ሁለንተናዊ የሆነ አገራዊ ልማትን ለማጎልበትና እድገት ለማስመዝገብ የዳያስፖራውን ማኅበረሰብ ተሳትፎ ማሳደግ ተገቢ ግብዓት እንደሆነ አያጠራጥርም። ዲያስፖራው በውጭ አገር እንደመኖሩ በውጭ ምንዛሬ ግኝት ለአገር ሊያበረክተው የሚችለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል፤ በአገሩ ልማት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ለመፍጠር የሚያስችል የካፒታልና የእውቀት አቅም አለው። አገር በውጭ ምንዛሬ እጥረት ውስጥ በቆየችበት በ2014 በጀት አመት ብቻ ዲያስፖራው 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገር ቤት ከላከበት ሁኔታ መገንዘብ የሚቻለውም ይሄንኑ ነው። በእውቀትና በክህሎት በኩልም እንዲሁ ዲያስፖራው ጉልህ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል።
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ፣ ለኢንቨስትመንት አቅም ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህ ዲያስፓራ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገንዘባቸውን ወደ ሀገር ውስጥ በቀጥታ ከመላክ በተጨማሪ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይም ተሰማርተዋል። ይህ የኢንቨስትመንት ተሳትፏቸውም የሥራ እድል መፍጠርን ጨምሮ በተጨማሪ ምርትና አገልግሎት እንዲሁም በማኅበራዊ ኃላፊነት ረገድ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።
ይሁን እንጂ ዳያስፖራው ማኅበረሰብ በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ያለው ተሳትፎ፣ አገሪቱ እንዲሁም ዳያስፖራው ካላቸው እምቅ አቅም አንፃር ሲታይ በቂ የሚባል እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ይገለጻል። ለዚህ ክፍተት ደግሞ የአመለካከት ችግርን ጨምሮ ሌሎች ተቋማዊና ፖለቲካዊ መሰናክሎች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
ከዓመታት በፊት የኦሮሚያ ተወላጅ ዳያስፖራዎች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የመረጃ እጥረትን ጨምሮ ሌሎች ችግሮች ይገጥሟቸው ነበር። በመረጃ እጥረት ምክንያት በየቦታው እየተንከራተቱና ለድካም እየተዳረጉ የኢንቨስትመንት ዓላማቸውን ሳያሳኩ ተመልሰው የሚሄዱትም ቁጥራቸው ብዙ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። ዳያስፖራዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በኢንቨስትመንት ስራዎች ለመሰማራት በሚሄዱባቸው ቦታዎችና ተቋማት የተለያዩ ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረዶች ያጋጥሟቸው ነበር።
ስለሆነም ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት ተሰማርቶ ውጤታማ እንዲሆን የራሱን አደረጃጀት ፈጥሮ መንቀሳቀስ ነበረበት። አደረጃጀቱ እያንዳንዱ ዳያስፖራ ራሱንና አገሩን ለመጥቀም እንደሚያስችለው በመታመኑ በ2007 ዓ.ም የኦሮሚያ ዳያስፖራ ማኅበር ተመሰረተ።
ማኅበሩ ከተቋቋመ በኋላ ለስራው የሚያግዙትን አደረጃጀቶች በመፍጠርና መዋቅሮችን በመዘርጋት ወደ ስራ የገባ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከ11ሺ በላይ አባላት አሉት። ማህበሩ ዳያስፖራዎች በአገራቸው በኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ መረጃዎችን ይሰጣል። ባለሀብቶች ከመንግሥት ተቋማት ጋር የስራ ግንኙነቶችን እንዲፈጥሩ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ተግባራትንም ያከናውናል። ማኅበሩ ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት ላይ እንዲሰማራ ላከናወናቸው በጎ ተግባራትም ሽልማቶችን አግኝቷል።
የኦሮሚያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ በስፋት እንዲሳተፉ ስላከናወናቸው የስራ እንቅስቃሴዎችና የዳያስፖራውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ በተመለከተ የኦሮሚያ ዳያስፖራ ማኅበር ምክትል ፕሬዚደንት ዶክተር ቶላ ገዳ በተለይ ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ የሰጡትን ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
የዳያስፖራው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ
በአሁኑ ወቅት በርካታ ዳያስፖራዎች በክልሉ በግብርና፣ በትምህርት፣ በሪል ስቴት፣ በሆቴልና በማምረቻ ዘርፎች ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛሉ። ለበርካታ ዜጎችም የስራ እድሎችን ፈጥረዋል። በኢንቨስትመንት ስራዎቻቸው ከፈጠሯቸው የስራና የአገልግሎት እድሎች በተጨማሪ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ባከናወኗቸው ተግባራትም ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል።
በኦሮሚያ ክልል ብዙ ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረዶችን አልፈው በአሁኑ ወቅት ጥሩ የኢንቨስትመንት ደረጃ ላይ የሚገኙት የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት፣ ለትልልቅ ኢንቨስተሮችም ተምሳሌት መሆን ችለዋል። አንዳንዶቹ ባለሀብቶች በውጭ አገራትም ትልልቅ ድርጅቶች ያሏቸው ናቸው። ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለያዩ ምክንያቶች ተመልሰው ወደ ውጭ የሄዱ ግለሰቦችም አሁን ወደ አገራቸው በመምጣት በኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ መሰማራት ይፈልጋሉ።
ማኅበሩ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድም ያከናወናቸው ተግባራት አሉ። ወደ አረብ አገራት ሄደው ተቸግረው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ዜጎችን የማቋቋም ስራዎችን ሰርቷል። ኅብረተሰቡ ስለህገ ወጥ ስደት ግንዛቤ እንዲኖረው በስድስት ከተሞች ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን ሰጥቷል። በተጨማሪም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን ሰጥቷል። የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስንና የምግብ ድጋፎችን አድርጓል።
የመንግሥት ድጋፍና ትብብር
መንግሥት ለማኅበሩ ልዩ ልዩ ድጋፎችን ያደርጋል። ባለሀብቶችን ለማበረታታት መሬት ያቀርባል። የኢንቨስትመንት ፈቃድ ይሰጣል። የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባል የሆኑ ባለሀብቶች በአገራቸው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ልዩ ልዩ ማበረታቻዎችንም ያደርጋል።
ማኅበሩ ሲመሰረት ዳያስፖራው የራሱን ሕጋዊ አደረጃጃት ፈጥሮ በኢንቨስትመንት ውጤታማ እንዲሆን ከማድረግ በተጨማሪ ቢሮክራሲያዊ መሰናክሎችን በማለፍ በኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ተሰማርቶ ከመንግሥታዊ ተቋማት ጋር አብሮ የመስራት ተምሳሌት የመሆን እቅድ ነበር። በዚህም መሰረት ማኅበሩ ዳያስፖራው በስፋት በኢንቨስትመንት ላይ እንዲሰማራ በማድረግ የዳያስፖራውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ውጤታማ ለማድረግ ከመንግሥት ተቋማት ጋር በትብብር ይሰራል። ለአብነት ያህል ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎች ተቋማት ጋር በተለያዩ መድረኮች በትብብር ሰርቷል። ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ያከናወናቸው ተግባራት ከእነዚሁ የመንግሥት አካላት ጋር በትብብር የተሰሩ ናቸው።
በአገር ውስጥ ገበያ የሚገኙ ለኢንቨስትመንት ስራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ጭምር ዋጋቸው በከፍተኛ ሁኔታ ሲጨምር ይስተዋላል። መንግሥት ይህ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ አካላት ላይ ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል። ቁጥጥሩ ለአጠቃላይ አገራዊ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አወንታዊ አስተዋፅዖ ስለሚኖረው መንግሥት በዚህ ረገድ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ አለበት። በተለይ በአገር ውስጥ የሚገኙና የሚመረቱ የምርት ግብዓቶች ዋጋ መናር ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል።
የዳያስፖራ ኢንቨስትመንት መሰናክሎች
የኢንቨስትመንት ስራ ራስን ማዘጋጀትን ይጠይቃል። ዳያስፖራውም ሆነ ሌላው አካል በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ሲሰማራ የሚያጋጥሙ ብዙ ችግሮች አሉ። የውጭ ምንዛሬ እጥረት ብዙ ተፅዕኖዎችን እየፈጠረ ይገኛል። በአገር ውስጥ ገበያ የሚገኙ ለኢንቨስትመንት ስራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ዋጋ መናርም በኢንቨስትመንት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል። ግብዓት አቅራቢዎች ከ10 እስከ 15 በመቶ ማትረፍ ሲገባቸው በአንድ ጊዜ ከ100% በላይ ማትረፍ የሚፈልጉ ሆነው ይስተዋላሉ።
በሌላ በኩል አንዳንድ አካላት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠሩትን የፀጥታ ችግሮች ለጥቅማቸው ብለው በእጅጉ አጋነው እያቀረቡ ያሉበት ሁኔታ ዳያስፖራው በሚፈለገውና ባለው አቅም ልክ ወደ አገሩ ገብቶ በኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ እንዳይሰማራ ጫና መፍጠሩ አይቀርም። ሰላምና የኢንቨስትመንት ስራዎች ፈፅሞ የማይነጣጠሉ በመሆናቸው የኦሮሚያ ዳያስፖራ ማኅበር ስለሰላም አስፈላጊነትና ግንባታ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮችን አከናውኗል።
ከዓለም አቀፋዊ ክስተቶች አንፃር ደግሞ በዩክሬይንና በሩስያ መካከል ያለውን ችግር መጥቀስ ይቻላል። ችግሩ የአንድ አገር ወይም የጥቂት አገራት ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ችግር ሆኗል። ይህ ችግር ደግሞ በኢንቨስትመንቱ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል።
አንድ ባለሀብት ለኢንቨስትመንት ስራ ሲሰማራ እርሱ ባለው አቅምና በአገሪቱ ሀብት ላይ መመስረት አለበት። ለምሳሌ አንድ ኢንቨስተር ወደ ኬንያ ሄዶ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ቢፈልግ በአቅም ልክ ማሰብ ይኖርበታል። ምክንያቱም በአቅም ልክ ካልታሰበ ስራው ተንጠልጥሎ ሜዳ ላይ ሊቀር ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም ፖለቲካን ለፖለቲከኞች መተው ሲገባ፤ ባለሀብቱም፣ ዳያስፖራውም፣ ተማሪውም … ፖለቲከኛ ሆኖ መገኘት በኢንቨስትመንትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚያስከትል ከእንዲህ ዓይነት ልማድና ተግባራት መቆጠብ ይገባል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት በአገር ውስጥ ያለው የተቋማት ቢሮክራሲ ባሰቡት ልክ ለመንቀሳቀስ ስላላስቻላቸው ተመልሰው የሄዱ ዲያስፖራዎችም አሉ። በኢንቨስትመንት ተሰማርቶ ውጤታማ ለመሆን የአሰራር ውጣ ውረዶችን መቋቋም ያስፈልጋል። ብዙ ተቋማዊ መሰናክሎችን አልፈው በአሁኑ ወቅት ጥሩ የኢንቨስትመንት ደረጃ ላይ የሚገኙት የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት፣ ለሌሎችም አርዓያ መሆን ችለዋል።
በእቅዳቸው መሰረት በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ተሰማርተው የሥራ እድሎችን የፈጠሩና ማኅበረሰቡን የጠቀሙ ዲያስፖራ ባለሀብቶች እንዳሉ ሁሉ፤ ከመንግሥት መሬት ወስደው በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ስራ ያልገቡና የኢንቨስትመንት ስራ ሳያከናውኑበት የቀሩ አንዳንድ ዲያስፖራ ባለሀብቶችም አሉ።
በእርግጥ ይህ ችግር የዳያስፖራ ባለሀብቶች ችግር ብቻ እንዳልሆነ ይታወቃል። እንዲያውም ይህ ችግር አገር ውስጥ ባለሀብቶች ላይ የበለጠ በስፋት ይስተዋላል። በእርግጥ ባለሀብቶች ከመንግሥት መሬት ወስደው ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያስገድድ በመንግሥት የሚቀመጥ የጊዜ ገደብ አለ።
የኦሮሚያ ዳያስፖራ ማኅበር አሁን ካለው አቅም የተሻለ አቅምና አደረጃጀት ፈጥሮ ዳያስፖራው በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ኢንቨስትመንት ላይ ሰፊ ተሳትፎ እንዲኖረው ጥረት እያደረገ ይገኛል። የክልሉ መንግሥትና ተቋማት እስካሁን ያደረጓቸውን በጎና አወንታዊ ተግባራትን በማጠናከር በኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራት ለሚፈልጉና ጥያቄ ለሚያቀርቡ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት ቀልጣፋ ትብብር ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ ዶክተር ቶላ አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስት ሊደረግባቸው የሚችሉና አዋጭነት ያላቸው በርካታ ዘርፎች እንዳሉ ይታወቃል። በተለያዩ የዓለም አገራት ለኢንቨስትመንት አቅም ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም አሉ። ዳያስፖራው ማኅበረሰብ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ያለው ተሳትፎ እየተሻሻለ መምጣቱ ባይካድም፣ ካለው አቅም አንፃር ግን በቂ ነው ለማለት አያስደፍርም። ስለሆነም ይህን የሀገርና የዜጎች አቅም በማስተሳሰርና በማስተባበር ለአገር ልማትና እድገት በማሰብ ፈተናዎችን ተጋፍጦ የነቃ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ማድረግ ይገባል። የዳያስፖራው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ይበልጥ እንዲጠናከር ደግሞ ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ በስፋት እንዲሳተፍ የሚያስችሉ የተቀላጠፈ ምላሽ የሚሰጡ የአሰራር ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።
ዳያስፖራውን በተለያዩ ዘርፎች በማሳተፍ በአገሩ ኢኮኖሚ ላይ አሻራውን እንዲያሳርፍ ማነሳሳት የሚያስችል ሁለገብ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል። ተከታታይነት ያለው፣ በጥናትና ማስረጃ የተደገፈ የቅስቀሳ ስራ መስራት እንዲሁም ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረዶችን መፍታትና የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት ላይም ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል።
ዳያስፖራው በበኩሉ በራሱ ተነሳሽነት ለአገሩ ልማትና ዕድገት የበኩሉን ለማበርከት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። ይህን ለማሳካትም ስለሀገሩ ወቅታዊና ትክከለኛ የሆነ በቂ መረጃ እንዲያገኝ ማድረግ ይገባል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2014