በደቡብ ጎንደር ደብረ ታቦር ከተማ ነው ተወልዳ ያደገችው። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷንም በዚያው አካባቢ ተከታትላለች። ወደ አዲስ አበባ አቅንታም በቀድሞው ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በአሁኑ ሜትሮ ፖሊቲያን ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ድግሪዋን አግኝታለች። የቢዝነስ ማኔጅመንት ትምህርቷን በመከታተልም ሁለተኛ ዲግሪዋን መያዝ ችላለች።
አጠር ያለው ቁመቷ ቀጠን ካለው ሰውነቷ ጋር ተደምሮ ቀልጠፍ ያለ እንቅስቃሴ እንዲኖራት አግዟታል። ለተመለከታት ገና በቤተሰብ ቁጥጥር ያለች ትመስላለች፤ የአንድ ድርጅት ሠራተኞችን የምታስተዳድርም አትመስልም፤ ይሁን እንጂ እሷ ግን ቤተሰብ ከማስተዳደር ባለፈ ድርጅት የምትመራ ናት፤ የፍቅር ጋርመንት ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፍቅርተ ታደለ።
በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኘው ወይዘሮ ፍቅርተ ባለትዳርና የሶስት ልጆች እናት ናት። ከፍተኛ የሥራ ሞራል አላት፤ ነገ ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ብዙ ተስፋ የሰነቀችና በየጊዜው ሥራዋን ለማዘመንና ለማሳደግ ጥረቶችን የምታደርግ ናት። ወይዘሮ ፍቅርተ በጋርመንትና ጨርቃጨርቅ የሥራ ዘርፍ ውስጥ ከትንሽ ተነስታ ትልቅ ቦታ የደረሰችበት መንገድ እንዲሁም እየሠራቻቸው ያሉት አዳዲስና ወቅታዊ ሥራዎቿ ለሌችም ተሞክሮ ይሆናሉ ብለን የዕለቱ የስኬት እንግዳችን አድርገናታል።
የፍቅር ጋርመንት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፍቅርተ ታደለ፤ ገና ተማሪ እያለች የእጅ ሥራዎችንና ጥልፎችን ትሞክር ነበር። ሙከራዋንም የአስረኛ ክፍል ተማሪ በነበረችበት ወቅት በተግባር አውጥታ ማሳየት የምትችልበትን ዕድል በማግኘቷ ከትምህርቷ ጎን ለጎን ትርፍ ጊዜዋን ሁሉ የእጅ ሥራ በመሥራት ማሳለፍ ውስጥ ገባች። የመጀመሪያ ዲግሪዋን ባገኘችበት የመምህርነት ሙያም በኦሮሚያ ክልል ለሚ በቾ በሚባል ከተማ ለአንድ ዓመት ያህል አገልግላለች። ታዲያ በአንድ ዓመት የመምህርነት ቆይታዋም ጥሩ የምትለውን ጊዜ ማሰላፏን ታስታውሳለች።
ከአንድ ዓመት የመምህርነት ሥራ በኋላ ግን በውስጧ ያለውን የእጅ ሥራ በማሳደግ በጋርመንትና ጨርቃጨርቅ ዘርፍ ለመሰማራት ወስና የመምህርነት ሥራዋን በፈቃዷ ለቃ ፊቷን ሙሉ ለሙሉ ወደ ልብስ ስፌት አዞረች። ሥራዋን የለቀቀችው ወይዘሮ ፍቅርተ፤ በቀጥታ በጋርመንት ሥራ ተቀጥራ መስራት ጀመረች። በወቅቱም ያላትን አቅምና ችሎታ አውጥታ በመጠቀም ዘርፉ የነብሷ ጥሪ ስለመሆኑ ታረጋግጣለች። ከቅጥር በኋላም በዘርፉ ወደ ተሰማሩ ዘመዶቿ በመጠጋት በስፌት፣ በጥልፍ፣ በዲዛይንና በአስተዳደር ጭምር ሠርታለች።
በይበልጥ በአስተዳደሩ ላይ ሰርቻለሁ የምትለው ወይዘሮ ፍቅርተ፤ ከምታውቃቸው ሰዎች ጋር በሠራችበት ጊዜ በአስተዳደር ዘርፉ ላይ በዲዛይንና አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠር ጥሩ ተሰጥኦ እንዳለት ተረዳች፤ በዚህም ሥራውን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል ያላትን ጥልቅ ዕውቀት ለመረዳት የሚያስችል ምቹ ሁኔታም ፈጠረላት።
በቆይታዋም ወደ አእምሮዋ የሚመጡ አዳዲስ ነገሮችን ወደ ሥራ በመቀየር ችሎታዋን በማዳበር አንድ እርምጃ ወደ ፊት የቀደመችው ወይዘሮ ፍቅርተ፤ የራሷን ሥራ ለመሥራት ሙከራ ላድርግ ብላ በግሏ ለመሥራት አምስት ሺ ብር ካፒታል በመያዝ ወደ ሥራው ገባች። በእጇ ያለውን ሙያ ተጠቅማ አንድ የስፌት መኪና ይዛ የተለያዩ አልባሳትን መስፋት ትጀምራለች፤ ፍቅር ጋርመንት በሚል የጀመረችው የጋርመንት ሥራዋ በአሁኑ ወቅት በተሻለ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኝ ሆኗል።
ተቀጥራ ትሰራ የነበረችው ወይዘሮ ፍቅርተ በፍቅር ጋርመንት በኩል በአሁኑ ወቅት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ለማስገኘት ችላለች። በፍቅር ጋርመንት የተማሪዎችን እና የመንግሥትና የግል ድርጅቶች የደንብ ልብሶችን /ዩኒፎርም/ እንዲሁም የወንዶች ሸሚዝ በስፋት ይመረታሉ። ዩኒፎርም ከምታቀርብላቸው ድርጅቶች መካከልም ሆቴሎች ቀዳሚ ሲሆኑ ለአብነትም ደብረዘይት ቶሚ ኢንተርናሽናል ሆቴል፣ አዲስ አበባ ከተማ ራዲሰን ብሉ ኢንተርናሽናል ሆቴል፣ ካፍቴሪያዎችና ሌሎችም ይገኙበታል።
በመደበኛነት ከሚመረቱት እነዚህ ምርቶች በተጨማሪም የህጻናት አልባሳትን በአዲስ መልክ ለማምረት ዝግጅቷን ያጠናቀቀችው ወይዘሮ ፍቅርተ፤ የህጻናቱ አልባሳትም ምቾት ያላቸው ስለመሆናቸው ትናገራለች። የህጻናቱን አልባሳት ለመሥራት ታዲያ ፈጠራን ከመጠቀም ባለፈ በተለያዩ ፊልሞች ላይ የሚታዩ አሻንጉሊቶች የሚለብሱትን በመመልከት ተመሳሳዩን ዲዛይን በማድረግ እየሠራች መሆኑን አጫውታናለች።
የህጻናቱ አልባሳት ምቾት ያለውና እንደሚፈለገው አይነት ተደርጎ የሚመረት በመሆኑ ብዙዎች ይፈልጉታል። ዘርፉ ብዙ ሥራ ሊሠራበት የሚችል ነውና በቀጣይም ይህንኑ የሕጻናት አልባሳት በስፋትና በጥራት በማምረት ከውጭ የሚገባውን ለማስቀረት የበኩሏን እንደምታደርግ ወይዘሮ ፍቅርተ ትናገራለች። ይህም የሚቻልና ቀላል እንደሆነ ነው ያስረዳችው።
‹‹ማንኛውም ምርት በጥራት ከተመረተ ህዝቡ ይወደውና ይቀበለዋል›› የምትለው ወይዘሮ ፍቅርተ፤ እርሷም ቅድሚያ ለጥራት ሰጥታ ማምረት በመቻሏ ገበያው ውስጥ በስፋት እየገባች መሆኑን ትናገራለች። ለአብነትም ባሳለፍነው የፋሲካ በዓል በኤግዚብሽን ማዕከል ምርቶቿን ይዛ በመቅረብ ጥሩ ገበያ አግኝታለች። በተለይም የወንዶች ሸሚዝ ጥራት ያለውን ምርት ባማረ አጨራረስ ማቅረብ በመቻሏ ሰፊ የገበያ ትስስር ተፈጥሮላታል።
ደንበኞቿ በጥሩ ሥራዎቿ አማካኝነት ሌሎች ደንበኞችን እየፈጠሩላት እንደሆነ ያነሳችው ወይዘሮ ፍቅርተ፤ በጨረታ ከምታገኘው ገበያ ይበልጥ በደንበኞቿ ምክንያት የምታገኘው ገበያ ሰፊ እንደሆነ ነው የምትናገረው። ለዚህም በየዕለቱ ጥራት ያለው ምርት ለማምረት በመትጋት ተወዳዳሪ ሆና ቀጥላለች።
ጥቂት የስፌት መኪናዎችን በመያዝ በኪራይ ቤት በ2005 ዓ.ም ወደ ጋርመንት ሥራው የገባችው ወይዘሮ ፍቅርተ፤ ሰሚት አካባቢ 250 ካሬ ሜትር ቦታ በሊዝ በመግዛት 190 ካሬ ሜትር የሚሆነውን ቦታ ሙሉ ለሙሉ ማምረቻ አድርጋዋለች። በዚሁ ቦታ ላይም የተለያዩ አውቶማቲክና ሲንግል የሚባሉ በድምሩ 60 ማሽኖችን በማቆም የጋርመንት ሥራዋን እያቀላጠፈች ትገኛለች።
