የተወለዱት ከአዲስ አበባ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሰንዳፋ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው በረህ ወረዳ ውስጥ ነው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደብረብርሃ ከተማ በሚገኙት አፄ ዘረ-ያቆብና ሃይለማርያም ማሞ በተባሉ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል። በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ገብተውም በህግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በደርግ ስርዓተ መንግስት በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በህግ መምሪያ ምክትል በመሆን ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ጊዜ ከሰሩ በኋላ ነፃ የትምህርት እድል አግኝተው በመሄድ በአሜሪካ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ በህግ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ያዙ። በተጨማሪም ኢስተርን በሚባል ሌላው ዩኒቨርሲቲ በኦርጋናይዜሽናል ሊደርሺፕ ሁለተኛውን የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል።
እንግዳችን በትምህርት ላይ ሳሉ የመንግስት ለውጥ ቢመጣም በቀጥታ ወደ አገራቸው በመመለስ በኮሎኔል ፍስሃ ይመራ በነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ውስጥ የህግ መምሪያ ኃላፊ ሆነው ተመደቡ። ሁሉንም የደርግ ህጎች ለ17 ዓመታት በማርቀቅና በማዘጋጀት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ሲሆን የማዕከላዊ ፕላን ወይም ዘመቻ መምሪያ የሕግ ክፍል ኃላፊነትንም ደርበው በመስራት ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነ ይጠቀሳል። የአሸባሪው ትህነግ መንግስት በትረ-ስልጣኑን ከተረከበ በኋላም ለስልጠና ከሄዱበት እንግሊዝ በአዲሱ መንግስት ተጠርተው የፍትህ ሚኒስትር ሆነው ለአንድ ዓመት ያህል አገልግለዋል።
ሆኖም ቃል በተገባላቸው መሰረት በነፃነት የሚሰሩበት ምህዳር ባለመኖሩ በገዛ ፍቃዳቸው ስልጣናቸውን ለቀቁ። የራሳቸውን ቢሮ ከፍተው ለሚድሮክና ለመሰል ትልልቅ ኩባንያዎች የህግ አማካሪ ሆነው ለረጅም ዓመት የሰሩት እኚሁ ሰው በኋላም የማማከር ስራቸውን እርግፍ አድርገው በመተው በበጎ አድራጎት ላይ ከሚሰራ ”ኮምፓሽን‘ ከተባለ ድርጅት ጋር በመሆን የበርካታ ወላጅ አልባ ህፃናትን ህይወት የመታደጉ ስራ ላይ ሙሉ ለሙሉ ትኩረታቸውን አደረጉ።
በኢትዮጵያም አልፈው በኬኒያ፣ ታንዛኒያ፣ ቶጎ፣ ቡርኪናፋሶና መሰል የአፍሪካ አገራት ላይ የህፃናት መርጃ ተቋማትን በማቋቋም ለአህጉሪቱ ጭምር የራሳቸውን አስተዋፅኦ ያበረከቱ ሰው መሆናቸውን ይጠቀሳል። እኛም በተለያየ እውቀትና ሙያ በየደረጃው አገራቸውን ያገለገሉትን የቀድሞ የፍትህ ሚኒስትር አቶ ሽፈራው ወልደሚካኤልን የዛሬው ‹‹የዘመን እንግዳ›› አድርገን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- በደርግ መንግስት ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ታጭተው እንደነበር ሰምተናል፤ እስቲ ስለዚህ አጋጣሚ ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ሽፈራው፡– ልክ ነው፤ ግን ይህ የሆነው የደርግ መንግስት ሊወድቅ ሲል ነው። በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ እንደሚመጣ አስቀድሞም ታውቆ ስለነበር አገሪቱን በተለያየ የስራ መስክ የሚያዘጋጁ ሰዎች ተመርጠው ነበር። ይህ ደግሞ የተደረገው በውጭ ኃይሎችና በመንግስት ነው። ብቻ እንዴት እንደሆነ ባላውቅም እኔን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ተመለመልንና እንግሊዝ አገር ለስልጠና ተላክን። እንዳልኩሽ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ስለሚመጣ መሰረታዊ የመዋቅር ዝግጅት ለማድረግ ታስቦ ነው። በዚያ መሰረት በህጉ ዘርፍ እኔ ነበርኩኝ የተመረጥኩት። በነገራችን ላይ ስልጠናው የሚሰጠው የዓለም ባንክ ነበር። አስቀድሜ እንዳነሳሁልሽ ደርግ እንደሚወድቅ ራሳቸው የደርግ ሰዎች ተገንዝበው ስለነበር ሰው ማደራጀት ጀምረው ነበር።
አዲስ መንግስት ሊቋቋም ሲያስቡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንድሆን በአቶ ፋሲካ በኩል ጥያቄ ቀርቦልኝ ነበር። በመሰረቱ እስከአሁን ድረስ ይህንን ሚስጥር እኔ ለማንም አልተናገርኩም ። በቅርቡ የአቶ ፋሲካ መፅሓፍ ሲመረቅ መድረክ ላይ ነው የተነገረው። ግን እኔ ፈቃደኛ አልነበርኩም፤ ምክንያቱም የማልሰራበትን ቦታ መያዝ አልፈልግም። ብዙ ጊዜ እንዳውም ፖለቲካ ውስጥ መግባትም ስለማልፈልግ የፖለቲካ ድርጅቶች እንድኖር አይፈልጉም ነበር። ግን ዋናው ሰውዬ (ኮሮኔል መንግስቱ ሃይለማርያም) ባልታወቀ ምክንያት ይወዱኝ ነበር። ሁልጊዜ ይህንን ሰውዬ አትንኩት እያሉ ይከራከሩልኝ ነበር። በዚህ ምክንያት እንደሌሎቹ ታስሬም ሆነ ጉዳት ደርሶብኝ አያውቅም። እኔ ለስልጠና እንግሊዝ ሳለሁ ግን የደርግ መንግስት ወደቀ።
አዲስ ዘመን፡- በኢህአዲግ መንግስት የፍትህ ሚኒስትር ሆነው ተሹመው ነበር፤ ይህስ እንዴት ነበር የሆነው?
አቶ ሽፈራው፡– የደርግ መንግስት እንደወደቀ ወዲያውኑ ደግሞ እዛው እንግሊዝ ሆኜ የሽግግር መንግስቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው አቶ ታምራት ላይኔ ደውሎ ‹‹በህገ-መንግስት የሚረዳን ሰው ስለምንፈልግ እርዳን›› አለኝ። እኔ ግን የእኔን ጓዶች በሙሉ ገድላችሁ፤ አስራችሁ፤ አባራችሁ እያለ እኔንም ከእነሱ ጋር ልትቀላቅለኝ ስለሚሆን አልመጣም አልኩት። እሱም ‹‹ግዴለም እኛ ስለእርሶ በደንብ እናውቃለንና መጥተው እንዲያግዙን እንፈልጋለን፤ የፍትህ ሚኒስቴር እንዲሆኑም መርጠኖታል›› አለኝ።
እኔ ግን ነገሩ ጥሩ ነው፣ ሆኖም ስሜን ነው ወይስ ሙያዬን ነው የምትፈልጉት? ብዬ ጥያቄ አቀረብኩለት። በመሰረቱ እኔ ደርግም ስድስት ቦታዎች ላይ ሚኒስትር እንድሆን ጠይቆኝ ነበር። እኔ ግን ፖለቲካ ውስጥ መግባት ስለማልፈልግ አሻፈረኝ ነው ያልኩት። ለእኔ ስልጣን አዲስ አለመሆኑን፣ በስሜ ለመነገድ ከሆነ እንደማልመጣ በነፃነት የሚያሰሩኝ ከሆነ ልመጣ እችላለሁ ብዬ ነገርኳቸው። እንዳውም እዚህ ስመጣ በፅሁፍ ተደራድሬ ነው የመጣሁት። የሚገርምሽ ወዲያውኑ ከኢትዮጵያ ኢምባሲ ማርቼዲስ ተልኮ ነው የተቀበሉኝ። እናም በስምምነታችን መሰረት ለአንድ አመት ያህል በነፃነት የፍትህ ሚኒስትር ሆኜ ብሰራም እየቆየ ሲሄድ ሊያሰሩኝ ባለመቻላቸው በፈቃዴ ለቅቄ ወጣሁ።
አስቀድሜ የለመንኳቸው ፍትህን ከሰጣችሁኝ እኔ ልስራው፤ ሳጠፋ ቅጡኝ በሚል ነው። በዚያ ተስማምተን ነበር የመጣሁት፤ ግን እንዳሰብኩት አልሆነም፤ ፈፅሞ ሊያሰሩኝ አልቻሉም። በነገራችን ላይ እኔ በድህነት ነው ያደኩት። ድህነት ፎቅና ምድር ቤት ሰርቶብኝ ስለኖርኩኝ ስልጣን ባጣ ምን እሆናለሁ ብዬ አልፈራም። እውነቴን ነው የምልሽ መራብን አውቃለሁ፤ መቸገርንም እንዲሁ። ለእኔ ምንም አይደንቀኝም፤ ውስጤ ግን ቆራጥ ነው። ለነገሩ እንደፈለኩኝ ማገልገል ካልቻልኩኝ ስልጣን ላይ መቆየቱ ለእኔ ትርጉም የለውም። ስልጣን እንሰጥሃለን ስላሉኝ ብቻ በማላምንበት ነገር ልሰራ አልችልም። ለዚህም ነው ስራዬን በገዛ ፍቃዴ ለቅቄ ለቀናት ቤቴ ቁጭ ነው ያልኩት።
ከዚያ በኋላ ግን የጥብቅና ፈቃድ ቤቴ ድረስ ተላከልኝና የህግ ቢሮ ከፍቼ በህግ አማካሪነት ቀጠልኩኝ። ለአላሙዲን ድርጅት ለሆነው ሚድሮክ ኩባንያና ገብረየስ ቤኛ ለተባለ ባለሃብት የህግ አማካሪ ሆኜ ሰርቻለሁ። የሚገርምሽ በዚያ ወቅት በመንግስት ቤት በወር አገኝ የነበረውን በቀን አገኝ ነበር። ስለዚህ ስልጣን በመልቀቄ ያጣሁትም፤ የሚቆጨኝም ነገር የለም። ደግሞም የኢትዮጵያ ዋና ችግር ኢኮኖሚ ነው ብዬ አላምንም። ለነመለስም ያልኳቸው ይህንኑ ነው። ዋናው ችግር የግለሰብና የህዝብ የፍትህና የመብት ጥያቄ እንደሆነ ነው የማምነው። ለዚህ ነው አስተዋፅኦ አበረክት ይሆናል ብዬ ኃላፊነት የተቀበልኩት።
እንዳለመታደል ሆኖእነሱ ይዘውት የመጡትን ዓላማ ስለነበር የሚተገብሩት አልተቻለም። በነገራችን ላይ ለእነሱ ስልጣን ስል እኔነቴን አልሸቅጥም ብዬ ስወጣም ከኢህዴግ ምንም አይነት መግለጫ ሳልሰጥና ወደ ውጭ ሳልሸሽ የቆየሁት። ብዙ ጊዜ ሰዎች ውጭ ሄደው በሚዲያ መግለጫ ይሰጣሉ። እኔ ግን አላደረኩትም።
አዲስ ዘመን፡- በማህበራዊና በበጎ አድራጎት ስራዎትም ይታወቃሉ፤ እስቲ ስለዚህ ስራዎት በጥቂቱ ያጫውቱን?
አቶ ሽፈራው፡- በህግ ማማከሩ ስራ ላይ ሳለሁ አንድ ደንበኛዬ ከአሜሪካ ይመጣና እዚህ xገር የድሃ ድሃ የሆኑ ልጆችን መርዳት ስለምፈልጉ ለእነሱ የህግ አማካሪ እንድሆን ጠየቀኝ። ኮምፓሽን ኢንተርናሽናል የተባለው ይሄው ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ በርካታ ህፃናትን ነው የሚረዳው። እኔ ደግሞ እንዳልኩሽ በድህነት ያደኩኝ በመሆኔ ሃሳቡን ወደድኩትና አብሪያቸው መስራት ጀመርኩኝ። በኢትዮጵያ ውስጥ ድርጅቱን በማቋቋም ሂደት ውስጥ የተሳተፍኩኝ ሲሆን በዚህ ምክንያት የጥብቅናውን ስራ እርግፍ አድርጌ ተውኩት። ያ ሲሆን ደግሞ ገቢዬ በ21 በመቶ ቀነሰ። ግን የምፈልገው ስራ በማግኘቴ ደስተኛ ሆንኩኝ።
በመሰረቱ በሂደት ገቢዬም አደገ፤ ቤትም አስቀድሜ ሰርቼ ስለነበር ምንም አልተቸገርኩም። እንዳውም ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት ልከውኝ በህይወቴ ትልቅ የምለውን ስራ ነው የሰራሁት። ታንዛኒያና ኬኒያ ላይ ተቀምጠን ታዛኒያ፣ ጋና፣ ቡርኪናፋሶ፣ ቶጎና ሌሎች አገራት ላይ በመዘዋወር የህፃናት መርጃ ማዕከል አቋቋምኩኝና የህፃናት ጉዳይ ማማከር ስራ እሰራ ነበር። የሚመለከተው አካላት በሙሉ በልጆች ጉዳይ ላይ ትኩረት እንዲሰጡ በመላው አፍሪካ ሰፊ ንቅናቄ ነው ያደረግነው። በነገራችን ላይ በልጅ ውስጥ ልጅን ብቻ ከማየት የበለጠ ስህተት የለም ብዬ ነው የማስበው፤ ልጅን ልጅ አድርጎ የሚያስቀር እይታ እርግማን ነው። ስለዚህ በዚህ ስራ በቆየሁባቸው ዓመታት መንግስታትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ለልጆች የሚገባቸውን ክብርና ስፍራ እንዲሰጡ ነው ብዙ ጥረት ያደረኩት።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ አሁን ላይ ያለው ህገመንግስት ለሚከሰቱ ብሔር ተኮር ግጭቶችና ችግሮች እንደ አንድ መንስኤ ይጠቀሳል። እርሶ በሶስቱ መንግስት ህግ ስርዓት ውስጥ እንዳለፈ ሰው በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ ሽፈራው፡– እኔ በመሰረቱ ብሔርተኝነት ወይም ዘረኝነት የሚባለውን ነገር አሸባሪው ትህንግ ፈጠረው ብዬ አላምንም፤ ይልቁኑ ቤንዚን ነው ያርከፈከፈበት። ምክንያቱም ስሜቱ ነበረ፤ የነበረው ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ነው። በተለይ አንዱ ብሔር ከፍ በማድረግ ሌላውን ዝቅ የማድረጉ ነገር ከአዕምሮ ስፋት አነስተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ነው። እኔ ለምሳሌ በአባቴ ኦሮሞ ነኝ፤ በእናቴ አማራ ነኝ፤ በዚያ ወቅት ይደረግ የነበረውን ነገር ጠንቅቄ አውቃለሁ። በተጨማሪም እኔ በአባቴ የባላባት ልጅ ስለነበርኩ ሰፊ መሬት ነበረን፤ ከብቶቻችን ተቆጥረው የማያልቁ ነበሩ፤ ግን ደጃች ውቤ የሚባሉ ሰው መጥተው በአንድ ቀን መሬታችንን ወሰዱት። ይህንን ያነሳሁልሽ ቀድሞም ቢሆን የመደብ ልዩነት ያመጣውን ችግር እንድትገነዘቢልኝ ነው።
በሌላ በኩል በልጅነቴ የእናቴ አገር ሄጄ ሳድግ በሌላኛው ብሔር ላይ የሚነሱት አንዳንዶቹ ንግግሮች ጨርቅ የሚያስጥሉ ናቸው። እኔ በመሰረቱ በኢትዮጵያውነቴ የማምን ሰው ነኝ። ግን አንዱ በሌላው ላይ የበላይ ልሁን ብሎ የሚያደርገውን ነገር ድሮም ቢሆን አየው ነበር። ይሄ ድንቁርና የሚባለውን ቃል አልወደውም እንጂ አዕምሮ ያለመስፋት ያመጣው ችግር ነው። እነ መለስ ይህንን ስሜት አልፈጠሩትም፤ እንዲገንና ለራሳቸው ዓላማ ሰውን የማባያ ጉልበት ሰጡት እንጂ!። ይህ የብሔርተኝነት ጉዳይ ከስር ከመረመርሽው በአጠቃላይ ሴጣናዊ ሃሳብ የያዘ ነው። ያንን ያመጡት እነሱ ሌላውን በማጣላት ስልጣን ለማቆየት ሲሉ ነው። ደግሞም እንዳየነው በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ የበላይ ሆነው የቆዩት በዚህ ዘዴ ነው። ግን እኛ ውስጥ የነበረን ነገር አቀጣጠሉት እንጂ አልፈለሰፉትም የሚለውን ነገር እንድታሰምሪበት እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ህገ-መንግስቱ በእርግጥ የመብት ጥያቄዎችን ቢመልስም በተጨባጭ መሬት ላይ ተግባራዊ ሆኗል ብለው የማያምኑ ሰዎች አሉ። የእርሶ ሃሳብ ምንድን ነው?
አቶ ሽፈራው፡– በነገራችን ላይ ሶስተኛ ዓለም የምንባለው አገራት አንዱ ምልክታችን በተፃፈውና በሚተገበረው ህግ መካከል ያለው ፍቺ የተለያየ መሆኑ ነው። ይህንን አይነት ችግር የሚታየው በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤ በአብዛኛው የሶስተኛ ዓለም አገራት የህግ አፈፃፀም ሁኔታ ይሄ ነው።
ህገ-መንግስት መፃፍ አያስቸግርም፤ እንደጨሌ ጌጥ ከዚህም ከዚያም ወስዶ መፃፍ ይቻላል። በመሰረቱ በንጉሱም ጊዜ በተለይ የተሻሻለው ህገ-መንግስት በእርግጥ ህይወት ብናለብሰው ኖሮ ጥሩ የሚባል ነበር፤ ይህ ሲባል የሚሻሻል ነገር አልነበረም ማለቴ አይደለም። ደግሞም በዛሬ አዕምሮ ትላንትን መፈረጅ ጥፋት ይመስለኛል። በደርግም ጊዜ በነገራችን ላይ ህገ-መንግስቱን እኛው ነን የሰራነው። የማንስማማባቸው የህግ አንቀፆች ነበሩ፤ እኔ በግሌ የማልስማማባቸውን አንቀፆች በፅሁፍ አቅርቤ ነበር።
ያ ህገ-መንግስት እንዳለ እንኳን ቢተረጎም ኖሮ በአግባቡ መጥፎ አልነበረም። በጥቅሉ ህገ-መንግስቶቹን ብቻ መፈረጅ ለእኔ ይከብደኛል፤ ምክያቱም የተፃፉትን እንኳን በአግባቡ መተግበር ባለመቻላችን ነው። ዋናው ነገር ህይወት መስጠቱ ላይ ነው። እኔ ህግን እንደመኪና ከመነዳሪ (ጎማ) ነው የማየው። የመኪና ከመነዳሪ አየር ከሌለው ራሱንም አይችልም፤ አየር ከተነፋበት አውሮፕላን እንኳን ሊያሳርፍ ይችላል። ምክንያቱም የአየሩ ጥንካሬ ነው የከመንዳሪው ወይም የጎማው ጥንካሬ። ምንማለት ፈልጌ መሰለሽ፤ መንግስት፤ ህዝቡም ሆነ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ልክ እንደጎማው ለህጉ አየር ቢሆኑት አሁን የምናየው ችግር ባልተፈጠረ ነበር።
እርግጥ ነው፤ ይህንን የምልሽ እንደህግ ሰው ሆኜ ሳይሆን እንደማንኛውም ሰው ከሚሰማኝ ስሜት ተነስቼ ነው። እንደተባለው አሁን ያለው ህገመንግስት የሚያከራክሩ አንቀፆች አሉት፤ በተለይ አንቀፅ 39 በሁሉም ሰው እንደሚብጠለጠል ይታወቃል፤ እኔም አልወደውም። ግን ዋናው ችግር እሱ ሳይሆን ሲጀመር ህጉ የተፃፈው ለአሜሪካ፤ ምዕራባውያኑንና ዓለም ባንክን ለማስደሰት ነው። ስለዚህ ለሌላ የተፃፈ ህግ እርስ በርስ ቢያባላን ሊገርመን አይገባም። ምክንያቱም አላማው ይህ ስለነበር ነው። በመሰረቱ እነሱ የፈለጉትን ሁሉ ሲጫንብን ጭነቱን ለማራገፍ የሚችል ህዝብ አልፈጠርንም።
