ተሰማ መንግስቴ፣ ዘውዴ መታፈሪያ እና ገብረየስ ገብረአምላክ ዛሬ ከወትሮ በተለየ መልኩ እንቅፋት ሲሉ በሚጠሯት ግሮሰሪ በጊዜ ተገናኝተዋል። በፊት በራሱም ይሁን በሌሎች ምክንያቶች ተገንጥሎ የሚቀመጠው ገብረየስ ‹‹ጉግ ማንጉግ›› የሚል ቅጽል ስም ወጥቶለት ነበር። ብቻውን ይበላል፤ ብቻውን ይጠጣል፤ ብቻውን ይቀመጣል፤ ደግሞም ብቻውን ያወራል። እና ይሄ ቅጽል ቢወጣለት ይደንቃል። ዛሬ ግን ምን ገጥሞት ይሆን መቀመጫውን ከዘውዴ እና ከተሰማ አጠገብ አድርጓል። አብሮ እየጠጣ ሊጫወት ዳር ዳር ማለት ቀጥሏል።
በአንድ ጠረጴዛ ሊጋራ የፈለገው ብርጭቆ ማስቀመጫውን ብቻ አይደለም፤ ሀሳቡን ጭምር ነው። ደግሞ እንኳን አሁንና ሌላም ጊዜ ቢሆን የሚወሩ ወሬዎች ሞልተዋል። የኑሮ ውድነት የወሬ ማዳወሪያው ነው። ይሔንን የኑሮ ውድነት እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ከወዲያ ወዲህ የሚያነሳ የሚጥለው ሞልቷል፤ ብዙዎች ባይተዋወቁ እንኳን እንደወሬ መግቢያ እንደ መግባቢያ ይጠቀሙበታል። የጋራ ጉዳይም አይደል። ሁሉን አንድ አድርጎ ያግባባል።
በየገበያው በየሱቁ ከሴቶቹ የተሰሙ ምሬቶች ታክለውበት ብዙ እውነት በትንሽ የውሸት ቅመም ጣፍጦ ጭምር የፖለቲካ አካል ሆኖ ወንዶቹም ያሽሞነሙኑታል። እውነቱ ግን እውነት ነው፤ የእያንዳንዱ ሸቀጥ በፊት ከምናውቀው በሁለትና በሶስት እጥፍ ዋጋው ጨምሯል። ይሄን ያላዩ ውድነት የሁሉንም ቤት የሚያንኳኳ በመሆኑ በጨዋታው አልሳተፍም የሚል አይኖሩም፤ ከወንበር ማዶ ያሉትም ቢሆኑ ሀሳብ ባይሰጡ እንኳን በማዳመጡ ይሳተፋሉ።
በአቀማመጡ ሲርቃቸው የቆየው የመጠጥ አጋራቸውም ገብረየስ ገብረአምላክ ይሄ የሰሞኑ ጨዋታ ቢስበው ብሶቱም ቢጨምር መሰለኝ ዛሬ ከጎናቸው መዶሉን በደንብ አምኖበት መርጧቸው ተቀላቅሏቸዋል። እነርሱም ግን አልከፋቸውም። አስጠግተውት ብሶቱን ሲነግራቸው እያባበሉ ያፅናኑታል። ለስጋ ብቻ ሳይሆን ለመንፈስም መደጋገፍ ጉልበት ይሆናልና የልብ ልብ እየተሰማው ከሰዎች ጋር መጠጋቱን እጅግ ወዶታል። ነፃ ሆኖ መወያየት ማውራት አንዳንዴም መከራከሩን ቀጥሎታል።
ዘውዴ መታፈሪያ ስለኑሮ ውድነት ሲወራ በሆዱም ቢሆን ያጉረመርማል። ምን የኑሮ ውድነት ብቻ ኑሮ የሚኖረው እኮ ሰላም ሲኖር ነው፤ መጀመሪያ እነዛ ጉደኞች በሰሜን የጀመሩትን ጦርነት አስቁሞ ሰላም ማስፈን ያስፈልጋል። ኑሮ ረከሰም ተወደደም መብላት መጠጣት የሚያቻለው ሰላም ሲኖር ነው። መዘመር ያለበት ከምንም በላይ ስለ ሰላም ነው እያለ ያንጎራጉራል።
‹‹ልክ ነው! አሁን በአገራችን ሰላም የጠፋበት ጊዜ ነው፤ እንደውም ከኑሮ ውድነቱ በላይ ሊያሳስበን የሚገባው የሰላሙ ጉዳይ ነው›› ብሎ የዘውዴን ውስጣዊ እንጉርጉሮ የሰማ ይመስል ገብረየስም ወሬውን ተቀላቀለው።
ዘውዴ በድጋሚ፤ ‹‹በሰሜኑ አካባቢ ያለው የሰላም መደፍረስ ደግሞም በዚህ በኦሮሚያ አካባቢ ያለው የሸኔ ጉዳይ ተወርቶ የሚያልቅ አይደለም።›› አለ። ተሰማ በበኩሉ ‹‹ጉድ እኮ ነው! ጉድ ነው የገጠመን የእናት ጡት ነካሽ ሁላ›› አለ። ገብረየስ ደግሞ የሚያሳዝነው ንፁሃኑ የትግራይ ህዝብ ነው። ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሲያለቅስ ይኖራል እንደሚባለው ሆኖበት ህዝቡ ከሕወሓት ሲፈጠር ጀምሮ የሰላም አየር ተንፍሶ አያውቅም። ሁሌ በጦርነት፤ ሁሌ ልጁን ለጥይት፤ ሁሌ አገሩን ለረሀብ ህዝቡን ለተረጂነት… ብሎ ምርር ብሎ ተናገረ ።
ዘውዴ መታፈሪያ የሌላውን ሰው ውስጥ የሚያነብ ይመስላል፤ ‹‹የሕወሓትን የሴራ ፖለቲካ መለስ ብዬ ሳወጣና ሳወርድ መልካም ነገር ልጣ›› አለ። ግንባሩን ጨምድዶ ፈታ ካደረገ በኋላ፤ በውስጡ ሀሳብ እንደሚያብላላ የፊቱ ገጽታ ላይ በሚያሳብቅ መልኩ ዘውዴ በድጋሚ ንግግሩን ቀጠለ። አይ ሕወሓት እንዲህ በሚሊየኖች ላይ ይቀልድ? አለ በድጋሚ።
የተጨነቀ ሰው ብሶቱን፣ ጭንቀቱን፣ ህመሙን የሚያስተነፍሰው በንግግሩ ነው። ቀጠለ ዘውዴ ዛሬ መረር ያለው ይመስላል። ‹‹የክፋቱ ክፋት ከሌላው ብሔር ጋር ተጋብቶ ተጋምዶ የኖረውን ህዝብ ሊያባላ መነሳቱን ሳስብ ያንገፈግፈኛል፤ ስንቱ የጎንደር ሰው ከትግራይ ህዝብ ጋር እንደተጋባ ሳስብ ይብስብኛል።›› አለ ።
ገብረየስ በበኩሉ ‹‹በእርግጥ ይህን ካላደረገ ከዚህ በኋላ በስልጣን ዘመኑ የረሳቸው የትግራይ ሰዎች ከፌዴራል እንደወጣው ከክልልም እንዲወጣ ያደርጉታል። ያለጦርነት መኖር አይችልም። በዛ ላይ ውስጣዊ ባህሪውም አይፈቅድለትም።›› ብሎ ዘውዴን መልከት አደረገው።
ገብረየስ ‹‹ሕወሓት ይህን ካላደረገ እንደበፊቱ በየት በኩል ይዘርፋል፤ በየት በኩል በሩቁ የሚቋምጠውን ስልጣን ያገኛል፤ እንዲህ ካልሆነ በሕይወት አለሁ ማለት ይችላል? አይችልም። በሴራ መንገዱ ትክክል ነው ይሄን ማድረግ አለበት። አሁን እኮ ገብቶትም እንዳልገባው እየሆነ ቢሆንም በትግራይ ህዝብ እየተጠላ ነው። አላመነም እንጂ በብዙዎቹ ዘንድ አክ እንትፍ ተብሏል። እናቶች እንቢ ልጆቻችንን ለጥይት ገብረን ቀባሪ አናጣም በቃን! እያሉ ነው። የወሰዳችኋቸው ወጣቶች የት ደረሱ? ብለው እየጠየቁ ነው፤ ግን መልስ የለም ማስፈራራት ዛቻ ብቻ ሆኗል። ያልደገፈን ከደገፈን እኩል መብቱ አይከበርለትም ብለው በሰብዓዊ እርዳታ በማስፈራራት ላይ ነው። ይሔ ደግሞ ብዙ አያቆየውም›› አለ።
ተሰማ መንግስቴ በበኩሉ መንግስት ደግሞ ደጋግሞ ሲዘረጋው የነበረውን የሰላም እጅ የረገጠው ሕወሓት አሁን ደግሞ ጦርነት መክፈቱ ያስገርማል ብሎ ሰሞኑን ጌታቸው ረዳ ሽንፈት ሲከናነብ የሚፖተልከው እና ቀደም ሲል ከአማራ ጋር ሂሳብ እናወራርዳለን ምናምን… ምናምን… ሲል የነበረውን አስታወሰ። የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ አይደል ነገሩ። ‹‹ደግሞ እንዴት እንዳበጠ? ብሎ ተሰማ ተሳለቀ።
ዘውዴ በበኩሉ ‹‹እርሱንማ ተወው ሽንፈት አሳብዶት ነው። ለነገሩ በእኛ በኩል ያለው ተዋጊ ጥበቡ ያስገርማል። ሕወሓት ህዝባዊ ማዕበል በሚል በገፍ ከኋላ እየተገፋ ሲመጣ የመንግስትን የመከላከል ጥበብ ብታይ እና ሳይንሱ ቢገባህ እጅግ ትደነቅ ነበር።›› አለ የውትድርናውን ሳይንስ የሚገልጽበት መንገድ በቦታው ሆኖ በውጊያው ተሳትፎ ያየ ሁሉ እስኪመስል አቀነባብሮና አጣፍጦ ነው። አዋጊም ሚስጢር አዋቂም እርሱ ይመስላል። ትንሽ ነገር አንብቦ ይሆን ወይስ ቀደም ሲል የውትድርናዋን ትምህርት ቀስሞ ብቻ እንጃ በእኔ ውስጥ የተመላለሰ ሀሳብ ብጤ ነው። ከተሳሳትኩ አፉ በሉኝ።
ጥቃት ከምንም በላይ ያማልና አንዳንዴ ሶስቱም ተጠቅቻለሁ የሚል ስሜት ይታይባቸዋል። የዘር ሀረጋቸውን እየመዘዙ ይሆን እንጃ ብቻ ስሜታቸው ይደበላለቃል። የዛኔ አንዱ ሌላውን ታግሶ የሚያልፍ አይመስልም። ነገር ግን በተደጋጋሚ በትዕግስት ይተላለፋሉ።
የዛሬው ተጠቅቻለሁ ባይ ዘውዴ ነው። ትንሽ ንግግራቸው ከረር ብሏል። በተለይ ዘውዴ አልፎ አልፎ ከገብረየስ ጋር የሚከራከሩት የሀሰት ትርክት ደግሞ አወቅኩ ባይነታቸው ለነገ እንገናኛለን የሚያስብል አይደለም። ዘውዴ ያዘዘውን ቢራ በቀኝ እጁ ሁለት ጣቶች መሀል አንስቶ እየተጎነጨ ‹‹የአንዱ ችግር ላይ መውደቅ ለእያንዳንዱ ሰው ጥሩ ስሜት አይሰጠውም፤ የአንዱ ቤት መቃጠል ለሌላው ጫካ ተቃጥሎ ከሰል እንደሚገኝ ተራ ነገር ይቆጥረዋል፤ የእኛ ቤት ሲቃጠል ለማጥፋት ብትረባረቡ አሁን ዞሮ ይሔ ሁሉ ነገር አይመጣም ነበር።›› አለ።
ዘውዴ ለወሬው ማድመቂያ አንድ ተረት ልንገራችሁ አለ። በአንድ አካባቢ አንድ ተፈሪ ሽፍታ ነበር። የፈለገውን እየዘረፈ፤ የፈለጋትን እያገባ ያልፈለጋትን እየፈታ ኖሯል። ሽፍታው በድንገት አንድ ጎረምሳ አብዝቶ የሚወዳትን ልጃገረድ እርሷን እና ቤተሰቧን አስገድዶ አገባት። ያቺ ሴት ሽፍታውን ሳይሆን የምትወደው ያንን ጎረምሳ ቢሆንም ለሽፍታው መልካም ሴት ሆነችለት። እርሱ ከሌላ ሴት የተለየች አድርጎ እንዲወዳት ማድረግ ቻለች።
ታታሪ በመሆኗ ሁልጊዜም ሲመጣ የሚበላ ሰርታ ቤቱን አሰናድታ ሁሉን አስውባ ታቀርብለታለች። ታጥባ ታጥና ትቆየዋለች። በጊዜ ሒደት አብዝቶ ወደዳት፤ የዘረፈውን ዋነኛ ንብረቴ የሚለውን ሁሉ የሚያስቀምጠው በእርሷ ቤት ሆነ። ወዶታልና አመናት። እንደወደዳት ስታረጋግጥ ጥያቄዎችን ማቅረብ ጀመረች። ከልቡ የወደዳት ሽፍታ ሴቲቱ የምትጠይቀውን ሁሉ ይሰጣት ቀጠለ። ነገር ግን አንድም ቀን ለአንድ ጊዜም ቢሆን እንደምትወደው ጠይቋት አያውቅም ነበር። እርሷም ‹‹እወድሃለሁ›› ብላው አታውቅም።
ሽፍታው አንድ ቀን አንድ ነገር ከማድረጉ በፊት ‹‹እወድሃለሁ›› እንድትለው ፈለገ። እወድሃለሁ በይኝ አላት። ሴቲቱ እንደገመታት ‹‹እወድሃለሁ›› አላለችውም። አልወድህም አለችው። ‹‹ለምን ? ›› አላት። ‹‹ በድለኽኛል። እንድወድህ ሳታደርግ አግብተኽኛል፤ ያየኸኝ እንዳንተ እንደሰው ሳይሆን እንደምትፈልገው ዕቃ በመሆኑ እኔ ልወድህ አልችልም ›› አለችው። በጥልቅ ፍቅር ውስጥ የነበረው ሽፍታ ከበደሉ በኋላ ማባበል ተቀባይነት እንደሌለው ተገንዝቦ መውደዱ ከልቡ መሆኑን ማሳየት ፈለገ።
‹‹መውደዴ ከልቤ ነው ምን ላድርግልሽ›› አላት። መልሷ ከወደድከኝ ከዛሬ ጀምሮ ፍታኝ አለችው። በማለት ተረቱን የጨረሰው ዘውዴ ሕወሓት በምንም መልኩ ለትግራይ ነጻነት እቆማለሁ፤ ለትግራይ ህዝብ ያለሁት እኔ ነኝ፤ ከትግራይ ህዝብ በላይ ለትግራይ ህዝብ አውቅለታለሁ ቢልም ህዝቡንም ክልሉንም ጠቅሞ አያውቅም። ከመፈጠሩ ጀምሮ ሲጎዳው ኖሯል። አሁን ላይ የትግራይ ህዝብ የሕወሓት ቡድን የሚወደን ከሆነ እንፋታ እያለ ነው። እወድሃለሁ የሚል ቡድን አልወድህም አልፈልግህም ከሚለው አካል ፍቅርን ማግኘት አይችልም። መውደዱን የሚያረጋገጠው ሲፋታው ብቻ ነው ብሎ ዘውዴ ተረቱን በቁም ነገር አስታኮ ሁሉንም አስደመመ።
ገብረየስ ለዘውዴ ‹‹ይህን ማለትህ ትክክል ነህ። አንድ ነገር ሲፈፀም አንዱ በትዕግስት ቢያልፍም ሌላው ሊነሳ ስለሚችል ምንጊዜም ቢሆን ስህተት ላለመስራት ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። ለነገሩ የሕወሓት ስራ ከስህተትም በላይ ሴራ ነው። በተደጋጋሚ የትግራይን ልጅ ለጦርነት ዳርጓል። አንዴ ከደርግ ሌላ ጊዜ ከኤርትራ አሁን ደግሞ ይኸው አንዴ ከአፋር ሌላ ጊዜ ከአማራ ብቻ ከሁሉም ጋር እያናከሰን ነው። ትክክል ብለሃል አንድ ሰው ግዴለሽ ከሆነ ወይም ጥንቃቄ ከሌለው በተለይ ለብልጣ ብልጦች መቀለጃ ከመሆን አያመልጥም። የትግራይ ሕዝብ የሕወሓት መቀለጃ ሆኗል። በሰዎች መካከል መቀራረብ፣ መስማማት፣ መዋደድና መተሳሰብ ሲኖር ሰላም እና ፍቅር ስለሚኖር የበለጠ ተጠቃሚ መሆን ሲቻል። ሕወሓት ግን ጥላቻ ውስጥ እየከተተን በቀጣይም ከማንም ጋር እንዳንኖር እየዳረገን መሆኑ በእርግጥ ያሳዝናል። በትክክልም ማስቆም አለብን ነገር ግን ውሉ የጠፋን እንዴት ብለን የሚለው ነው።›› አለ።
ተሰማ በበኩሉ ለገብረየስ መልስ መስጠት ፈለገ ‹‹አንዳንድ ጊዜ ያልታሰበ የተወሳሰብ ችግር ያጋጥማል፤ የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ ሃዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ እንደሚባለው አሁን እየሆነ ያለው ይኸው ነው። ነገር ግን መረዳት ያለባችሁ አሁን ሕወሓት የአንድ የብልፅግና ወይም የመንግስት ጠላት ብቻ አይደለም። የትግራይም ጠላት ነው። ከነቃችሁ ጠላቴን የሚያጠቃልኝን እንደወዳጄ እቆጥረዋለሁ ብላችሁ ከመንግስት ጎን ቁሙ። እንደእባብ ዱካ ሆናችሁ የሕወሓትን ሴራ የውሃ ሽታ አድርጉት ይህንን ለማድረግ ከቆረጣችሁ የሁላችንንም ጠላት ሕወሓትን ማጥፋት ይቻላል። ሕወሓት ጠላቴ ነው የጠላቴ ጠላት ደግሞ ወዳጄ ነው። አቦ ለዛሬው ይብቃን እንውጣ።›› ብሎ ከኪሱ ብር አውጥቶ ጠረጴዛ ላይ እያስቀመጠ ከመቀመጫው ተነሳ።
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3/2014