የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን(ዋልያዎቹ) ለ2023 የኮትዲቯር አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ወደ ማላዊ ሊሎንግዌ አቅንተው የምድብ የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎችን ከማላዊና ግብፅ ጋር አድርገው ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል። ከትናንት በስቲያም በማላዊ ስለ ነበራቸው ቆይታ መግለጫ ተሰጥቷል።
በመግለጫው ቴክኒካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች በቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተና በፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ማብራሪያ ተሰጥቷል።
የቡድኑን ቴክኒካዊ ጉዳይ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት አሰልጣኝ ውበቱ፣ በአጠቃላይ የማላዊ ጉዞና ቆይታቸው መልካም መሆኑን ገልጸዋል። በመጀመሪያው ጨዋታ ዋልያዎቹ በሁለት የፍጹም ቅጣት ምቶች በተቆጠሩባቸው ግቦች መሸነፋቸውን ያስታወሱት አሰልጣኙ በጨዋታው ከእረፍት መልስ መጠነኛ ለውጦችን አድርገው አንድ ግብ ቢያስቆጥሩም ማሸነፍ እንዳልቻሉ አብራርተዋል። እንደ አሰልጣኙ ማብራሪያ በዚህ ጨዋታ ተፈላጊውን ውጤት ማስመዝገብ ባይቻልም የቡድኑን ጠንካራና ደካማ ጎን ለመመልከት ተችሏል።
ይህም በቀጣይ ከግብጽ ጋር ለነበረው ጨዋታ ግብአት ሆኖ በተለየ አቀራረብ ማሸነፍ እንደተቻለ ተናግረዋል። ‹‹ግብፅን ማሸነፍ ትልቅ ነገር እንደሆነ ይሰማኛል። ግን ከዛ በላይ በወጥነት ከሜዳ ውጭ ያደረግናቸውን ትላልቅ ጨዋታዎች በተረጋጋ መንገድ ለማከናወን መሞከራችን ቡድናችንን የበለጠ ተስፋ እንድንጥልበት አድርጎናል›› ብለዋል፡፡ ይህን ከባድ ፍልሚያ ዋልያዎቹ ማሸነፍ የቻሉትም ቀደም ብለው የፈርኦኖቹን ጨዋታ በመገምገም አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል። ፈርኦኖቹ ከጨዋታው በፊት ዋልያዎቹን አሳንሰው ማየታቸውም ዋጋ እንዳስከፈላቸው አክለዋል፡፡
‹‹ቅድመ ጨዋታ ላይ ተጫዋቾቹን ከማነሳሳት ውጭ የተለየ ነገር አላደረግንም። ጨዋታው እየተከናወነ ግን የሚሰማህ ስሜት አለ። ተጫዋቾቹ ያደረጉት ነገር ደግሞ የበለጠ የራስ መተማመናችን ከፍ እንዲል አድርጎታል። ግን መጠንቀቅ እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር። ምክንያቱም ግብፅ ግብፅ ነች። ጨዋታውን በሆነ መንገድ ልትነጥቅህ ትችላለች›› ያሉት አሰልጣኙ ዋልያዎቹ ግብጽን በጨዋታ በልጠው በማሸነፋቸው የተሰማቸውን ደስታ መሸሸግ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።
‹‹ከግብፅ ጨዋታ የተቆጨሁበት ነገር የለም። ከበቂ በላይ ነው›› ያሉት አሰልጣኙ በማላዊው ጨዋታ ግን ዋልያዎቹ ላይ የተቆጠሩ ግቦች በተከላካይ መስመር ጥቃቅን ስህተቶች መሆኑን አስረድተዋል። ምናልባትም እነዛ ስህተቶች ባይፈጠሩ የጨዋታው ውጤት ሊቀየር ይችል እንደነበር ተናግረዋል። በተጨማሪም በዚያ ጨዋታ ዋልያዎቹ የተንቀሳቀሱበት መንገድ ቢያንስ አንድ ነጥብ እንኳን ከጨዋታው ማግኘት እንዳለባቸው የሚያስቆጭ መሆኑን በመግለጽ ተጫዋቾቹ ግን የሚቻላቸውን ሁሉ እንዳደረጉ አብራርተዋል።
