‹‹በአሁኑ ጊዜ የትግራይ ሕዝብ ነገር ‹ጩኸት ለቁራ መብል ለአሞራ› እንደሚባለው ነው:: አንዱ ይደክማል፤ ይጮኻል፤ ይሞታል:: ሌላው ይበላል፤ ይጠቀማል:: የትግራይ ሕዝብ ጮኸ የኢትዮጵያ መንግሥትም ጩኸቱን ሰምቶ እርዳታ እንዲገባ ፈቅዶ እርዳታ ወደ ትግራይ ገባ:: ነገር ግን እርዳታውን የተቀበለው፣ የሚሰጠው እና የሚከለክለው፤ ለፈለገው የሚያከፋፍለው በእርዳታው የሚጠቀመው አሸባሪው ቡድን ነው::›› አለ ገብረየስ በምሬት::
የመሸታ ጓደኛው ዘውዴ ‹‹ፍሬ ነገሩን ትቶ የማይረቡና ጥቃቅኖቹን ማንሳት፤ የፈረስ ጭራ ስንጠቃ ጊዜን ከማጥፋት ውጪ ምንም ረብ የለውም:: ሕወሓት እንደሆነ ሲወለድ ያጠለቀውን የሚያወልቀው ሲሞት ነው:: ‹ድመት መልኩሳ አመሏን አትረሳ› እንደሚባለው ማለት ነው:: አሸባሪው ሕወሓት ለትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ጠላት ነው:: ምንም ቢሆን ዓመል አያረጅም፤ ወያኔ ሲወለድ ጀምሮ ለትግራይ ሕዝብ የተሰጠ እርዳታን ሸጦ ጥይት የገዛ ጨካኝ መሆኑን የትኛውም የትግራይ ተወላጅ ደም ውስጥ የታተመ የማይረሳ ታሪክ ነው:: የማይማር ጠላት በእጅ ሲገኝ ደግሞ መቅጣት ነው:: ጠላት ሲገኝ በጥርስ እንጂ በልምምጥ አይሆንም::
ጠላት ምንጊዜም ጠላት ነው:: ምንም ቢያባብሉት ቂሙን ስለማይረሳ ወይም ስለማይተው ለጠላት መዘናጋት አይገባም:: የትግራይ ሕዝብም ቢሆን ጠላቱን ወያኔ ከጉያው አውጥቶ መጣል አለበት:: ይህንን ክፉ ጠላት በእጅ አስገብቶ በጥርስ መንከስ እንጂ መሬት አይንካህ እያሉ መለማመጥ እና ማሽሞንሞን አልፎ ተርፎ ቅዠቱ እንዲሳካለት መደገፍ በራስ ላይ እባብ መጠምጠም ነው:: ወደድክም ጠላህ ጠላቱን በጉያው ይዞ የሚያባብል እንደትግራይ ዓይነቱ ሰው አሁን እየፈፀመ ያለው እንዲያውም እባብ ሳይሆን ራሱ ላይ የሚጠመጥመው ዘንዶ ነው::›› አለና ገብረየስን ለመገሰፅ ሞከረ::
የዘውዴን ንግግር በእርጋታ ሲያዳምጥ የነበረው ተሰማ በበኩሉ ‹‹ትክክል ነው:: በአንድ ጊዜ ሁለቱንም የወደደ ሁለቱንም ያጣል:: ተረቱ እንኳን ሁለት የወደደ አንዱን ሳያገኝ ሔደ ነው፤ የሚባለው:: ብልጣብልጦቹ በከንፈራቸው እየሳቁ በጭካኔያቸው የትግራይን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብን ሲያስጨንቁ በዝምታ ማለፍ እና አንዳንዴም ከወያኔ ጎን ሆኖ መስዋዕትነት መክፈል ለመከራ ያለው መነኩሴ ዳዊቱን ሸጦ፤ አህያ ይገዛል የማለት ያህል ነው:: መነኩሴን የሚያስፈልገው ዳዊት ሆኖ ሳለ፤ ልክ ምርት ወደ ገበያ እንደሚወስድ ነጋዴ ወይም ጭነት እንደሚጭን ገበሬ ዳዊት ሸጦ አህያ መግዛትን እንደባህል ወይም አንዳንዴ እንደግዴታ መቁጠር ተገቢነት ያለው አይደለም::
የትግራይ ሕዝብ ሳይወድ በግዱ በወያኔ የፊጥኝ ተይዞ ለስቃይ ተዳርጓል። «ልጅ አምጣ፣ ስንቅ አቅርብ እየተባለ የቁም ስቃይ ያያል። መንግሥት ቢፈቅድም ሆነ ቢሰጥ አሁንም ቢሆን የትግራይ ሕዝብ ጋር እርዳታ ይደርሳል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው:: ራስ ወዳዱ፤ የሰውን ደም ለማፍሰስ የሚተጋው ቡድን የሚቀልበው ከእርሱ ጎን ቆመው የሚዋጉትን ነው:: ምናልባት እርዳታውን እንደአንድ ማታለያ ሊጠቀምበት ይችላል:: አሁን ስለእርዳታ መድረስ አለመድረስ ከመጨነቅ ይልቅ ዋናው ጉዳይ ይህንን አገርና ወገን ጠል የሆነ የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላት ማሳፈር እና ማጋለጥ፤ ከጎንህ አንቆምም በማለት መገፍተር ይገባል:: አሁን እኮ ሕዝቡም ግራ ገባው….›› አለና በረጅሙ ተነፈሰ ::
ገብረየስ በተሰማ እና በዘውዴ ተከታታይ ድብደባ የተፈፀመበት መሰለውና ትንሽ ቅር ተሰኘ:: ግን ደግሞ ሊሞግታቸው ፈልጓል:: የትግራይ ሕዝብ ወያኔን በጉያው የያዘበትን ምክንያት ለማስረዳት አዳገተው:: ሁለት ሃሳብ ብልጭ አለለት:: ሆኖም በምን መንገድ ያስረዳ? ‹‹ነገር ግን›› ብሎ ጀመረ:: ቀጠለና ‹‹ለማኝ ቢያብድ ስልቻውን አይጥልም፤ ምንም ዓይነት እክል ቢያጋጥም ዓላማን መሳት የማይሆን ነው:: በእርግጥ ወያኔ የትግራይን ሕዝብ ለጦርነት፣ ለርሃብ እና ለሰቆቃ አስጥቶታል:: ይህንን ሳስብ ያመኛል:: እንዴት የወጣበትን ሕዝብ መጠቀሚያ ያደርጋል? እንዴት እስከ ሞት፤ ትውልድ እስከመፍጀት የሚያደርስ ዋጋ ያስከፍላል? ብዬ የጨከነበትን ምክንያት ለማስቀመጥ እቸገራለሁ::
ሕዝቡም አምኖ መቀበል ያቃተው ይህንን ነው:: የትግራይ ሕዝብ ሕወሓትን ወልጃለሁ የሚለው እና የወለደው ነፃነቱን ለማግኘት እንጂ ራሱንም ሆነ ሌሎችን ለመጉዳት አይደለም:: ወይም ኢትዮጵያን ለማፍረስ አይደለም:: ነገር ግን ደግሞ እውነት እውነት ነው:: ሕወሓት የወጣው ከትግራይ ሕዝብ ነው:: ልክ ክፉ ልጅ እንደወለደች እናት የትግራይ ሕዝብ በሕወሓት ክፋት እየተሰቃየ ነው:: ሕወሓት ትናንትም ዛሬም ትግራዋይን ከአጋም የተጠጋ ሲያለቅስ ይኖራል እንደሚባለው አድርጎናል::›› አለ::
ገብረየስ ቀጠለ፤ ‹‹ ሕወሓት ሲታሰብ ፖለቲከኞች እና ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን በሙሉ ማሰብን ያስገድዳል:: የፖለቲካ ሰዎች ሲባሉ አንዳንዱ ስልጣን ብቻ ሲፈልግ፤ አንዳንዱ ሀብት ይፈልጋል:: አንዳንዱ ለሕዝብ እና ለአገር ሲያስብ፤ አንዳንዱ ለስልጣኑ እና ለክብሩ ሲል ይጨነቃል:: ፖለቲከኛ እና ባለስልጣን ብቻ ሳይሆን ታች ያለው ባለሞያውም ቢሆን አንዳንዱ ሲሠራ እና ሲታትር በሥራው ለመርካት ብቻ ሲሆን፤ ለአገሬ ምን ጠብ አደረግኩ ብሎ ሁሉንም ከአገሩ ጥቅም አንፃር ይመዝናል:: የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ይወጣል:: የአገር ፍቅሩን በአፉ ሳይሆን በተግባር በትጋት ሠርቶ ያሳያል:: አንዳንዱ ደግሞ በተቃራኒው ስለሚያገኘው ገንዘብ ብቻ በማሰብ የሥራ ጊዜውን ያባክናል::
አንዳንዱ ባለሙያ ሹመትን ሲፈልግ በስልጣን ዘመኑ ሊዘርፍ ስለሚችለው ገንዘብ እና ስለሚሰራው ቤት እያሰበ ይቃዣል:: ሀብት መፈለግ የፖለቲካኞች እና የባለስልጣኖች ብቻ ሳይሆን የብዙሃን ባለሞያዎችም ፍላጎት ነው:: የወያኔ ባለስልጣናት ደግሞ ጭንቀታቸው የሕዝብ እና የአገር ጉዳይ ሳይሆን፤ የራሳቸው ክብር፣ ስልጣናቸውን ማጣታቸው እና እንደፈለጉ የሚንደላቀቁበትን ገንዘብ ማግኘት አለመቻላቸው የሚያሳብዳቸው መሆኑ መለያ ባህሪያቸው ነው::
አሁንም ጭምር ለሕዝብ ሳይሆን ለራሳቸው ለስልጣናቸው፣ ለክብራቸው እና ቀጣይነት ያለው ዘረፋ ውስጥ መሰማራት ባለመቻላቸው ሕዝቡን ይማግዳሉ:: መዝረፍ ካልሆነላቸው አገር እስከማፍረስ የደረሰ ጥፋት ለመፈፀም ወደ ኋላ አይሉም:: አሁንም ጭምር እንደማይሆንላቸው እያወቁ ሕዝቡን ያወናብዳል:: ሕዝቡ ምን ያድርግ? ምን አቅም አለው? የትግራይ ሕዝብ ላይም ለመፍረድ ያስቸግራል::›› ሲል እያስተባበለ ጥያቄ አቀረበ::
ምላሽ አልጠበቀም በድጋሜ ሌላ ሃሳብ ጨመረ:: ‹‹ አሁን ላይ የትግራይ ሕዝብ ምንም እንኳን ቡድኑን ባይደግፍ ሊያደርግ የሚችለው ምን አለ? ምርጫ አጥቷል:: እነርሱ ዓላማቸው ስልጣን እና ዝርፊያ ብቻ ነው:: ለማኝ ምንም ቢያብድ ስልቻውን እንደማይጥለው ሁሉ እነርሱ ምንም እንኳ የእብደት ደረጃ ላይ ቢደርሱም ፅኑ ፍላጎታቸው በትግራይ ወጣት ደም ተጠቅመው ስልጣን የማግኘት ፍላጎታቸውን ሊተዉት አይችሉም:: ለዚህ ስልቻቸው ሲሉ እንኳን ሕዝቡ እራሳቸውም ቢሆኑ የትኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ናቸው:: ›› አለ::
ገብረየስ ዛሬ ማንም እንዲያስቆመው የፈለገ አይመስልም:: ያለወትሮ አልፎ አልፎ ድምፁ ከቁመቱ በላይ እየተሰማ በምሬት መናገሩን ቀጥሏል:: ‹‹መፍረድ ቀላል ነው:: እያንዳንዳችሁ የትግራይ ተወላጅ ሆናችሁ ዛሬ ትግራይ የምትገኙ ቢሆን ኖሮ የምታደርጉት አሁን ካለው ሕዝብ ተመሳሳይ ነው:: ምክንያቱም ሕወሓትን ልቃወም ብትሉ ከሕወሓት የበቀል ጥርስ ማምለጥ ቀላል አይሆንም:: በኅብረት መነሳትም ቀላል አይደለም:: የሰው ልጅ አስተሳሰብ ፍላጎት እና የድፍረት ደረጃ የተለያየ ነው:: አንዱ ሲደፍር ሌላው ይፈራል:: የደፈረው ፈሪው ሳይደግፈው ወደ ኋላ ሲል የደፈረው ሕይወቱ እንደቀልድ ያልፋል:: የደፈረው ላይ እርምጃ ሲወሰድ ያየው ሌላኛው ለመድፈር ጫፍ ላይ ደርሶ የነበረው መልሶ ወደ ኋላ ይሸሻል:: የበለጠ መፍራት ይጀምራል::
ማንም ቢሆን ከመሞት በምንም መልኩ ቢሆን መኖርን ይፈልጋል:: በተረፈ የውጭዎቹም የትግራይ ተወላጆች አንዳንዶቹ የቀደመው የሕወሓት የጥቅም ተጋሪ በመሆናቸው፤ አሁንም ድረስ ሕወሓትን ደግፈው በአደባባይ ሳያፍሩ ሰልፍ ይወጣሉ:: አንዳንዶቹ ሕወሓትን ባይደግፉም አያገባንም ብለው ጥጋቸውን ይዘው ቆመዋል:: አንዳንዶች ደግሞ የሕወሓትን ሴራና ክፋት ሳያጣሩ እንዲሁም ድርጅቱ የትግራይ ተወላጅን ጨምሮ መላ ኢትዮጵያን ምን ያህል እንደጎዳ ሳያገናዝቡ በዘር ትግሬ ስለሆኑ ብቻ ‹ነገር ወዳጅ ከመንገድ ዳር ቅበሩኝ አለ› እንደሚባለው ተራ ወሬ ላይ አተኩረው መንግሥትን በመቃወም ጊዜ ያጠፋል::›› ሲል ዘውዴ ቆጣ ብሎ የገብረየስን ንግግር ለማስቆም ጥያቄ ማንሳት ጀመረ::
‹‹ደፍሮ ተባብሮ ሕወሓትን ነጥሎ አጋልጦ ስላልሰጠ ከሞት ያመለጠ ማን ነው? የትግራይ ሕዝብ ሕወሓት ይገድለኛል በሚል ስጋት ለመደገፍ ተገዷል ካልክ፤ ሕወሓትን ቢደግፍም በጦርነት እየሞተ ነው:: መሞት ካልቀረ ፈርቶ ሳይሆን ደፍሮ ቢሆን ተመራጭ ነው:: የዘላለም ጠላትን ደፍቶ መሞት ሞት አይደለም ሕይወት ነው:: እንዲህ እንደመዥገር ተጣብቆ ለዓመታት የትግራይን ደም ሲመጥ የኖረን ቡድን አጥፍቶ መሞት ትልቅ ጀግንነት ነው:: ጦርነት ውሎ ከፊት ለፊት ሆኖ ወገን አልገድልም ብሎ ወደ ኋላ ሲመለሱ በሕወሓት አጫፋሪ ከመገደል:: እዛው ከሕወሓት ጋር ተናንቆ ማለቅ ይሻላል::›› አለ ዘውዴ:: ይሔንን በሚመለከት ገብረየስ ምንም ማለት አልቻለም:: ለማሳመን መንገድ አጣ:: ቃላቶች አጠሩት::
የዘውዴን ምት መመለስ አቅቶት ሲያሰላስል፤ ተሰማ ተጨማሪ ሃሳብ መሰንዘር ቀጠለ:: ‹‹ በእውነት ይህንን በተለይ የትግራይ ጠላት የሆነን ድርጅት ሕዝቡ በትክክል ያወቀው አይመስለኝም:: በትክክል አውቆት ለማስወገድ የሚፈልጉ ካሉ ግን በጥቂቱ በጥቂቱ ይሞላል ልቃቂቱ ነው:: የፈለጉትን ሥራ ለማከናወን ስልት ነድፎ በጥንቅቄ አስቦ የሚንቀሳቀስ ካለ መፈፀሙ ሕወሓትም ላይነሳ መቀበሩ አይቀርም:: ለዚህ ደግሞ ጊዜ መስጠት አያስፈልግም:: ማንኛውም ተግባር መከናወን ያለበት በጊዜው እንጂ ጊዜው ካለፈ በኋላ መሯሯጥ ጥቅም የለውም::
