ልጆች እንዴት አላችሁ፤ አዲሱ የትምህርት ዓመት እንዴት እየሄደ ነው? እርግጠኛ ነኝ ጥሩ ነው ብላችሁኛል። ምክንያቱም ከናፈቃችኋቸው ጓደኞቻችሁና መምህራኖቻችሁ ጋር ተገናኝታችኋል፡፡ በዚያ ላይ በጉጉት የጠበቃችሁት የትምህርት ጊዜ ተጀምሯል፡፡ እናም ደስተኛ ጊዜን እያሳለፋችሁ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ ዛሬ ደግሞ የበለጠ ደስተኛ የሚያደርጋችሁና ከትምህርታችሁ ጋር የሚገናኝ ነገር እነግራችኋለሁ፡፡ ምንድነው ካላችሁ ንባብን ይመለከታል፡፡ ሁሉም ሕጻን በእኩል ደረጃ የማንበብ እድሉ እንዲኖረው የሚያደርገውን አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት እነግራችኋለሁ፡፡
ድርጅቱ ‹‹ኢትዮጵያ ሪድስ›› ይሰኛል፡፡ በልጆች ንባብ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራ ነው፡፡ ይገርማችኋል ልጆች ይህ ድርጅት በጋራ መኖሪያ መንደር ውስጥ ሳይቀር ዘመናዊ የህፃናት ቤተ መጽሐፍት እየሰራ ልጆች አንባቢ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ላሉ ልጆች የተለያዩ ቦታዎች ላይ ቤተ መጽሐፍትን የሰራ ሲሆን፤ አንዱ በቅርቡ በጋራ መኖሪያ ቤት አካባቢ የሰራው ጎተራ አካባቢ የሚገኘው ቤተ መጽሐፍት ነው፡፡ ከዚያም ውጭ በሀዋሳም ይህንኑ ያደርጋል፡፡ እናም በእነዚህ ሁለት ከተሞች የሕፃናትና የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት በመክፈት በአካባቢ ላሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የንባብ አገልግሎት ይሰጣል፡፡
ልጆች ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በሁሉም ክልሎች ከ70 በላይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ቤተ መጻሕፍትን አቋቁሟል፡፡ በዚህም እስካሁን ድረስ ከ130,000 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች፣ መምህራንና ሌሎች የትምህርት ቤት ማኅበረሰብ በተለያዩ ትምህርትና ንባብ ተኮር በሆኑ ፕሮግራሞች ድጋፍ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ከ300,000 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ አገር መጻሕፍትን በተለያየ መንገድ ለሕፃናትና ለተማሪዎች አድርሷል፡፡
ከመጽሐፍ ኅትመት ጋርም ተያይዞ ድርጅቱ ከዚህ በፊት ያሳተማቸው መጽሐፍ አሉት፡፡ ሀገርኛ ሲሆኑ፤ ስድስት ቋንቋዎችን ያካተተም ነው፡፡ በ22 ርዕሶች በማዘጋጀትና በማሳተም በአዲስ አበባ፣ በሐዋሳ፣ በሲዳማ በባህር ዳር፣ በጎንደር፣ በደሴ፣ በድሬዳዋና በሐረሪ ክልሎች ለሚገኙ 300 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በተለይም ከ1ኛ እስከ 4ኛ ላሉ ተማሪዎች በቤተ መጻሕፍት ውስጥ እንዲጠቀሙ አስችሏል፡፡
ልጆች ኢትዮጵያ ሪድስ በክረምት መርሃ ግብር ሳይቀር የተለያዩ አስተማሪ፣ አዝናኝ እና የክህሎት ማጎልበቻ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ የሚሰራ ነው፡፡ ባሳለፍነው ክረምትም ለአምስት ሳምንታት ከቅደመ መደበኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉ ልጆች የክረምት ጊዜአቸውን በተሻለ ሁኔታ እውቀት እየገበዩ፣ መጽሐፍ እያነበቡ፣ ያላቸውን ልዩ ልዩ ችሎታ እያጎለበቱ እና በተለያዩ መዝናኛዎች እየተዝናኑ እንዲቆዩ አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያ ሪድስ ዓመታዊ የሕፃናት ንባብ ጉባዔም ያካሂዳል፡፡እንደውም በቅርቡ ለሦስተኛ ጊዜ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ- መጽሐፍት አገልግሎት (ወመዘክር)ና ትም ህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን አካሂዷል፡፡ የዚህ ዋና ጉባኤ አላማ የማንበብ ባህልን ማሳደግ፣ ሙያዊ ትምህርትን ለቤተ መጻሕፍት ዕድገት ማድረግ፣ አገራዊ መጽሐፎችን ውጤታማነታቸውና ፈተናዎ ቻቸው ማሳየትና የኢትዮጵያን የንባብ ባህል ማስተዋወቅ ነው፡፡
ከዝግጅቶች መካከል የመጽሐፍ ንባብ፣ የተለያዩ ትምህርት አይነቶች ጥናት እገዛ፣ የቋንቋ ትምህርት (ቻይንኛ እና አረብኛን ጨምሮ)፣ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ትምህርት፣ የጥሩ ስብእና ግንባታ ትምህርት፣ ስፖርት፣ ሙዚቃ፣ ስነ-ስዕል፣ የተለያዩ መዝናኛ ጨዋታዎች (ገበጣ፣ ቼዝ) እና ሌሎች ይጠቀሳሉ፡፡
ልጆች ኢትዮጵያ ሪድስ መቼ እንደተመሰረተ ታውቃላችሁ? እ.ኤ.አ. 2002 ነው፡፡ ራዕዩም ሁሉም ሕፃናት በአካልና በሥነ ልቦና የማደግ ዕድል እንዲኖራቸውና በትምህርታቸውም ጠንካራና በራስ የመተማመን ስሜት ኖሯቸው እንዲያድጉ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የንባብ ባህልን፣ ትምህርትን በማስፋፋትና በማሳደግ ወላጆች ልጆቻቸውን በትምህርታቸው በመደገፍ ብርቱ ሚና እንዲጫወቱ ያደርጋል፡፡ ለተማሪዎቹም ምቹና ደኅንነቱ የተጠበቀና የማንበብ ፍላጎትን የሚጨምር ሥፍራን በመፍጠር እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ የልጆች መጻሕፍትን ማሳተምን ዋነኛ ዓላማው አድርጎ የሚሰራ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ትምህርትና ቤተ መጻሕፍት ተኮር ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ በክልሎች፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች በመሥራትም ላይ ይገኛል፡፡ እዚህ ላይም ነው ፈረስና አህያን በመጠቀም ቤተ መጸሐፍት እንዲኖሩ ያደረጉበትን ነገር የምናነሳው፡፡
ትምህርት ቤት ባልተከፈተባቸውና ራቅ ያሉ በአን ዳንድ የደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች በንባብ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ እንዴት ከተባለ ከላይ እንዳልኳችሁ መኪና አይገባምና ፈረስና አህያን ይጠቀማሉ፡፡ ከአምስት ሺህ ለሚበልጡ ሕፃናትም በዚህ ሁኔታ ደርሰዋል፡፡ ይህንን ሲያደርጉ በየመንደራቸው በመግባት መጻሕፍትን ይዞ የንባብ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ነው፡፡
ልጆች ብዙዎቻችሁ የምታውቁት ቤተ መጽሐፍት በቤት ውስጥ ያለ ነው፡፡ መደርደሪያዎቹ የሚያምሩ ናቸውም፡፡ ከዚያ በመቀጠል የምታነቡባቸው ጥሩ ጠረጴዛና ወንበሮችም አሏቸው፡፡ ቤተመጸሐፍት ባትሄዱም በቤታችሁ ቤተሰቦቻችሁ የሚገዙላችሁ አጋዥ መጽሐፍት ይኖሯችኋል፡፡ እናም የማንበብ እድላችሁ በጣም ሰፊ ነው። በፈረስና በአህያ እየተጫኑ የሚሄዱበት የቤተመጽሐፍት አገልግሎት ግን ከዚህ በብዙ መልኩ የተለየ ነው፡፡
የመጀመሪያው ባልተመቻቸ ቦታ ውስጥ ያሉ ልጆችን መደገፍ ሲሆን፤ ሩቅ ተሄዶ የማንበብ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩበት የሚደረግበት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ቦታው ባይመችም ልጆቹ እንዲያነቡ እድል የሚሰጥበት መሆኑ ነው፡፡ እናም እንደ እናንተ ቤት አለያም ቤተመጽሐፍት የሚመች ቦታ ላይ ባይቀመጡም መጽሐፍ ግን አግኝተው ያነባሉ፡፡ እንዴት ሆነው ካላችሁ ደግሞ በድንጋይ ላይ አለያም በዛፍ ስር ተቀምጠው ነው። በእርግጥ መጽሐፉ ሲጓጓዝ በሁለት አይነት መልኩ ነው። አንደኛው ሙሉ ለሙሉ በጀርባቸው ላይ አድርጎ በመጫን ሲሆን፤ ሁለተኛው እንደጋሪ ተደርጎ የሚጎተት ነው፡፡ በውስጡ መቀመጫም ሊኖረው ይችላል። ይህ ማለት ተማሪዎች ሊያነቡ ሲሉ እንደእናንተ በወንበር ላይ የመቀመጥ እድል ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ታዲያ ልጆች ኢትዮጵያ ሪድስን አታደንቁትም፡፡ ይህንን እያደረገላችሁ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ልጆች እያሰባችሁ በአቅራቢያችሁ ያሉ ቤተመጽሐፍትን ሳትጠቀሙባቸው እንዳታልፉ ላስጠነቅቃችሁ እወዳለሁ፡፡ በሉ ለዛሬ በዚህ ልሰናበታችሁ፡፡ በሚቀጥለው በሌላ ጉዳይ እንገናኛለን፡፡ መልካም ሰንበት!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2015 ዓ.ም