ዋልያዎቹ ከባድ የተባለውን ጨዋታ ያሸነፉት በፈርኦኖቹ ደካማነት እንጂ ዋልያዎቹ ጠንካራ ሆነው አይደለም በሚል ለሚሰነዘሩ ሃሳቦች ቅሬታ እንዳላቸው የተናገሩት አሰልጣኝ ውበቱ፣ ዋልያዎቹ ከዚህ በፊት ኒጀርን ገጥመው ሲያሸንፉ ተመሳሳይ ሃሳብ ሲነሳ እንደነበር አስታውሰዋል። ‹‹ደካማዋን ኒጀር አሸነፉ ተባለ። ከዛ ማዳጋስካርን ገጠመን ያኔም ተመሳሳይ አስተያየት ተሰጥቷል። እኛ ያሸነፍናቸው ቡድኖች ሁሉ ሲሸነፉ ደካማ ከሆኑ እንዴት እናድርግ። ግብፅ አሠልጣኝ ቀይራለች።
የተወሰኑ ተጫዋቾችንም አታለች። ይሄ የተወሰነ ተፅዕኖ ይኖረዋል። እንደ ብሔራዊ ቡድን ግን እኛ በልጠናል። ስለዚህ ክሬዲቱን ለተጫዋቾቹ እንስጥ። ግብፆች ወረዱ ያስባለው የእኛ መብለጥ ነው። በዛ ቀን ኢትዮጵያ ጥሩ ስለሆነች ግብፅ አንሳለች። በዛ ጨዋታ የሚችሉትን ሞክረዋል። ተጫዋችም ቀይረው ሞክረዋል። ግን የእኛ ተጫዋቾች በልጠው ነበር።
ግብፅ ደክማ አይመስለኝም። ምክንያቱም ከሦስት ቀን በፊት ጊኒን አሸንፋለች። ዞሮ ዞሮ የኢትዮጵያ ቡድን ከግብፅ ተሽሎ ስለነበረ ነው ያሸነፈው። በተሸነፍንበትም ሆነ ባሸነፍንበትም ጨዋታ ተጋጣሚ ደክሞ ከሆነ ያስቸግራል። ደግነቱ ጨዋታው በቴሌቪዥን ስለታየ ቡድኑ የነበረውን ብቃት ሁሉም ሰው አይቶታል። በጨዋታው ጥሩ ልንጫወት እንደምንችል ላስብ እችላለሁ ግን አምስት ስድስት የግብ እድል እንፈጥራለን ብዬ አላስብም ነበር›› በማለት በዚህ ረገድ የሚሰጠው አስተያየት ተገቢ አለመሆኑን አሰልጣኙ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ከሁለቱ ጨዋታዎች በኋላ ቡድኑ ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶችን በተመለከተ አሰልጣኝ ውበቱ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡም ‹‹ቦታው ለዚህ ነገር ቅርብና ክፍት ነው። ከትችቶቹ የሚጠቅምህን እየወሰድክ የማይጠቅሙህን እየተውክ ትሄዳለህ። ግላዊና ከቤተሰብ ጋር የተገናኙ ነገሮች ሲሆኑ እንደ ሰውኛ በስጨት የምትልበት አጋጣሚ ይፈጠራል እንጂ የትልቅ አገር ብሔራዊ ቡድንን እያሰለጠንክ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል ማለት አይደለም። ተፅዕኖ የለውም ማለት ግን አይቻልም።
ተጫዋቾች ጋር ይጋባል። እኔ ግራ የሚገባኝ አንድ ነገር ግን አለ፣ እኛ ባለሙያዎች፣ የውጭ ሰዎች የሚሰጡን እና እዚህ የሚሰጠን አስተያየት ያምታታኛል። ይህ እኔም ተጫዋቾቹም ሆነ ቡድኑ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል። ከእንደሱ አይነት ጫና የምንጠበቅበት ነገር ቢኖር ጥሩ ነው። ምክንያታዊ የሆነ ትችት የሚሰጡ ሰዎችና ባለሙያዎች አሉ። አለፍ የሚለውን ነገር መሸከም ነው ያልቻልነው። እኔ ልኖርም ላልኖርም እችላለሁ። የሚኖረውን ሰው ግን በደንብ መደገፍ አለብን›› ብለዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8 /2014