የምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በስልጤ ዞን ውስጥ ከሚገኙ ወረዳዎች አንዷ ስትሆን፤ ከዞኑ መዲና ወራቤ በ86 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ 3 ሺህ ገደማ ወረዳዎች መካከል ለወረዳ ትራንስፎርሜሽን እንደ መመዘኛ የተቀመጡ መስፈርቶችን በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ በማድረግ ከተሸጋገሩ ስምንት ወረዳዎች አንዷ ናት። በወረዳዋ የተሞክሮ እና የልምድ ልውውጥ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
የወረዳዋ ነዋሪዎች ዘመናዊ ሽንት ቤቶችን በመገንባትና በመጠቀም፤ በደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ፤ በቤት አያያዝ፤ በአካበቢ አያያዝ፤ ለእናቶችና ህፃናት ጤና በተሰጠው ትኩረት የተመዘገበውን ለውጥ ተከትሎ የህብረተሰቡ አኗኗር ላይ የታየው ተጨባጭ ለውጥ ወረዳዋ ትራንስፎርሜሽኑን ካሳኩት ውስጥ ሞዴል አድርጓታል።
በወረዳው በምዕራብ ሙጎ ቀበሌ ነዋሪዋ ወ/ሮ መርዲያ አብዱልመና በጤና ፓኬጅ ትግበራ ባሳዩት ንቁ ተሳትፎ የልማት ቡድንን በሞዴልነት ከመምራት አንስተው እስከ ክልል ደረጃ ተሸላሚ ለመሆን ችለዋል። እርሳቸው እንደሚሉት ጽዳት ከራስ ይጀምራል ከዚያም ቤት፣ ቤተሰብ፣ ጎረቤት፣ አካባቢ፣ ከዚያም መንደር ቀበሌ እያለ ይቀጥላል። ይህንን ተገንዝበን በመተግበራችን ቀበሌያችን ትራንስፎርሜሽን አፈፃፀም ሞዴል ሆናለች ይላሉ።
ወይዘሮ መርዲያ እንደሚሉት፤ የግል ንፅህናቸውን በተገቢው ሁኔታ ከመጠበቅ ባሻገር የተሻሻለ መፀዳጃ ቤት አስገንብተው በተገቢው መንገድ እየተጠቀሙ ነው። መፀዳጃ ቤት ከተጠቀሙ በኋላ እጃቸውን በውሃና በሳሙና መታጠብም የሰርክ ተግባራቸው ነው። የፈሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ እና ገየላ መታጠቢያ አዘጋጅተው በየጊዜው ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎችን ያስወግዳሉ። ከጤና ባለሙያዎች ባገኙት ትምህርት መሰረት የእንስሳትና የሰው መኖሪያ ለይተዋል። በእርግዝና ወቅት ተገቢውን ክትትል ያደርጋሉ።
በህክምና ተቋማት ውስጥ ይወልዳሉ።
እርሳቸው በሚመሩት የልማት ቡድን የታቀፉትም ተመሳሳይ በሆነ መልኩ የግል እና የአካባቢ ንፅህናን እየጠበቁ መሆናቸውን የተናገሩት ወይዘሮ መርዲያ፤ የተሻሻለ መፀዳጃ ቤት፣ የፈሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ እና የገላ መታጠቢያን አዘጋጅተው እየተጠቀሙ መሆናቸውን አብራርተዋል። ሁሉም የመንደሩ ነዋሪዎች በእሳቸው አስተባባሪነት ዘወትር እሁድ ጠዋት አካባቢያቸውን በጋራ እንደሚያፀዱም ተናግረዋል።
እንደ ወይዘሮ መርዲያ ገለፃ ቀበሌያቸውን እጅግ ልዩ የሚያደርገው ነገር ቢኖር ስለ ቤት ውስጥ ወሊድ ጎጂነት በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው ግንዛቤ ነው። አሁን ላይ ስለ አካባቢያቸው ማህበረሰብ ስለ ቤት ውስጥ ወሊድ ጎጂነት አይነገርም። ምክንያቱም በቤት ውስጥ መውለድ የሚያስከትለውን ጉዳት ከመቀበል አልፎ ቤት መውለድ ነውር ነው ብሎ እስከ ማውገዝ ደርሷል። የግልና የአካባቢ ንፅህና መጠበቅ በመቻላቸው እሳቸውና የአካባቢያቸው ነዋሪዎች በተላላፊ በሽታዎች ከመጠቃት ድነዋል።
