በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ የሕግ ጥሰቶችና ሥርዓት አልበኝነቶች ምንጫቸው የሥነ ምግባር ዝቅጠታችን ነው የሚሉ በርካታ ናቸው። ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የኃይማኖትና የፍትህ ተቋማት ሚናቸውን ባለመወጣታቸው ሕግ አክባሪ ማህበረሰብ መፍጠር ፈተና መሆኑም ይገለፃል።
ከሀገራችን ህዝብ ውስጥ አብዛኛው ወጣት በመሆኑ የሥነ ምግባር ጉዳይ ትልቅ ሥፍራ ሊሰጠው ይገባል የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ መምህር፣ ደራሲና ገጣሚ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ናቸው። ዶክተሩ ይህን የተናገሩት መጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ‹‹ከመጋቢት እስከ መጋቢት›› በሚል የለውጡ
አንደኛ ዓመት አስመልክቶ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ባቀረቡት ወግ ነው።
በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማስረፅ ዳይሬክቶሬት የሕግ ጥናት ቡድን ዐቃቤ አቶ ሳምሶን ተገኔ በበኩላቸው የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ሥርዓተ ትምህርት ሲቀረፅ ሥነ ምግባሩ የተስተካከለ ዜጋ በማፍራት በሕግ የሚገዛ፤ የተሻለ ሰብዕና ያለው ዜጋና ማህበረሰብ ለማፍራት ነው። በዚህም ዜጋው መብትና ግዴታውን በማወቅ የሌሎችን መብት ያከብራል የሚል እምነት ተይዟል ይላሉ።
ከሥነ ምግባር ትምህርት ጥቅሞች ውስጥ አንዱ ዜጎች መብትና ግዴታ እንዲያውቁ ማድረግ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድነትን፣ መከባበርን፣ መቻቻልን፣ አብሮነትን፣ ሠላምን ያስተምራል። በዚህም የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብ ቶች ዕኩል እንዲከበሩ ጭምር በትምህርት ይዘቱ ተካቷል ሲሉ የአቶ ሳምሶምን ሐሳብ የሚጋሩት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ፕሮግራሞች ጀነራል ዳይሬክተር አቶ ለገሰ ነጋሽ ናቸው።
ይሁን እንጂ በተሰጠው የሥነ ዜጋና የሥነ ምግባር ትምህርት ሕግ አክባሪ ማህበረሰብ ማፍራት ተችሏል ወይ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠት አንችልም የሚሉት አቶ ለገሰ፣ ምክንያቱም በተ ግባር እየታዩ ያሉት ነገሮች ሕግን የሚያከብርና የሚያስከብር ዜጋ ሳይሆን ኢ-ሥነ ምግባራዊ የሆኑ አስነዋሪ ተግባራት እየተፈፀሙ ስለሆነ ‹‹ያልተዘራ
አይታጨድም›› ሲሉ ያለውን የሥነ ምግባር ዝቅጠትና የሕግ አክባሪነት ተዛንፎን ያሳያሉ።
የመንጋ ውሣኔዎች እና ምክንያታዊ አለመሆን የሚያሳዩት የሥነ ምግባርና የሥነ ዜጋ ትምህርታችን በሚፈለገው ደረጃ ውጤት አለማምጣቱን ነው። ለዚህ ደግሞ የኃይማኖት ተቋማት፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድርሻ አላቸው ሲሉም አቶ ለገሰ ይገልፃሉ።
የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ መጋቤ ዘሪሁን ደጉ እንደሚሉት በኢትዮጵያ 95 ከመቶ የሚሆነው ህዝብ ወደ ቤተ-ዕምነት ይሄዳል። ቤተ-ዕምነቶች በየዓመቱ በሚሊየን የሚቆጠር ምዕመንን እንደሚደርሱና የሥነ ምግባር ትምህርት እንደሚሰጡ በጉባኤው ሥር ሆነው ከሚንቀሳቀሱ ሰባት የኃይማኖት ተቋማት መገንዘብ እንደሚቻል ያስረዳሉ።
‹‹ሥነ ምግባርን በሚመለከት የዕምነት አስተምህሮት በየጊዜው የሚሻሻል ነገር የለውም። ቤተ-ዕምነቶች ሁሌም አገሩን የሚወድ፣ ታዛዥ ፣ ሰብአዊነትን፣ አብሮ መኖርን፣ ተካፍሎ መብላትን በአጠቃላይ በጎነትን በሥነ ምግባር አስተምህሮታቸው ይሰብካሉ›› ብለዋል።
በኃይማኖታዊ አስተምህሮ ሥነ- ምግባሩ የማይለወጥ ሊኖር ይችላል ያሉት መጋቤ ዘሪሁን፣ የትምህርት አሰጣጡን እና የአስተማሪዎችን የሥነ- ምግባር ችግር በመፈተሽ የተሻለ ሆኖ መቅረብ ግን ጊዜው ያስገድዳል ይላሉ።
ሥነ- ምግባር ላይ ባለመሠራቱ በተለይ የወጣቱ ምክንያታዊ አለመሆን እና የጅምላ ውሣኔ መቀበሉ በማህበረሰቡ እና በልማት ተቋማት ላይ ችግሮች ተፈጥረዋል የሚሉት አቶ ለገሰ፤ ኢንዱስትሪዎች ሲቃጠሉ፣ መንገዶች ሲዘጉ፣ ንብረቶች ሲወድሙ፣ ሰዎች ሲሞቱ አይተናል። እነዚሁ ሁሉ የሥነ- ምግባር እና የሕግ አክባሪነት ልካችን አዘቅት ውስጥ መግባቱን አሳይተውናል ብለዋል።
‹‹የሥነ- ምግባር ጉድፎቻችን ሕግ አክባሪ አለመሆንን አስከትለዋል፤ ዘመኑ የለውጥ ቢሆንም ነውጥ ይበዛዋል›› ያሉት ዶክተር በድሉም፣ ነውጡ የበዛው የማህበረሰባችን ጠቅላላ የሥነ- ምግባር እሴት ስለጎደለው ነው ባይ ናቸው። በተለይ ወጣቱ ይህን ልብ ማለት አለበት ሲሉም ይመክራሉ። ማህበረሰባችን የሚገኝበት የሥነ- ምግባር ልኬት ከግለሰባዊ ችግር አልፎ ወደ ማህበረሰባዊ የሥነ- ምግባር ዝቅጠት እየገሰገሰ ነው።
አንድ ማህበረሰብ አጥፊዎችን እያነወረ፤ እግረ መንገዱን ህፃናቱን እያስተማረ በማያቋርጥ የሥነ- ምግባር ጥበቃ ልኬቱ እንዳይናጋ ይጠብቃል። አጥፊዎችን በማህበረሰባዊ አደባባይ ጠርቶ አቁሞ ያለመገሰፅ፤ በሕግ ፊት አቁሞ አለመቅጣት ወንጀልን ያበረታታል፤ ያበረክታል ሲሉም ዶክተሩ ያስረዳሉ። በዚህም ሌሎች የግፍና የወንጀልን ፍሬ እንዲመኙ ያደርጋል ባይ ናቸው።
‹‹አንድ ማህበረሰብ ገሚሱ ወንጀል ፈፃሚ፤ ገሚሱ አጨብጫቢ፤ ገሚሱ በዝምታ ታዛቢ ሆኖ ሰው በአደባባይ ተሰቅሏል፤ ዜጎች ወልደው ከብደው ከኖሩበት ተፈናቅለዋል። ሰው ሲቃጠልና ተዘቅዝቆ ሲሰቀል ኳስ እንደሚያይ ተመልካች በሚመለከተው፣ በሩን ዘግቶ በሚታዘበውና ያንን ዜና ሰምቶ ተኝቶ ባደረው መካከል ልዩነት የለም። እንደ ማህበረሰብ ዘቅጠናል። በመሆኑም ግፍ የሚበረክተው ግፈኞች በዝተው አይደለም፤ ማህበረሰቡ በይሉኝታ በጥቅም ትስስርና በምን አገባኝነት በብብቱ ታቅፎ የግፍ መፈልፈያ ስለሆናቸው ነው›› ይላሉ ዶክተር በድሉ።
‹‹ሥነ-ምግባር በሕግ የሚገዛ ማህበረሰብን ከመፍጠር አኳያ ሲመዘን ‹ሕግ አክባሪነቱ የለም› የሚል መነሻ ከተያዘ አገሪቱ አሁን ያለችበት አንፃራዊ ሠላም ላይ አትደርስም። ስለዚህ ማህበረሰቡ በአጠቃላይ ሕግን ተላልፏል ብሎ መውሰድ ጥቅል ፍረጃ ስህተት ውስጥ ይከተናል›› ሲሉ አቶ ሳምሶን የዶክተር በድሉን ሐሳብ ተገቢ አይደለም በማለት ይሞግታሉ።
