ባለፈው አርብ የተጠናቀቀው የ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እስከ መጨረሻው ሳምንት ለቻምፒዮንነትና ላለመውረድ በሚደረጉ ትግሎች አጓጊ ሆኖ ተጠናቋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 15ኛ ድሉን ባሳካበት የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታ በተመሳሳይ ሰዓት በተካሄዱ ጨዋታዎች የተመዘገቡ ውጤቶች መነጋገሪያነታቸው ቀጥሏል።
በተለይም በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በፋሲል ከነማና ድሬዳዋ ከተማ መካከል በተካሄደው ተጠባቂ ጨዋታ የተመዘገበው ውጤት አወዛጋቢና አነጋጋሪ ሆኗል። ከፈረሰኞቹ በአንድ ነጥብ ርቀው ላለመውረድ የሚታገለው ድሬዳዋን የገጠሙት አፄዎቹ የቻምፒዮንነት እድላቸውን ጨዋታውን በማሸነፍ የፈረሰኞቹን ነጥብ መጣል መጠባበቅ ነበረባቸው። በዚህም አፄዎቹ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 13 ደቂቃ እስኪቀረው ድረስ ሁለት ለዜሮ መምራት ቢችሉም በቀሪ ደቂቃዎች 2ለ3 መሸነፋቸው የስፖርት ቤተሰቡን አስደንግጧል።
በዚህ ጨዋታ አፄዎቹ ተፎካካሪያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቻምፒዮን ለመሆን የሚያስችለውን ውጤት በእጁ እንዳስገባ አረጋግጠው ሆን ብለው ለተጋጣሚያቸው ድሬዳዋ ውጤት በመልቀቅ ከመውረድ ታድገውታል የሚል ትችት እየተሰነዘረባቸው ይገኛል። ይህን ወቀሳ የሚያቀርቡ የስፖርት ቤተሰቦች በምንም መመዘኛ የሁለቱ ቡድኖች(ድሬዳዋና ፋሲል) ያላቸው ወቅታዊ አቋምና አቅም እንደማይገናኝ ይሞግታሉ።
ለዚህም ማሳያነት በእኩል 29 ጨዋታዎች 62 ነጥብና 30 ነጥብ የሰበሰቡ ክለቦች በአቅም ደረጃ ሊገናኙ እንደማይችሉ ያስቀምጣሉ። በመጀመሪያ ዙር ፋሲል ከነማ ድሬዳዋን 4ለ0 መርታቱን በማስታወስም በጨዋታው ሆን ብሎ ውጤት የማስቀየር ሸፍጥ መሰራቱን ይከራከራሉ።
ይህን ሙግት የሚያነሱ ወገኖች ተፈፀመ ለሚሉት ውጤት ሆን ብሎ የማስቀየር ውንጀላ ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ ባይችሉም ውጤቱ ሊጉን በቅርበት ለሚከታተሉና ገለልተኛ የሆኑ የስፖርት ቤተሰቦች ጭምር ልባቸው እንዳልተቀበለው አልሸሸጉም።
ከጨዋታው አስቀድሞ የአፄዎቹን የቻምፒዮንነት ተስፋ ይዞ ወደ ሜዳ የገባው አዲስ አበባ ከተማ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ውጤት ለቋል ብለው ካሰቡ አፄዎቹ ለድሬዳዋ በተመሳሳይ ውጤት እንደሚለቁ አሉባልታዎች ሲነዙ ነበር። በጨዋታዎቹ የተፈጠረውና የተመዘገበውም ይሄው መሆኑን ለመናገር ያልሸሸጉ ገለልተኛ የስፖርት ቤተሰቦችም አልጠፉም። አፄዎቹ ካቻምና ዋንጫ የማንሳት የተሻለ እድል በነበራቸው ሰዓት ስሁል ሽረ ለመቀለ 70 እንደርታ ውጤት በመልቀቁ ተመሳሳይ በደል ደርሶባቸው እንደነበር የሚያስታውሱ የእግር ኳስ ወዳጆች ተመሳሳይ ነገር መፈጠር እንዳልነበረበት ወቀሳቸውን ይሰነዝራሉ።
