‹‹ኮካ-ኮላ›› የሚለው ስያሜ ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም ታዋቂ የሆነ ስም ነው። ይህ ከዓለም ግዙፍ የንግድ ተቋማት መካከል አንዱ በሆነው የኮካ-ኮላ ኩባንያ (Coca-Cola Company) የሚመረተው ለስላሳ መጠጥ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረተው እ.አ.አ በ1886 ዓ.ም በአትላንታ ሲሆን፣ የመጠጡ ቀማሚ ደግሞ አሜሪካዊው ጆን ስቲዝ ፔምበርተን ነው።
ከሦስት ዓመታት በኋላ አሳ ግሪግስ ካንድለር የተባሉ አሜሪካዊ ባለሀብት የኮካ-ኮላን አሰራር ቀመር ከቀማሚው በመግዛት እ.አ.አ በ1892 ዓ.ም ኮካ-ኮላ ኩባንያን (Coca-Cola Company) አቋቁመው ዛሬም ድረስ በመላው ዓለም ተወዳጅ ሆኖ መዝለቅ የቻለውን ለስላሳ መጠጥ በማምረት ለገበያ ማቅረብ እንደጀመሩ የኮካ-ኮላ ታሪክ መረጃዎች ያስረዳሉ።
የኮካ-ኮላ ኩባንያ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ኩባንያው ምርቱን ከአሜሪካ በማሻገር እ.አ.አ በ1928 ዓ.ም ወደ አፍሪካ ገበያ ገብቶ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በ14 የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ 40 ማምረቻ ፋብሪካዎችን ገንብቶ ከ17ሺ በላይ ለሚሆኑ አፍሪካውያን የሥራ እድል ፈጥሯል።
ኮካ-ኮላ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ስራ የጀመረው በ1951 ዓ.ም ሲሆን በአሁኑ ወቅት የአምቦ የማዕድን ውሃ ማምረቻ ድርጅትን ጨምሮ የአምስት ፋብሪካዎች ባለቤት ነው። ኩባንያው ከቀጥተኛ የስራ እድል ፈጠራ ሚናው በተጨማሪ ከ70 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎችንም በንግድ ትስስር ተጠቃሚ አድርጓል።
ከመጀመሪያው የአዲስ አበባ ፋብሪካው በተጨማሪ በድሬዳዋ እና በባህር ዳር ፋብሪካዎቹ ኮካኮላን እያመረተ ለሕብረተሰቡ ሲያቀርብ የቆየው ኩባንያው፣ በቅርቡ ደግሞ በሰበታ ከተማ ያስገነባውን ፋብሪካ አስመርቋል። በ100 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው ‹‹ሰበታ ዲማ ፋብሪካ (Warshaa Sabbataa Diimaa)›› የተሰኘው ይህ ፋብሪካ፣ ኩባንያው በአምስት ዓመታት ውስጥ ለማከናወን የያዘው የ300 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት እቅድ አካል ነው። በሦስት ዓመታት ተገንብቶ የተጠናቀቀውና ጊዜው በደረሰባቸው ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የተደራጀው ይህ ፋብሪካ፤ የስራ እድል ፈጠራን፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትንና የሀገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተገልጿል። በዓመት ከ100 ሚሊዮን በላይ የሚሆን የታሸጉ የኮካ ኮላ የለስላሳ መጠጥ ምርቶችን ለማምረት አቅም ያለው ፋብሪካው፤ ለ500 ሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ ዜጎችን ደግሞ በንግድ ትስስር ተጠቃሚ የሚያደርግ ይሆናል።
የኮካኮላ ቢቨሬጅስ አፍሪካ-ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዳረል ዊልሰን፣ ኮካኮላ ኩባንያ ሰበታ ላይ የገነባው ፋብሪካ ኩባንያው በሚቀጥሉት ዓመታት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንቱን ለማስፋፋት የያዘው እቅድ አካል እንደሆነ ተናግረዋል። እርሳቸው እንዳሉት፣ ኩባንያው ኢንቨስትመንቱን ለማስፋፋት የወሰነው የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ጀምስ ኩዊንሲ ከሦስት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ነው።
የፋብሪካው ሥራ መጀመር ተጨማሪ የወጪ ንግድ ዕድሎችን ይከፍታል። በዋናነት ከሚያመርተው የለስላሳ መጠጦች ባሻገር ለፋብሪካው ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ለማምረት የሚያስችሉት የምርት መስመሮች ያሉት ፣ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን፣ የጠርሙስ ክዳኖችንና ሌሎች ግብዓቶችንም ማምረት ይችላል። የእነዚህ ምርቶች በፋብሪካው መመረት ደግሞ ከውጭ የሚገቡ ተመሳሳይ ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱና ለምርቶቹ ግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀር ይሆናል። እነዚህን የፕላስቲክ ጠርሙሶችንም በጎረቤት ሀገራት ለሚገኙት እህት ኩባያዎቹ ለመላክ ያስችለዋል።
ኩባንያው ኢንቨስትመንቱን በማስፋፋት ቀጣዩን ፋብሪካውን በሃዋሳ ለመገንባት ማቀዱንና የኢትዮጵያውያንን የለስላሳ መጠጥ ፍላጎት ለማርካት እንዲሁም በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር እንደሚሰራም ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የኮካ-ኮላ ቢቨሬጅስ አፍሪካ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዣክ ቨርሙለን፣ ኮካ-ኮላ ላለፉት 60 ዓመታት በኢትዮጵያ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ኩባንያው በንግድና ኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ከመሰማራቱ ባሻገር ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉና ለማኅበረሰቡ ኑሮ መሻሻል አጋዥ የሆኑ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱንም ገልጸዋል። ‹‹ስራውን ስንጀምር በኢትዮጵያ እንደምንተማመንና ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንደምናከናውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ነግረናቸው ነበር። ይህ ስኬታችንም የዚያ ቃላችን አካልና ማሳያ ነው። ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ፋብሪካ መገንባታችን ለእኛም ኩራት፣ ለኢትዮጵያም ትልቅ አቅምና እድል ነው። ኢትዮጵያ የቀጣይ ዓመታት ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሀገር እንደምትሆን እናምናለን›› በማለት ተናግረዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና ሌሎች ችግሮች በስራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ቢያሳድርም ፈተናዎቹን በመቋቋም ፋብሪካውን ለስኬት ማብቃት መቻሉን ተናግረዋል። የኩባንያውን ምጣኔ ሀብታዊ አስተዋፅኦ በተመለከተም ‹‹ … ኮካ-ኮላ ቢቨሬጅስ አፍሪካ-ኢትዮጵያ ግዙፍ ካፒታል ከሚያንቀሳቅሱ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑንና ከፍተኛ ታክስ ከሚከፍሉ ድርጅቶች መካከልም ተጠቃሽ እንደሆነ ጠቁመዋል። ኩባንያው በቀጣይ አዳዲስ ምርቶችን ወደ ገበያ በማስገባት የደንበኞቹን ፍላጎት ለማርካት እንደሚሰራም ገልጸዋል።
የኮካ-ኮላ አፍሪካ ፕሬዚደንት ብሩኖ ፔትራቺ በበኩላቸው፣ ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ካሉ የኮካ-ኮላ ፋብሪካዎች ሁሉ እጅግ ዘመናዊው እንደሆነ ጠቅሰዋል። ኩባንያው በየጊዜው በሚያዘምነው አሰራሩ ኅብረተሰቡን የሚጠቅም እንዲሁም ብክነትን የሚቀንስ የውሃ አጠቃቀም ሥርዓትን መዘርጋት እንደቻለ የገለጹት ፕሬዝደንቱ፣ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት የሚሰጥ፣ ሴቶችንና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራርን በመተግበር ዘላቂ ልማትን መሰረት ያደረገ የኢንቨስትመንት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ‹‹የንግድ ስራችንን ከማሳደግ ባሻገር ከአፍሪካ የሚገኘውን የሰው ኃይል ክህሎት አቅም ማሳደግም ዓላማችን ነው። ከማሕበረሰቡ ጋር በጋራ የማደግ ፍላጎት አለን። በየቀኑ የምናከናውናቸው ተግባራት ማሕበረሰባዊ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ እንዲሆኑ እናደርጋለን›› ብለዋል።
ማሕበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ ኮካ-ኮላ ቢቨሬጅስ አፍሪካ-ኢትዮጵያ የትምህርትና የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማትን በመገንባት የኩባንያው ፋብሪካዎች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የማሕበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጉንም ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ዳረል ዊልሰን ገልጸዋል። ለአብነት ያህልም በአምቦ እና በባህር ዳር ከተሞች ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን አስገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱን ጠቅሰዋል። የአካባቢ ብክለትን ለማስወገድም ከ14ሺ በላይ ሴቶች የኮካ-ኮላ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን እንዲሰበስቡ ስልጠና ሰጥቷል።
‹‹የፋብሪካው ግንባታ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የተደረገ ጥረት ውጤት ነው›› ያሉት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ኩባንያው በአጭር ጊዜ ውስጥ ያስገነባው ዘመናዊና ምቹ የሥራ ከባቢ ያለው ፋብሪካ ለሀገራዊ ምርትና እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉን የኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝና የክልሉ መንግሥት ኢንቨስተሮችን ለመደገፍ ዝግጁ እንደሆነ አረጋግጠዋል።
አሰራሮችን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንና ለባለሀብቶች (በተለይም ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች) ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑም አስረድተዋል። አቶ ሽመልስ ‹‹ከምጣኔ ሀብት ማሻሻያው በኋላ በተከናወኑ ተግባራት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አሰራሮች ተግባራዊ በመደረጋቸው 10ሺ የሚሆኑ አርሶና አርብቶ አደር ባለሀብቶችን ማፍራት ተችሏል›› ብለዋል።
የኢንዱትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ኮካ-ኮላ ኩባንያ በኢትዮጵያ የአምራች ዘርፍ ታሪክ የማይተካ አስተዋፅኦ ያለው ተቋም መሆኑን ጠቅሰው፤ የፋብሪካው ግንባታ በኢትዮጵያ ለአምራች ዘርፉ ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ የሚያመለክት መሆኑንና ፋብሪካው ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለአጠቃላይ ሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
ኩባንያው ማሕበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የጤናና የትምህርት መሰረተ ልማቶችን በመገንባት እንዲሁም ሴቶችንና ወጣቶችን በማብቃት ረገድ እያከናወናቸው ላሉት ተግባራት መንግሥት እውቅና እንደሚሰጥና ይኸው ተግባሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የኢንዱትሪ ዘርፉ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብታዊ መዋቅራዊ ሽግግር ያሳካል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትና ልዩ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ መሆኑን የተናገሩት አቶ መላኩ፤ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አሁን ካለበት ደረጃ እንዲሻሻል መንግሥት በርካታ የሪፎርም ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ‹‹ለአብነት ያህልም በጥሬ እቃ፣ በፋይናንስ፣ በመሰረተ ልማትና በሰው ኃይል አቅርቦት ረገድ ማሻሻያዎችን በማድረግ፣ በተለይም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ (Home Grown Economic Reform) መርሃ ግብሩ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተመቸ ሁኔታ እንዲፈጠርና ዘርፉ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ የገቢ ምርቶችን ለመተካት እና ለስራ እድል ፈጠራ የሚገባውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል፤ ተጠናክሮም ይቀጥላል›› ብለዋል።
የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት አምነው በግዙፍ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ የተሰማሩ ትልልቅ ኩባንያዎች መንግሥት ለአምራች ዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ተገንዝበው የኢንቨስትመንት ስራዎቻቸውን በማስፋፋትና አጠናክረው በመቀጠል በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያላቸውን ድርሻ እንዲያሳድጉም ጠይቀዋል።
በአሁኑ ወቅት የሃገራዊ ኢኮኖሚ ማነቆዎች ከሆኑ ችግሮች መካከል አንዱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው። የኮካኮላ ቢቨሬጅስ አፍሪካ-ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዳሪል ዊልሰንም ይኸው ችግር በስራቸው ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ገልፀዋል። ‹‹የውጭ ምንዛሬ እጥረት አንዱ ችግር እንደሆነ ይታወቃል። በመንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሮች ስለምንተማመን ችግሩን ለመፍታት ከመንግሥት ጋር በትብብር እንሰራለን›› ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው ‹‹ኮካ-ኮላ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በስራው ላይ ጫና እንደፈጠረበት ቢገልፅም እኛ ግን ኮካ-ኮላ ለዚህ ችግር መፍትሄ አለው ብለን እናምናለን። ኢትዮጵያ የምትገኝበት ተፈጥሯዊ አቀማመጥ ስትራቴጂካዊ በመሆኑ የኮካኮላ ምርቶችን በዝቅተኛ ወጪ ኢትዮጵያ ውስጥ ማምረት ከተቻለ ምርቶቹን ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በመላክ ምናልባትም ከኮካ-ኮላ የውጭ ምንዛሬ የምንጠብቅና የምንጠይቅ እንጂ ኮካ-ኮላ ፋብሪካ ከመንግሥት ሊጠይቅ አይችልም የሚል ውይይት አድርገናል። የኮካ-ኮላ ምርቶችን ወደ ሌሎች ሀገራት መላክ እንችላለን። የትራንስፖርትና የፓኬጂንግ ስራዎች ከተስተካከሉ የውጭ ምንዛሬ ችግርን መቅረፍ እንችላለን ብለን እናምናለን። ስለሆነም ኮካ-ኮላ ይህን አሰራር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ›› በማለት ኩባንያው ራሱ ለውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር መፍትሄ መሆን እንደሚችል አመልክተዋል።
እንደ አቶ መላኩ ገለፃ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጀምሮ በስፋት እየቀጠለ ያለው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅምና አጠቃቀማቸውን የማሳደግ ዓላማ ስላለው ኮካ-ኮላ ፋብሪካም በዚህ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል። ኮካ-ኮላ ኩባንያ በቀጣይ ዓመታት የኢንቨስትመንት ስራውን ለማስፋት በሚያደርገው ጥረት መንግሥት ለኩባንያው ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም