ሰሞኑን በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና በክልሉ በሰሜን ሸዋ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች የታጠቁ ኃይሎች በሠላማዊ ዜጎች ላይ ተኩስ ከፍተው የንፁሃንን ህይዎት ቀጥፈዋል። የታጠቁት ኃይሎች የንብረት ዝርፊያም ከመፈፀ ማቸው ባሻገር የዕምነት ቤቶችን እስከማቃጠልና ዜጎችን አፍኖ እስከመውሰድ የደረሰ ሽብር የሚመስል ድርጊት መፈፀማቸውን ከዞኑ አስተዳደር ባለሥልጣናትና ከአካባቢው ነዋሪዎች የተገኘ መረጃ ያመለክታል። ጥቃቱን አስመልክቶ ክልሉን በበላይነት የሚመራው የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በማዕከላዊ ጽህፈት ቤቱ አማካኝነት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የፓርቲው ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው የደረሰው የሰው ህይወትና የንብረት ጥፋት አዴፓ ማዘኑን ገልፀው፤ “የአሁኑን ጨምሮ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች የአዴፓ እና የአማራ ህዝብ አንድነት የሚያስፈራቸው ኃይሎች የፈጠሩት ሴራ ነው” ብለዋል።
የቴክኒክ ቡድን ተቋቁሞ ጥናት እያደረገ በመሆኑ የጠፋውን የሰው ህይዎትና የንብረት መጠን ለማወቅ የቡድኑን ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን ጠቁመው፤ እየተወሰደ ያለውን የመፍትሄ እርምጃ በተመለከተም “ክልሉ ውስጥ ወንጀል ሠርተው በሌላ ክልል እንደበቃለን ብለው የሚያስቡ ካሉ ተስፋቸውን ይቁረጡ፤ ከአጐራባች ክልሎች እስከ ፌዴራል መንግሥት ድረስ ወንጀለኞችን ለመያዝ በጥምረት እየሠራን ነው” ብለዋል።
የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) በበኩሉ የተከሰተውን ችግር አስመልክቶ ከትናንትና ወዲያ መግለጫ አውጥቷል። በሀገሪቱ ያለውን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋትና ማንኛውንም አካል በነፃነት በመደራጀት የፈለገውን የፖለቲካ አጀንዳ በሠላማዊ መንገድ እንዲያራምድ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንና በዚህም ተስፋ ሰጭ ውጤ ቶች መታየት ቢጀምሩም አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች
ግን ለውጡን ተጠቅመው ችግር እየፈጠሩ መሆናቸውን ኦዴፓ በመግለጫው አመላክቷል። “…ሆኖም አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች ዲሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በሰለጠነና በሠላማዊ መንገድ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ከማራመድ ይልቅ የብሔር ጽንፈኛ አስተሳሰብን አንግበው በመነሳት፣ ህጋዊና ሠላማዊ የፖለቲካ ትግል እንቅስቃሴን ከህገ ወጥና የግጭት መንገድ ጋር እያጣቀሱ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ታይቷል” ብሏል መግለጫው።
“ሰሞኑንም በእነዚህ ኃይሎች ቀስቃሽነት ግጭቶች መከሰታቸውና በሰው ህይወት፣ በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል” ያለው ኦዴፓ በግጭቱ ለጠፋው የሰው ህይወት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል። የጥፋት ድርጊቱንም አጥብቆ አውግዟል።
በህዝብ ደም የሚነግዱ የፖለቲካ ቁማርተኞች የተፈፀመው ጥፋት በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት የሌለውና ማንኛውንም ህዝብ የማይወክል መሆኑን የጠቆመው የኦዲፓ መግለጫ፤ “የግጭቱን ጠንሳሾች እና ተሳታፊዎች ለሕግ ለማቅረብ በሕግ አስከባሪ አካላት የሚደረገውን የሕግ የበላይነት የማስከበር እንቅስቃሴ እንዲሳካ ፓርቲያችን ያልተቆጠበ ድጋፍ ያደርጋል” ብሏል።
ህዝብን በማስተዳደር ላይ የሚገኙት የሁለቱ ክልሎች መሪ ፓርቲዎች የጥቃት ፈፃሚውን አካል ማንነት በግልፅ ከመናገር ተቆጥበዋል። ከዚያ ይልቅ “አንድነት የሚያስፈራቸው ኃይሎች” እና “ጽንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች” የሚሉ የተለመዱ ግልፅነት የጎደላቸው አገላለፆችን መጠቀም መርጠዋል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለአዲስ ዘመን የሰጡ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች በበኩላቸው “ጥቃት ፈፃሚው አካል በግልፅ የሚታወቅ ሆኖ እያለ ማንነቱን ለመሸፋፈን መሞከር ወንጀለኛው ለሕግ እንዳይቀርብና ችግሩ ከመሰረቱ እንዳይፈታ የሚያደርግ ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው” በማለት መንግሥትን ይወቅሳሉ።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ “ጥቃት አድራሾቹ እነማን እነደሆኑ እኮ ህዝብ ያውቃቸዋል፤ ጥቃቱ የደረሰባቸው አካባቢዎችና አስተዳዳሪዎች ሳይቀር ጥቃት አድራሾቹ እነማን እንደሆኑ እየገለፁ ባሉበት ሁኔታ አንዳንድ አካላት ምናምን እያሉ መሸፋፈን በእውነቱ ያሳዝናል።
ስለሆነም በተለይም ክልሉን በሚመራው ፓርቲ የመንግሥት ባለሥልጣናት ዘንድ “የጥቃት ፈፃሚዎችን ማንነት ወደፊት ጥናት አድርገን እንገልፃለን” የሚለው አባባል የህዝብን ደህንነት መጠበቅ በለመቻላቸው ኃላፊነትን ለመሸሽ የሚደረግ ትግል ነው ብለዋል።
እናም ህዝብ የሚያውቀውን እውነት ክዶ ወንጀለኛን ለመሸፋፈን መሞከር ህዝብን የበለጠ የሚጎዳ የተሳሳተ አካሄድ ነው። ስለሆነም መንግሥት አጉል መሸንገሉን ትቶ የህዝብን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አለበት፤ በጥቃት ፈፃሚዎቹ ላይም የማያዳግም እርምጃ በመውሰድና ወንጀለኞቹን ለሕግ በማቅረብ በቀጣይም ህዝብ ለተመሳሳይ ጥቃት እንደማይጋለጥ ማረጋገጫ መስጠት ይገባል ብለዋል፤ ፕሮፌሰሩ።
የኢትዮጵያ አገር አቀፍ ንቅናቄ ሊቀ መንበር ኢንጅነር ይልቃል በበኩላቸው “እኔም ሆንኩኝ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያውቀው ጥቃት የደረሰበት አካባቢ ህዝብና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም የሚናገሩት ጥቃቱን የፈፀመው የሰለጠነና የግልና የቡድን መሣሪያ የታጠቀ ኃይል በህዝብ ላይ መተኮሱን ነው” ይላሉ።
ስለሆነም በመንግሥት ዘንድ “ግጭት” እየተባለ የሚገለፀው በጣም የሚያሳዝን ነው። የተደራጀና የታጠቀ ኃይል በሠላማዊ ህዝብ ላይ ተኩስ መክፈቱን ህዝቡ እየተናገረ ባለበት ሰዓት ግጭት ሲባል ማን ከማን ነው የተጋጨው? አያይዘውም “ግጭት ለመፍጠር የሚፈልጉ አካላት የሚለው አገላለጽ መንግሥት በሁሉም ዘንድ ተወዳጅ ለመሆን እየተጠቀመበት የሚገኝ አደገኛ አካሄድ በመሆኑ ነው” ሲሉ በፕሮፌሰር በየነ ሃሳብ ይስማማሉ።
“የመንግሥት ዋነኛ ተግባሩ የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ በመሆኑ መንግሥት እያለ፣ መከላከያ እያለ፣ ደህንነት እያለ በዜጎች ላይ እንዲህ ዓይነት አሰቃቂ ጥቃት መፈፀሙ በጣም የሚያሳዝን ነው” ይላሉ። በመሆኑም ለችግሩ ኃላፊነት መውሰድ ያለበትም መንግሥት መሆኑን ያመላክታሉ።
ወደፊት ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር መደረግ የሚገባውን ነገር በተመለከተም “መንግሥት ሁሉንም አካላት ለማስደሰት መሞከሩን ትቶ የሠላማዊ ዜጎችንና የህዝቡን ደህንነት በመጠበቅና በጽንፈኞች ላይ ደግሞ ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት መቻል አለበት” በማለት የመፍትሔ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 ዕትሙ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና መንግሥት ጊዜ በማራዘም ፖለቲካዊ ቀውሱን ሊወጣው እንደማይችለው ተገንዝቦ… በየአካባቢው ቁጥራቸው እየተበራከቱ የመጡትን የጎበዝ አለቆችና ታጣቂዎችን በሕግ አግባብ ሊያስታግሳቸው ይገባል ማለታቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2011
በይበል ካሳ