አዲስ አበባ፡- የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ ለሦስተኛ ጊዜ ለሚተገበረው የማህበራዊ ተጠያቂነት መርሐ ግብር ማስፈፀሚያ የሚውል የ10 ሚሊየን ዩሮ ዕርዳታ ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር ተፈራርሟል።
ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት ልዑካን ትብብር ኃላፊ ሚስተር ኤሪካ ሃበርስ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ በሚገኘው በገንዘብ ሚኒስቴር አዳራሽ ተፈራርመዋል።
አቶ አድማሱ እንደተናገሩት፤ የአውሮፓ ሕብረት ያበረከተው ዕርዳታ በኢትዮጵያ ውስጥ በመተግበር ላይ ያለውን የማህበራዊ ተጠያቂነት መርሐ ግብር አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚረዳ ነው። መርሐ ግብሩ ህብረተሰቡ ስለ አገልግሎት ሰጪው አካል በቂ መረጃ ኖሮት መብቱን አውቆ እንዲጠይቅ በማድረግ የህዝብ ገንዘብ በታለመለት ዓላማ ላይ እንዲውልና መንግሥት የሚያቀርባቸው አገልግሎቶች ውጤታማ፣ ቀልጣፋ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው ያስችላል።
እንደ አቶ አድማሱ ማብራሪያ፤ ከዚህ ቀደም ሁለት ዙር የማህበራዊ ተጠያቂነት መርሐ ግብር በ233 ወረዳዎች ተተግብሯል። ለሁለቱ ዙር ስኬታማነት የአውሮፓ ሕብረት የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። በተሠራው ሥራ መልካም ውጤቶችም ተመዝግበዋል።
ተግባራዊ የተደረገባቸው ወረዳዎች ምን ያህል በጀት እንደተመደበ ለህብረተሰቡ በተለያዩ መንገዶች ማሳወቅ ጀምረዋል። በሁለቱ ዙሮች ጥሩ ውጤት በመመዝገቡ ሦስተኛ መርሐ ግብር ሊጀመር ችሏል። ሦስተኛው መርሐ ግብር ለቀጣይ ሦስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን መርሐ ግብሩ
ተግባራዊ የሚደረግባቸው ወረዳዎች ቁጥርም ወደ 500 ለማሳደግ ዕቅድ ተይዟል።
ለማህበራዊ ተጠያቂነት መርሐ ግብር የሚውለውን አብዛኛው ገንዘብ በኢትዮጵያ መንግሥት ሲሸፈን የቆየ ሲሆን፤ ከአውሮፓ ሕብረት በተጨማሪ ሌሎች አጋር አካላትም ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት ልዑካን መሪ ሚስተር ኤሪክ ሃበርስ በበኩላቸው፤ የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ ሲያበረክት የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።
ባለፈው ሁለት ዙር ለተካሄደው የማህበራዊ ተጠያቂነት መርሐ ግብር ሕብረቱ ድጋፍ ሲያበረክት የነበረ ሲሆን፣ መርሐ ግብሩም መልካም ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል። በመሆኑን የአውሮፓ ለሦስተኛ ዙር መርሐ ግብርም ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን ተናግረዋል።
ማህበራዊ ተጠያቂነትን ለማስፈን ለመንግ ሥት ከሚደረገው ድጋፍ ባሻገር የሲቪክ ማህ በራት ለማህበራዊ ተጠያቂነት ለማስፈን ከፍታ አስተዋጽኦ የማበርከት አቅም ስላላቸው ሕብረቱ በኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ለሚሰማሩ የሲቪክ ማህበራትም ድጋፍ የማድረግ ዕቅድ እንዳለው አመልክተዋል።
እንደ ሃብርስ ማብራሪያ ሕብረቱ ከማህበራዊ ተጠያቂነት መርሐ ግብር ባሻገር በተለያዩ ዘርፎችም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የመሥራት ፍላጎት አለው። አሁን ያለው ሪፎርም ስኬታማ እንዲሆን በቅርቡ ድጋፍ አድርጓል። አሁንም ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በቅርቡ የአውሮፓ ሕብረት ዋና ኃላፊ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሪፎርም ለመደገፍ ዝግጁ ነታቸውን ገልፀዋል። 100 ሚሊየን ዩሮ የበጀት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁነታቸውን መግለፃቸውም የሚታወቅ ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2011
በመላኩ ኤሮሴ