በ2014 ዓ.ም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ክስተቶች ለኢንቨስትመንቱ ዘርፍ መሰናክል እንደነበሩ በተደጋጋሚ ተገልጿል:: የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትንና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው መረጃ፤ በአገሪቱ የነበረው አለመረጋጋትና ጦርነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው የኢትዮጵያ ከአጎዋ መታገድ እና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጫና በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተግዳሮቶች መካከል እንደሚጠቀሱ አመልክቷል:: ለአብነት ያህል በበጀት አመቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ማሳካት የተቻለው የዕቅዱን 64 ነጥብ አራት በመቶ (ከሦስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ) እንደሆነ የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል::
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተከሰተው የሰላምና ፀጥታ መደፍረስ በኢንቨስትመንት ተግባራትና በኮርፖሬሽኑ ዓመታዊ እቅድ አፈፃፀም ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረ ማስታወቁ የሚታወስ ነው:: ሰላምና መረጋጋት ከኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ በተለይ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረው የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ በኮርፖሬሽኑ የእቅድ አፈፃፀም ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል:: የፀጥታ መደፍረሱ በኮርፖሬሽኑ ውስጥ የነበሩ ትልልቅ አምራች ድርጅቶችን ትልቅ ጫና ውስጥ አስገብቷቸዋል:: አለመረጋጋቱን ተከትሎ የመጣው የውጭ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘመቻና ጫና አምራች ድርጅቶች ተረጋግተው እንዳይሠሩና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች በቀላሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ ተፅዕኖ አሳድሯል:: በተጨማሪም ኤምባሲዎች ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ ስለነበር አምራቾች በጫና ውስጥ ሆነው ለመሥራት የተገደዱበት ዓመት ነበር::
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሠሩና ምርቶቻቸውን ለዓለም አቀፍ ገበያዎች የሚያቀርቡ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን በረጅም ጊዜ የግዥ ውል ለገዢዎች ስለሚያቀርቡ ምርቶቻቸውን በሌሎች አገራት ወደሚገኙ ቅርንጫፍ ማምረቻዎች እንዲያዞሩ ጫናዎች ነበሩባቸው፤ ግዢዎችም ይሰርዙባቸው ነበር:: በበጀት ዓመቱ አገራዊ የሕልውና ማስከበር ዘመቻ ስለነበር፣ አጠቃላይ የመንግሥት እንቅስቃሴ ቅኝት በሕግና ሰላም ማስከበር ተግባራት ላይ ያተኮረ ስለነበር፣ በልማት/ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖ ነበረው:: በኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት የምርት አገልግሎትና አቅርቦት መቋረጥ፣ የምርት ሽያጭ ገቢ መቀነስ፣ የሥነ ልቦና ጫናዎችንና ሌሎች ችግሮችን አስከትሏል:: ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጣ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱም ይታወቃል።
የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲቀዛቀዝ ምክንያት ለነበረው የሰላም መደፍረስ መፍትሄ ይሆናል የተባለውና በቅርቡ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥት እና በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ለኢንቨስትመንት ዘርፉ መነቃቃትና ማንሰራራት ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል:: የሰላም ስምምነቱ በተለያዩ ጫናዎች ሳቢያ ተቋርጠው የነበሩ የማምረት ሥራዎች እንዲጀመሩ፣ ተቀዛቅዘው የነበሩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሥራዎች እንዲያንሰራሩ እና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ አገሪቱ እንዲመጡ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የተቀዛቀዘው የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲነቃቃ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ የኢንቨስትመንት ማነቃቂያ አሠራር መተግበር እንደሚያስፈልግ የምጣኔ ሀብት ጥናት ባለሙያዎች ያስረዳሉ::
በጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር እና የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ጥናትና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ግርማ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአገሪቱ የተፈጠሩት የሰላም መደፍረሶች የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲቀንስ ማድረጋቸውን ጠቁመው፤ የሰላም ስምምነቱ ለኢንቨስትመንትና ለሌሎች ዘርፎች ያመጣውን ተስፋ ገቢራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆን እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ::
እርሳቸው እንደሚሉት በጦርነቱ ምክንያት የተዳከመውን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማነቃቃት ሕዝብን ያሳተፈ እና የውጭ ፋይናንስ ድጋፍን ያማከለ አሠራር መተግበር ይገባል:: የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (Foreign Direct Investment) ሀብት ለመፍጠር ካለው ሚና በተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ምንጭም ሆኖ ስለሚያገለግል የተቀዛቀዘውን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዳግም በማነቃቃት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግም ያስፈልጋል:: በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠረውን የኢንቨስትመንት መቀዛቀዝ ከችግርነቱ ባሻገር አገር በቀል አምራቾችን ለማነቃቃት እንደጥሩ አጋጣሚ መጠቀምም ይቻላል:: የኢንቨስትመንት ማነቃቂያ እቅዶችም የአገር ውስጥ የማምረት አቅምን በሚያጠናክር መልኩ መታቀድ ይኖርባቸዋል:: ከዚህ በተጨማሪም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት የሚገኙ የገንዘብና የእውቀት አቅም ያላቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎችን ማሳተፍ እንደሚገባም ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ይገልፃሉ::
‹‹የድህረ ጦርነት ምጣኔ ሀብት ግንባታ ራሱን የቻለ ስትራቴጂ ያስፈልገዋል›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ፤ ‹‹የድህረ ጦርነት የምጣኔ ሀብት ግንባታ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ይፈልጋል:: የውጭ ፋይናንስ ምንጭ አማራጮችን ማስፋትን ይጠይቃል:: ለዚህ ደግሞ በጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ በመታገዝ ለጋሽ አገራትንና ተቋማትን ማሳመን እጅግ አስፈላጊ ነው›› ይላሉ::
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የአውሮፓን ምጣኔ ሀብት ለማነቃቃት የተተገበረውን ‹‹የማርሻል እቅድ›› (Marshall Plan) በምሳሌነት የሚጠቅሱት ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ፤ ኢትዮጵያም ከነባራዊ ሁኔታዎቿ ጋር የሚጣጣሙ መሰል እቅዶችን በመተግበር የኢንቨስትመንት ዘርፉንም ሆነ አጠቃላይ ምጣኔ ሀብቱን ማነቃቃት እንደሚገባ ያስረዳሉ::
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ‹‹ፍሮንቲየርአይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁም መንግሥት የተዳከመውን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማነቃቃት በልዩ ትኩረት መሥራት እንዳለበት ይመክራሉ:: እርሳቸው እንደሚሉት፤ የታክስ እፎይታ መስጠትን ጨምሮ፣ ታክስ የመቀነስ፣ የብድር አቅርቦትን የማፋጠን አሠራሮችን በመተግበር የኢንቨስትመንት ዘርፉን ማነቃቃት ይገባል:: ለአገር እድገት ወሳኝ ናቸው ለሚባሉ ዘርፎች ብድርና የውጭ ምንዛሬ ቅድሚያ መስጠትም ያስፈልጋል:: ከፍተኛ የፕሮሞሽን ሥራ በመሥራት በአገሪቱ ሰላም ስለመስፈኑና ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አቅም እንዳላት የማስተዋወቅ ሥራን በላቀ ትኩረት ማከናወን ያስፈልጋል:: ‹‹ከሁሉም በላይ መተማመንን መፍጠር ያስፈልጋል›› ይላሉ::
