችን አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው ከእናታቸው ቤት አባረሯቸው። አባቴም ባንዳ የሚለውን ስሙን ብቻ ይዞ ቀረ። ይህን ተከትሎ በአጉል ተስፋ ተደልሎ የእኛን እናት መንካት ትርፉ ውርደት መሆኑን አባቴ በአንክሮ ነገሮኝ ነበር።
ነገር ግን ሞኝ በራሱ ብልህ ከሰው ይማራል ሆኖብኝ አባቴ የነገረኝን ምክር አልሰማ ብዬና ምስርን እና መርዝ ወጊውን ሃኪም ተማምኜ ራሴን እንደ ጉንዳን እናታችንን እና ቤተሰቦቻችን እንደ ትል ቆጥሬ ተዋጋኋቸው። ዳሩ ምን ይሆናል? እኔ የትል ያህል ጥንካሬ እንዳለኝ የተረዳነው ቆይቼ ነው ።
ጨዋ የሆነ ሰው ተሹሞ ከፍ ክፍ ያለ እንደሆነ ትሁት ይሆናል፤ አይታበይም ። ባለጌ ግን የተሾመ እንደሆነ ይታበያል ። በትዕቢት ታውሮም ግብዝ ይሆናል። ይህ አንደበቱ የማይጠግበው በህልሜ ያገኘሁት የፈላስፈው ቃል ነው ።
እኔም በስልጣን ላይ በነበርኩበት ጊዜ ምስር እና መርዝ ወጊውን ሃኪም በሚመሩኝ የክፋት መንገድ እየተጓዝኩ በትዕቢት ታውሬ ታበይኩ። የእናቴ እና የወንድሞቼን እንዲሁም እህቶቼን ጠባቂ በሆነው «ቅራት» ላይ ግፍ ፈጸምኩ። ይህ የሰራሁት ግፍ ይሔው ዛሬ ዋጋ እያስከፈለኝ ነው። እናም ሞረሽ አንተ ግን ገና ሳትሾም ግብዝነት አጥቅቶህ ለምን እንኳን እንደምትታዘዝ ሳታውቀው ከቆላ ከደጋ ስትንገላጀጅ እንኳንስ እናታችንን ይቀርና ተልዕኮ የሰጡህን እና የጥፋት አጋር ወንድምህ እኔንም እጅ እጅ ብለውኛል።
የሚገርመው ደግሞ አንተና መሰል ወንድሞችህ ግን በማን እንድምትመሩ እና ማን ተልዕኮ እንደሚሰጣችሁ እንዲሁም ዓላማችሁ ግልጽ አይደለም። እኔ እኮ በአንድ ዕዝ ሰንሰለት የምመራ፤ ትልዕኮዬንም ጠንቅቄ የማውቅ እና በእኛ ሰፈር ያሉትን ሰዎች ሙሉ በሙሉ ደጋፊ ማድረግ የቻልኩ ነበርኩ። እናንተ ግን በእኛ ልክ እንኳን አይደላችሁም ። ጭራሽ ተልዕኮ የሚሰጣችሁንም አካል ከሁለት እርምጃ በኋላ የምትረሱ ክንቱዎች መሆናችሁን ሰማሁ ።
ወንድሜ ሞረሽ እመነኝ! ምስርን ሆነ መርዝ ወጊውን ሃኪም እና ምስር የሚነግሩህ የተስፋ ቃል አንዱንም በፍጹም አትቀበላቸውም። እነሱ የማይጨበጥ ተስፋን ተጠቅመው የሚሰሩብንን ግፍ በአንድ የሮበርት ሙጋቤ ሁነኛ አባባል ላሳይህ ። ከአውሮፓ አንድ ነጭ ወደ አፍሪካ ከመጣ የውጪ ዜጋ ጎብኚ ይባላል። ከአፍሪካ አንድ አፍሪካዊ ወደ አውሮፓ ከሄደ ግን ህገ ወጥ ስደተኛ ይባላል። በቡድን ነጮች ወደ አፍሪካ ከመጡ ቱሪስት ይባላሉ። በብዛት አፍሪካውያን ወደ አውሮፓ ከሄዱ ደግሞ ረፍዩጂስ (ስደተኞች) ይባላሉ። ነጮች አፍሪካ ውስጥ መጥተው የአፍሪካውያን አሰሪ ይሆናሉ። አፍሪካውያን አውሮፓ ሄደውም የነጮች ሰራተኛ ነው የሚሆኑት። በቃ! እነሱ እንዲህ ናቸው።
ፈላስፋው እንዲህ ይላል… «ብልህ እና አስተዋይ የሆነ ሰው ውሸታም ሰው ቢወደው አይደሰትም። ምክንያቱም እወድሃለው የሚለው ሰው ውሸቱን እንደሆነ ስለሚረዳ።» እኔ እና አንተ ግን ጥበብ እና ማስተዋል ጎድሎን ውሸታሙ መርዝ ወጊ ሃኪም እና ምስር የነገሩንን ውሸት አምነን ተቀበልን። በቤተሰባችንም የሰው ልጅ ይሰራዋል የማይባል ግፍ ፈጸምን።
አሁን ላይ አንድ እንድትገነዘብልኝ የምፈለገው ነገር አለ። ይህም በእኔ እና በአንተ ሰበብ የተጎዱ ቤሰቦቻችንን ስነልቦና ለመጠገን መስራት እንዳለብን ነው። እስከመቼ ላልተገባ ሹመት እና ስልጣን በራሳችን ቤተሰብ ላይ ቁማር እንቆምራለን ? የውሸታሞች እኩይ ተግባር ማስፈጸሚያስ እንሆናለን ?