የራሱን እድል በራሱ የሚወስን ትውልድ አላፈራንም። ስለዚህ በህገመንግስት ላይ ትችት ከማቅረብ ይልቅ አተገባበራችንን ብንፈትሽ የተሻለ ይመስለኛል። ምክንያቱም ችግሩ ወረቀቱ አይደለም። ለምሳሌ ከወጡ ከ100 ዓመታት በላይ የሆናቸው የሌላ አገር ህገ-መንግስቶች አሉ፤ እነዚህ አገራት አሁንም ለዛሬ እንደሚመች አድርገው ነው ተፈፃሚ የሚያደርጉት። ይህንን የሚደርገው ደግሞ የዛሬው ሰው ነው። ህግን ህያውና አስፈላጊ የሚያደርገው ሰው ነው። ለዚህ የሚሆን ወይም ይህንን መተግበር የሚያስችል ሰውም ሆነ ተቋማት አልፈጠርንም። እኛ ሳንዘጋጅ የሌሎችን ወስደን ለመተግበር በምናደርገው ጥረት ውስጥ ነው ችግር እየተፈጠረ ያለው። ልክ እንደ እግረኛ መሻገሪያ መንገድ ህጉንም አላከበርነው፤ ምክያቱም የአዕምሮ ዝግጅት የሌለን በመሆኑ ነው። እኔ እንዳውም ስለህገመንግስት ይህንን ያህል መሟገት ቅንጦት ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፤- ግን እኮ በዚህ ህገ-መንግስት ምክንያት ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲከናወን እንደነበር ይታወሳል፤ ይህንን እንዴት እንደቅንጦት እናየዋለን?
አቶ ሽፈራው፡- በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ሁኔታ ዋጋ ቢያስከፍልም ሁልጊዜ እየተሻሻለ ነው የመጣው። በንጉሱ ጊዜ የነበሩ መሰረታዊ የህግ ክፍተቶች በደርግ ጊዜ ተለውጠዋል። ለምሳሌ የአርሶ አደሩ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ተመልሷል፤ ንብረት የማፍራት መብት ደግሞ በኢህአዴግ ዘመን ተመልሷል። ባለፉት 27 ዓመታት የመጣውን ለውጥ መካድ አይቻልም። በአጠቃላይ በየጊዜው እየተሻሻሉ የመጡ ነገሮች አሉ። በተለይ በኢህአዴግ ዘመን ህዝቡ መብቱን ሲያውቅ አይኑ ተከፈተ፤ ለምን? ብሎ መጠየቅ ጀመረ። ይህ ደግሞ መልሶ ለአሸባሪው ሕወሓት መንግስት ችግር ሆነ። ልክ እንደእነሱ ሁሉ ሌላውም ህዝብ ከአገሪቱ ሃብት የመጠቀም መብት ጥያቄ አቀረበ።
ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞቹም ይታሰሩ የነበሩት የሚደረገውን ነገር ስለሚያጋልጡ ነው። በተጨማሪም ኢኮኖሚውንም ሆነ ፖለቲካውን በሙሉ እኛ ብቻ እንቆጣጠር ማለታቸው ነው በህዝብ ዘንድ ቅሬታ የፈጠረው። በመሰረቱ እነሱ መብትን በህገ-መንግስቱ እንዲካተት ያደረጉት አምነውበት አይመስለኝም። አስቀድሜ እንዳልኩሽ በራሱ ህግን ተፈፃሚ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጁነት አልነበረም። ለአዲሱ ትውልድ የሚመጥንና ጥያቄውን ለመመለስ የሚስችል ስርዓትም ሆነ አካል መፍጠር አልተቻለም። በድሮው አዕምሮና ሁኔታ ላይ ነበር አዲስ ሃሳብ ለመጨመር ትግል ይደረግ የነበረው። ከዚህ አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስለአዕምሮ ለውጥ ብዙ ይናገራል፤ ጭንቅላት ላይ ለመስራትም እየሞከረ ነው ያለው፤ ምንያህል እንደተሳካለት ባላውቅም ግን ይሞክራል።
እንደዚህ አይነት ጥረት ባለፉት ሶስት መንግስታት አላየሁም። ዶክተር አብይ ግን በሰው አዕምሮ ላይ መስራት እንደሚገባ ያምናል፤ ይናገራል፤ ፅፏልም። የትኛው መሪ ነው ታዲያ ይህንን ያደረገው?። ኢህአዴግ ዋና ትኩረቱ ምዕራባውያን መንግስታት ማስደሰት ነበር። ለእነሱ ደስ የሚላቸውን የደርግና እዚህ ደግሞ የፈለገውን ይሰራል፤ ያ ነው እንግዲህ ተቃርኖው የነበረው። እንዳልሽው የሰብአዊ መብት ጥሰቱ በሽበሽ ሆኖ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የምዕራቡ ዓለም አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብተው የሚያደርጉትን ጫና እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ሽፈራው፡- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአጠቃላይ የፖለቲካ ውጤት እንደሆነ አውቃለሁ። በምዕራባውያኑ የሚመራው ይህ ድርጅት አንዲት እናት ጡቷን የገዛ ልጇን እንዳታጠባ ከልክሎ ለሌሎች ልጆች እንድታጠባ የሚያስገድድ ድርጅት ነው። በአባይ ውሃ ላይ ያደረጉት ይህንን ነው። በነገራችን ላይ ከዚህ ጋር በተያያዘ ‹‹ትውልድም እንደአባይ›› የሚል ፊልም አሰርቻለሁ። እናም ምዕራባውያኑም ሆነ ተመድ ውስጥ ያሉ አገራት ይህንን ያህል የደነቆረ ህሊና ያላቸው ናቸው። ምዕራብውያኑ በተመድ ውስጥ የራሳቸውን ሰዎች በመሰግሰግ የሚፈልጉትን ጉዳይ ብቻ እንዲፈፀም ሲያደርጉ ኖረዋል። በመሰረቱ ድርጅቱ ‹‹የተባበሩት መንግስታት›› ይባል እንጂ ከስም ውጭ የሌለ ተቋም ነው።
ይቅርታ አድርጊልኝና ምዕራባውያኑ ድርጅቱን ደፍረውታል፤ አዋርደውታል። ስለዚህ በእነሱ ህሊና የሚንቀሳቀስ ስለሆነ ጥሩ ነገርም ቢያመጡ እኔ ጥሩ ነው ብዬ ለመቀበል እቸገራለሁ። ምክንያቱም ሁልጊዜም ከጥሩ ስራቸው በስተጀርባ ሌላ ፍላጎትና ተንኮል በመኖሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአፍሪካ ህብረት በኩል ከአሸባሪው ትህነግ ጋር የሚደረገው የሰላም ንግግርስ ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል ብለው ያምናሉ?
አቶ ሽፈራው፡- በአፍሪካ ህብረት በኩል መነጋገር የኢትዮጵያ መንግስትም አቋም ነው። እነሱ ይህንን ያሉት ተገደው እንጂ ፈልገው ነው ብዬ አላምንም። ምዕራባውያኑ በአፍሪካ ህብረት በኩል የሚደረገውን ድርድር የተቀበሉት ምርጫ ስላጡ ነው። ቀድሞም ቢሆን የእነሱ እቅድ ይህ አልነበረም። በተለይ እንግሊዝ የምትባል አገር ድሮም ቢሆን ኢትዮጵያ እንዳታድግና በሃብቷ እንዳትጠቀም ያልማሰችው ጉድጓድ የለም። የአባይ ወንዝ እንዳንጠቀምበት ከማድረግ ጀምሮ የቀለበት መንገዱም እንዳይጠናቀቅ ብዙ ጥረት አድርጋ እንደነበር ይታወቃል።
እንደሚታወቀው ቀለበት መንገዱ መግጠም ያልተቻለው በእንግሊዝ አሻጥር ምክንያት ነው። አሁንም ቢሆን የአዲስ አበባ አብዛኛውን መሬት ያየዘችው እንግሊዝ ነች። የኢትዮጵያ ካርታ በዚህ መልኩ እንዲሰራ ያደረጉትም እነሱ ናቸው። በነገራችን ላይ ቅኝ ግዛት እኮ ከሌሎቹ የአፍሪካ ሃገራት በላይ ክፉቱ አግጥጦ የሚታየው እኛ ላይ ነው። ምክንያቱም አልሸነፍ ባይነታችንን ቀድመው ስለሚያውቁ በቻሉት ሁኔታና አጋጣሚ እኛን ከመጉዳት ተኝተው የማያድሩ በመሆናቸው ነው። ምዕራባውያኑ ስለሰብአዊ መብት ለመናገር የሞራል ብቃት የላቸውም። ዩክሬን ውስጥ ከራሺያ ጋር ከሚያዋጓቸው ሰዎች መካከል አልቃይዳዎች አሉበት። የአሜሪካ ህዝብና መንግስት ገንዘብ ከፍሎ ነው የሚያዋጋው። ይህንን ታዲያ እያየን የሰብአዊ መብትን ያከብራሉ፤ ስለሰብአዊ መብት ይጨነቃሉ ተብሎ አይታመንም።