ምክንያቱን ሲያብራሩም ‹‹ጥቂት ቡድኖች ወይም ኃይሎች የተለያዩ ተግባራትን እየፈፀሙ ሳለ እነዚህን ሕጉ ባስቀመጠው አግባብ እርምጃ ወስዶ ወደ ትክክለኛ መስመሩ ማስገባት አለመቻል እንጂ ማህበረሰቡን የችግሩ ባለቤት ማድረግ አይገባም፤ በመሆኑም ማህበረሰቡ ባልሠራቸው ሥራዎች እንጂ በሌሎች ስህተት መወቀስ አይገባውም፤ ተገቢም አይደለም። የሥነ-ምግባር ችግሮቹ ወንጀል መፈፀም ላይ ከደረሱ ማህበረሰባዊ አይደሉም በሕግ ሊዳኙ ይገባል››።
ሥነ-ምግባር ለሁሉም ወሳኝ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ሳምሶን፣ ማህበረሰቡ ሕግ አክባሪ ባይሆን ኖሮ የመንግሥት መዋቅር ብቻውን ሠላም ማምጣት አይችልም። ስለዚህ ‹‹ማህበረሰቡ መብትና ግዴታውን ያውቃል የሚል እምነት አለኝ›› ባይ ናቸው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሕግ አክባሪ ዜጎች አሉ፤ እነዚህን ሰዎች ማፍራት የተቻለው ደግሞ በተደረገው ማህበረሰባዊ ጥረትም ጭምር ነው ሲሉ ያስገነዝባሉ።
እንደ አቶ ለገሰ እና ሳምሶን ገለፃ፣ በአገሪቷ በሠላማዊ መንገድ የሚኖሩ ዜጎች ሕገ መንግሥቱ ባስቀመጠው ልክ የሚተዳደሩ ዜጎች አብላጫውን ይወስዳሉ። ከዚህ ውስጥ የተወሰነ ብጥብጥና ሥርዓት አልበኝነት ሲኖር የፀጥታ መዋቅርን ተጠቅሞ ማስተካከል ይቻላል ወይም ደግሞ በመንግሥት ደረጃ የተቋቋሙ ተቋማት ተግባራዊ ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ። በእርግጥ ሥነ-ምግባር እና የሕግ አክባሪነት ሚዛኑ እንዳይዛነፍ ከቤተሰብ ጀምሮ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች ሊከናወኑ ይገባል።
በመሆኑም ህዝቡ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ ሠላም እንዲሰፍን፣ መቻቻል እንዲረጋገጥ ሰፊ የሥነ- ምግባር ሥራ እንዲሠራ የአንበሳውን ድርሻ ሊወስድ ይገባል ሲሉ ይናገራሉ። የተጠናከረ የሥነ ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት ያስፈልጋል። ለዚህም ወላጅ ትልቅ ሚና አለው። ከወላጅ ቀጥሎ ማህበረሰብ፣ ትምህርት ቤት ሁሉም ሚና እንዳላቸው ይገልፃሉ።
ባለፈው አንድ ዓመት ከኢትዮጵያዊ ሥነ- ምግባር ውጭ በሆኑ መልኩ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ዜጎች በጅምላ ውሣኔ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። ከ‹‹ክልል ውጣ›› በሚልም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
ዶክተር በድሉ በቀጣይ በሦስት ጉዳዮች ላይ ሰፊ ሥራ መሠራት አለበት ይላሉ፤ አንደኛው የምንገኝበትን የሥነ-ምግባር ይዞታ ማወቅና መቀበል፤ሁለተኛው ከገባንበት አዘቅጥ ለመውጣት ዕቅዶችና የምንከተላቸው መንገዶች አካታች እንዲሆኑ ማድረግ፤ ሦስተኛው ከፖለቲካ ውይይት በበለጠ ሥነ-ምግባራዊ ውይይት ላይ ማተኮር ናቸው። እነዚህ ሥራዎች ካልተሥሩ አገራችን ወደ ከፋ ሥርዓት አልበኝነት ትገባለች ሲሉ ሥጋታቸውን አስቀምጠዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2011
በለምለም መንግሥቱ