የምዕራብ ሙጎ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ሙርሰላ ሰማን እንደተናገሩት፤ በቀበሌዋ 749 አባወራዎች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 709 አባወራዎች ሁሉንም የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጆችን ተግባራዊ በማድረግ የሞዴልነት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። የቀበሌዋ ነዋሪዎች ለለውጥ ዝግጁ በመሆናቸው መሪ እና ተመሪ ይናበባል።
ችግሮችን በመወያየት በጋራ የመፍታት ልምድ ዳብሯል። አንድም እናት በቤት ውስጥ አትወልድም፤ ሁሉም እናቶች በጤና ተቋም ይወልዳሉ። ምክንያቱም በቤት ውስጥ በመውለዳቸው ምክንያት ለሞት የተዳረጉትን እናቶችን በማስታወስ ቤት ውስጥ መውለድ ጎጂ መሆኑን ተረድተዋል። ሁሉም የቀበሌዋ ነዋሪዎች የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ተጠቃሚ ናቸው።
የሌራ ጤና ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱልፈታ መሐመድ እንደተናገሩት፤ ጤና ጣቢያ ደረጃ መሰጠት ያለበትን ሁሉንም አገልግ ሎቶች በጥራት እየተሰጠ ነው። የአዋቂዎችና ህፃናት የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው። የእናቶች የቅድመ ወሊድ እና ድህረ ወሊድ አገልግሎቶችም እንዲሁ።
ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ጤና ጣቢያው የእናቶች ማቆያ ባለቤት ሆኗል። የእናቶች ማቆያም ማህበረሰቡ ነው የገነባው። ማቆያው በመኖሩ ምክንያት እናቶች በወሊድ ወቅት እየቆዩበት ነው። የእናቶች ሞትን በመቀነስ ረገድ አስተዋጽኦ አበርክቷል። የእናቶች ማቆያው ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ መሟላት ያለባቸው ዘመናዊ ነገሮች እንዲሟሉላቸው የተደረጉ ናቸው።
ከጤና ጣቢያ አቅም በላይ የሆኑ አንዳንድ ህክምናዎችን ለመስጠት የሚያስችል ሆስፒታል በአቅራቢያ ባለመኖሩ ህብረተሰቡ ለችግር እየተጋለጠ መሆኑን አንስተዋል። ከጤና ጣቢያ አቅም በላይ ለሆኑ ህክምናዎች ቢያንስ 100 ኪሎ ሜትር ገደማ በመጓዝ ሆሳዕና ወይም ወራቤ ለመሄድ እንደሚገደዱ አንስተዋል። ችግሩ እንዲፈታ ህብረተሰቡ ጥያቄ እያቀረበ መሆኑን አቶ አብዱልፈታ ተናግረዋል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሳህረላህ አብዱላሂ እንደተናገሩት፤ ወረዳዋ ሁሉንም የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጆችን እያንዳንዱ አባወራና እማወራ በማወቅና በመተግበር ለጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን እንደ ምርጥ ተሞክሮ ሊታይ የሚችል ሥራ ሠርታለች።
አመራሩና ህዝቡ ተቀራርቦ መሥራት ከቻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ማሳያ ነች። ችግሮችን ለበላይ አካል ሪፖርት ማድረግ ብቻ ሳይሆን ከአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ችግሮችን መፍታት እንደሚቻልና ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ ከወረዳዋ መማር ይቻላል።
እንደ ወይዘሮ ሰህረላህ ማብራሪያ በተለይም እናቶች በጤና ተቋም ውስጥ እንዲወልዱ በጤና ባለሙያዎች የሚደረገው ክትትልና ድጋፍ፤ ህብረተሰቡ በራሱ ተነሳሽነት የእናቶች ማቆያዎችን መገንባቱ፤ ሊወልዱ ወደ ጤና ተቋም በሚመጡበት ወቅትና ወልደው ወደ ቤታቸው በሚመለሱበት ወቅት ወደ ቤታቸው የሚያደርሷቸው የባጃጅ አገልግሎት በወጣቶች በነፃ መሰጠቱ ለሌሎች ወረዳዎችም እንደ መልካም ተሞክሮ መወሰድ ያለበት ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2011
በመላኩ ኤሮሴ