በዚህ መካከል ከሊጉ የወረደው የአዲስ አበባ ከተማ ደጋፊዎች ደረሰብን ለሚሉት በደል አፄዎቹ ተጠያቂ መሆናቸውን ከመናገር አልተቆጠቡም። አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውም ‹‹በዚህ አይነት መንገድ ከፕሪሚየር ሊጉ መውረድ ወንጀል ነው፣ ይሄ የሀዘኔ ቀን ነው›› ብለው መናገራቸው ጨዋታዎቹ በጤናማ መንገድ አለመጠናቀቃቸውን እንደሚጠቁም በርካቶች በማህበራዊ ሚዲያው አስተያየት ሲሰጡበት ለመታዘብ ተችሏል። በርግጥ እኚህ አሰልጣኝም ቢሆኑ ላለመውረድ የሚጫወት ቡድን ይዘው ‹‹ለክብር ነው የምንጫወተው›› ማለታቸውና በወሳኝ ሰዓት ለተጫዋቾቻቸው ዕረፍት መስጠታቸው ለፈረሰኞቹ ውጤት እንደለቀቁ ማሳያ ተደርገው የሚቀርቡ ክርክሮችም በሌላ ወገን ሲነሱ ታይተዋል።
በእለቱ በተመሳሳይ ሰዓት በተካሄደው ሶስተኛ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ መርሃግብር ለማሟላትና ደረጃውን ከፍ አድርጎ ለማጠናቀቅ ወደ ሜዳ ሲገባ በተቃራኒው አዳማ ከተማ ላለመውረድ የመጨረሻውን ፍልሚያ ሊያደርግ ወደ ሜዳ እንደ ገባ ይታወቃል። አዳማ ከተማ በቀድሞ የአዳማ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚሰለጥነው ሀዋሳን ሊያሸንፍ ይችላል ተብሎ ቢገመት እንኳን በጨዋታው መላቀቅ አልነበረም ወይ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው::
የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር እነዚህን ጉዳዮች አጣርቶ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በዋናነት በቀጣይ ዓመታት እግር ኳሱ በንፁህ ስፖርታዊ ጨዋነትና ፍትሃዊ ፉክክር እንዲቀጥል ክለቦች ከአቅም በታች መጫወት ወይም መላቀቅ እንዳይኖር ቀደም ብሎ ከክለቦች ጋር በመነጋገር አንድ ወጥ ሕግና ደንብ በማዘጋጀት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረም እንዳለባቸው ከዘንድሮው የመጨረሻ መርሃ ግብር ጨዋታዎች ትምህርት መውሰድ እንዳለበት የብዙዎች እምነት ነው።
ከአቅም በታች የመጫወት ጉዳይ ለአገሪቱ እግር ኳስ ሌላ አሳሳቢ ችግር መሆኑ ቢታመንም ከሊጉ የወረዱ ክለቦችን በተመለከተ ሁሉንም የስፖርት ቤተሰብ በሚባል ደረጃ የሚያስማሙ እውነታዎች እንዳሉ ግን መካድ አይቻልም። ኢትዮጵያ ላይ በችሎታ ደረጃ ደካማ የሚባል ክለብ የለም፣ ነገር ግን ደካማ አመራር የሌለበት ክለብ ፈልጎ ማግኘት አዳጋች ነው። የወረዱትን ክለቦች ለአብነት ብንመለከት እንኳን በእግር ኳሳዊው ፉክክር ተመጣጣኝ ቢሆኑም አመራሮቻቸው ደመወዝ ባለመክፈል፣ የስራ ቦታን አመቺ ባለማድረግ የክለቦቹን ስነልቦና በመግደል እንዲወርዱ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳላቸው መሸሸግ አያስፈልግም።
በዚህ ላይ አሁን ካሉት ክለቦች አብዛኞቹ እራሳቸውን የክለብ አወቃቀር ውስጥ ለማስገባት እየሞከሩ አለመሆኑ ደሞ ለአገሪቱ እግር ኳስ ሌላኛው እራስ ምታት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ክለቦች የራሳቸውን ገቢ ለማመንጨት የግድ ፕሮፌሽናል የክለብ አመራር ሊኖር ይገባል። ብዙዎቹ ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ግን የኢትዮጵያ ክለብ አመራሮች ዳኞችን በጥቅም ሲያማልሉ እንጂ አደረጃጀታቸውን ለመቀየር ያላቸው ፍላጎት እምብዛም መሆኑ ሚስጥር አይደለም። የሊግ ካምፓኒውም ከአቅም በታች የመጫወት ጉዳይን ብቻ ሳይሆን አንዳንድ አስገዳጅ ህጎችን እያወጣ የተበላሸውን ኢ እግር ኳሳዊ አካሄድ እንዲያከትም ጉልህ ሚና ሊጫወት እንደሚገባው ይታመናል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 27 /2014