አዲስ አበባ፡- እሁድን ባለመሥራት ብቻ 40 የሚደርሱ እሁዶች በመባከናቸው 400 ኩንታል የመጫን አቅም ያላቸው 4 ሺ299 ተሽከርካሪዎች በትንሹ ከ230 ሚሊየን ብር በላይ ማግኘት የሚችሉበትን ዕድል ተነፍገዋል ሲል የፌዴራል ትራንስፖርት ሚኒስቴር ያስጠናው ጥናት አስታውቋል።
ጥናቱ እንዳመለከተው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ጠቅላላ የባከነ ሰዓት 61 ሺ 9 መቶ 8 ሲሆን ይህም በአማካይ 4ሺ 299 ተሸከርካሪዎች ያለ አግባብ ለ6 ቀናት እንደቆሙ ያመለከተወ ጥናቱ 20 ሺ 440 ተሽከርካሪዎች 24 ሰዓት ያለሥራ
እንደቆሙ በጥናቱ ተገልጧል። በተለይም በማዳበሪያ መጫኛና ማራገፊያ ቦታዎች 5 ሺህ 352 ተሽከርካሪዎች በአማካይ 3 ቀን በመቆማቸው የማንሳት አቅማቸው መገደቡን ጥናቱ ጠቁሟል።
በመሆኑም የሥራ ሰዓትን ያለማሻሻል፣ ተሽከርካሪዎች በመነሻ (በወደብ ) እና በመድረሻ (በመጋዘኖች) ለቀናት መቆም፣ በመጋዘን ቦታ የሠራተኞች ውስንነት፣ የመጋዘን እጥረት፣ የመንገድ ምቹ አለመሆን፣ የመረጃ እጥረት፣
ጭነትን በፕሮግራምና ዕቅድ ያለመምራት፣ በኬላዎችና ቀረጥ ቦታዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ያለመስጠት፣ የገቢ ምርቶች ስታንዳርድ ችግር መኖር እንደምሣሌ ተጠቅሰዋል። እነዚህ ችግሮች መኪኖቹ ፈጣን ምልልስ እንዳያደርጉ እንቅፋት መሆናቸው በጥናቱ ተመላክቷል።
መርከቦች የጫኑትን በፍጥነት አራግፈው ወደ ሥራ እንዳይሠማሩና በወደብ ላይ በሚያደርጉት ቆይታ የዲሜሬጅ ክፍያ እንዲ ከፍሉ ስለሚገደዱ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንደ ሚጎዳም ጥናቱ አፅንኦት ሰጥቶ አስገንዝቧል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2011
በኢያሱ መሰለ