ወንድሜ ሞረሽ፣ በህልሜ ያገኘሁት ፈላስፋ በተደጋጋሚ ያሏትን አንድ አባባል ልንገርህ ፤ የነፍስ መከራዋ አለም እና ሹመትን መሻት ነው። ሹመትን በማይገባ መልኩ የሿት እንደሆነ ቅናትን ታመጣለች። ቅናት ሃሰትን ትወልዳለች፤ ሐሰት ሃሜትን ትወልዳለች ። ሐሜት ጥልን ትወልዳለች ። ጥል ግፍን ይወልዳል ። ግፍ ግድያን ይወዳል። መግደልም ሌላ መግደልን ይወልድና እልቂትን ይፈጥራል ።
ሹመትን በተገቢው መንገድ ያሿት እንደሆነ ግን ፍቅርን ትወልዳለች፤ ፍቅር ደግሞ ስምምነትን፣ መስጠትን እውነት መናገርን ትወልዳለች። የሹመት አፈላለግ እንዲዚህ የሆነ እንደሆነ ህግ ትጸናለች። ዓለምም ትታነጻለች።
እኔ እና አንተ ግን ሹመትን በማይገባ መልኩ ስንሻት ኖረናል። ይህ ደግሞ እኔ እና አንተን ጨምሮ በቤተሰቦቻችን ላይ አሰቃቂ ዕልቂትን አመጣች። ስለሆነም ሹመትን በተገቢው መልኩ በመሻት የቤታችንን መሰረት እናጽና!
የአንድ ዓመት ራዕይ ባለቤቶች አበባን አሳደጉ፤ የአስር ዓመታት የራዕይ ባለቤቶች ዛፎችን አሳደጉ፤ የዘላለም ራዕይ ባለቤቶች ደግሞ ሰዎችን ያሳድጋሉ። ይህ ምርጡ እና ተወዳጁ የሩቅ ምስራቅ ፈላስፎች አባባል ነው። ስለዚህ እኛም ከዚህ በፊት ከነበረን ስህተት ተምረን የዘላለም ራዕዮች ባለቤት በመሆን ሰዎችን እናፍራ አደራ!
የአጭር ጊዜ ባለራዕዮች አንሁን። ይህ እኛም ሆንን ቤተሰባችን የትም አያደርሰንም። ይልቁንም ሰፋ አድርገን እናልም ። ህልማችንም በተግባር እንደግፈው። እናታችን ከእኛ ማግኘት የሚገባትን ነገር እንስጣት ።
ይህን ያህል ጊዜ አጥፍቼ ልጽፍልህ የወሰንኩት በእኛ ሰበብ እድገት እና ሰላም ያጣውን ቤታችንን ወደ ትክክለኛው መንገድ ለመመለስ ብዬ ነው ። አይ የለም የምፈልገውን ስልጣን እስካገኝ ድረስ ሎሌነቱ ተመችቶኛል ካልክ አንተም እኔ እንደ ዱቄት መበተንህ አይቀርም ።
ፈላስፈው እንዲህ ይላል «ሰው ሁሉ ልብ ብሎ እንዲሰማህ አንደበትህን እውነት መናገር አስለምዳት ። በሁሉም ዘንድ እንድትወደድ ነፍስህን ሰው መውደድ አስለምዳት» ሞረሽ ወንድሜ ይህ ድንቅ ምክር ነው። በዚህ የፈላስፋው ምክር ምስር እና መርዝ ወጊው ሃኪም ቤተሰባችን ለማጥፋት ያቀዱትን የጥፋት እቅድ ማክሸፍ የሁላችንም ድርሻ ነው። ያልሆነ ተስፋ እና ውሸት ቤተሰብን አይገነባም። ይልቁንም ያጠፋናል እንጂ።
በመጨረሻም ለአይነ ስጋ እስኪያበቃን ሰላም ለሁላችን ይሁን ። እናታችንንም ሆነ እኛን ከክፉ ሁሉ ነገር እንዲጠብቅልን እመኛለሁ። የአንተው ውድ ወንድምህ ሞረሽ ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ኅዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም