᎐በሶስት ብሄራዊ ፓርኮች የእሳት ቁጥጥር፣ አያያዝ ጥናት ሊደረግ ነው
᎐የህግ የበላይነትን ለማስከበር በትኩረት ይሰራል
አዲስ አበባ፡- ሰሞኑን በባሌ እና በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርኮች ላይ የደረሰው የደን ቃጠሎ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ 99 ሄክታር በሚገመት ደን ላይ ጉዳት ማድረሱን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለጸ፡፡
የኮሚሽኑ የደን ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ግርማ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ሰሞኑን በባሌ ተራራ ብሄራዊ ፓርክ አንድ ሺህ 657 የሚበልጥ ሄክታር ፣ በሰሜን ተራራ ብሄራዊ ፓርክም እንዲሁ 342 ሄክታር በድምሩ ሁለት ሺህ ሄክታር ደን በእሳት ቃጠሎ ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡
ፓርኮቹ በተራራማና ገደላማ መልክአ ምድር አካባቢዎች የሚገኙ በመሆናቸው የተከሰተውን የእሳት አደጋ በፍጥነት ለመቆጣጠር አዳጋች እንደነበር የገለጹት አቶ ሀብታሙ፤ በተለይም በመሬት ላይ ያለው የቅጠል ርጋፊና አስታ የተባለው እጽዋት ቃጠሎውን እንዳባባሱት ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በትናንትናው እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ባለስልጣኑ የእሳት ቃጠሎ አደጋን ለመቀነስ በሶስት ፓርኮች የእሳት ቁጥጥርና አያያዝ ጥናት ያደርጋል። በዚህም መሰረት፤ የባሌ
ተራራዎች ብሄራዊ ፓርክ፤ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ እና ሲንቂሌ ፓርኮች በቅድሚያ ተለይተዋል ብለዋል።
እንደ አቶ ኩመራ ማብራሪያ፤ ባለስልጣኑ በሚያደርገው ጥናት በተለየ መልኩ የእሳት ቃጠሎ ሳይከሰት ቀድሞ መከላከልና መቆጣጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ያደርጋል። ቃጠሎ ከተከሰተ በኋላም በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ መቆጣጠር የሚያስችለውን አቅም መፍጠር፤ እንዲሁም ቃጠሎ ከደረሰ በኋላ የደን ሀብቱን መልሶ እንዲያገግም የሚደረግበት ሁኔታ ጥናቱ ትኩረት አድርጎ የሚሰራቸው ዓብይ ጉዳዮች ናቸው።
የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን በበኩላቸው፤ በህብረተሰቡ ዘንድ የግንዛቤ እጥረት መኖሩን ጠቅሰው፤ ይህም በሀገራችን በተለያዩ ፓርኮች እየደረሱ የሚገኙት የእሳት ቃጠሎዎች ለግጦሽ ለእርሻ መሬት ፍለጋ የሚለኮሰው እሳት ዋነኛ ምክንያት ተደርገው ይጠቀሳሉ። ሰሞኑን በባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ለደረሰው የእሳት አደጋ መንስኤ ተመሳሳይ መሆኑን አስታውሰው፤ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን የግንዛቤ ጉድለት ለመሙላት የመስራቱ አስፈላጊነት በባለስልጣኑ ቀጣይ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አመላክተዋል።
የህግ የበላይነት ማስከበር በባለስልጣኑ በኩል ሌላኛው ትኩረት የሚደረግበትና ለድርድር
የማይቀርብ ጉዳይ መሆኑን አክለው የገለጹት አቶ ሰለሞን፤ በባሌ ተራሮች አካባቢ በነበረው ቃጠሎ ወቅት በአንድ ጎኑ ህብረተሰቡ ለማጥፋት ርብርብ ሲያደርግ እንደነበረው ሁሉ፤ አንዳንድ ግለሰቦች ደግሞ ሆን ብለው እሳቱን ለማዛመት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር። በወቅቱ በዚህ ተግባር ላይ ተሳታፊ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በህግ አስከባሪ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሰው፤ በአንዱ ተጠርጣሪ እጅ ተጨባጭ ማስረጃ ተገኝቶበት በስድስት ወር እስር መቀጣቱን ገልጸዋል።
አቶ ሰለሞን አያይዘውም፤« ባለስልጣኑ በቀጣይ እንዲህ አይነት ተግባር የሚፈጽሙ ግለሰቦችን ከህብረተሰቡና ከህግ አካላት ጋር በመቀናጀት ለመቆጣጠር በትኩረት ይሰራል። በተጨማሪም ባለስልጣኑ ጋርም ችግሩ ሲፈጠር የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመግባት ፓርኮቹን ከችግር ለማዳን ሊሰሩ በሚቻልበት ሁኔታ በጥምረት እየሰራ ነው» ብለዋል።
ከ2006 እስከ 2008 ዓ.ም የተጣሉ የጂ ፒ ኤስ ነጥቦችን በመከተል በሳተላይት በተደረገው ሀገራዊ የደን ጥናትና ዳሰሳ የተወሰዱ መረጃዎችን መሰረት አድርጎ የተገኘው ውጤት የሀገራችን አጠቃላይ የደን ሽፋን 15 ነጥብ 5 በመቶ እንደነበር አመላክቷል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2011
በዳንኤል ዘነበ