በአጠቃላይ እነሱ ለሚያወጡት ሪፖርት ምንም ትኩረት አልሰጠውም። በመሰረቱ የሰላም ውይይቱ ውጤታማ ስለመሆኑ ጥርጥር አለኝ፤ ይህንን የምልሽ በአሸባሪው ትህነግ በኩል ብቻ ሳይሆን የምዕራባውያኑ ብዙ እጅ ስላለበት ነው። በተለይ አሜሪካኖች ጉዳዩን ሙጭጭ አድርገው የያዙት በመሆኑ ከስኬት ይደርሳል ብዬ አላምንም። ይህም ቢሆን ግን በእኛ ላይ የሚደረገው ተፅዕኖና በብዙ መከራ ውስጥ ብንሆንም ለቀረው የአፍሪካ ህዝብ የምዕራባውያን ማንነትን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። እኛ ዋጋ ብንከፍልም፤ ትግላችን በራሱ ሌሎችን አፍሪካውያንን ያነቃል። ሰው እንወዳለን ቢሉም፤ እነሱ ሰብአዊ መብት ከራሳቸው ውጪ አያውቁም።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ደግሞ እስቲ ከፃፋዋቸው አራት መፅሓፍቶች መካከል የተወሰኑትን ይዘት ያብራሩልን?
አቶ ሽፈራው፡- በቅርቡ ከፃፉኩት መካከል አንደኛው ‹‹ የሰው ተመኑ ስንት ነው? ›› የተሰኘ ሲሆን ይህንን መፅሃፍ ልፅፍ የቻልኩት ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በአገራችን እየሆነ ባለው ነገር መተኛት ስላቃተኝ ነው። ሰው እንዴት እንደአፈር በአካፋ ይወረወራል? እርጉዝ ሴት እንዴት ነው ከኖረችበት አካባቢ የምትባረረው፤ የምትታረደው?። ሰው እንዴት ተዘቅዝቆ ይሰቀላል? የሚል ጥያቄ ሁልጊዜ ይመላለስብኝ ነበር። ስለዚህ ሁለት ሃሳቦች ወደልቤ መጥተው አነቁኝ። ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰው ምን እንደሆነ የራሴን አስተዋፅኦ ላበርክት ብዬ ነው። ሆኖም መፅሓፉ ገና ገበያ ላይ አላወጣሁትም፤ ምክንያቱም በብዛት እንዲሰራጭ ስለምፈልግና ለዚህ ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን ድጋፍ ስለሚያሻኝ ነው። በነገራችን ላይ የሽያጩን ገቢ ሙሉ ለሙሉ የሚውለው ለበጎ አድራጎት ነው።
ወደ ጥያቄሽ ስመለስ ይህንን መፅሃፍ መፃፍ የጀመርኩት የኢትዮጵያ ህዝብ አማኝ ስለሆነ ሰው በፈጣሪ እይታ ምን ይመስላል ከሚል ነው። መፅሃፉ በአብዛኛው አራት ሃሳቦች ነው ያሉት አንደኛው ሰው በእግዚአብሔር እይታ ምን ይመስላል?፤ እግዚአብሔር ሁሉን ከፈጠረ በኋላ ሰውን የፈጠረው ለሰው ልጅ ያለውን ክብር ነው የሚያሳየው። ምክንያቱም እኛ ልክ የክብር እንግዳ እንደምንቀበል ነው ሁሉን ለሰው ልጆች ምቹ አድርጎ ሲጨርስ የፈጠረን። ያ ነው ለሰው ልጅ ያለው ቦታ። ሌላኛው የመፅአፉ ክፍል ሰው በሰው እይታ ምን እንደሚመስል ነው የሚተነት ነው። ሰው በዓለም ጦርነት፤ በመደብ ትግል፤ በሃይማኖት ምክንያት እንዴት እንደተጨራረሰ ያሳያል፤ ሰው በሰው እይታ ዥንጉርጉር መሆኑን ይገልፃል። አሁን ደግሞ ብሶ ብሶ በዘር መከፋፈል ጀመረ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ተበደልን የሚሉ ሰዎች ጉልበት ሲያገኙ በዳይ ሆነዋል፤ ስለዚህ ሁሉም ጥፋተኛ ነው የሚል ሲሆን ከመካሰስ ይልቅ የፊቱን ረስተን ለወደፊቱ ጥሩ እንስራ የሚል ነው። ሶስተኛው ደግሞ የዓለም አቀፍ ህብረተሰብ ይህንን እብደት አይቶ ልዩ ልዩ ህጎችን አወጡ፤ አራተኛው ክፍል ከመቃብር የገማ ነገር እያመጣን ዛሬ በፈካው አበባ ላይ አናፍስ የሚል ነው። ጥፋት የምንለውን እንዘርዝር፤ ጀግና እንሁን። ጀግንነት ማለት ደግሞ ‹‹ተበድዬ ነበር ይቅርታ አደርጋለሁ››፤ ‹‹በድዬ ነበር ይቅርታ እጠይቃለሁ›› ማለት መቻል ነው። እንማማር፤ ይህንን የሚያሳይ ሃውልት በየክልሉ ይተከል፤ በየትምህርት ቤቱ ወደፊት ላለመካሰስ ቃል ገብተን አርማ እናስቀምጥ።
ያለፈው ትላንት ዛሬን አይጠቅምም የሚል ድምዳሜ ነው ያለው። ሁለተኛው መፅሃፍም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፤ ርዕሱ ”የግለሰብ ሚና‘ ሲሆን ክፋትን ለመቃወም ፤ መልካምን ለመደገፍ አስተዋፅኦ ማድረግ እችላለሁ፤ እኔ ቁም ነገር ነኝ የሚል ሃሳብ ነው ያለው። እኔ ልዩነት ማድረግ እችላለሁ ብዬ በራሴ አምናለሁ። ይህንንም ስፅፍ መፅሃፍ ቅዱስን ጨምሮ ማዘር ትሬዛንና ዶክተር አብይን እንደምሳሌ ተጠቅሜያለሁ። ዶክተር አብይ የቆሸሸችውን አዲስ አበባን ውብ አድርጓታል፤ ይህ የሚያሳየው አንድ ሰው ብቻውን ለውጥ ማምጣት እንደሚችል ነው። በአጠቃላይ ይህ መፅሀፍ አርአያ የሆኑ ሰዎችን እንደምሳሌ በማንሳት አሁን ያለው ትውልድ የተፈጠረው በዓላማ መሆኑን ተረድቶ ለዓላማው መኖርና ለውጥ ለማምጣት እንዲጨክን የሚያበረታታ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ በማህበራዊ አገልግሎት ብዙ የሰሩ እንደመሆኑ ለትውልዱ ያሎት ራዕይ ምንድን እንደሆነ ይግለፁልንና ውይይታችንን በዚሁ እናብቃ?
አቶ ሽፈራው፡- አስቀድሜ እንዳነሱት ሰው ልጁን ‹‹አንቱ›› ካላለና ካላከበረ ራሱ ‹‹አንተ›› እና ‹‹አንቺ›› ተብሎ ነው የሚያልፈው። እኛ ልጅን ስናከብር እኛ አንቱ መባላችን ገሃድ ይሆናል። ልጅን ስናሳድግ ገና ከማህፀን ጀምሮ የተከበረ፤ ቁምነገር መሆኑን እየነገርነው ልናሳድገው ይገባል። እኔ እንዳውም የኢትዮጵያ ዋና ችግር ትውልድ ላይ መስራት ያለመሰራቱ ነው ብዬ ነው የማምነው። በተለይ ደግሞ ህፃናት ላይ አልሰራንም። የኢትዮጵያ ንጋት የሚሆነው የኢትዮጵያ ወላጆች ልጆቻቸውን አንቱ ማለት ሲጀምሩ ነው። ትውልድን ‹‹አንቱ ››ያላለ ህብረተሰብ ‹‹አንቱ›› ሳይባል ነው የሚያልፈው፤ አይለወጥም። ስለዚህ የልጆች ነገር ትልቅ ስፍራ ሊሰጠው ይገባል፤ እናክብራቸው፤ ለቁም ነገር ከጡት መጥባት ጀምሮ እናዘጋጃቸው። ምክንያቱም ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳልና ነው። በፍቅርና በአክብሮት ያደገ ልጅ ሌላውን ማክበርና መውደድ አይቸገርም።
አሁን የምናየው የማንነት ግጭት አይፈጠርም ነበር። የኢትዮጵያ እናቶች ስለሰው ልጅ እኩልነት እየነገሩ ልጆቻቸውን ቢያሳድጉ ኖሮ ትውልዱ በማንነቱ ምክንያት አይጣላም ነበር። መጀመሪያውኑ ጥላቻን ማረፊያ ነው የምናሳጣው። በነገራችን ላይ እኔ ይህንን በማሰብ ነው ሰንዳፋ ላይ የልጆች እድገትና ስልጠና ምርምር ማዕከል የከፈትኩት። በዚህ ማዕከል ላይ ወላጆች፤ የመንግስት ባስልጣናት፤ መምህራን ሄደው ይሰለጥናሉ። ይሁንና አሁን ላይ አመራር በተለወጠ ቁጥር ማዕከሉን ለመውሰድ የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሙኛል፤ አሁንም ቢሆን ስራውን ይሰራል። ግን ጉልበቴ ስራው ከማስፋት ይልቅ ቦታውን ለማፅናት መሆኑ ያሳዝነኛል። መስራት ያለብኝን ሳልሰራ የማዕከሉን ህልውና ለማቆየት ሆኗል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ። አቶ ሽፈራው፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2015