በግ የሌለው ቀበሮ አውሬ አትመስለውም እንደሚባለው አንዳንዱ አሁንም ድረስ ሕወሓትን ያመነ ይኖራል:: ግን ደግሞ አስቀድሞ ማንንም የማይምር ዓላማውን ለማደናቀፍ የሚሞክረውን ብቻ ሳይሆን የከፋ ድርጊት ሲፈፅም የማይደግፈውንም ጭምር ለመጉዳት እና ለማጥፋት ወደ ኋላ የማይል መሆኑን ያልተገነዘበ ሰው ለወደፊት ችግር ያደርስብኛል ብሎ ባይጠረጥርም ተጎጂ መሆኑ አይቀርም:: ስለዚህ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለ የትኛውም ሰው ይህ አጥፊ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቀንና ሌሊት የሚሠራ ቡድን በትግራይ ያለውን ተቀባይነት ሙሉ ለሙሉ እንዲያጣ ለማድረግ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል:: ምንም ቢሆን ተቀባይነት በሌለበት ቦታ አንድ ጉዳይ ለመፈፀም ያስቸግራል:: በዚህ በኩል የእነርሱን ያህል በትጋት አሁንም አልተሠራም:: ስለዚህ መሥራት አለባችሁ ›› አለው::
ገብረየስ ‹‹ትክክል ነው:: በቅርብ የሚኖሩ ሰዎች ላይተዋወቁ ይችላሉ:: በእርግጥም ዓይንና ጆሮ ቅርብ ለቅርብ ቢሆኑም ሳይተዋወቁ እንደሚኖሩት ሁሉ ሕወሓት እና የትግራይ ሕዝብ ሙሉ ለሙሉ ተዋውቀዋል የሚል እምነት የለኝም:: ሕወሓትን ላወቀው ‹አይነደረቅ ሌባ ከነቃጭሉ ይገባ› እንደሚባለው ኢትዮጵያን ሲዘርፍ የትግራይን ሕዝብ መነገጃ ሲያደርግ ኖሮ ያለምንም ይሉኝታ በድርቅና መልሶ ትግራይ ጉያ ስር መግባቱ ሲታይ፤ ትግራይዋዮች ቡድኑን አውቀውታል ለማለት ያዳግታል:: ደግሞ ሕወሓት በምንም መልኩ የትግራይን ሕዝብ ከመጥቀም ይልቅ ዕድሜውን በሙሉ የትግራይን ሕዝብ ዕርዳታ ሲሰርቅ፤ በሰረቀው የዕርዳታ ገንዘብ ጥይት ሲገዛ፤ የትግራይን ሕዝብ ደም ሲያፈስ እና ሲያስፈስስ ስልጣን ላይ ከወጣም በኋላ በስሙ ሲነግድ መኖሩን የሚያውቀው ሕዝብ ቁጥር ቀላል አይደለም::
አሁን ላይ የትግራይ ሕዝብ አሸባሪው ሕወሓት በሆነ መንገድ ከሕዝቡ ተነጥሎ ይለቅ ቢባል ዓይኑን ሳያሽ ደስ ብሎት የሚቀበለው ሃሳብ ነው:: ፍፃሜውንም በንቃት ይከታተላል ብዬ አምናለሁ:: እስከዚያው ግን የትግራይ ሕዝብ ላይ መፍረድ ያስቸግራል:: ሕወሓትን ለመቅበር የትግራይ ሕዝብ ሊተባበር ቢገባም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት::›› ሲል ተሰማ በበኩሉ የዕለቱ የመሸታ ቤት ውይይት ለዛሬ በዚህ ላይ እናብቃው ብሎ የጠጡበትን ለመክፈል እግሩን ዘርግቶ እየተንጠራራ ቀኝ እጁን ኪስ ውስጥ ከተተ::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ.ም