የስፌት መኪኖቹ 50 ሲሆኑ፤ ስምንቱ ደግሞ ኢምብሮደሪ የሚባል ማተም የሚችሉ ዘመናዊ የስፌት ማሽኖች ናቸው። ይህ ዘመናዊ የህትመት ሥራን የሚያቀላጥፈው ማሽን በአሁኑ ወቅት ዘመኑ የደረሰበት ቴክኖሎጂ መሆኑን ነው የምትገልጸው። ማንኛውንም በኮምፒዩተር የተሠራለትን ዲዛይን በፍላሽ ተቀብሎ የሚፈለገውን ውጤት በልብሱ ላይ በክር መጥለፍ ይችላል። የቀረቡለትን የተለያዩ ክሮችን በቦታ በቦታቸው በማስገባት የሚፈለገውን አይነት ጥልፍ ይሰራል። ይህ ማሽንም አሁን ባለው ገበያ አንድ ሚሊዮን ብር ያወጣል። ማሽኑ በአንድ ጊዜ ስምንት ዲዛይን ማምረት ይችላል። ይህም ማለት አንድ ዲዛይን ስምንት ልብሶች ላይ አትሞ ያወጣል እንደማለት ነው።
በኪራይ ቤት ከአንድ ሁለት፤ አምስትና አስር ማሽን እያለች በአሁኑ ወቅት 60 ዘመናዊ የስፌት ማሽኖችን ማፍራት የቻለችው ወይዘሮ ፍቅርተ፤ 22 አካባቢ ጊዜያዊ የመሸጫ ቦታ አላት። በቅርቡም ሰሚት እና ቄራ አካባቢ ሌሎች የመሸጫ ቦታዎችን ለመክፈት አቅዳለች። በተለይም ባደረገችው የገበያ ጥናት መሰረት በአሁኑ ወቅት የህጻናት አልባሳት ኮንፈርት ተፈላጊ ነው፤ በዚህም ላይ በስፋት ወደ ማምረት መግባትና ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ የክልል ከተሞችም ለማከፋፈል በሚያስችላት ቁመና ላይ መሆኗን ነው የጠቆመችው።
ወይዘሮ ፍቅርተ እንዳለችው፤ በቋሚነት ለ30 ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንዲሁም ባመረቱት ልክ ለሚከፈላቸው 30 ሰዎች የኮንትራት ሥራም ፈጥራለች። ከአስተዳደር ሠራተኞች ውጭ በማምረት ሥራ ብቻ በድምሩ ለ60 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችላለች። በእዚህ የሰው ኃይል በቀን ከ500 እስከ 700 የሚደርሱ አልባሳትን ማምረት እንደሚቻል የምትናገረው ወይዘሮ ፍቅርተ፤ አንዳንድ ሥራዎች እጅ የሚይዙ ባይሆኑባት ድርጅቱ ከዛም በላይ የማምረት አቅም ያለው መሆኑን ትናገራለች።
በአስር ዓመት የጋርመንት ሥራ እንቅስቃሴዋ መሰረት በመጣል ውጤታማ መሆን የቻለችው ወይዘሮ ፍቅርተ፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከዓለም አልፎ በአገሪቱ በተከሰተበት ወቅት ዘርፉ በተወሰነ መጠን ተቀዛቅዞ እንደነበር ታስታውሳለች። እንዲያም ሆኖ ግን እጆቿን አጣጥፋ አልተቀመጠችም፤ ፈተናውን እንደ መውጫ ተጠቅማበታለች፤ በወቅቱ አስፈላጊ የሆነውን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማምረት ውስጥ ገብታለች። ያመረተቻቸውን ጭምብሎችም ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት በወረዳ አማካኝነት በአካባቢው ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ማድረግ ችላለች። ለመከላከያ ድጋፍ በማድረግ፣ ለአባይ ቦንድ በመግዛትና በሌሎችም አገራዊ ለሆኑ ጥሪዎች ምላሽ በመስጠት ማኅበራዊ ኃላፊነቷን እየተወጣች ትገኛለች።
ወይዘሮ ፍቅርተ በተለይም በውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ አልባሳት በአገር ውስጥ ምርት መተካት እንደሚቻል ታስገነዝባለች። ጥራት ያለው ምርት በተገቢው መጠን በማምረት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ በማቅረብ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ምርት ማስቀረት ባይቻል እንኳን የመቀነስ ፍላጎት አላት። በዚህ በኩል ብዙ ሊሠራበት እንደሚገባም ነው የምትመክረው።
በአምስት ሺ ብር የጀመረችው የጋርመንት ሥራም በአሁኑ ወቅት ከሃምሳ ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማፍራት አስችሏታል። በአሁኑ ወቅትም የኢንቨስትመንት ፈቃድ በማውጣት ፋብሪካ ለመገንባት በሂደት ላይ ናት። ፋብሪካ በመገንባት ሰፊ ቁጥር ላለው የሰው ኃይል የሥራ ዕድል በመፍጠር ትርጉም ያለው ሥራ ሠርታ አገሯን የማስጠራት ራዕይም አላት። ይህን ራዕይ ለማሳካትም በተለይም ጥራት ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች መሆኑን ትገልጻለች።
የአገር ውስጥ አልባሳት በብዛት አጨራረሳቸው ያማረ እንዳልሆነም ጠቅሳ፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ያለውን ክፍተት ለመድፈን ዘመናዊ ማሽን ከመጠቀም ጀምሮ የጥራት ተቆጣጣሪዎችን በመቅጠር ውጤቱን ማምጣት እንደሚቻል ታስረዳለች። ‹‹የምንጠቀማቸው ማሽኖች ደረጃቸውን የጠበቁና ሲሰፋባቸው ክር የማያዝረከርኩ ጥርት አድርገው የሚያወጡ ናቸው›› የምትለው ወይዘሮ ፍቅርተ፣ እነዚህን ማሽኖች በመጠቀም እንዲሁም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይልን በማሳተፍ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ነው የምትናገረው። በአሁኑ ወቅት ያለው ዘመናዊ የስፌት ማሽንም መሰል ችግሮችን ሊያቃልል እንደሚችል ጠቁማለች።
በአገር ውስጥ የተመረቱ አልባሳት የሌሎች አገራትን ስም ለጥፈው ለገበያ እንደሚቀርቡም ተናግራ፣ የፍቅር ጋርመንት ምርቶች በሙሉ ፍቅር በሚለው የንግድ ምልክት ስም ብቻ የሚወጡ እንደሆኑ አጫውታናለች። ማህበረሰቡ ለውጭ አልባሳት ፍላጎት ቢያሳድርም በጥራት ሠርቶ ማሳመን ያስፈልጋል የምትለው ወይዘሮ ፍቅርተ፣ ይህም ጊዜ ሊወስድ ይችል ይሆናል እንጂ ተቀባይነቱ ይመጣል ባይ ናት። ያኔ የአገር ውስጥ ምርትን ከመጠቀም ባለፈ አገርን በማስተዋወቅ በኩልም የላቀ ድርሻ ይኖረዋል ትላለች።
ለአብነትም በአሁኑ ወቅት በስፋት እየገባችበት ያለው የህጻናት ኮንፈርት እጅግ ውብና ማራኪ እንደሆነ ገልጻ፣ ከውጭ አገር ከሚመጣው ምንም ልዩነት የሌለው ስለመሆኑም ነው የምትናገረው። ይህ ምርቷን እጅግ ተፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ ለክልሎች ጭምር ለማከፋፈል ዝግጁ ናት።
በአልባሳት ዘርፉ በስፋት የተሰማሩት ሴቶች መሆናቸውን በመጥቀስ እነዚህ ሴቶች የግል ቢዝነሳቸውን ማሳደግ እንዲችሉ ከመንግሥትም ይሁን ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ቢገኝ መልካም መሆኑን አስገንዝባ፣ በርካታ ተደብቀው ያሉና ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስ የሚችሉ ሰዎች ስለመኖራቸውም ትናገራለች። እነዚህ ያልታዩ ሰዎችን ማየት ከተቻለ አቅማቸውን በመጠቀም ዘርፉን ማሳደግ እንደሚቻል ነው የምትመክረው።
‹‹ጊዜዬን በአግባቡ ተጠቅሜ ውጤታማ መሆን ችያለሁ›› የምትለው ወይዘሮ ፍቅርተ፤ ለጊዜ ትልቅ ቦታ ያላት በመሆኑ ወጣቶችም ወጣትነታቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ካሰቡት እንዲደርሱ ታስገነዝባለች። የተለያዩ ፈታኝና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢገጥማቸውም ተስፋ ሳይቆርጡ ከጣሩ ማንኛውንም ችግር ማለፍ ይችላሉ ስትል ከተሞክሮዋ ባጋራችው ሀሳብ አበቃን።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2014