ልጃገረዶቹ ከፀጉር እስከ እግር ጥፍራቸው ለመዋብ የማያደርጉት የለም። ፀጉራቸውን ሹሩባ ይሰራሉ፤ የእጅና የእግር አልቦው፣ከብር የተሰራ የአንገት ጌጥ የአይን ኩሉም አይቀርም። የሚለበሰውም በእጅ የተፈተለ የሀገር ባህል ልብስ ነው።
አሸንድዬ የሚባል ቄጠማ ደግሞ ከወገብ በታች በልብሱ ላይ ይውላል። ከወገብ በታች የሚንዘረፈፈው ቄጠማ በጨዋታ ወቅት ሲወዛወዝ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ሻደይ ለሚጫወቱ ልጃገረዶች ድምቀት ይሰጣቸዋል።
ከልጃገረዶቹ መካከል ግጥም ለማውጣት የተመረጠችው ውዳሴ፣ ሙገሳና ወቀሳ በዘፈን መልክ ስታቀርብ በተቀባዮች በከበሮና በጭብጨባ ሲታጀብ ታዳሚውን ያስደምማል።አልባሳቱም መዋቢያውም ዘመን አመጣሽ አለመሆኑ ደግሞ ለባህል የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል።
በግጥምና ዜማ የሚጫወቱትም ባህልን መሠረት ያደረገ ነው። ልጃገረዶቹ ምንም እንኳን በእለቱ የበለጠ ተውበው ቢታዩም፣ ባአካባቢው የሚገኙ ባህላዊ መዋቢያዎችን ነው የሚጠቀሙት። ከአዘቦቱ ለየት ብለው መታየታቸው ደግሞ ቀልብን እንዲስቡ ያደርጋቸዋል። የሁሉም አይን ያርፍባቸዋል። አጠቃላይ ባህላዊ እሴቱ ያመዝናል።
በእንዲህ ካለው የልጃገረዶች ጨዋታ እጮኛ ለመፈለግ የሚያንዣብብ ወንድ አይጠፋም። ይህም አንዱ የባህል መገለጫ ነው። አሁን በምንገኝበት ዘመን በተለያየ አጋጣሚ በሚፈጠር ግንኙነት ሳይሆን አንድ ወንድ ለትዳር የምትሆነውን ለመፈለግ እንዲህ ያለውን አጋጣሚ ይጠቀማል።
ታዲያ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ከሚጫወቱት መካከል እጮኛ የሚፈልግ ወንድ ምርጫው ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ይመከራል። ምክንያቱ ደግሞ በእለቱ በሚጠቀሙት መጋጌጫ ውበታቸው ጎልቶ ስለሚወጣና ሁሉም አይንን የሚስቡ በመሆናቸው መልክ መረጣ ላይ ያኔ በውበቷ ተማርኮ በኃላ ላይ እንዳይቆጭ ነው ምክሩ። በዚህ ምክንያት በዚህ ጊዜ የሚደረግ የእጮኛ ምርጫ ቢቀር የሚሉም አይጠፉም።
ልጃገረዶቹ ንጹህና ውብ ሆነው ለመጫወት ከነሐሴ ወር መግቢያ ጀምሮ በየአካባቢያቸው ይሰባሰባሉ፤ ይመካከራሉ፤ ቀኑንም በጉጉት ነው የሚጠባበቁት። እንኳን ልጃገረዶቹ ባልቴቶቹም ቢሆኑ የጨዋታው ተሳታፊዎች በመሆናቸው ይናፍቃሉ።
የልጃገረዶች ጨዋታ ተብሎ የሚታወቀው አሸንድዬ፣ሶለል፣ሻደይ መነሻው ወይንም ይዘቱ ኃይማኖታዊ ነው። በኦርቶዶክስ አማኞች ዘንድ የፍልሰታ ጾም ለ16 ቀናት ከተጾመ በኃላ በ16ኛው ቀን ጾሙ ይፈታል። ልጃገረዶቹ ከጾም ፍችው ቀን ጀምሮ ለቀናት በየቤቱ እየዞሩ የሚጫወቱት ደግሞ ባህላዊ መልክ አለው። መልካም ተብሎ ከሚጠቀሰው የማህበረሰብ እሴቶች አንዱ መመራረቅና ቸር መመኘት በመሆኑ ልጃገረዶቹ በየቤቱ እየዞሩ ሲጫወቱ ይመረቃሉ፤ እነርሱም ይመርቃሉ፤ ለከርሞ በሰላም ለመገናኘት ቸር ይመኛሉ።
ይህ ሁሉ ባህላዊ እሴቱ የሚናፈቅ በመሆኑ ነው ማህበረሰቡም ልጃገረዶቹን በየቤቱ ተዘጋጅቶ የሚጠብቃቸው። ቤቱ ሲገቡም ቤት ያፈራውን ለበዓል የተዘጋጀ ምግብና የሚጠጣ ይቀርብላቸዋል። እነርሱም የሄዱበትን ቤት ባለቤት ገና ከበር ጀምሮ ነው እያወደሱ ወደ ውስጥ የሚዘልቁት።
ቤት ውስጥ ከገቡ በኃላ ደግሞ የሚደረግላቸው መስተንግዶ ጥሩ ከሆነ ሙገሳውን ያዥጎደጉዱታል፤ በደንብ ይጫወታሉ። መስተንግዶው ለስሜታቸው ጥሩ ካልሆነ ደግሞ ስድብ አዘል ነቀፌታ በማቅረብ የቤቱ ባለቤት መልእክታቸው እንዲገባው በጨዋታቸው ጠቆም በማድረግ ወደሚቀጥለው ቤት ያመራሉ።
በዚህ ሁኔታ አካባቢያቸውን ያካልላሉ። ቤተሰብ ለልጆቹ ነፃነት የሚሰጥበት ጊዜ ነው። በአካባቢው የሚፈራ ወይንም ከማህበረሰቡ በኑሮ የተሻና የሚከበር እንኳን ቢሆን ቤቱ ለሚጫወቱት ልጃገረዶች ክፍት ነው። መስተንግዶውንም ካላሳመረ ከመተቸት አያመልጥም። የነፃነት ልኩ እስከዚህ ድረስ ነው የሚገለጸው። የቤተሰብ ቁጥጥር ያለባት ልጃገረድ እንኳ በዚህ የጨዋታ ጊዜ አትከለከልም። ከጓደኞችዋ ጋር በጨዋታ እንድታሳልፍ ይፈቀድላታል።
ከነሐሴ 16ቀን ጀምሮ የሚካሄደው የልጃገረዶች ጨዋታ ተብሎ የሚታወቀው ይህ ወቅት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በእጅጉ ይታወቃል። በተለይ ደግሞ በትግራይና አማራ ክልሎች በየአመቱ ይከበራል። ባህላዊ ጨዋታውም በአንዳንድ ነገር ካልሆነ በስተቀር መሰረታዊ የሚባል ልዩነት እንደሌላው ነው መረጃዎች የሚያሳዩት። ይህ የልጃገረዶች ጨዋታ የአዲስ አመት መድረስንም የሚያሳይ በመሆኑ ድባቡና ስሜቱ ይለያል።
ዘንድሮም በአሉን ለማክበር ዝግጅቶች እየተደረጉ ናቸው። ከዋዜማው ጀምሮ ድባቡ አካባቢን የሚያደምቀው የልጃገረዶች ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማንም ሞቅ ደመቅ እያደረጋት ነው። በዓሉን አስመልክቶ የሚከናወኑ ዝግጅቶችም በማስታወቂያ አስቀድሞ ተላልፈዋል። ዋናው በዓሉ የሚካሄድባቸው በተለይም የአማራ ክልል የተለያዩ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን በተለያየ የመገናኛ ዘዴ አስነግሯል። በማህበራዊ ድረገጾች የሚለቀቁት መረጃዎች የበዓሉን መድመቅ የሚያሳዩ ናቸው።
ከጥቂት አመታት በፊት ኑሮዋን አዲስ አበባ ከተማ ያደረገችው ወጣት ገነት መብራቱ ተወልዳ ባደገችበት ትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ከአካባቢ ጓደኞችዋ ጋር የነበራትን የአሸንድዬ የጨዋታ ጊዜ ሁሌም ታስታውሰናለች። እርስዋና የአካባቢዋ ልጆች በእለቱ ስለሚለብሱትና ስለሚያደርጉት ጫማ እንዲሁም ስለሚዋቡበት መጨነቅ የሚጀምሩት ከነሐሴ ወር መግቢያ አንስቶ ነው።
ይህንንም የሚያሟላላቸው ቤተሰብ በመሆኑ ቀድሞ ቤተስብን ማሳሰብ አለባቸው። አዲስ ልብስ መግዛት ባይቻል እንኳን በእለቱ የሚለበሰው የባህል ልብስ በመሆኑ እናቶቻቸው የሚለብሱትን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል። የባህል አልባሳቱ በጥልፍ የተዋቡ ቢሆኑ ይመረጣል። ዋናው ግን የባህል ልብስ መሆኑ ነው የሚፈለገው።
ለመዋቢያ ስለሚጠቀሙባቸው ጌጣጌጦች ወጣት ገነት እንደነገረችኝ በሹርባው ላይ በግንባር ላይ ‹‹ጩጉኻጉሂት››የሚባል ጌጥ ይደረጋል። በጨሌ የሚሰራ ጌጥ ነው። ጨሌ ካልተገኘም የተለያየ ቀለማት ባለው ክር ይዘጋጃል። ድሪ የሚባል ደግሞ በእጅና በአንገት መካከል ከቀሚሱ በላይ የሚውል ጌጥ ነው። ይሄም ጌጥ የተለያየ ቀለም ባለው ክር ነው የሚሰራው። በወገብ ላይም መቀነት ይደረጋል።
ለአንገት ጌጥ ደግሞ በመጠን የተለያዩ ሶስት መስቀሎች በክር አጭር፣መካከለኛና ረጅም ሆኖ ውበት ባለው መልኩ ይደረጋል። በመጠን አነስተኛዋ መስቀል በአካባቢው ‹‹ህንቆ››ተብላ ትጠራለች። ትልቁ መስቀል ደግሞ ‹‹ዝብጦ››ይባላል። ሶስቱን መስቀል ማድረግ ካልተቻለ ከነሀስ ወይንም ከብር የተሰራ ጌጥ ይደረጋል። ከብር የተሰራ ቢሆን ግን ይመረጣል። የእግር አልቦው አስገዳጅ ባይሆንም ማሟላት ከተቻለ ቢደረግ ይመረጣል። ለእግር ጫማ ደግሞ ኮንጎ ነው የሚደረገው። በዚህ ሁኔታ ነው ልጃገረዶቹ ደምቀው ለመታየት ጥረት የሚያደርጉት።
የልጃገረዶቹ ጨዋታ የሚጀምረው ነሐሴ 16 በመሆኑ ለጨዋታው የሚሰባሰቡትም በዚህ ቁጥር የተገደቡ ይሆን ብዬ አሰቤ ወጣት ገነትን ጠየኳት። እርስዋም የአካባቢው ልጆችና ጓደኛማማቾች ናቸው የሚሰባሰቡት። ስብስቡም በቁጥር አይገደብም አለችኝ።
ጨዋታው የሚጀመረው ነሐሴ 16ቀን ከሰአት በኃላ ነው። ጨዋታውም በምስጋና ለመጀመር በዕለቱ አብረው ለመጫወት የተሰባሰቡት ልጃገረዶች አስቀድመው በየአካባቢያቸው ወደሚገኘው ቤተእምነት ይሄዳሉ። ከእምነት ተቋም መልስም ተሰባስበው ‹‹መፀት፣መፀት አሸንዳ…››ብለው በዓሉን የሚያበስር ጨዋታ ይጫወታሉ።
ወደ መኖሪያ ቤቶች በመሄድ የሚጫወቱት ግን በማግሥቱ ነው። የሚሄዱበት ቤትም አይመረጥም። አቅማቸው እስከፈቀደ ድረስ አካባቢያቸውን ያዳርሳሉ። ወደየቤቱ ሲሄዱም ሲቃረቡ ‹‹ዞማአዲ አንበሳ አድሎሚ ህዝምበለ ሀውደርህገዞኦሚ››ይላሉ። እዚህ ቤት ውስጥ አንበሳ አለ ወይ ከቤቱ በስተኃላ ድምጽ ይሰማል እንደማለት ነው።
የሄዱበት ቤት በሩ ዝግ ከሆነባቸው ደግሞ የቤቱ ባለቤት በሩን እንዲከፍትላቸው ‹‹አጋፋሪ ጎይታይ በሪህዘኛ ክፈት እዚህ በረኛ››ይላሉ። ጌቶች ከበርዎ ላይ ቆመናል፤ በሩን ክፈቱልን እንደ ማለት ነው። የደጁ በር ተክፍቶላቸው ወደ ውስጥ እንዲገቡ ሲጋበዙ ማወደስ ይጀምራሉ። የቤቱን እማወራ ‹‹አቲ እቤቴ ፀሐዬ መፃዬ ኮ መፃዬ…››እያሉ ያወድሳሉ። የቤቱ ባለቤትም ከተጫወቱ በኃላ ምግብ ያቀርባሉ። ገንዘብም ይሰጣሉ።
እዚህ ላይ ግን ስጦታውና መስተንግዶው በአቅም ነው። ሁሉም አቅሙ የቻለውን ነው የሚያደርገው። ተጫውተው ሲወጡም ጥሩ መስተንግዶ ከተደረገላቸው እንደ ነሐሴ ዝናብ ፈሰሰልን ብለው ምስጋናቸውን በዘፈን ያቀርባሉ። ስስት ያሳየውን ደግሞ ‹‹ይሄ ሰው ሽሮ ነው የሚበላው እንዴ በዓሉን የረሳው››የሚል መልእክት ያስተላልፋሉ። እንዲህ በየቤቱ ዞረው ያገኙትን ገንዘብ አለመከፋፈላቸው ደግሞ ለየት ያደርጋቸዋል። ገንዘቡን በሙሉ ለቤተክርስቲያን ነው የሚሰጡት።
ወጣት ገነት በሀገር ቤት የነበራትን የልጅነት ትዝታዋንም እየቀሰቀስኩባት ስለነበር በጨዋታችን መካከል ሀሳብ ውስጥ ገባች። እንደ ልጅነቷ ባይሆንም ቀኑን ለማሰብ ከጓደኞችዋ ጋር ለመዋል ነው እቅዷ። በዓሉ ለእርስዋ ልዩ ስሜት ይሰጣታል። በአሉን ‹‹ውስጤን እስኪያመኝ ድረስ ነው የምወደው›› የምትለው ወጣት ገነት፣ በልጅነትም፣በዕድሜም ከፍ ቢሉ ለጨዋታው ያለው ስሜት አይለያይም ትላለች። እንደውም ከፍ ሲባል የበዓሉን ትርጉም ለመረዳት ጥረት እንደሚደረግና በዓሉ ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ እንዲከበር መቆርቆሩ የበለጠ እንደሚሆን ነው ያጫወተችኝ።
አሁን ላይ በዓሉ በተለይ በከተሞች ባህላዊ ይዘቱን ይዞ እየቀጠለ እንዳልሆነ ይሰማታል፤ ተበርዟል ብላ የምታምነው በአልባሳቱ ነው። በተለይ በከተማ የባህል አልባሳት ሽፎን በሚባል የጨርቅ አይነት መተካቱ ነው። ፀጉርም ሹሩባ መሰራት ያለበት ሰውሰራሽ ዊግ የሚባለው ተቀጥሎ ሳይሆን፣የተፈጥሮ ፀጉር መሆን እንዳለበትና ከተፈጥሮ ውጭ የሆነው መዋቢያ ከባህል ውጭ አንደሆነ ታስረዳለች።
የበዓሉ መገለጫዎች የሆኑት ሁሉ መቅረት እንደሌለባቸው ታምናለች። እንደርታ፣ተንቤን፣ራያ አካባቢዎች ባህሉን ጠብቆ የሚካሄደው የልጃገረዶች ጨዋታ በከተሞችም በተመሳሳይ መሆን እንዳለበት ትገልጻለች።
ከተማ ተወልዳ ብታድግም ከመቀሌ ወጣ ብሎ በሚገኝ ሶፎሎ በሚባል አካባቢ ነዋሪ የሆኑ አክስቷ ጋር ሄዳ የአካባቢው ልጃገረዶች በዓሉን በምን ሁኔታ እንደሚያከብሩት ለማየት ዕድሉን አግኝታለች። በዚህም በከተማና በገጠሩ መካከል ያለውንም የበዓል አከባበር ልዩነትም ተገንዝባለች።
በዕድሜ ከፍ ማለቷና በትምህርት መግፋቷ ደግሞ የበለጠ ለባህሉ ትኩረት እንድትሰጥ አድርጓታል። ከእንግዲህ በኃላ ጨዋታውን መጫወት ብቻ ሳይሆን፣ ባህሉ ተጠብቆ እንዲቀጥልና ዓለምም እንዲያውቀው ለማድረግ የግሏን አስተዋጽኦ ለማበርከት እቅዱና ፍላጎቱ አላት፤ ነገሮች ከተመቻቹላት።
ወጣት ገነት ባህሉን ጠብቆ ለማቆየትም ሆነ ሁሌም በደስታ በዓልን ለማሳለፍ ሰላም መቅደም አለበት ትላለች። አሁን በሀገሪቱ የሚታየው የሰላም እጦት ተወግዶ ህዝቦች በሰላምና በፍቅር እንዲኖሩ ምኞቷ ነው። ‹‹አሸንዳ ማለት አንድነት፣ሰላም፣ነጻነት የሚገለጽበት ነው››በማለት ሁሉም በዚህ እሳቤ ለሰላምና ለፍቅር ከተጋ የተሻለ ነገር ይመጣል የሚል እምነት አላት።
ወጣት ገነት የሰላም እጦት የምትወደውን አሸንዳ የልጃገረዶች ጨዋታ በትውልድ አካባቢዋ እንዳታከብር አድርጓል። በአሁኑ ጊዜም በተለምዶ ቡና ጠጡ በሚባለው ንግድ ሥራ ላይ ተሰማርታ ኑሮዋን እየመራች ትገኛለች። የሰላም እጦቱ በባዮቴክኖሎጂ የትምህርት ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪ እያላት ከሙያዋ ውጭ በሆነ ሥራ ላይ እንድትሰማራ እንዳደረጋትም ትናገራለች።
አሸንዳ የልጃገረዶች በዓል አንዱ የቱሪዝም መስህብ ሆኖ ለሀገር ገቢ ማስገኛ ሊሆን እንደሚችል መዘንጋት የለበትም። ይሁን እንጂ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባጋጠመው ጦርነት በዓሉ በተለይም በዋናነት በሚከበርባቸው አካባቢዎች ተቀዛቅዞ መቆየቱ ይታወቃል።
አሁን ላይ ደግሞ በሚታየው አንጻራዊ ሰላም መነቃቃቶች ተፈጥረዋል። በአሉ ባለፈው አመት ከጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ባይከበርም ዘንድሮ እንደሚከበር ታውቋል።
በዚህ ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ተጠይቀው በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ በዓሉ ለሀገሪቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ እንዲኖረው በተለይም በላልይበላ ከተማ ላይ በዓሉን መሠረት የደረገ ሲፖዚየም ለማካሄድና በዚህ ላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንዲካሄድባቸው መድረክ ለማዘጋጀት ታቅዷል።
ዝግጅቱ የቱሪዝም ማህበረሰቡንም ለማነቃቃት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጠር ታምኖበታል ይላሉ። የላልይበላ አካባቢ ማህበረሰብ አብዛኛው በቱሪዝም ኢንዱስትሪው የሚተዳደር በመሆኑ በሆቴል፣በትራንስፖርትና በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ዝግጁ እንዲሆን ይነቃቃል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም በዚህ አቅጣጫ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል አጋጥሞ በነበረው ጦርነት ተቋርጦ የነበረው የአየር በረራ በመጀመሩ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው መልካም የሆኑ አጋጣሚዎች እንደሚፈጠር ተስፋ ተጥሏል ይላሉ።
አሸንዳ፣አሸንድዬ፣ሻደይ፣በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ ወካይ ቅርሶች ለማስመዝገብ ጥረቶች እንደነበሩ ይታወሳል።መልካም በዓል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15 ቀን 2014 ዓ.ም