በብሔራዊ ፓርኮች ላይ የሚከሰትን እሳት አዳጋ ለመከላከል ስትራቴጂ እየተቀረፀ መሆኑን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።
የባለሥልጣኑ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይግዛው እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ እስካሁን ድረስ እንደ አገር ኢትዮጵያ ብሔራዊ ፓርኮች ላይ የሚከሰትን የእሳት ቃጠሎ መከላከል የሚያስችል ስትራቴጂ የለውም። የእሳት ቃጠሎ ሲነሳም በአካባቢው ማህበረሰብ ርብርብ አካፋና ዶማ በመጠቀም በቁጥጥር ስር ይውላል እንጂ ዘመናዊ የእሳት ማጥፊያ የለም።
በቅርቡም በባሌ ተራሮች፣ በቃፍታ ሽራሮና በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርኮችም የእሳት ቃጠሎ ተነስቶ በህብረተሰቡና በፀጥታ ኃይሎች ርብርብ በቁጥጥር ስር ሊውል መቻሉን ያወሱት አቶ ጌትነት፤ ይህንን አይነት ችግር ለመቅረፍ ስትራቴጂ እየተቀረፀ ነው ብለዋል።
በስትራቴጂውም የእሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪ፣ እሳት ማጥፊያ ኬሜካሎች፣ ሄልኮፍተሮችንና አውሮፕላኖችን በፓርኮች አካባቢ ዝግጁ ማድረግን የሚያካትት መሆኑን አብራርተዋል።
ሰሞኑንም በሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ዳግም የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ጓሣ የሚባለው የሣር አይነት ተቀጣጣይ በመሆኑ እሳቱን በቀላሉ መቆጣጠር እንዳልተቻለ ገልፀው፣ በአካባቢው ህብረተሰብ ተሳትፎ ለመቆጣጠር ጥረት በመደረግ ላይ መሆ ኑን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2011 በጌትነት ምህረቴ