በድህረ ጦርነት ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል አንዱ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ሊደረግ የሚገባው ድጋፍ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ:: ዛሬ በምጣኔ ሀብታቸውና በፖለቲካ ተፅዕኗቸው የዓለም ኃያላን የሆኑት አገራት የአገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸውን በመደገፍ ረገድ ትልቅ ተሞክሮ አላቸው:: እንዲያውም ለአሁኑ የምጣኔ ሀብት ኃያልነታቸው መሠረት የሆናቸው ከውጭ ጥገኛነት ያላቀቃቸው የአምራችነት አቅማቸው ማደግ እንደሆነ ይታወቃል::
ኢትዮጵያውያን የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎና ድርሻ በየጊዜው እየተሻሻለ እንደመጣ ባይካድም በቂ የሚባል ግን አይደለም:: የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ተሳትፎና ድርሻ እንዲሁም ተወዳዳሪነት ላቅ ያለ እንዳይሆን የሚጠቀሱት ምክንያቶች ዓይነተ ብዙ ናቸው::
ኢትዮጵያ ዘላቂ የምጣኔ ሀብት እንድታስመዘግብ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍና ተወዳዳሪ ማድረግ ይገባል:: ‹‹የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ›› እንዲሉ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት:: የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍና ተወዳዳሪ የማድረግ ጉዳይ በምጣኔ ሀብት ትብብርና በእርዳታ ስም የሚደረግን የሀብታም አገራትንና ተቋሞቻቸውን ጣልቃ ገብነት በማስቀረት ሉዓላዊነትን እስከማስከበር ድረስ የዘለቀ ትርጉምና ፋይዳ አለው::
አምራችነቱን ያላሳደገ እና ፍላጎቱንና አቅርቦቱን በራሱ የማምረት አቅም ላይ ያልመሰረተ ምጣኔ ሀብት፣ ዘላቂ እድገትን ሊያስመዘግብ አይችልም:: የአምራችነት አቅምን ለማሳደግና ፍላጎትን በማሟላት ከንግድ ሚዛን ጉድለትም ሆነ ጉድለቱ ከሚያስከትላቸው ምጣኔ ሀብት ዘለል ጫናዎች ለመላቀቅ አገራዊ አምራችነትን ማሳደግ ያስፈልጋል:: አገራዊ የማምረት አቅምን በማሳደግ ምጣኔ ሀብታዊ እድገትን ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ደግሞ ሁነኛው መፍትሄ ደግሞ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመደገፍ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴው ዋነኛ ተዋንያን እንዲሆኑ ማድረግ ነው::
የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍ ጥረት በብዙ መልኮች ሊገለፅ ይችላል:: የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን የሚያበረታቱ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችን በመቅረፅ፣ ፋይናንስን ጨምሮ ግብዓቶችን በማቅረብ፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦትን በማሟላት እንዲሁም ቢሮክራሲያዊ የአሠራር ውጣ ውረዶችን በማቃለል ለባለሀብቶቹ ድጋፍ ማድረግ ይቻላል::
ዶክተር ሞላ የድህረ ጦርነት ኢንቨስትመንት ማነቃቂያ በይበልጥ የሚመለከተው የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ነው›› ይላሉ:: እርሳቸው እንደሚሉት፣ የውጭ ባለሀብቶች ካላቸው የገንዘብ አቅም አንፃርም ሆነ ከሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎች አንፃር ልዩ ትኩረቱና ድጋፉ መሰጠት ያለበት ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ነው:: የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ጥያቄ ሊነሳበት የማይገባ ጉዳይ እንደሆነና ተጨባጭ ምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ የሚያስረዱት ዶክተር ሞላ፤ ባለሀብቶቹ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በማቅረብ ከሚኖራቸው ሚና ባሻር ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ገቢ ምርቶችን በመተካት እና የወጪ ንግድን በመጨመር ትልቅ አስተዋፅዖ ስለሚኖራቸው ይህን ሚናቸውን የበለጠ እንዲያሳድጉ በመንግሥት ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ያስረዳሉ::
ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ፣ መንግሥት ቢሮክራሲያዊ የአሠራር ውጣ ውረዶችን በማቃለል ረገድ ትልቅ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ ይናገራሉ:: ‹‹መንግሥት አሰልቺ የሆኑ የአሠራር ሰንሰለቶችን በማሳጠርና አገልግሎትን በማቀላጠፍ እንዲሁም የንብረት ጥበቃ በማድረግ ለባለሀብቶቹ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል:: በተጨማሪም ባለሀብቶቹ በኢንቨስትመንት ላይ የሚኖራቸው ተሳትፎ ዘላቂ እንዲሆን መንግሥት የኃይል አቅርቦትን፣ የመንገድና የሎጂስቲክስ አገልግሎቶችን ጨምሮ ለሌሎች የመሠረተ ልማት ችግሮችም መፍትሄዎችን ማበጀት ይጠበቅበታል:: የውጭ ምንዛሬን በፍትሐዊነት ማቅረብም የመንግሥት ኃላፊነት ነው›› ይላሉ::
ሰላምና መረጋጋት በሌለበት አገር የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴና እድገት ፈፅሞ የሚታሰብ አይደለም:: የኢንቨስትመንት ሥራ ሰላም ይፈልጋል:: ግጭትና ጦርነት ያለባቸው አካባቢዎች አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ማግኘት ይቅርና ቀደም ሲል በአካባቢዎቹ የነበሩ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎችና ተቋማትም በነበሩበት የመቀጠል ዕድላቸው እጅግ ዝቅተኛ ይሆናል:: እንኳን በተግባር የሚታይ የሰላም እጦት፣ ተጨባጭ ማስረጃ የሌለው ወሬም ኢንቨስትመንትን ያስደነግጣል:: ለዚህም ነው ሰላም የኢንቨስትመንት መተንፈሻ ነው የሚባለው::
ኢንቨስተሮች የሰላም አየር በማይተነፍሱ አካባቢዎች ለመሰማራት ፍላጎት አያሳዩም:: በእነዚህ አካባቢዎች ቀደም ሲል በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ተሰማርተው የነበሩ ባለሀብቶችም ሥራቸውን ለማቋረጥ ይገደዳሉ:: የሰላም መደፍረስ የኢንቨስትመንት ተግባራትን በሚያሳልጡ መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ስለሚያደርግ የኢንቨስትመንት ተግባራትን በፍጥነት ለማከናወን የሚደረገውን ጥረት እንዲጓተት በማድረግ በጥቅል ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል::
ከዚህ በተጨማሪ የሰላምና ፀጥታ አለመኖር በኢንቨስትመንት ላይ ሊሰማራ የሚገባውን አምራች የሰው ኃይል ከኢንቨስትመንት በማራቅ የዘርፉ እድገት ፈጣን እንዳይሆን ያደርገዋል:: ይህም የምርትና አገልግሎት ተግባራትን ፍጥነትና ጥራት በማዳከም ዝቅተኛ የምጣኔ ሀብት እድገት እንዲመዘገብ ምክንያት ይሆናል::
በአጠቃላይ፤ የሰላም መስፈን ለኢንቨስትመንት ማደግ የመጀመሪያውና ዋናው ቅድመ ሁኔታ ነው:: ያለሰላም የሚታሰብም ሆነ የሚከናወን የኢንቨስትመንት ተግባር የለም:: ሰላም ያልሰፈነባቸው አካባቢዎች፣ ቀደም ሲል የነበራቸውን ኢንቨስትመንት የተነጠቁና ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ዕድሎችንም የማያገኙ እንደሆኑ ከዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ ነባራዊ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል:: የሰላም መስፈን ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የላቀ ሚና እንደሚጫወት ሁሉ ኢንቨስትመንትም ሰላምን ለማስፈን ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ እንዳለው ይገለፃል::
ሰላም ከኢንቨስትመንት ጋር ምን ዓይነት ቁርኝት እንዳለው ኢትዮጵያ ጥሩ ምስክር መሆን ከሚችሉ አገራት መካከል እንደምትመደብ አያጠራጥርም:: በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱ አለመረጋጋቶች በኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ ጉዳት አድርሰዋል::
በቅርቡ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥት እና በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ለኢንቨስትመንት ዘርፉ መነቃቃትና ማንሰራራት ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል:: ይህ የሰላም ስምምነት የታሰበውን ውጤት እንዲያስገኝ ለሰላም ስምምነቱ ገቢራዊነት ቁርጠኛ ከመሆን በተጨማሪ፣ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ መነቃቃትና ማንሰራራት ዋስትና ሊሆኑ የሚችሉ የድህረ ጦርነት የኢንቨስትመንት ማቃቂያ ስትራቴጂዎችን ማዘጋጀትና በብቃት መተግበር ይገባል::
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ኅዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም